በመገባደድ ላይ ባለው በዚህ ዓመት ኢትዮጵያ የህይወት ዘመናቸውን ሙሉ ስለአገራቸው እና ለህዝባቸው ደፋ ቀና ያሉ ብርቅዬ ልጆቿን አጥታለች። ከእነዚህም መካከል ዶክተር ተወልደ ገብረእግዚአብሔር፣ ጋሽ ዘሪሁን አስፋው እና እማሆይ ፅጌ ማርያም ይጠቀሳሉ። ከሰሞኑ ደግሞ የአንጋፋ እና ድምፀ መረዋ ሂሩት በቀለ እና የሙዚቀኛ የዳዊት ኃይሉ ዜና እረፍት አሳዛኝ ክስተት ሆኗል። በዛሬው ባለውለታ አምዳችንም የአንጋፋዋን አርቲስት ሂሩት በቀለን የሙዚቃ ህይወት እና ለአገሯ ባበረከተቻቸው ድንቅ የሙዚቃዎች ዙሪያ ትኩረቱን ያደርጋል።
ሂሩት በቀለ ከ50ዎቹ መጀመሪያ እስከ 80ዎቹ መጨረሻ ድረስ በጊዜው ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ጥቂት ስመጥር የሴት አርቲስቶች መሃከል አንዷ እና ተወዳጅ ድምፃዊ ናት። በግጥም እና የዜማ ደራሲነቷም ትታወቃለች። ሂሩት የተጫወተቻቸው ዘመን ተሻጋሪ ሙዚቃዎቿ አሁን ድረስ በህዝብ ዘንድ ተወዳጅ ሲሆኑ ለብዙ አዳዲስ ወጣት ሴት አርቲስቶች መነሳሻ እና አቅም መፈተሻ እንደሆኑ ይነገራል።
በዘመናዊ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ከግንባር ቀደም እንስት ድምፃውያን ተርታ የምትመደበው የቀድሞዋ ሙዚቀኛ እና በኋላም በዘማሪነት ያገለገለችው ተወዳጇ ሂሩት በቀለ በአዲስ አበባ ከተማ ቀበና አካባቢ መስከረም 28 ቀን 1935 ዓ.ም ነው የተወለደችው። ዕድሜዋ ለትምህርት ሲደርስም ቀበና ሚሲዩን ትምህርት ቤት በመግባት የአንደኛ ደረጃ ትምህርን ተከታትላለች። ሂሩት በትምህርት ቤት በነበረችበት ወቅት ለክፍል ጓደኞቿ እና ለሰፈሯ ልጆች ማንጎራጎር ታዘወትር እንደነበር የታሪክ ማህደሯ ይመሰክራል። ይህን ችሎታዋን የተመለከቱት ጓደኞቿም ወደ ሙዚቃው ዓለም እንድትገባ በተደጋጋሚ ያበረታቷትና ይገፏፏት ነበር።
አንጋፋዋ ዜመኛ ሂሩት በቀለ ወደ ሙዚቃው ዓለም የገባችው ከ1952 ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን፤ በአንድ ወቅት ለኢትዮጵያ ራዲዮ በሰጠችው ቃለ ምልልስ የመጀመሪያ ሥራዋ‹‹የሐር ሸረሪት›› የሚል እንደነበር ተናግራለች። ሂሩት በዚህ ቃለ መጠይቋ ላይ ሲሳይ የተባለ ወታደር ጎረቤታቸው የድምጿን ማማር ተመልክቶ ወደ ሙዚቃው እንድታዘንበል እንደገፋፋት አውስታለች። ከቅርብ ጓደኛዋ ጋር በመሆን ወደ ምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል በመሄድ በድምፃዊነት ተፈትና ለመቀጠር መብቃቷን ተናግራለች። ከዚያ ከጨቅላ ዕድሜዋ ጀምሮ ለትምህርት ቤት ጓደኞቿ በመዝፈን ያገኘችው ማበረታቻና በልጅነቷ፣ በአገር ፍቅር ትያትር ቤት የሙዚቃ ዝግጅቶችን መታደሟ፣ ወደ ሙዚቃው ዓለም ለመግባት እንዳነሣሣት አስረድታለች።
ድምፃዊቷ ለመጀመሪያ ጊዜ ተወዳድራ ባለፈችበት የምድር ጦር ኦርኬስትራ በ60 ብር ተቀጥራ ሥራ ስትጀምር ቤተሰቦቿ መረጃው እንዳልነበራቸው የጠቀሰችው ሂሩት፤ በቆይታዋም ልጃቸው ሙዚቀኛ እንደሆነች በብሔራዊ ትያትር ቤት በሥራ ላይ ሳለች የተመለከቱት ቤተሰቦቿ በቅድሚያ ሐዘን ቢሰማቸውም ከጊዜ በኋላ ሞያዋን አምነው እንደተቀበሉት ተናግራለች።
ብዙም ሳትቆይ ለመጀመሪያ ግዜ በተጫወተችው ‹‹የሐር ሸረሪት›› በተሰኘው ዜማ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን እና ተቀባይነትን ያገኘችው ይህች ተወዳጅ የጥበብ ሰው ወዲያውኑ ነበር የፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ ክፍል ዓይን ውስጥ የገባችው። በ1952 ዓ.ም ከምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል እውቅና ውጪ የፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ ሂሩትን በመጥለፍ በጊዜው ኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ ወደሚባለው የፖሊስ ማሰልጠኛ ካምፕ በመውሰድ በልዩ ኮማንዶዎች የ24 ሰዓት ጥበቃ እየተደረገላት ከወር በላይ ተደብቃ ቆየች። ከአንድ ወር ያላሰለሰ ጥረት በኋላ የምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል ፍለጋውን ለማቋረጥ በመገደዱ የፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ ክፍል ሂሩትን በይፋ በቋሚነት የሠራዊቱ የሙዚቃ ክፍል አባል አድርጎ ቀጠራት።
ሂሩት ከተጫወተቻቸው በርካታ ሙዚቃዎቿ መካከል እንደ ህዝብ መዝሙር በአገር አቀፍ ደረጃ የሚታወቀው እና ከትንሽ እስከ ትልቅ በአገር ፍቅር ስሜት እስከአሁን የሚያዜመው ‹‹ኢትዮጵያ›› የተሰኘው ሙዚቃ አንዱ እና ዋነኛው ነው። በፖሊስ ሰራዊት የሙዚቃ እና የትያትር ክፍል ውስጥ በቅንነት ለ35 ዓመት ያገለገለች ሲሆን፤ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ከ200 በላይ ሙዚቃዎችን በመጫወት ለህዝብ ጆሮ አድርሳለች። ከእነዚህም ውስጥ በሸክላ የታተሙት ከ38 በላይ ሙዚቃዎች ሲሆኑ በካሴት ደረጃ ደግሞ 14 ካሴቶች እያንዳዳቸው 10 ዘፈኖችን የሚይዙ ለሙዚቃ አፍቃሪዎቿ አበርክታለች።
በበርካታ ድምፃውያን ከሚያቀነቅኑት የፍቅር ዜማዎች በተጨማሪ ዛሬም ድረስ በአድናቆት የሚደመጡ፣ አገረ ኢትዮጵያን እና ብሔራዊ ስሜትን የተመለከቱ ሙዚቃዎችንም ተጫውታለች። ለአብነትም ‹‹ደጋ ወይና ደጋ›› እና ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚሉት ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎች ተጠቃሽ ሲሆኑ ከትላንት እስከ ዛሬ እንደተወደዱ ዘልቀዋል።
የሂሩት በቀለ አብዛኞቹ ሥራዎች፣ ዘመን ተሻጋሪ እና ለበርካታ ሴት ድምፃውያን ማሟሻ እንደሆኑ የሚመሰከርላቸው ሲሆን የዜማ ድርሰቶችንም ትደርስ እንደነበረም ይታወቃል። በተጨማሪም ሂሩት በሙዚቃ ዓለም በቆየችባቸው ዓመታት ውስጥ ከብዙ ስመጥር ድምፃውያን ጋር በመሆን ስራዋን ለህዝብ አቅርባለች። ከእነዚህም መካከል ማህሙድ አህመድ፣ አለማየሁ እሸቴ፣ ቴዎድሮስ ታደሰ፣ መልካሙ ተበጀ፣ ታደለ በቀለ፣ መስፍን ኃይሌ፣ ካሳሁን ገርማሞ እና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው።
ሂሩት በቀለ በሙዚቃ ዓለም በነበረችበት ጊዜ ከፍተኛ አድናቆትን እና ዝናን ያተረፈች እንዲሁም ደግሞ በመንፈሳዊ ህይወቷ ደስታን እና የመንፈስ እርካታን ያገኘች ቢሆንም የግል ህይወቷን በተመለከተ ግን ያላትን ትርፍ ግዜ ሁሉ ከልጆቿና ከቤተሰቧ ጋር ማሳለፍ እጅግ እንደሚያስደስታት በቅርበት የሚያውቋት ይመሰክሩላታል። አርቲስቷ ከሙዚቃ ስራዋ እና ከመንፈሳዊ ህይወቷ በተጨማሪ በጨዋታ አዋቂነቷ የስራ ባልደረቦቿ፣ ጓደኞቿ እንዲሁም ቤተሰቦቿ ይናገራሉ።
ድምፀ-መረዋ ሂሩት በቀለ በሙያዋ ላበረከተችው አስተዋፅኦ ከአገር ውስጥ እና ከውጭ አገር በርካታ ሽልማት እና የእውቅና ምስክር ወረቀት አግኝታለች። ከእነዚህም መካከል ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ እጅ ከወርቅ የተሰራ የእጅ አምባር እና የምስጋና ደብዳቤ አግኝታለች። በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ፖሊስ ሰራዊት ኮሚሽነር የከፍተኛ ስኬትና የላቀ አስተዋጽኦ ሽልማት ከምስክር ወረቀት ጋር፣ በሙዚቃው ዓለም ላበረከተችው ተሳትፎ ከፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ የብር ዋንጫና የምስጋና ደብዳቤ፣ በሙዚቃው ዘርፍ ለእናት አገሯ ላበረከተችው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት ኮሎኔል መንግስቱ ኃማርያም እጅ ሰርተፍኬት፣ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በኢትዮጵያና በሱዳን ህዝቦች መካከል ያለውን ወዳጅነት ለማደስ ላበረከተችው አስተዋፅኦ የእውቅና የምስክር ወረቀት፣ ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላበረከተችው የሙዚቃ አስተዋፅኦ ከኢትዮጵያ አብዮታዊ ጦር የፖለቲካ አስተዳደር ያገኘችው የምስጋና ደብዳቤ ሽልማት ተጠቃሽ ናቸው።
በተጨማሪም ከፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ የቲያትር እና ሙዚቃ ክፍል የ25 ዓመታት ከፍተኛ ስኬት እና የላቀ አስተዋፅኦ የምስክር ደብዳቤ ከፍተኛ ሽልማት ጋር፣ ከቀድሞ የሰሜን ኮርያ ፕሬዚዳንት ኪም ኢል ሱንግ እጅ ከወርቅ የተሰራ ሜዳልያ፣ ከኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽነር ለፖሊስ ኃይል ስፖርት ፌስቲቫል ላበረከተችው አስተዋፅኦ የእውቅና ሰርተፍኬት፣ ከመሠረተ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ላበረከተችው አስተዋፅኦ ልዩ እውቅና እና የምስጋና ሰርተፍኬት ማግኘቷን በእሷ ታሪክ ዙሪያ የተፃፉ ፅሁፎች ያመለክታሉ።
ይሁንና ይህ ፍቅርን፣ ኢትዮጵያዊነትን እና ጀግንነትን ያደመቀ፤ ያሞካሸ ልሳን ግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም ላይመለስ ተዘጋ። ባደረባት ህመም በህክምና ስትረዳ የቆየችው ሂሩት ይህ የህልፈቷ ዜና የሰሙ በተለይም አድናቂዎቿ ሐዘናቸውን በመግለፅ ላይ ይገኛሉ። ህልፈተ ህይወቷን ተከትሎ በእሷ ሥራዎች ላይ ከፍተኛ አሻራ ያኖሩት አንጋፋው አርቲስት ተስፋዬ አበበ ድምፀ መረዋ እና አንጋፋዋ ድምጻዊት ሂሩት በቀለ በሙዚቃ ዓለም በቆየችባቸው ከሦስት አስርተ ዓመታት በላይ ጊዜያት ከ200 በላይ ዘፈኖችን ያበረከተች መሆንዋን መስክረዋል። ‹‹በተለይም በፖሊስ ሰራዊት የሙዚቃ ክፍል ከ1953 ዓ.ም ጀምሮ ከ30 ዓመታት በላይ አገልግላለች። በዚህ ጊዜ ውስጥ የዘፈነችው የፍቅር ዘፈኖች በጣም ጥቂቶች ነበሩ። አብዛኛዎቹ ስለ ኢትዮጵያ እና ስለኢትዮጵያ ጀግኖች ነው የዘፈነችው›› በማለት ተናግረዋል። በፖሊስ የቲያትርና የሙዚቃ ክፍል ባልደረባ ሆና በሠራችባቸው ዓመታት ሠራዊቱን ግንባር ድረስ በመሄድ ማጀገኗን፤ ስለአገር መስዋዕትነት ክብርና መዓረግ በጥበባዊ አንደበቷ ማነቃቃቷን፣ አንዳንዴም መድረክ ላይ እየዘፈነች ጥይት በጆሮዋ እያፏጨ ሲያልፍ እንኳን በተመስጦ እንባዋ እየወረደ ጭምር ሠራዊቱን ታጀግን እንደነበረ አርቲስት ተስፋዬ አበበ ያዩትን በዕማኝነት አስታውሰዋል።
‹‹የኪነት ቡድኑ ካራማራ ድረስ ሄዶ ስራዎቹን ሲያቀርብ ጥይት ሲያፏጭ ሙዚቀኞቹ ጥይት ይመታናል ብለው ቁጭ ብለው ሲጫወቱ እሷ ግን ቆማ ‹ሺ ገድሎ ከድንበሩ ላይ፤ አልፏል ያ ጀግና ተጋዳይ› እያለች እንባዋን እያፈሰሰች ነበር የዘፈነችው፤ ይህ እራሴ ያየሁት ነው›› ሲሉም አክለዋል። ድምጻዊቷ ስለአገር ካዜመቻቸው ድንቅ ሙዚቃዎች በተጨማሪ በሕይወት ዙሪያ በርካታ ሥራዎችን ማበርከቷን አመልክተዋል። ከእነዚህም መካከል «ሕይወት እንደ ሸክላ» የሚለው ዘፈኗ እጅግ ታዋቂ እና ጆሮገብ እንደነበር አንስተዋል።
አንጋፋዋ ድምፃዊት ሂሩት በቀለ፣ ወደ ኋለኛ ዘመኗ፣ ከ1952 እስከ 1987 ዓ.ም ድረስ ከቆየችበት የሙዚቃዋ ሞያዋ ራሷን ማግለሏን በማስታወቅ፣ ፊቷን ሙሉ ለሙሉ ወደ መንፈሳዊ ሕይወት እና የዘማሪነት አገልግሎት አዙራለች። የመሰረተ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባል የነበረችው ሂሩት በቀለ ፊቷን ሙሉ ለሙሉ ወደ መንፈሳዊ ዓለም ካዞረች በኋላ ሦስት የመዝሙር አልበሞችንም በማሳተም ለእምነቱ ተከታዮች አድርሳለች።
የሰባት ልጆች እናት፣ የአስር የልጅ ልጆች አያት እና የሰባት ልጆች ቅድመ አያት የነበረችው ድምፃዊት ሂሩት በቀለ ባደረባት ሕመም በአገር ውስጥና በውጭ በህክምና ስትረዳ ቆይታ በ83 ዓመቷ በሞት ተለይታለች። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም ለመላው አድናቂዎቿ እና ቤተሰቦቿ መፅናናትን እየተመኘ በህይወት ዘመኗ የነበራትን አበርክቶ በእንዲህ መልኩ ዘክሮታል።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ግንቦት 9/2015