የንግዱ ማኅበረሰብ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በስፋት እንዲሳተፍ ንቅናቄ እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፡- ሁሉም የንግዱ ማኅበረሰብ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በስፋት እንዲሳተፍ ንቅናቄ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፤ ከአዲስ አበባ፤ ከሸገር ከተማ እና ከኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጋር በመሆን በትናንትናው ዕለት በእንጦጦ ተራራ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የችግኝ ተከላ አካሂዷል።

ወቅት የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰብስብ አባፍራ አባጆብር እንደተናገሩት፤ ምክር ቤቱ በንግድ ዘርፍ የተሰማሩ አካላት በእኔነት ስሜት በመሥሪያ ቤታቸው፤ በቤታቸው እንዲሁም፤ ከከተማ መስተዳድሮች ቦታ ጠይቀው በችግኝ ተከላ በስፋት እንዲሳተፍ የንቅናቄ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

የንግዱ ማኅበረሰብ በሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ሁሉ መንግሥት ቀርፆ ተግባራዊ በሚያደርጋቸው ሀገራዊ ፖሊሲዎችም ውስጥ ተሳትፎው የጎላ መሆኑን የገለጹት አቶ ሰብስብ፤ የግሉ ዘርፍ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የንግድ ዘርፍ ማኅበሩ ከሚያከናውናቸው ማኅበራዊ ጉዳዮች አንዱ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በስፋት መሳተፍ መሆኑን ጠቁመው፤ የተተከሉ ችግኞችን በኃላፊነት በየጊዜው መንከባከብ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሐምሌ አምስት እንደ ሀገር የንግዱ ዘርፍ በጋራ ወጥቶ ችግኝ የሚተክልበት ቀን እንዲሆን መወሰኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፤ በዚህ መሠረት በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ ከ516 በላይ የንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ችግኝ መትከላቸውን አስረድተዋል። የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱል ሐኪም ሙሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የንግዱ ማኅበረሰብ ተፈጥሮን መንከባከብ የራሱ ኃላፊነት እንደሆነ በመገንዘብ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በንቃት እየተሳተፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ሦስት ዋና ዋና ጠቀሜታዎች እንዳሉት ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ከአካባቢ ጥበቃ አንጻር የአየር ለውጥን ለመቋቋም የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው። ከኢኮኖሚ ጋር ተያይዞም ዘላቂ ልማት እና አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በኢኮኖሚ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የሀገር ገቢን የተሻለ ለማድረግ እና ድህነትን ለመቀነስ የሚያስችል ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ለመኖር ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ማኅበራዊ ትስስር ያጠናክራል ሲሉ ተናግረዋል።

የንግዱ ማኅበረሰብ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በርካታ ችግኞችን መትከል እና መንከባከብን ባህል እንዲያደርግ እንደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት እየተሠራ መሆኑን በመጠቆም፤ በመርሐ ግብሩ ለሚሳተፉ የግል ዘርፍ አካላትም ምስጋናቸውን አስተላልፈዋል።

በዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You