ባለፈው አርብ ሚያዝያ 27 ቀን 2015 ዓ.ም 82ኛው የአርበኞች ቀን በአራት ኪሎ የድል አደባባይ ተከብሯል:: ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ክስተቱን የሚያስታውሱ የታሪክና የኪነ ጥበብ ሥራዎች ቀርበዋል:: በማግስቱ በነበሩት የቅዳሜና እሁድ የመገናኛ ብዙኃን የመዝናኛ ፕሮግራሞች ክስተቱን የሚያስታውሱ ዝግጅቶች ቀርበዋል::
እዚህ ላይ ታዲያ ብዙ ጊዜ ልብ የማይባሉትና ትኩረት የማይሰጣቸው የሕዝብ የሆኑት የሥነ ቃል የጥበብ ሥራዎች ናቸው:: በመገናኛ ብዙኃኑ ሲደጋገም የሚታየው ወቅታዊ የሆኑ ክስተቱን አስመልክቶ የሚዘጋጁ የጥበብ ሥራዎች ናቸው:: አዎ! እነርሱ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል:: ሆኖም ግን ለእነዚህ ሁሉ መነሻ የሆኑት የሕዝብ የሥነ ቃል ሥራዎችም አብረው ሊታወሱ ይገባል:: እስኪ ጀግንነት በባህላችንና በሕዝብ የጥበብ ሥራዎች እንዴት ሲገለጽ እንደኖረ የቻልነውን ያህል እንሞክር!
ጀግንነት በኢትዮጵያ ውስጥ ልዩ ቦታ ያለው ይመስላል:: በወቅታዊ የጥበብ ሥራዎች ብቻ ሳይሆን የአንድን ማኅበረሰብ ምንነት በሚያሳየው ባህል ውስጥ ራሱ ይታያል:: ጀግንነት ባህላችን ነው:: ለዚህም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ባህሎችን ልብ ብንል በቂ ምስክር ናቸው:: ከጥንታዊው የአደን ሕይወት ጀምሮ ዛሬ ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ጀግንነት ከባህል ጋር የተሳሰረ ነው:: ከዘመን ዘመን የተለያየ ቢሆንም ዛሬም ድረስ ጀግንነት ትልቅ ዋጋ ያለው ነው:: ለምሳሌ በቀድሞው ጊዜ ‹‹አንበሳ ገዳይ፣ ነብር ገዳይ›› እየተባለ ይሞገስ ነበር:: አነጣጥሮ ዒላማውን የሚመታ ሰው ‹‹ተኳሽ›› እየተባለ ይጠራ ነበር::
እንደየዘመኑ የተለያየ መሆኑን የምናውቀው ደግሞ አሁን ላይ በምናየው የጀግንነት ትርጉም ነው:: ለምሳሌ በገጠር አካባቢ አንድ አርሶ አደር ለእርሻ አስቸጋሪ የሆነን ማሳ አለሳልሶት ከታየ ‹‹እገሌ እኮ ጀግና ነው›› ይባላል:: በዝናብ ሰብል ሲያርም የታየ ገበሬ ‹‹አይ ጀግንነት›› እየተባለ ሲሞገስ ይሰማል:: በትምህርት ቤት እንኳን ብንሄድ አንደኛ የሚወጣ ተማሪ ‹‹የእገሌ ልጅ ጀግና እኮ ነው›› ይባላል፤ በጓደኞቹ ዘንድም ትልቅ ክብር ይሰጠዋል::
ሌላው ጀግንነት በኢትዮጵያ ውስጥ ባህል መሆኑን የምናውቀው በሠርግ እና በሌሎች የድግስ ጉዳዮች ላይ ሲጫወቱ የሚወዳደሱት ጀግንነትን መሠረት በማድረግ ነው:: የድሮ አባቶችን ገድል መዘከር ብቻ ሳይሆን የአሁን ልጅም ጀግና መሆን እንዳለበት ይጠቁማሉ:: አባቴ ጀግና ነበር ማለት ብቻ ሳይሆን ራሱ ሠርቶ ማሳየት እንዳለበት ለመጠቆም እንዲህ እየተባለም ይዘፈናል::
አርገው ሞቅ ሞቅ እንደ ደሬ ፍም
የአባት ጀግንነት ለልጅ አያልፍም!
ደሬ የሚባለው የዛፍ ዓይነት ነው፤ ሲደርቅ ማገዶ ይሆናል:: የደሬ እንጨት ፍሙ ቶሎ አይጠፋም:: ለዚህም ነው ደሬ የተባለውን እንጨት የመረጡት::
የእረኞችን ጨዋታ እንኳን ብናስተውል በማሸነፍና በመሸነፍ ላይ የተመሠረተ ነው:: ድንጋይ በማቆም ዒላማ መጫወት ነው:: ከርቀት ሆኖ የቆመውን ድንጋይ በተወርዋሪ ድንጋይ መምታት የጀግንነት ምልክት ነው:: እረኞች ከኮባ ወይም ከሸንበቆ የተዘጋጀ ጠመንጃ መሰል ነገር መያዝ ይወዳሉ:: ይሄ እንግዲህ ከአካባቢያቸው ሁኔታ ተነስተው የሚያደርጉትና የተለመደ ነው::
ጀግንነት ባህልም ጥበብም ነው:: በጦርነት ታሪክ ውስጥ በተለይም ኢትዮጵያውያን በጥበብ እንደሚያሸንፉ በብዙ የታሪክ ጸሐፍት ተጽፏል:: ታላቁን የዓድዋ ድል እንኳን ብንወስድ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የታጠቀው የጣሊያን ሠራዊት በጦር፣ በጎራዴና በኋላቀር መሣሪያ ነው ዓለም አቀፍ ውርደትን የተከናነበው:: ለዚህም ኢትዮጵያውያን አርበኞች የተጠቀሙት ጥበብ ነው:: ባለፈው አርብ ባከበርነው የአርበኞች ቀን ድል እንኳን ብዙ ጥበብ የተሞላባቸው አሸናፊነቶችን መጥቀስ እንችላለን:: ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983›› በሚለው በታሪክ ተመራማሪው ባህሩ ዘውዴ መጽሐፍ ላይ ተጽፎ እንደምናገኘው ራስ አበበ አረጋይ ይህን ስልት ተጠቅመው ነበር::
በ1932 ዓ.ም ራስ አበበ አረጋይ ለጣሊያን ‹‹እጄን ሰጥቻለሁ›› በማለት አጃጅሏቸው ነበር:: ይህ መጭበርበር የደረሰበትም ምክትል እንደራሴና የሸዋ ገዥ የነበረው ጄኔራል ናዚ ነበር:: ራስ አበበ አረጋይ ለናዚ ‹‹እጄን ሰጥቻለሁ›› በማለት ለአርበኞች ጓደኞቹ ‹‹አይዟችሁ እንዲህ እያልኩ እያታለልኳቸው ነው›› እያለ ይልክባቸው ነበር:: ናዚም ምንም ሳይጠረጥር እውነት መስሎት የሰላም ድርድሩን ተያያዘው:: በኋላም ራስ አበበ አረጋይ ጦሩ ቀደም ሲል የደረሰበትን ጥቃት ማገገሙን ሲያረጋግጥ ጣሊያንን ‹‹ዞር በል!›› በማለት ትግሉን ቀጠለ::
ሌላኛው የጦርነት ስልታቸው ደግሞ በወቅቱ የማይጠረጠሩትን ሴቶችን ማሰለፍ ነበር:: ለዚህም እነ ሸዋረገድ ገድሌና አርበኛ ከበደች ሥዩም ተጠቃሽ ናቸው:: በዓድዋው ጦርነትም የእቴጌ ጣይቱን ጥበብ ተደጋግሞ መጠቀሱን ልብ ይሏል:: የጣሊያን ምርኮኛ መስለው የሠራዊቱን ጥንካሬና ድክመት ያጠኑ የነበሩ ሰላዮችም ነበሩ::
በሌላ በኩል ደግሞ በተለያየ መንገድ ያታልሏቸው ነበር:: በወቅቱ ኢትዮጵያውያን በባዶ እግራቸው የሚሄዱም ስለነበሩ የእግራችንን ዳና እየተከተለ ጠላት ያጠቃናል ብለው የጠረጠሩ አርበኞች አንድ ዘዴ ፈጠሩ:: ለምሳሌ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ መሄድ ፈልገው ከሆነ የእግር ዳና በመፍጠር ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ ይሄዳሉ:: ከዚያም የእግር ዳና ሳይፈጥሩ ወደ ምዕራብ ይመለሳሉ:: ጠላት ወደዚያ ነው የሄዱ መስሎት ዳና ተከትሎ ሲሄድ ከኋላ ያጠቁት ነበር::
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የጀግንነትን ነገር እናንሳ ከተባለ እያንዳንዷ ዕለት ጀብዱ የተፈጸመባት ትሆናለች:: ዳሩ ግን ሦስት ቀኖች ደግሞ በተለየ መልኩ ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው ናቸው:: የካቲት 12፣ የካቲት 23 እና ሚያዝያ 27 በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ልዩ ቦታ አላቸው:: የካቲት 12 ግፈኛው ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያውያንን የጨፈጨፈበት ሲሆን የካቲት 23 እና ሚያዝያ 27 የድል ቀኖች ናቸው:: በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያላቸው እነዚህ ሦስት ቀናት ሁሉም ከጣሊያን ወራሪ ጋር መሆናቸው ነው::
እነዚህን ሁሉ ድሎች ከየት አመጣናቸው ከተባለ፤ ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ የኢትዮጵያ ባህል ስለሆነ ነው:: ለዚህም ነው የጥበብ ሥራዎቻችን ጀግንነትን ገላጭ የሆኑት:: እነዚህ የጥበብ ሥራዎች የሕዝብ ናቸው:: የመድረክ ቴአትሮች ወይም ፊልሞች ቢሆኑ ኖሮ ከእነዚህ ድሎች በኋላ የታሰበ ሊመስለን ይችል ነበር:: እንዲያውም ፊልሞቻችን ናቸው ሕዝባዊ የጥበብ ሀብቶቻችንን መነሻ አድርገው የተሠሩት::
የአርበኞች ቀን የተለያዩ ታሪካዊ ክስተቶችን በማስታወስ ይከበራል:: ታሪኩን በ‹‹ሳምንቱን በታሪክ›› ዓምዳችን አስታውሰነዋል፤ በዚህ ዓምድ ደግሞ አርበኝነትን የሚገልጹ የሕዝብ ቃል ግጥሞችን እናስታውሳለን ማለት ነው::
የኢትዮጵያ ጀግኖች ስማቸው ሲነሳ
በሩቅ ያስፈራሉ እንደ ዱር አንበሳ
ይህ የአርበኝነት ስንኝ በተለይም በዘፈኖች ውስጥ ነው የሚሰማው:: ምናልባትም መነሻው የሕዝብ ሆኖ ይሆናል በብዙ የአርበኝነት ዘፈኖች ውስጥ እንሰማዋለን፤ እንዲህ እንደ አርበኞች ቀን ዓይነት የድል በዓላት ሲከበሩ ደግሞ በቡድን በቡድን ሆነው በሕብረ ዝማሪ ይጫወቱታል::
በኢትዮጵያ ውስጥ ጀግንነት ባህል ነው ብለናል:: ኢትዮጵያዊ መደፈርን አይቀበልም፤ ይህ መደፈርን ያለመቀበል ባህል ነው ወራሪን ሁሉ እያሳፈረ የመለሰ:: ለዚህ የጀግንነት ባህል ደግሞ ፉከራዎቻችን ምስክር ናቸው:: ትዕግስትንም ይችልበታል፤ ታግሶ ታግሶ ካልሆነ ግን ልኩን ያሳየዋል::
እልም ነው ውሃ አይላመጥም
ጠላት ወዳጅ ላይሆን አልልመጠመጥም!
ይህ ስንኝ የሚነግረን ጠላትን መለማመጥ ብቻ ለውጥ እንደማያመጣ ነው:: የፈሩኝ ከመሰለው ጭራሽ እየባሰበት ነው የሚሄድ:: በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ የጀግንነት ባህል ውስጥ ፀብን ቀድሞ መጀመር የፈሪ ምልክት ነው:: ጀግና ማለት በትዕግስት የሚያሸንፍ ነው:: ለዚህም ነው ጀግንነትን ከነብር ጋር ያመሳስሉታል::
ቆራጥ ጎበዝ እና ነብር አንድ ናቸው
ሰው ደርሰው አይነኩም ካልደረሱባቸው!
ነብር በባህሪው እንደ ሌሎች እንስሳት ቀድሞ የመተናኮል ባህሪ የለውም፤ ከተተናኮሉት ግን አይለቅም:: የጦር መሣሪያ የያዘ ሰው ሳይቀር ይተናነቃል:: የጀግንነት መጀመሪያው ፀብን ቀድሞ አለመጀመር መሆኑን ለመግለጽ ነው ነብርን ተምሳሌት ያደረጉት::
ተመክሮ ተመክሮ አልመለስም ያለ ጠበኛ ዋጋውን ማግኘት እንዳለበት ያምናሉ:: ዳግም እንዳያስበው አድርገው አይቀጡ ቅጣት መቀጣት እንዳለበት ነው የሚያምኑት፤ ለዚህም ይመስላል እንዲህ እያሉ የሚያንጎራጉሩት::
በክላሽ መንጥሮ በምንሽር ማረስ
አረም አያበቅልም እስከወዲያው ድረስ
ከዕለት ከዕለት ሥራዎቻቸው ጋር አገናኝተው ይገልጹታል ማለት ነው:: ምንጣሮ ማለት ለእርሻ የሚሆን ማሳ ዛፎችንና ሌሎች ነገሮችን ማንሳት ማለት ነው:: በሚገባ ተለሳልሶ የታረሰ መሬት አረሙ አያስቸግርም:: በዚህ ቅኔ ሲገልጹት እንግዲህ፤ በክላሽ መንጥረን መንጥረን ከጣልነው ድጋሜ አያንሰራራም ማለታቸው ነው::
እነዚህ ጀግኖች አስቀድመው ‹‹ተው ሰላም ይሻለናል›› ብለው የሚለማመጡ ናቸው:: የፈሪ ባህሪ ግን ሲታገሱት የፈሩኝ ይመስለዋል::
ኧረ ተው አንተ ሰው ስሸሽ አታባረኝ
ለአንተም ግፉ በዛ እኔንም መረረኝ!
ይለዋል:: ይህን ብሎት ካልተመለሰ የግፉን ዋጋ ያገኛል ማለት ነው:: አንዳንድ ፈሪ የሆነ ነገር ስላለው ብቻ የሚፈራ ይመስለዋል:: ምናልባት የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ስላለ የሚፈራ ይመስለውም ይሆናል:: ለዚህ ደግሞ ቆራጡ ድሃ እንዲህ ይላል::
አትንኳት ጎጆዬን በአንድ እግሯ ቆማለች
ትልቁን አዳራሽ ይዛው ትጓዛለች!
ይላል:: አንተ ሀብታም ነኝ ብለህ ብትመጻደቅም ሌሎችን ካላከበርክ ያንተ ቤትም ይፈርሳል፤ እንዲያውም ከእኔ በላይ አንተ ትጎዳለህ ማለቱ ነው::
አሁን ደግሞ ከሕዝብ ሥነ ቃል እንውጣና ከጣሊያን ፋሽስት ጋር የተያያዙ ግጥሞችን እንጠቃቅስ:: እነዚህ ግጥሞችም መነሻቸው የኢትዮጵያ የጀግንነት ባህል ነው:: ግጥሞቹን ከተክለጻድቅ መኩሪያ የታሪክ መጽሐፎች ላይ ያገኘናቸው ናቸው::
ጥሊያን ኮሶ ጭኖ ሸዋን ሊያጠጣው
ገና ሲበጠብጥ ዳኘውን ቀናው
ቅዳሜ ተግዞ እሁድ ተበራየ
መስኮብም ገረመው ጣሊያንም ጉድ አየ!
አገርክን ምኒሊክ እንዳሁን ፈትሻት
ባያይህ ነውና ጠላትህ የሚሻት!
እነዚህ በዓድዋ ጊዜ የተገጠሙ ስንኞች በአምስት ዓመቱ የጣሊያን ወረራ ጊዜ ለኢትዮጵያ አርበኞች ትግል ወኔ ሆነዋል:: ጣሊያን ለ40 ዓመታት ያህል ተዘጋጅታ ስትመጣ ‹‹እስኪ ያንኑ የለመደችውን መድኃኒት (ጎራዴና ጥይት) ስጧት›› ተብሏል::
እስኪ ለጣሊያኖች መድኃኒት ስጧቸው
የሚያስቀምጥ ሳይሆን የሚያስመልሳቸው
በማለትም ኢትዮጵያውያን ተቀኝተዋል:: ጣሊያኖችም በድጋሜ በመጣ እግራቸው ተመልሰዋል:: ሲመለሱም ቆሳስለው ነው::
የሞሶሎኒ አሽከሮች ሁሉም ሎጋ ሎጋ
ሲመጡ በፈረስ ሲመለሱ በአልጋ
ተብሎላቸዋል:: የሞሶሎኒ አሽከር የነበሩት እነ ግራዚያኒ በጀግኖች በእነ ሞገስ አስገዶምና አብርሃም ደቦጭ ቦምብ ተጥሎባቸው ቆሳስለው ነው የተመለሱት::
በአርበኞች ቀን የሚታወሱት በአምስት ዓመቱ የጣሊያ ወረራ ጊዜ የተሳተፉት ብቻ አይደሉም:: በአጠቃላይ ኢትዮጵያን ያስከበሩ ጀግኖች ናቸው:: ስለዚህ በአርበኞች ስም ሁሉንም እያመሰገንን ከተወደሱባቸው ስንኞች በሚከተሉት እንሰናበታለን::
በሠራው ወጨፎ ባመጣው እርሳስ
ተፈፀመ ጣሊያን ሐበሻ እንዳይደርስ
ጣሊያን ሰሀጢ ላይ እግሩን ቢዘረጋ
እንደ ገብስ ቆላው አሉላ አባ ነጋ
ዮሐንስ መብቱን ላሉላ ቢሰጠው
እንደ ቀትር እሳት ቱርክን ገላመጠው
ጣልያንም ወደቀ እያንቀጠቀጠው
አጭዶና ከምሮ እንደ ገብስ አሰጣው!
አሉላ አባነጋ የደጋ ላይ ኮሶ
በጥላው ያደክማል እንኳንስ ተኩሶ!
አሉላ አባነጋ ካስመራ ቢነሳ
ቢቸግረው ጣሊያን አለ ፎርሳ ፎርሳ::
ጣሊያን በሀገርህ አልሰማህም ወሬ?
የበዝብዞች አሽከር የነ ሞት አይፈሬ
ዘለው ጉብ ይላሉ እንደ ጎፈር አውሬ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ግንቦት 3/2015