በሞያሌ በኩል ኮብልለው ለማምለጥ የሞከሩ ተያዙ፣ 63 ቤት አለኝ ብሎ አበል የተቀበለው በእስራት ተቀጣ፤ አምሳውን ቤት ዘንዶ አፈረሰው አለ፣ ወዝ አደሮች በአዲስ አቋም በመደራጀት ላይ ናቸው፣ በመሬት መሰርጎድ 516 ሰዎች ሰፈር ለቀቁ፣ በእነዚህና በሌሎችም አርዕስቶች ዙሪያ አዲስ ዘመን ቆየት ባሉ ዓመታት ለንባብ ያበቃቸውን ዘገባዎች መለስ ብለን እናስታውስ፡፡
በሞያሌ በኩል ኮብልለው ለማምለጥ የሞከሩ ተያዙ
ሌተና ኮሎኔል ጌታቸው ኃይሌ ባለቤቱንና አራት ልጆቹን ይዞ ኃይሉ የማነ ብርሀን ከተባለው ግብረ አበሩ ጋር በሞያሌ በኩል ወደ ኬንያ ኮብልሎ ለማምለጥ ሲሞክር ሜጋ ላይ በፀጥታው አስከባሪዎች መያዙን አንድ የጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስት ቃል አቀባይ ትናንት አስታወቀ።
ሌተና ኮሎኔል ጌታቸው ኃይሌ እና ግብረ አበሩ ኃይሉ የማነ ብርሀን በሞያሌ በኩል ወደ ኬንያ ለማምለጥ ሲሞክሩ፤ ከተያዙም በኋላ እንደገና ለማምለጥ ሙከራ አድርገው ሌተና ኮሎኔል ጌታቸው ኃይሌ በፖሊሶች የተያዘ ሲሆን፤ ኃይሉ የማነ ብርሀን ደግሞ በአካባቢው የገበሬ ማህበራት ጥረት መያዙን ቃል አቀባዩ ገልጧል።
ሌተና ኮሎኔል ጌታቸው ኃይሌ ከነቤተሰቡና በግብረ አበሩ ከኃይሉ የማነ ብርሀን ከአዲስ አበባ ወደ ሞያሌ የሄደው በግል ፔዦ መኪና ሲሆን በተያዘበትም ወቅት በኮሎኔሉ ኪስ ውስጥ 4 ሺህ 818ብር ከ65 መገኘቱን ቃል አቀባዩ አስታውቋል።
የህብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስት ለሰፊው ህዝብ ያስጨበጠውን መብትና በመካሄድ ላይ ያለውን አብዮት በመቃወም አገሩን ጥሎ ለመኮብለል የሞከረው ሌ/ኮሎነል ጌታቸው ኃይሌና ግብረ አበሩ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ካላት አቅም በላይ አስተምራ ለከፍተኛ ደረጃ ያበቃቻቸው መሆናቸውን ቃል አቀባዩ ገልጧል።
ጨለማን ተገን በማድረግ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ለመኮብለል የሚቃጣ አድኃሪ ከሰፊው ህዝብ አብዮት ሊያመልጥ የማይችል መሆኑን ቃል አቀባዩ ገልጦ፤ የገበሬ ማህበራትም አወናባጆችን አድኖ በመያዝ በኩል ላሳየው መተባበር አመስግኗል።
ሌተና ኮሎኔል ጌታቸው ኃይሌ፣ ቤተሰቦቹና ግብረ አበሩ ከኃይሉ የማነ ብርሀን በልዩ ምርመራ መምሪያ የሚገኙ ሲሆን ምርመራውም እንዳበቃ ለፍርድ የሚቀርቡ መሆናቸው ታውቋል። (አዲስ ዘመን መስከረም 16 ቀን 1968 ዓ/ም)
63 ቤት አለኝ ብሎ አበል የተቀበለው
በእስራት ተቀጣ
አምሳውን ቤት ዘንዶ አፈረሰው አለ
ከአዲስ ዘመን ጋዜጠኛ
የሚከራየዉ ቤት ሳይኖረዉ አበል በመቀበል ያታለለው አለቃ በቀለ አይተንፍሱ አድራጎቱ በማስረጃ ስለተረጋገጠ በ(3) ወር እስራት እንዲቀጣና 102 ብር መቀጮ እንዲከፍል የከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ፈርዶበታል።
ተከሳሹ አድራጎቱን የፈጸመዉ በአዲስ አበባ ከተማ ጉለሌ በመስከረም ወር _ ዓ. ም ነበር። ተከሳሹ በተባለዉ ጊዜ ከጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስት ስለከተማ ቤቶች ምዝገባ በተሰጠዉ ዓዋጅ መሰረት ከተቋቋመዉ ኮሚቴ ዘንድ ቀርቦ 63 የሚከራዩ ቤቶች ያሉት መሆኑንና እነዚህም ቤቶች 1680 ብር እንደሚከራዩ ከገለጸ በኋላ ቤቶቹን በሀሰት አስመዝግቦ የቤቶቹን አበል 250 ብር ሲቀበል ወዲያዉኑ እጅ ከፍንጅ ተይዟል። (አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7 ቀን 1967 ዓ/ም)
ወዝ አደሮች በአዲስ አቋም በመደራጀት ላይ ናቸው
ከአዲስ ዘመን ጋዜጠኛ
የሰራተኞችን መብትና ኃላፊነት የሚያመለክት ዓዋጅ ኅዳር _ ቀን ከጸናበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ ወዝ አደሮች በአዲስ አበባ አቋም እንዲደራጁና በቀድሞ ደንብ መሰረት የተቋቋሙትም በዓዋጁ መሰረት መተዳደርያ ደንባቸውን አሻሽሎና መሪዎቻቸውን መርጠው በዘጠና ቀኖች ውስጥ ሕጋዊነታቸውን ለማስመስከር በሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲመዘገቡ በተሰጠዉ ገደብ መሰረት እስከ አሁን በአዲስ አበባና አከባቢዉ ብቻ _ ማኅበሮች ሕጋዊ አቋማቸዉ እንዲታወቅላቸዉ በመመዝገብ ጥያቄ ማቅረባቸዉ ተገለጠ።
እስከ አሁን በአዲስ አበባና በአከባቢዉ _ የሰራተኛ ማህበራት ህጋዊ አቋማቸዉ የገለጡት አቶ አሰፋ በሱፍቃድ በሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የእንዱስትሪ ግንኙነቶችና የሥራ ሁኔታዎች መቆጣጠርያ ዋና ክፍሎች ኃላፊ አቶ አባተ ተፈራ የሚኒስቴሩ የሰራተኛና የማህበር ማደራጃ ክፍል ኃላፊዎች ናቸዉ። ሁለቱ ኃላፊዎች በሰጡት መግለጫ ተቋማቸዉ ሕጋዊነት እንዲመዘገብላቸዉ ከጠየቁት 520 የሠራተኛ ማህበሮች መካከል አራት የእርሻ ድርጅቶች ሠራተኛ ማህበሮች __400 ያህሉ___የልዩ ልዩ አገልግሎት መስጫ ድርጅቶች የሰራተኛ ማህበሮችና እንዲሁም የፋብሪካ ሰራተኛ ማኅበሮች የሚገኙባቸዉ መሆናቸዉን ገልጧል። (አዲስ ዘመን የካቲት 12 ቀን 1969 ዓ/ም)
በመሬት መሰርጎድ 516 ሰዎች ሰፈር ለቀቁ
ከአዲስ ዘመን ጋዜጠኛ
በጋሙ ጎፋ ክፍለ ሀገር በገሙ አዉራጃ በደሮ በተባለዉ ቀበሌ ሁለት ኪሎ ሜትር ካሬ መሬት በመሰርጎዱ በዛዉ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ 516 ሰዎች ቤታቸዉን ለቀዉ መሰደዳቸዉ ሁኔታዉን እንዲመረምር ወደ ስፍራዉ ተልኮ የነበረዉ አጥኝ ቡድን ገለጠ።
በእርዳታ ማስተባበርያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን፣ የከርሰ ምድር ጥናት ክፍልና ከዕጸዋት ጥናት ክፍል የተውጣጣዉ ቡድን የመሬት መሰረጎዱ የደረሰበትን ቀበሌ ተዘዋዙሮ ከተመለከተ በኋላ በቀረበዉ ሪፖርት በደረሰዉ የተፈጥሮ አደጋ በሰብልና በንብረት ላይ መጠነኛ ጉዳት ለመድረሱ 86 ቤተሰቦች የኤለና የቻሮ ቀበሌዎችን ለቀዉ በአቅራቢያቸዉ ወደ ሚገኘዉ ቆላማ ስፍራ በመሰደድ አዲስ መንደር መቆርቆራቸዉን ገልጧል።
(አዲስ ዘመን ጥር 8 ቀን 1968 ዓ/ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2015