
አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ መንግሥት በተገበረው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ የታየው የመንግሥት ቁርጠኛነት አስደናቂ እንደሆነ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደርና በአፍሪካ ኅብረት የሀገሪቱ ተወካይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ ተናገሩ።
አምባሳደሩ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ መንግሥት በኢኮኖሚ ማሻሻያው ትግበራ ላይ ባሳየው ቁርጠኝነት መደነቃቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብቷን ለማሳደግ የወሰደቻቸው ርምጃዎች እጅግ ጠቃሚ ተግባራት እንደሆኑ የተናገሩት አምባሳደሩ፣ ብዙ የምጣኔ ሀብት ዘርፎችን ክፍት ለማድረግ የተወሰደው ርምጃ ኢኮኖሚውን ለማዘመን፣ የምርትና አገልግሎትን ጥራት ለማሳደግ እንደሚያስችል ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ትልቅ እድገት የሚያስመዘግብበትና በንግድና ኢንቨስትመንት ውስጥ ሁነኛ ተዋናይ የሚሆንበት ጠንካራ ኢኮኖሚ እንድትገነባ መደገፍ ስለሚያስፈልግ፣ ፈረንሳይ የኢትዮጵያን የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ እንደምታበረታታ ጠቁመዋል።
‹‹የኢኮኖሚ ማሻሻያውን አፈፃፀም ለመደገፍ የወሰንነውም በዚህ ምክንያት ነው። ለመጀመሪያው የሀገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሐ ግብር አፈፃፀም ድጋፍ አድርገናል። ለሁለተኛው የሀገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሐ ግብርም ድጋፍ እናደርጋለን። ለሀገሪቱ እድገት ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው የልማት ፕሮጀክቶች ላይ የምናደርገውን ተሳትፎ አጠናክረን እንቀጥላለን›› ብለዋል።
አምባሳደሩ እንዳሉት፣ ፈረንሳይ በቡድን 20 የዕዳ ሽግሽግ ማሕቀፍ መሠረት የኢትዮጵያን ዕዳ ለማሸጋሸግ በነበረው ሂደት ተሳትፋለች። በዚህ ሂደት ባለፈው ሳምንት በተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት የኢትዮጵያ ዕዳ እንዲሸጋሸግ ማድረግ ተችሏል። ይህ ተግባር ብዙ ሀገራት ለኢትዮጵያ ሌሎች ብድሮችን እንዲፈቅዱ የሚያስችል ወሳኝ ርምጃ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያን የባሕር በር ተጠቃሚነት ጥያቄን በተመለከተም፤ ‹‹አንዲት ሀገር፣ በተለይም ትልቅ የሆነች ሀገር፣ የባሕር በር ተጠቃሚነት አማራጮቿን ማስፋቷ ሕጋዊ ነው። ዓለም አቀፍ ሕግን ተከትሎና ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሚደረግ ምክክር እስከተከናወነ ድረስ ጥያቄው ተገቢና ሕጋዊ ነው። የጥያቄውን ተገቢነት እንረዳለን። ይህ የኢትዮጵያ ፍላጎት ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሚደረግ ምክክር በጥሩ ትብብርና በሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንደሚያገኝ አምናለሁ›› በማለት አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ማደራጀቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላምና ፀጥታን ለማስፈን የራሷን አስተዋፅዖ እንድታበረክት እንደሚያስችላት ጠቁመው፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት በቀረበ ጥያቄ መሠረት ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ ባሕር ኃይል የሥልጠና ድጋፎችን እያደረገች እንደምትገኝ ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ፣ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ፣ የብዙ ፈረንሳውያን ባለሙያዎች የጥበብ ዐሻራዎች እንዳሉ የተናገሩት አምባሳደሩ፣ ፈረንሳይ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በቅርስ ጥበቃ ዘርፍ በርካታ ሥራዎችን እየሠራች እንደምትገኝም አስረድተዋል።
ለአብነት ያህልም የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና የብሔራዊ ቤተ መንግሥት እድሳትን ጠቅሰዋል። የፈረንሳይ የኢትዮጵያ ጥናት ማዕከልም የሁለቱን ሀገራት ትብብር የሚያሳድጉ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያና ፈረንሳይ የ125 ዓመታት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ታሪክ እንዳላቸው ያስታወሱት አምባሳደር ላሜክ፤ የሀገራቱ ግንኙነት ታሪክ ብቻ ሳይሆን ጥልቅና ተጨባጭ የወዳጅነት ትስስር እንደሆነ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፈረንሳይ ያደረጓቸው ጉብኝቶች እና ያካሄዷቸው ጥልቅና የመተማመን ውይይቶች የዚህ ሁነኛ ማሳያዎች እንደሆኑ ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በጋራ የመሰረቷቸው ብዙ ተቋማትም እንዳሉም ተናግረዋል።
በሕዝቦች፣ በንግድ ኩባንያዎች እና በትምህርት ተቋማት መካከልም ጠንካራ ትስስሮች እንዳሉ ጠቁመው፣ በሁለቱ ሀገራት የሚገኙ የሚዲያ እና የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት የእርስ በርስ ግንኙነታቸው እንዲጠናከር እንዲሁም የፈረንሳይ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ እንደሚያበረታቱም ገልጸዋል።
አምባሳደር ላሜክ ‹‹ከኢትዮጵያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከመሠረቱ ከመጀመሪያዎቹ ሀገራት መካከል ፈረንሳይ ሁለተኛዋ ሀገር ናት። ረጅም ታሪክ እንጋራለን፤ በዚህም ኩራት ይሰማናል›› ብለዋል።
በ አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 6 ቀን 2017 ዓ.ም