በዚህ ሳምንት ባለፈው ዓርብ የአርበኞች ቀን አክብረናል። በዚሁ ሳምንት ደግሞ የዓድዋው ጦርነት መነሻ ሰበብ የነበረው የውጫሌ ውል ይታወሳል። እነዚህን ሁለት ታሪኮች ዘርዘር አድርገን ከማስታወሳችን በፊት በዚህ ሳምንት ሚያዚያ 23 ቀን ተከብሮ የዋለውን የላብ አደሮች ቀን በጥቂቱ እናስታውስ፡፡
ቀኑ የተለያዩ ስያሜዎች አሉት። የላብ አደሮች ቀን ይባላል፣ የወዝ አደሮች ቀን ይባላል፣ የሠራተኞች ቀን ይባላል። የሁሉም ቃላት ትርጉሞች ተመሳሳይ ናቸው። በብዛት የላብ አደሮች ቀን በመባል የሚታወቅ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ለመደበኛ አገላለጽ የሠራተኞች ቀን ሲባል በተለምዷዊ አገላለጾች ደግሞ የላብ አደሮች ቀን ይባላል። በውጭዎች ደግሞ May day እና Labor day በመባል ይታወቃል፡፡ የላብ አደሮች ቀን ማለት የሠራተኞች ቀን ማለት ነው፤ በላቡ ሰርቶ የሚያድር ማለት ነው። በተለይም በገጠር አካባቢ ‹‹ላቤን ጠብ አድርጌ›› ሲሉ ይሰማል፤ የለፋሁበት ነው ማለታቸው ነው። ወዝ አደር ማለትም ይሄው ነው፤ ወዝ የሚባለው ላብ ነው፡፡
የ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ፤ ሠራተኛው መደብ በቀን የሚሠራበት ሰዓት ከስምንት ሰዓት እንዳይበልጥ ከፍተኛ ትግል ማድረግ የጀመረበት ወቅት ነበር:: በዘመኑ በቀን ከ10 እስከ 16 ሰዓት ለሥራ ምቹ ባልሆኑ አካባቢዎች ለአደጋ ተጋልጦ መሥራት የተለመደ ጉዳይ ነበር:: በሥራ ላይ በሚደርስ አደጋ ሕይወትን ማጣት፣ አካል መጉደል፣ ለዘላቂ የጤና ችግር መዳረግም የተለመዱ ሁኔታዎች እንደነበሩ በርካታ የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ:: በካፒታሊስት አገሮች የተጀመረው የሠራተኛው መደብ የመብት መጠየቅ እንቅስቃሴ በኋላ ላይ የሶሻሊስት ሥርዓት አቀንቃኞች ማታገያ ሆነ። በአገራችንም መከበር የጀመረው ከደርግ ሥርዓት በኋላ ነው። እነሆ ከእነዚያ እንቅስቃሴዎች በኋላ የላብ አደሮች ቀን በዓለም አቀፍና በሀገራችን በየዓመቱ ሚያዚያ 23 ይታወሳል።
ዳግማዊው ድል
ባለፈው ዓርብ ሚያዚያ 27 የአርበኞች ቀንን አክብረናል። ይህ የአርበኞች ቀን በጀግኖች አባቶቻችን ተጋድሎ ዳግም የተገኘ ድል ነው። በዓድዋ ጦርነት ሽንፈት የተከናነበው ጣሊያን ለ40 ዓመታት ያህል ዝግጅት አድርጎ ዳግም ወረራ ሞክሮ ነበር። ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በለመዱት የጀግንነት ስልትና ወኔ ባደረጉት ተጋድሎ ነፃነታቸውን አስከብረዋል። በዛሬው የሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ይህን ድል ነው የምናስታውስ። የተክለ ጻድቅ መኩሪያ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ›› የባሕሩ ዘውዴ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983›› መጽሐፎችን እና የተለያዩ ድረ ገጾችን በምንጭነት ተጠቅመናል።
ኢትዮጵያ ከ82 ዓመታት በፊት በአምስት ዓመቱ የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ሰንደቅ ዓላማዋ ከታጠፈ፣ ሉዓላዊነቷ ከተደፈረ 5 ዓመታት በኋላ ነፃነቷን ያስመለሰችው ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ በ11 ሰዓት ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ በአርበኞች ብርታትና መስዋዕትነት የጣሊያንን ባንዲራ አውርደው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በታላቁ ቤተ መንግሥት ሲሰቅሉ ነው፡፡የሚያዝያ 27 የንጉሠ ነገሥቱ አዲስ አበባ ገብቶ ሰንደቅ ዓላማ መስቀል ሌላው ታሪካዊነቱ ከአምስት ዓመታት አስቀድሞ ሚያዝያ 27 ቀን 1928 በዚያው ቀን ወደ ኢትዮጵያ የዘመተው የጣሊያኑ ጦር አዛዥ ጄኔራል ባዶሊዩ አዲስ አበባ ገብቶ በታላቁ ቤተ መንግሥት የጣሊያንን ባንዲራ የሰቀለበት ቀን መሆኑ ነው። ጣሊያን ከዓድዋ ሽንፈቷ 40 ዓመታት በኋላ በዘመናዊ የጦር መሣሪያና በወታደራዊ ኃይል ይበልጥ ደርጅታ ኢትዮጵያን ከሦስት አቅጣጫዎች ወረረች። ከዓድዋው ዘመቻ ያልተሻለ የጦር ትጥቅ የነበራት ኢትዮጵያም የጣሊያንን ጦር በፅናት ተዋጋች፡፡ የወቅቱ ኃያላን እንግሊዝና ፈረንሳይ የጦር መሣሪያ በግዢ እንዳታገኝ ለጣሊያን ተደርበው ስላሴሩባት ኢትዮጵያ ብቻዋን ጦርነቱን በመጋፈጧ ድል ማግኘት አልቻለችም ነበር፡፡
የየግንባሮቹ የኢትዮጵያ የጦር አዛዦች ብዙዎቹ ሞተው ሠራዊቱም በመርዝ ጋዝና በአውሮኘላን ቦምብ ተደብድቦ ያለቀው አልቆ የቀረው ቀርቶ ጣሊያን ጊዜያዊ ድል አግኝታ ዋና ዋና ከተሞችን ብትቆጣጠርም ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በገጠሩ ክፍል እምቢ ለነፃነቴ፣ እምቢ ለአገሬ ብለው የሽምቅ ውጊያ ጀመሩ። ንጉሠ ነገሥቱም ስደት ሄደው በጊዜው ለነበረው የመንግሥታቱ ማኅበር(ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) አቤቱታ አቀረቡ። የሚሰማቸው ግን አላገኙም። የኢትዮጵያ አርበኞች ግን ከቀን ወደ ቀን ድል እየተቀዳጁ የጣሊያን ወታደሮችን መፈናፈኛ ፤ መግቢያ መውጫ አሳጧቸው።
ከጣሊያን ወታደሮች ይማርኳቸው በነበሩ መሣሪያዎች ራሳቸውን እያደራጁ አብዛኛውን የገጠር ክፍል ተቆጣጠሩት፡፡ በዚህ መሐል እንግዲህ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መቀስቀስ ለኢትዮጵያ ትልቅ ቦታ ነበረው። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲቀሰቀስ ጣሊያን የናዚ ጀርመን አጋር ሆነች። ያን ጊዜ እንግሊዞች የጣሊያን ጠላት ሆነው ኢትዮጵያን መደገፍ ጀመሩ።
ወታደራዊ ድጋፍ ሰጥተው፤ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ እረዷቸው፡፡ በጄኔራል ካኒንግሂም የሚመራው የእንግሊዝ ጦር ከኬንያ ተነስቶ በደቡብ አቅጣጫ ወደ መሐል ኢትዮጵያ ሲገሰግስ ፤ በጄኔራል ፕላት የሚመራው ጦር ከሱዳን ተነስቶ ወደ አሥመራ፤ ከዚያም በሰሜን አቅጣጫ ወደ መሐል ኢትዮጵያ ተንቀሳቀሰ፡፡
በቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ የሚመራውና የአርበኞችና የእንግሊዝ አማካሪዎች የሚገኙበት ‹‹ጌዲዮን›› ተብሎ የተሰየመው ጦር ከሱዳን ተነስቶ በኦሜድላ አልፎ በጐጃም በኩል ወደ መሐል አገር ገሠገሠ፡፡ በመካከለኛው ኢትዮጵያ አርበኞች በጣሊያን ወታደሮች ላይ ጥቃታቸውን አፋፋሙ፡፡ ጣሊያኖች ክፉኛ ተሸነፉ። በየቦታው ድል የመሆናቸው ዜና ናኘ፡፡ ዘመቻው ከተጀመረ ሁለት ወራት ሳይሞላው፤ ጣሊያኖች አዲስ አበባን ለቀው ፈረጠጡ፡፡ መጋቢት 28 ቀን 1933 ዓ.ም የጄኔራል ካኒንግሃም ጦር አዲስ አበባን ተቆጣጠረ፡፡
እንግሊዞች ኢትዮጵያውያን አርበኞች ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ስላልፈለጉ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴን በደብረ ማርቆስ ለአንድ ወር ያህል እንዲቆዩ አደረጓቸው። ይሁንና በአዲስ አበባ በአርበኞች ተፅዕኖና ቅሬታ የተነሳ አርበኞች ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ፈቀዱ። አፄ ኃይለ ሥላሴም ወደ አዲስ አበባ እንዲጓዙ ፈቀዱ። ንጉሠ ነገሥቱም አዲስ አበባ በታላቁ ቤተ መንግሥት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ሰቀሉ። አዲስ አበባ ገብተውም የሚከተለውን ንግግር አደረጉ።
‹‹ይህ የምትሰሙት ድምጽ የኔ የንጉሣችሁ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ነው። አባቶቻችን ደማቸውን አፍሰው አጥንታቸውን ከስክሰው በነፃነት ያቆዩልን አገራችንን ወደ ከፍተኛው የሥልጣኔ ደረጃ ለማራመድ የምንደክምበት ጊዜ ከጥንት ጀምሮ ስለሆነ ደመኛ ጠላታችን ኢጣሊያ ይህንን እይታ ወሰናችንን ጥሳ የግፍ ጦርነት እንዳደረገችብን ሁላችሁም የምታውቁት ነው። እኛም በተቻለን ከተከላከልን በኋላ ርዳታ ለመጠየቅ ወደ መንግሥታት ማኅበር ወደ ወዳጆቻችን መንግሥታቶች መጣን፤ እዚህ ስንነጋገር በቆዬንበት ጊዜ የኢትዮጵያ አርበኞች ሰይፋችሁን ሳትከቱ ፊታችሁን ሳትመልሱ ሰንደቅ ዓላማችሁን ሳታጥፉ ለባዕድ አንገዛም በማለት በመሣሪያ ብዛት ከሚበልጣችሁ ጨካኝ ጠላት ጋር የባሕርይ የሆነውን ጀግንነታችሁን መሣሪያ አድርጋችሁ በኢትዮጵያ አምላክ ብቻ ተማምናችሁ በጀግንነት ቀንና ሌሊት በዱር በገደል ስትጋደሉ ቆይታችሁ ይኸው አሁን እንደምታዩት የማያቋርጥ የአምስት ዓመት ትግላችሁ የድካማችሁንና የመስዕዋታችሁን ፍሬ ለማየት እንድትበቁ አደረጋችሁ።
የሀገሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ!
ዛሬ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ዘርግታ እልል እያለች ምስጋናዋን የምታቀርብበት ደስታዋንም ለልጆቿ የምትገልጽበት ቀን ነው። የኢትዮጵያ ልጆች ከባድ የመከራ ቀንበርና ከዘለዓለም ባርነት ነፃ የወጡበት ቀንና እኛም አምስት ዓመት ሙሉ ተለይተነው ከነበረው ከምንወደውና ከምንናፍቀው ሕዝባችን ጋር ለመቀላቀል የበቃንበት ቀን ስለሆነ ይህ ቀን የተከበረና የተቀደሰ በየዓመቱም ታላቁ የኢትዮጵያ በዓል የሚውልበት ነው። በዚህም ቀን ለሚወዷት ለሀገራቸው ነፃነት ለንጉሠ ነገሥታቸውና ለሰንደቅ ዓላማቸው ክብር ካባቶቻቸው የተላለፈውን ጥብቅ አደራ አናስወስድም በማለት መስዋዕት ሆነው ደማቸውን ያፈሰሱትን አጥንታቸውን የከሰከሱትን ጀግኖቻችንን እናስታውሳለን። ለዚህም ለጀግኖቻችን የኢትዮጵያ ታሪክ ምስክር ይሆናል።
ባለፈው አምስት ዓመታት ውስጥ በዝርዝር ተነግረውና ተቆጥረው የማያልቁ ያገኘናቸው መከራና ስቃይ ትምህርት ሆነውን ሠራተኛነት አንድነት ኅብረትና ፍቅር በልባችሁ ተጽፈው ለምናስበው ለኢትዮጵያ ጉዳይ ረዳቶች ለመሆን ዋና ትምህርት የሚሰጣችሁ ነው። ባዲሷ ኢትዮጵያ ከእንግዲህ ወዲያ የማትነጣጠሉ በሕግ ፊት ትክክልና ነፃነት ያላችሁ ሕዝቦች እንድትሆኑ እንፈልጋለን። አገር የሚለማበትን ሕዝብ የሚበለጽግበትን እርሻ፣ ንግድ፣ ትምህርትና ጥበብ የሚሰፋበትን የሕዝባችን ሕይወቱና ሀብቱ የሚጠበቅበትን የሀገር አስተዳደርም ባዲሱ ሥልጣኔ ተለውጦ ፍጹም የሚሆንበትን ይህን ለመሰለው ለምንደክምበት ሥራ አብሮ ደካሚ መሆን አለባችሁ።
የኢጣሊያ መንግሥት ኢትዮጵያን ድል አድርጎ ለመያዝ ችሎት ከሰጠው መሣሪያ በቀር ኢትዮጵያን ለመግዛት ሌላ ተስፋ ያደረገው ነገር ነበር ይኸውም የኢትዮጵያ የነገድ ልዩነት ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ እርሱ ሀሳብ አንደኛው ወገን ከሴም ዘር የመጣው የትግሬና የሸዋ፣ የጎጃም፣ የበጌምድር፣ በጠቅላላው አማራ የሚባለው፣ ሁለተኛው በኢትዮጵያ ምዕራብና ደቡብ የሚገኙትን እነወለጋ፣ እነጅማ፣ እነሲዳማ፣ እና አሩሲ እነዚህን የመሳሰሉት አገሮች ከካም ዘር የመጡ በነገድም በቋንቋም በሃይማኖትም የተለያዩ ናቸው። አንደኛው ወገን ቢያምጥብኝ ሁለተኛውን ወገን ይዤ አጠፋዋለሁ የማለት ተስፋ ነበረውና ይህንንም ሊሠራበት እንደጣረ በጉልህ ታይቷል። ዳሩ ግን የ3ሺህ ዓመት ባለው የነፃነቱ ዘመን በታሪኩ ውስጥ ምንም የሚያሳፍር ገጽ የሌለበት የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነቱን አሳይቶ ለጠላቱ ሳይመች ቀረ።›› ብለው ነበር ንጉሡ፡፡
ይሄ የኢትዮጵያውያን የድል ብስራት የሆነው የአርበኞች ቀን ከፍተኛ ዋጋ የተከፈለበት ነው። በዚህ ጦርነት ውስጥ ምላጭ ስቦ ጥይት ከተኮሰው አርበኛ በተጨማሪ በየቤቱ ሆኖ የተባበረውም ቀላል አልነበረም። በትግሉ ጊዜ የአርበኞች ዋናው ችግር ቀለብ ነበር። ቀለባቸውን የሚያገኙትም ከአርሶ አደሩ ቤት ነው። ይሄ ነገር የሚሆነው ታዲያ በግድም በውድም ነበር። ፈቃደኛ የማይሆን አርሶ አደር ካለ ፋኖ እስከማሰማራትም ተደርሶ ነበር። በተለይም ከጠላት ጋር የሚያብሩ ሰዎችን ደግሞ እህላቸው እንዲዘረፍና ለሠራዊቱ ቀለብ እንዲሆን ተደርጓል።
ሠራዊቱ ‹‹ደረቅ ጦር›› እና ‹‹መደዴ ጦር›› ተብሎ ለሁለት ተከፍሎም ነበር። ደረቅ ጦር የተባለው ሙሉ በሙሉ ውጊያ ላይ የሚያተኩር ሲሆን ‹‹መደዴ ጦር›› የተባለው ደግሞ እንደሁኔታው የእርሻ ሥራ ላይ እንዲሠማራ ይደረጋል። ነገሩ ሲከፋ ግን አርበኞች ፍራፍሬ፣ ቅጠላቅጠልና የዱር አውሬ ሁሉ እየበሉ ተዋግተዋል። እናቶች ከሠራዊቱ ጋር አብሮ በመዝመት ምግብና ውሃ ከማቀበል በተጨማሪ ባሕላዊ ሕክምና እየሰጡ ሠራዊቱን ታድገዋል። የወደቀውን በማንሳት የቆሰለውን በመጠገን ተሳትፈዋል። ይህ የአርበኞች ቀን የሁሉም ኢትዮጵያዊ የተጋድሎ ድል ነው ማለት ይቻላል።
የውጫሌ ውል 133ኛ ዓመት
በዚህ ሳምንት የሚታወሰው ሌላኛው ክስተት ከ134 ዓመታት በፊት ሚያዚያ 25 ቀን 1881 ዓ.ም የተፈረመውና ለዓድዋ ጦርነት ሰበብ የሆነው የውጫሌ ውል ነው።
የውጫሌ ውል በአሁኗ አምባሰል ወረዳ ውጫሌ በምትባል ቦታ በአጼ ምኒልክና በጣሊያኑ ንጉሥ ኢምቤርቶ ተወካይ ኮንት አንቶሎኒ መካከል ተፈረመ። ውሉ 20 አንቀጾች ያሉት ሲሆን ከእነዚህ አንቀጾች ውስጥ ሰበበኛዋ አንቀጽ 17 ለጣሊያን የውርደት ካባ ያለበሰውን የዓድዋን ጦርነት አስከተለች፤ ለኢትዮጵያውያን ደግሞ ድል በማጎናጸፍ የጥቁርን ጀግንነት ያስመሰከረ ክስተት ሆነ። አንቀጽ 17 በአማርኛ ‹‹የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከአውሮፓ ነገሥታት ለሚፈልጉት ጉዳይ ሁሉ በኢጣሊያ መንግሥት አጋዥነት መላላክ ይቻላቸዋል›› የሚል ሲሆን ቀጥተኛ ትርጉሙም የኢትዮጵያ መንግሥት ከፈቀደ ወይንም ከፈለገ በኢጣሊያ በኩል ከውጭ መንግሥታት ጋር ግንኙነት ማድረግ እንደሚችል የሚጠቅስ ነው፡፡
የአንቀጹ የጣሊያንኛ ትርጉም ግን ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ከውጭ ሀገር መንግሥታት ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት በኢጣሊያ መንግሥት አማካኝነት ማድረግ ይገባዋል›› የሚል ነበር። ይህም የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት በቀጥታ በጣሊያን በኩል እንዲከናወን የሚያስገድድ ነበር፡፡ በአንቀጽ 17 አማካኝነት ጣሊያን የውሉን ሀሳብ በጣሊያንኛ በመቀየር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመገርሰስ የጣሊያን ሞግዚት እንድትሆን ቀዳዳ እያበጀች ነው ብለው ነገሥታቱ እና መኳንንቱ ስለተገነዘቡ የውጫሌ ውልን እንደማይቀበሉት አሳወቁ።
የጣሊያን መንግሥት ውሉን ለማፍረስ አሻፈረኝ በሚልበት ጊዜ፣ የውጫሌ ውል እንዲፈርስና ኢትዮጵያ ለማይቀረው ጦርነት እንድትዘጋጅ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ካበረከቱ ግለሰቦች መካከል የዳግማዊ አጼ ምኒልክ ባለቤት የሆኑት እቴጌ ጣይቱ ብጡል እንደነበሩ ታሪክ ይናገራል፡፡ እቴጌዋ ‹‹እኔ ሴት ነኝ፣ ጦርነት አልወድም። ግን እንዲህ መሳዩን ውል ከምቀበል ጦርነት እመርጣለሁ›› ብለው ነበር። በወቅቱ ‹‹ይስሙ ንጉሥ!›› የሚል ታሪካዊ ንግግር አድርገዋል። ይህን ንግግራቸውን ተከትሎም በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ የሚገኘውና የውጫሌ ውል የተፈረመበት ቦታ ‹‹ይስማ ንጉሥ›› የሚል ስያሜ አግኝቷል።
ይህ ታሪካዊ ቦታ የባሕል ማዕከል ተገንብቶለት የቱሪዝም መዳረሻ ሆኗል። የባሕል ማዕከሉ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያሳዩ መረጃዎችን ያካተተ ሲሆን የቀለም ቅቡም የአሸናፊነትና የተሸናፊነትን እንዲወክል በነጭና ጥቁር ተደርጎ የተዘጋጀ ነው። በማዕከሉ ጣሪያ ላይ አሸናፊነትን የሚያመለክት የእጅ ምልክት ተሰርቷል። በ25 ሚሊየን ብር የተገነባው ይህ ባሕል ማዕከል፤ የመግቢያ በሩ የኢትዮጵያ ቁጥር ፲፯ (17) ተጽፎበታል፡፡
ዋለልኝ አየለ አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 29 ቀን 2015 ዓ.ም