ከራስ አልፎ ለሌሎች ደስታና ደህንነት መኖር፣ ትርጉም ያለው ሕይወት የመኖር ትልቅ ማሳያ ነው። ትናንት በችግር ላይ ወድቀው የነበሩና ከችግራቸው ወጥተው ዛሬ ሌሎች የተቸገሩ ወገኖችን የሚረዱ ግለሰቦች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ደስታና ስኬት በመኖር ትርጉም ያለው ሕይወት የሚኖሩ መልካም ሰዎች ናቸው። ላለፉት 25 ዓመታት በአስከፊ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ለነበሩ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ድጋፍና እንክብካቤ እያደረገ የሚገኘው ምግባረ ሰናዩ ‹‹የወደቁትን አንሱ የነዳያን መርጃ ማኅበር›› በእንዲህ ዓይነት መልካም ሰዎች የተመሠረተና የሚንቀሳቀስ ተቋም ነው። የማኅበሩ መሥራች አቶ ስንታየሁ አበጀም ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ደስታና ስኬት ከኖሩ በጎ አድራጊ ሰዎች መካከል የሚመደቡ ናቸው።
ገና በስድስት ዓመታቸው እናታቸውን በሞት ያጡት አቶ ስንታየሁ፣ እድገታቸው መከራ የበዛበት ነበር። የአዕምሮ ጭንቀትን ጨምሮ ለ23 ዓመታት ያህል በሌሎች የጤና እክሎች ይሰቃዩ ነበር። በ1981 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ መጥተው በሰው ቤት ተቀጥረው መሥራት ከጀመሩ ከጥቂት ጊዜያት በኋላም በዚሁ ሕመማቸው ምክንያት ለከፍተኛ ችግር ተዳርገዋል። ሕመማቸው ሲበረታባቸው ይሠሩባቸው የነበሩ ሰዎች ሊረዷቸው ባለመፈለጋቸው ጎዳና ላይ ወድቀው ነበር። በወቅቱ ችግራቸውን ተመልክተው ያስጠጓቸው አንድ መልካም ሰው ሌላ ቤት ገዝተው ሲወጡ አቶ ስንታየሁ ብቻቸውን ቀሩ፤ ሕመማቸውም ፀንቶባቸው እግሮቻቸውና እጆቻቸው መንቀሳቀስ አቆሙ። ሕይወት ፈተናዋን አበረታችባቸው።
አቶ ስንታየሁም ‹‹ፈጣሪዬ ሆይ፣ እባክህ ለ15 ቀናት ያህል እድሜ ስጠኝና እንደእኔ መንቀሳቀስ፣ መልበስ፣ መጉረስ የማይችሉ፤ ቤተሰብና ወገን የሌላቸውን ሰዎችን ገላቸውን አጥቤ፣ ምግብ አጉርሻቸው፣ ችግራቸውን ለሰው ነግሬላቸው በ15ኛው ቀን ‹ተመስገን› ብዬ ልሙት›› ብለው ፈጣሪያቸውን ተማጸኑ። አቶ ስንታየሁም ፀሎታቸው ተሰምቶላቸው ከሕመማቸው አገግመው ሊረዷቸው ለፈጣሪ ቃል የገቡላቸውን ሰዎች ፍለጋ ገቡ። በወቅቱ ከሕመማቸው ሙሉ በሙሉ ባይድኑም ለፈጣሪያቸው የገቡት ቃል ብርታት ሆኗቸውና አቶ ስንታየሁ ‹‹አግዙኝ›› ብለው የጠየቋቸው በጎ አድራጊዎች መልካም ፈቃድ ታክሎበት እጅግ አሳዛኝ በሆነ ሕይወት ውስጥ የነበሩ ሰዎችን ከወደቁበት ማንሳት ጀመሩ። ወደ ገነተኢየሱስ እና እንጦጦ ኪዳነ ምሕረት አብያተ ክርስቲያናት ሄደው 16 ሰዎችን ከወደቁበት አነሱ።
በሂደትም የ15 ዓመት እድሜ የነበራቸው ሁለት ታዳጊ ወጣቶች ከአቶ ስንታየሁ ጋር አብረዋቸው መሥራት ጀመሩ። አስከፊ በሆነ ሕይወት ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ግለሰቦችን ከወደቁበት እያነሱ ሰውነታቸውን የማጠብ፣ ምግብ የማብላትና ፀሐይ የማሞቅና የመንከባከብ በጎ ተግባራቸውን ተያያዙት። ከብዙ ውጣ ውረዶች በኋላ አቶ ስንታየሁና አጋሮቻቸው ከሚያገኟት ገንዘብ ላይ ቆጥበው ሕልማቸውን እውን አደረጉ። መስከረም 1 ቀን 1990 ዓ.ም ‹‹የወደቁትን አንሱ የነዳያን መርጃ ማኅበር››ን አቋቋሙ።
‹‹በኢትዮጵያ ቱሪስት ሥራ ንግድ ድርጅት በ150 ብር ወርሐዊ ደመወዝ የጥበቃ ሠራተኛ ሆኜ ተቀጠርኩ። ማታ ማታ ብቻ ነበር የምሠራው። በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ምግብ እየበላሁ በምቆጥበው ገንዘብ በሳምንት ለሦስት ቀናት ምግብ ማዘጋጀት ጀመርን። ሥራውን በዚህ ሁኔታ ከቀጠልን በኋላ ቤት ስለመከራየት አሰብን…›› በማለት ወደ ሥራው መግባታቸውን አቶ ስንታየሁ ያስታውሳሉ።
በ120 ብር ቤት ተከራዩ። ‹‹ኪራዩን ማን ይከፍልላችኋል?›› የሚለው ሰው በዛ። የፈጣሪንና የመልካም ሰዎችን እርዳታ ተስፋ ያደረጉት እነአቶ ስንታየሁ ተስፋቸው እውን ሆነላቸው። የኪራዩ ወጪ በአንዲት በጎ ፈቃደኛ ግለሰብ ተሸፈነ። ይህን በጎ ተግባር የተመለከተው የአካባቢው ቀበሌ አስተዳደር ሰባት ሰዎችን መያዝ የሚችል አንድ ክፍል ቤት ሰጣቸው። እነአቶ ስንታየሁም ጧሪና አስታማሚ የሌላቸውን ወገኖችን ፍቅርና እንክብካቤ እየሰጡ ቀጠሉ።
በሂደትም ማኅበሩ ድጋፍ የሚያቀርብበትን አካባቢ በማስፋት የበጎ ፈቃደኞችን ቁጥር በመጨመር ለብዙ ሰዎች ደራሽና ተስፋ ሆነ። ለሀገር ውለታ ውለው እንደዋዛ የተረሱ የሀገር ባለውለታዎች ‹‹ውለታችንን የሚያውቅ አስታዋሽ አገኘን›› ብለው ተደሰቱ። የእነአቶ ስንታየሁ ድጋፍና እንክብካቤ በጎ ፈቃደኞችን ቀልብ ሳበ። አንዳንዶችም ሙሉ ጊዜያቸውን ለማኅበሩ ለመስጠት ወሰኑ።
ሥራቸውን የሰሙ አንድ መሐንዲስ ካሉበት ቦታ ሄደው የእነአቶ ስንታየሁን በጎ ተግባር ተመለከቱ። ለማኅበሩም አዲስ ምዕራፍ ተከፈተለት። አቶ ስንታየሁ ሁኔታውን ሲያስታውሱ እንዲህ ይላሉ፡- ‹‹ቦታ ካላችሁ ልሥራላችሁ አለን። በወቅቱ ቀበሌው ሥራችንን ተመልክቶ ቦታ ሰጥቶን ነበር። ቦታውን አሳየነውና 40 ሰዎችን የሚይዝ ቤት ሠራልን። እንክብካቤ የምናደርግላቸውን ሰዎች ወደተሠራው አዲሱ ቤት አስገባናቸው። አዲሱ ቤት ለቢሮና ለእቃ ማስቀመጫ የሚያገለግሉ ክፍሎችንም የያዘ ነበር። በዚህ ወቅት ነበር አንድ በጎ ፈቃደኛ መጥቶ ‹በእጅህ ብር አልሰጥህም፤ ለእነርሱ የሚረዳ ነገር አደርጋለሁ› አለኝ። ሌሎች በጎ ፈቃደኞችም አገዙን›› ይላሉ።
በጎ ነገር መሥራት በሰውም በፈጣም የሚወደድና የሚከበር ተግባር ነውና የእነአቶ ስንታየሁ ሥራ የተሻለ ተግባርን ወለደ። ሕክምናን ጨምሮ መሠረታዊ አገልግሎቶች የተሟሉለት የአረጋውያን መጠለያ ማዕከል የመገንባት ፍላጎት ተጠነሰሰ። ለማዕከሉ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ቀን ጀምሮ በጎ ፈቃደኞች እርዳታ ማድረግ ጀመሩ። የእነአቶ ስንታየሁ ሃሳብና የበጎ አድራጊዎች ድጋፍ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ዘመናዊ የአረጋውያን መጦሪያ ማዕከል እውን ሆነ። ከመንግሥት በተገኘ መሬት ላይ የተገነባው የማኅበሩ ዘመናዊ የአረጋውያን የመጦሪያ ማዕከል ብዙ አረጋውያን የማምሻ እድሜ በኃዘንና በሰቆቃ እንዳያሳልፉ ደርሶላቸዋል።
አረጋውያኑ ከእድሜያቸውና ከቆዩበት አስከፊ የሕይወት ጉዞ አንፃር ጥሩ የጤና ክትትል እንደሚያስፈልጋቸው ግልፅ ነው። ስለሆነም ማኅበሩ አረጋውያኑ ሕክምና የሚያገኙበት ተቋም እንዲኖር ክሊኒክ አቋቁሞ አገልግሎት የመስጠት ተግባርንም አሳክቷል። ይህም ተግባር አረጋውያን ወደ ሕክምና ከሚሄዱ ይልቅ ሕክምናውን ለአረጋውያኑ ባሉበት ማቅረብ አዋጭና ውጤታማ እንዲሆን አስችሏል።
ማኅበሩ ከተቋቋመ ጀምሮ ደጋፊ የሌላቸውን አረጋውያንን ከጎዳና ላይ በማንሳት በማዕከሉ ውስጥ ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዲያገኙ እያደረገ የሚገኝ የበጎ አድራጎት ተቋም ነው። በአረጋውያን መጦሪያ ማዕከል ውስጥ ከሚሰጠው ድጋፍ በተጨማሪ የምገባ አገልግሎት የሚሰጣቸው ወገኖችም አሉ። የእነአቶ ስንታየሁ የበጎ ፈቃድ ተግባር ብዙዎችን ከጎናቸው እንዲሰለፉ አድርጓል። በማኅበሩ ውስጥ የሚያገለግሉ በጎ ፈቃደኛ ባለሙያዎችም ማኅበሩ ውስጥ ማገልገላቸው ልዩ ስሜትን እንደሚፈጥርባቸው ይናገራሉ።
ላለፉት 25 ዓመታት በአስከፊ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ለነበሩ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ድጋፍና እንክብካቤ ያደረገው ምግባረ ሠናዩ ‹‹የወደቁትን አንሱ የነዳያን መርጃ ማኅበር››፣ በአሁኑ ወቅት ለ300 ሰዎች ድጋፍና እንክብካቤ እያደረገ ይገኛል። ከእነዚህም መካከል 200 በማኅበሩ የአረጋውያን መጦሪያ ማዕከል ውስጥ የሚገኙና 100 ደግሞ በተመላላሽ ድጋፍ የሚደረግላቸው ናቸው። የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ዓይናለም ኃይሌ እንደያሚስረዱት፣ ማኅበሩ በአረጋውያን መጦሪያ ማዕከሉ ውስጥ እንክብካቤና ድጋፍ ከሚያደርግላቸው 200 ሰዎች በተጨማሪ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ለሚገኙ 100 ሰዎች ዕለታዊ የምሳ ምገባ መርሐ ግብር ያከናውናል፤ ሲታመሙ ነፃ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙም ያደርጋል።
የጤና ችግራቸው ከማኅበሩ ክሊኒክ አቅም በላይ ሲሆን ደግሞ ማኅበሩ ከቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጋር በፈጠረው የሥራ ግንኙነት አማካኝነት ነፃ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ያደረጋል፤ ከሆስፒታሉ የሚታዘዙ መድኃኒቶችን ማኅበሩ ገዝቶ ለታካሚዎች በነፃ ያቀርባል። ማኅበሩ 60 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ 15 የአስተዳደር እና 45 ከተገልጋዮቹ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው የድጋፍና እንክብካቤ ባለሙያዎች ናቸው።
‹‹የወደቁትን አንሱ የነዳያን መርጃ ማኅበር›› የአረጋውያንን ጤና በዘላቂነት ለመንከባከብ የሚያስችል አሠራር አስፈላጊ እንደሆነ በማመን በአረጋውያን ጤና እንክብካቤ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን አስመርቋል። ወይዘሮ ዓይናለም ስለባለሙያዎቹ ስልጠና ሲናገሩ ‹‹አረጋውያን ደጋፊ አጥተው ከመውደቃቸው በፊት የጤና እንክብካቤ ማግኘት አለባቸው። የአረጋውያን ጤና እንክብካቤ በኢትዮጵያ ያልተለመደ የጤና እንክብካቤ ዓይነት ነው።
‹የወደቁትን አንሱ የነዳያን መርጃ ማኅበር› ደጋፊ የሌላቸውን አረጋውያንን ከወደቁበት በማንሳት ፈር ቀዳጅ እንደመሆኑ መጠን ጤናቸውን በሰለጠነና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በመንከባከብ ረገድም ቀዳሚ መሆን ስላለበት 21 የአረጋውያን ጤና እንክብካቤ ባለሙያዎችን (ነርሶችን) አሰልጥኖ አስመርቋል። ባለሙያዎቹ የሰለጠኑት በማኅበሩ የሥልጠና ማዕከል ውስጥ ሲሆን፣ በርካታ ተቋማትና ግለሰቦች ሥልጠናው እንዲሳካ ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን አድርገዋል›› በማለት ይገልፃሉ።
ወይዘሮ ዓይናለም ስለማኅበሩ ቀጣይ እቅድ ሲናገሩ ‹‹አረጋውያን የሕክምና አገልግሎት የሚያገኙበት ራሱን የቻለ ሆስፒታል ያስፈልጋቸዋል። በሀገራችን በአረጋውያን ሕክምና ስፔሻላይዝ ያደረገ አንድም ሐኪም የለም። ስለሆነም ይህ ጉዳይ ትኩረት አግኝቶ፣ ሥርዓተ ትምህርት ተቀርፆለት ሥልጠናው በትምህርት ተቋማት እንዲሰጥ ማድረግ ያስፈልጋል። ‹‹የወደቁትን አንሱ የነዳያን መርጃ ማኅበር›› ይህ እንዲሳካ የአረጋውያን መታከሚያ ሆስፒታል ለማስገንባት ዲዛይን አሠርቷል። የማኅበሩ ትልቁ እቅድ ይህን ሆስፒታል ማስገንባት ሲሆን፣ ግንባታውን በቀጣዩ ዓመት ለማስጀመር ታቅዷል›› ብለዋል።
አቶ ስንታየሁ ‹‹እውነተኛ ተረጂዎችን ለይተን በአንድ ቦታ ካደረግናቸው፣ ጉልበት ያላቸው ሰዎች ሠርተው ይበላሉ። እውነተኛ ድጋፍ አድራጊዎችም ለትክክለኛዎቹ ተረጂዎች ይለግሳሉ። በየመንገዱ የሚደረግ ተገቢ ያልሆነ ምፅዋት እውነተኛ ተረጂዎች ድጋፍ እንዳያገኙ አድርጓል›› በማለት ድጋፍ ሲደረግ ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት በሚያስችል ሥርዓት መሆን እንዳለበት ያስገነዝባሉ።
‹‹ችግርን ድል ነሳሁት አልልም። ውስጤን የማውቀው እኔ ነኝ። ብዙ በጎ ነገር ሠርቻለሁ ብዬ አላምንም፤ በሠራሁት አልረካሁም። ያለችኝ ሀብት እጄ ብቻ ናት፤ በእጄ እሠራባታለሁ። ሁሉም ነገር የኢትዮጵያ ሕዝብ ንብረትና መልካም ተግባር ውጤት ነው። ሰዎቹ ሲታጠቡ፣ ሲበሉና ሲጠጡ ደስ ይለኛል። ለእኔ ሕይወት ማለት ይህ ነው። ‹ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን› ብለው ሀገሬን ሲመርቁልኝ እጅግ በጣም ደስ ይለኛል›› በማለት የደስታቸው ምንጭ የበጎ አድራጎት ሥራቸው እንደሆነ ይናገራሉ። ለበጎ ስራቸው ከበርካታ ተቋማት ምስጋናና ሽልማቶችን አግኝተዋል። አቶ ስንታየሁ የሠሩት ሥራ እጅግ አስደናቂ እንደሆነ የሚታወቅ ቢሆንም፣ እርሳቸው ግን ‹‹ብዙ ሠርቻለሁ›› ብለው አያምኑም።
የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ዓይናለም ‹‹እድለኞች ከሆንን ሁላችንም ወደ አረጋዊነት የእድሜ ምዕራፍ ላይ እንደርሳለን። በአረጋዊነት የእድሜ ዘመን ብዙ የጤና ችግሮች ያጋጥማሉ። ይህ ከመሆኑ በፊት ግን ጥሩ እንክብካቤ ማድረግ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያውያን አረጋውያን ተገቢውን ሕክምናና እንክብካቤ ሊያገኙ ይገባል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ከውጭ አካላት እርዳታ ሳንጠብቅ ለራሳችን ወገኖች ራሳችን ልንደርስላቸው ይገባል። አረጋውያንን መንከባከብ ዋጋ እንደሚያስገኝ ሁሉም ሰው መገንዘብ አለበት። ኅብረተሰቡም ሆነ መንግሥት የየራሳቸው ኃላፊነት አለባቸው። ሀገርንና ትውልድን ሲረግሙ እና መፈጠራቸውን ሲያማርሩ ያገኘናቸውን ወገኖች ‹አይዟችሁ› ብለን ፍቅርና እንክብካቤ ሰጥተን ወደተሻለ ሕይወት ተመልሰው ሀገራቸውንና ትውልድን እንዲመርቁ ማድረግ ትልቅ ቁም ነገር ነው›› በማለት የአረጋውያን እንክብካቤ ትልቅ ትኩረት እንደሚስፈልገው አስገንዝበዋል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2015