ሰዎች ደስታቸውን ለመግለፅ የተለያዩ መንገዶችን ይጠቀማሉ። አንዳንዶች ይጮኻሉ፤ ሌሎች ስቅስቅ ብለው ያለቅሳሉ። እሚያደርጉት የሚጠፋ ቸውም አሉ። ሻምፓኝ የሚከፍቱ፣ መሳሪያ ወደ ሰማይ የሚተኩሱ፣ወዘተ፣ጥቂት የሚባሉ አይደሉም።
ደስታቸውን በርችት የሚገልጹ ሰዎች ነገር ታዲያ ጉድ ማፍላቱን ሰሞኑን ለንባብ የበቃ የኦዲቲ ሴንትራል ድረገፅ መረጃ ያመለክታል። ነገሩ የተፈጠረውም ካኢ ናን የተሰኘው ቻይናዊ የዡዙው ነዋሪ ቤቱ በአዲስ መልክ የተሰራበትን ቀን እ.ኤ.አ ከ2018 ጀምሮ በርችት ተኩስ ባከበረበት ወቅት ነው።
እርሱና ቤቱን ሲሰሩ የነበሩ ግለሰቦች ደስታቸውን ለመግለፅ በቤቱ ጠራ ላይ በርካታ ርችቶችን በማስቀመጥ ከሦስት እስከ አራት ለሚሆኑ ደቂቃዎች ወደ ሰማይ ይተኩሳሉ። ይሁን እንጂ ካኢና አብረውት የነበሩ ሰዎች ርችቱ ሲተኮስ የሚያሰማው ድምፅ በቤቱ አቅራቢያ በሚገኘው እርሻ ውስጥ ያሉትን ጥንቸሎች አይደለም ለሞት ማብቃት ይረብሻቸዋል ብለው አልጠረጠሩም።የርችቱ ድምጽ ግን ከ11 ሺ በላይ ጥንቸሎችን ይጨርሳቸዋል።የቤቱ ባለቤትም ህግ ፊት ይቀርባል።
ዣንግ የተሰኘው የካኢ ጎረቤት በዡዞው ፍርድ ቤት ቀርቦ እንደተናገረው በርችት ተኩሱ ምክንያት ጥንቸሎች የሚውሉበት የእርሱ መሬት በጥንቸል ሬሳ ተሞልቶ ያገኘዋል።ከ11 ሺ 500 በላይ የሚሆኑ ጥንቸሎች ከርችቱ በወጣው ከባድ ድምፅ ተደናግጠው ለሞት ተዳርገዋል። ከእነዚህም መካከል 10 ሺ የሚሆኑት ግልገሎች ናቸው።15 ሺ የሚሆኑ ሴት ጥንቸሎች ደግሞ በዚሁ ድምፅ ምክንያት አስወርደዋል።
እንደ መረጃው ከሆነ ዣንግ ጎረቤቱ ካሳ እንዲከፍለው የጠየቀ ሲሆን፣ ይሁን እንጂ ካኢ ካሳውን ለመክፈል ፍቃደኛ ባለመሆኑ ፍርድ ቤት ይከሳል። የዡዞው ፍርድ ቤት ካኢ ለጥንቸሎቹ እልቂት ተጠያቂ መሆኑን በማረጋገጥ ለደረሰው እልቂት ለጎረቤቱ ካሳ እንዲከፍል ወስኖበታል።በዚህ መሰረትም ካኢ በአሥር ቀናት ውስጥ 440 ሺ የቻይና ዩዋን ወይም 65 ሺ 500 የአሜሪካ ዶላር ለጎረቤቱ ካሳ መክፈል ይኖርበታል።
የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ ካኢ ይግባኝ ቢጠይቅም ፍርድ ቤቱ የካኢን የይግባኝ ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ውሳኔውን አፅንቷል። ዕዳ ከሜዳ ፣ሲያጌጡ ይመላለጡ ማለት እንዲህ ነው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22/2011
በአስናቀ ፀጋዬ