የወባ ትንኞች ከሌሎች እንስሳት ይልቅ በርካታ ሰዎችን በመግደል ይታወቃሉ።የአለም ጤና ድርጅት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤የወባ ትንኝ በየአመቱ ከአንድ ሚሊየን በላይ ሰዎችን ለሞት ይዳርጋሉ።በወባ ፣በቢጫ ወባና በመሳሰሉት በየአመቱ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለሞት ይዳረጋሉ።
ይህን ችግር ለመፍታት ቤቶችን በወባ መከላከያ መዳሂኒት ማስረጨት ፣አጎበር መጠቀም፣ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን መድፈን እንዲሁም በወባ የተነደፉ ሰዎችን ማከም ሁሉ በቂ አይደለም፤የወባ ትንኞችን ማጥፋት ወሳኝ ይሆናል።ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል ?
ጉግል ግን የአለም ህዝብን ከወባ የሚታደግ አዲስ መላ ይዞ መጥቷል።በቅርቡ የቤተሰብ ዘመቻ አልፋቤት በሚል ይዞት የመጣው መላ ታዲያ የወባ ትንኝን ቀስ በቀስ ከምድር የማጥፋት አላማ ያነገበ ድንቅ ሀሳብ ነው። ይህ በአለም የሚካሄድ ወባን የማጥፋት ፕሮጀክት የወባ ትንኞችን ለማጥፋት ወንድ የወባ ትንኞችን በስፋት ማርባት ውስጥ መግባትን ይፈልጋል።
ኤንዲቲቪ የተሰኘው ድረ ገጽ ሰሞኑን እንዳስነበበው ፤ይህ የጉግል የወባ ትንኝን ከመላ አለም የማጥፋት ፕሮጀክት የወባ ትንኝን በ95 በመቶ ማጥፋት የሚያስችል መሆኑ ታምኖበታል።
አልፋቤት በተሰኘው ድርጅት የሚመራው ቬሪሊይ የተባለው የምርምር ተቋም እአአ በ2017 በካሊፎርኒያ ግዛት ፍሬስኖ ተጀምሯል።ዲበግ የተሰኘው ይህ ፕሮጀክት የወባ ትንኝን ለማጥፋት አገልግሎት የሚውሉ ወንድ የወባ ትንኞችን በላቦራቶሪ ውስጥ የማራባት ስራ እያካሄደ ይገኛል። በዚያም የሚራቡት ወንድ የወባ ትንኞች ዎልባቺያ በተሰኘ ባክቴሪየም እንዲመረዙ ይደረጋል።
ዘገባው እንዳመለከተው፤የተመረዙት የወባ ትንኞች በተወሰነ አካባቢ ላይ ይለቀቃሉ፤ ከሴቷ የወባ ትንኝ ጋር ግንኙነት ሲያደርጉም የወባ ትንኟ የምትመክን ሲሆን፣ በሂደትም የወባ ትንኝ የመራባት እድልን በማመንመን ጨርሶ እንዲጠፋ ማድረግ የሚያስችል ነው።
ይህ የሙከራ ስራ ምን ያህል ውጤታማ ሊሆን ይችላል ሲል ዘገባው ይጠይቃል። እስከ አሁንም 15 ሚሊየን የወባ ትንኞች በቤተ ሙከራ ውስጥ እንዲመረዙ ተደርጓል።በዚህም የወባ አምጪዋን ሴት ትንኝ ቁጥር በሁለት ሶስተኛ መቀነስ እንደሚቻልም ታምኖበታል።ፕሮጀክቱ አጠቃላይ የወባ ትንኝ ቁጥርን በ95 በመቶ መቀነስ የሚያስችል እንደሆነም ተጠቁሟል።
ዲበግ በድረ ገጹ እንዳስታወቀው፤ፕሮጀክቱ አጀማመሩ ጥሩ ነው፤እንዲያም ሆኖ ሰፊ ስራ ይጠብቀዋል። በቂ የተመረዙ የወባ ትንኞችን ወደ መስክ በመልቀቅ በወባ ትንኝ እና በሽታ ማጥፋት ተግባር ላይ ለሚያከናውነው ተግባር የህብረተሰቡ ሚና ከፍተኛ ይሆናል።
ዲበግ በዚህ ሁሉ ስራ በኋላም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ረጅም እድሜ እንዲኖሩ እንዲሁም ጤነኛ ህይወት እንዲመሩ ለማድረግ ተስፋ እንዳለውም አስገንዝቧል። ይህ የወባ ትንኝን የማጥፋት ፕሮጀክት ለእኛም ያስፈልጋል። መቼ ይሆን እኛ ዘንድ የሚደርሰው?
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22/2011
በዘካርያስ