ዓለም አቀፉ የሰራተኞች ቀን ዛሬ ይከበራል። ይህ በዓል የሚከበረው በዓለም ለ130ኛ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ44ኛ ጊዜ ነው። በዓሉ በአገራችን ሰራተኞች ዘንድ “ሰላም ለአገር ዕድገት፤ ለሰራተኛው መደራጀትና ሁለንተናዊ እድገት መሰረት ነው” በሚል መሪ ቃል ይከበራል።
አዎን የሁሉም ነገር መሰረቱ ሰላም ነው። የኢንዱስትሪ መኖርና መስፋፋትም ይህንን ዕውነታ ያጠይቃል። እናም አገር ሰላም ስትሆን ህዝብ በሰላም ወጥቶ ይገባል፤ ሰራተኛ ሰርቶ ያፈራል። የኢንዱስትሪ ሰላም ግን ከጸጥታ ጋር ብቻ የሚያያዝ ጉዳይ አይደለም። በዚህ ውስጥ ያለው ሰላም ተቀጣሪ ከመሆን ጀምሮ፤ ለተመሳሳይ ስራ እኩል/ተመሳሳይ ክፍያ እስከማግኘትና ራስን ጠቅሞ አገርንና ህዝብን እስከመጥቀም የሚደርሱ ግላዊ መብቶች፤ ማህበራዊ ኃላፊነቶችና ግዴታዎች ያሉበት ነው።
አገራችን የምትፈልገውና የጀመረችው የግብርና መር የኢንዱስትሪ ልማት እና ዕድገት በተፈለገው መልክና ይዘት እንዲሰፍን ቅድሚያውን ሰላም ይወስዳል። ይህ ሰላም ደግሞ የህዝቦቿን እንደልብ በየአካባቢው እየተዘዋወሩ የመስራት መብታቸውን እውን ያደርጋል።
የፖለቲካ ኢኮኖሚ ምሁራን እንደሚያስተምሩት በየትኛውም ስልተ ምርት ውስጥ ዓይነተኛውን ሚና የሚጫወተው አምራቹ ክፍል ነው። አምራቹ ደግሞ ሰራተኛው ነው። ይህ ክፍል በአገሩም፤ በስራ አካባቢውም የሚያሰራ አውድና ከባቢ ይሻል። አሊያ ምርታማነቱ ጥያቄ ውስጥ ይወደቃል። ይህ ሁሉ ሲያድግ ደግሞ በአገር ልማትና ዕድገት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል።
የሰራተኛው ደህንነት መጠበቅ በአብዛኛው በአሰሪው ጫንቃ ላይ የሚያርፍ ግዴታ ቢሆንም፤ ከመንግስት የልማት ፖሊሲና አቅጣጫ የሚጀምር መነሻ አለው። በኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉት ሁለቱ ወገኖች በሚነደፉ ፖሊሲዎችና በሚረቀቁ አዋጆች የሚጠቃለል የመንግስትን ዋስትና ይፈልጋሉ።
አሰሪና ሰራተኛ በመንግስት በኩል በእኩል ዐይን የሚታዩ ናቸው። እናም ፖሊሲውና አዋጁ የነዚህን ወገኖች ፍላጎትና መብት ተደራሽ ሲያደርግ መንግስትም ዋስትና የመስጠት ሀላፊነቱን መወጣቱ ይረጋግጣል።በዚህም አንዳቸው ለሌላኛው፤ ሁለቱም ለሀገር እና ለህዝብ ያለባቸውን ኃላፊነትም ሆነ ግዴታ ይተነትናል። እንዲህ ሲሆን የኢንዱስትሪው የሥራ ሰላም ይሰፍናል።
በአሁኑ ወቅት እንደሚታየው፤ በአብዛኛው የኢንዱስትሪ ሰራተኞች ዘንድ የሚነሳው ቅሬታ የኢንዱስትሪውን ሰላም በማስፈን ረገድ ከመንግስት የሚጠበቅ አንድ ዕርምጃ መኖሩን የሚያመልክት ነው። በዚህ ረገድ እንደ ጉድለት ከሚታዩት ውስጥ የሰራተኞች በማህበር የመደራጀት መብት መገደብ፣ የደመወዝ መነሻ ወለል አለመወሰን፣ ለተመሳሳይ ስራ ዕኩል ክፍያ የማግኘት አሰራር አለመኖር ይጠቀሳሉ። የአብዛኞቹ ሰራተኞች ጥያቄዎች መነሻም እነዚህ ናቸው።
በየትኛውም አገር የሰራተኛውን መብት ያላከበረ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ትርፋማ አይሆንም፤ ዘለቄታም አይኖረውም። እናም፤ የኢትዮጵያ ሰራተኞች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች በአግባቡ ሊመለሱላቸው ይገባል።
በኢፌዴሪ ህገ መንግስት መደራጀት መብት ነው። ይህ ህገመንግስታዊ መብት ሊከበር ይገባል። ወዲህም ደግሞ የአንድ ኢንዱስትሪ ሰራተኞች መደራጀት ለራሳቸው ብቻም ሳይሆን ለድርጅቱና ለባለሀብቶቹ፤ ብሎም ለሀገር ተጨማሪ ጉልበት ነው።ምርትና ምርታማነት ለማሳደግም ይጠቅማል።በመሆኑም ይህ መብታቸው ሊከበር ይገባል። መንግስትም ከለላ የመስጠት ግዴታውን መወጣት ይኖርበታል።
ከዚሁ ጋር አብሮ የሚነሳው፤ የመደራደርና የህብረት ስምምነት ነው። በየትኛውም ማህበራዊ መስተጋብር ውስጥ በስምምነት የተፈጸመና በውል የታሰረ ግዴታ ከተዋዋዮቹ ውዴታ የሚመነጭ ነውና አስገዳጅነቱም ሆነ አሰሪነቱ በሦስተኛ ወገን ወይም በመንግስት ከሚወጣ ህግ ይበልጥ እንደሁ እንጂ አያንስም።
ዓለም አቀፍ ተሞክሮውም የሚያሳየው ይህንን ነውና እንደ መብት ሊከበር ይገባል። ጥቅሙንም ቢሆን ማስረዳቱና ግንዛቤ ማስጨበጥ አገባብ ይሆናል። በሌላ በኩል፤ የሰራተኛው የደመወዝ መነሻ ወለል ውሳኔ ያለማግኘቱ ጉዳይ ተመሳሳይ ክፍያ ለተመሳሳይ ስራ የሚለውን መርህ የሚጻረር ነውና ይህም ሊታሰብበት ይገባል።
በአጠቃላይ፤ የሰራተኛውን መብት ለማስከበርና የኢንዱስትሪውን ሰላም ለማስጠበቅ አሰሪውንና ሰራተኛውን፤ ከሁሉም በላይ ሁለቱም ወገኖች የሚገኙበትን ስልተ ምርት መሰረት ያደረገ ህጋዊ ማዕቀፍ ሊዘጋጅ ይገባዋል።
የዚህ ህጋዊ ማዕቀፍ ዝግጅት ደግሞ የሁለቱ ወገኖች ይሁንታ ያረፈበትና ስምምነታቸውን የያዘ እንደሆነ ፈቃደኝነት የሚገዛው ህግ ይሆናልና ዘላቂነት ይኖረዋል። በዚህ ረገድ እስከዛሬ ዘግይቶ የነበረውና በአሁኑ ሰዓት ግን የአሰሪና ሰራተኛ ወገኖች ተስማምተውበት ለውሳኔ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ዕልባት ሊያገኝ ይገባዋል።
እንዲህ ዓይነቱ የመንግስት ኃላፊነት ህገመንግስታዊ ኃላፊነትን ከመወጣት የሚመነጭ ብቻ ሳይሆን የኢንዱስትሪውን፤ አልፎም የአገርን ሰላምና ደህንነት ከማስከበር ጋር የሚያያዝ ነውና ችላ ሊባል አይገባም።
ሰራተኛውም የዘንድሮውን በዓል ሲያከብር ለበዓሉ ዕውን መሆን፤ ለዓለም ሰራተኞች መብት መከበርና ለሰላማዊ የኢንዱስትሪ ድባብ መፈጠር ሲሉ የተሰው ቀደምት የሰራተኛ መሪዎች፤ ሰራተኞችና ተባባሪዎቻቸውን በመዘከርና በማመስገን ብቻ ሳይሆን ቀጣይ ኃላፊነትንና ግዴታንም በማሰብ ጭምር መሆን አለበት።
አገራችን በለውጥ ሂደት ውስጥ ናት። ይህ ለውጥ ደግሞ አንድነታችንንና ህብረታችንን አጠንክረን በመቆም፤ በተቃራኒ የቆሙትን ሀይሎች ስርዓት በማስያዝ፤ አጥፊ ሀሳባቸውን ባለመጋራትና ተቀባይ እንዳይኖረውም በማድረግ፤ ይልቁንም እነርሱን ትተውት እንዲደመሩ በማስተማር መሆን ይገባዋል።
የሁሉም ነገር መሰረቱ የአገር ሰላም ነውና የኢንዱስትሪውን ሰላምና ደህንነት ለማስፈን ስንነሳ ቅድሚያውን ትኩረት ለአገራዊው ሰላም ልንሰጥ ይገባል። የዛሬውን በዓል ከርሞና ከዚያም ቀጥሎ ማክበር የምንችለው በሰላም ስንሻገር ነውና የለውጥም የሰላምም ሀዋርያ ልንሆን ይገባል።ስለሆነም ሰራተኛውም ለመብቱም ለሃገራዊ ሰላምም ዘብ መቆም አለበት፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23/2011