ትላንት ማታ የልጅነቱ ጨረቃ በሰማዩ ወገብ ላይ ነበረች:: ለረጅም ጊዜ አስተውሏት ወደ ቤቱ ሲገባ እየከፋውና ደስ እያለው ነበር:: ጨረቃ እንዲ ስትሆን እድል አለው..መከራም::
በበነጋታው ሳሎን ተቀምጦ አንድ ሀሳብ ያስባል..እሷ ያለችበትን ሀሳብ:: ሳያስቃት ውሎ አያውቅም:: ሻወር ቤት ናት እየታጠበች እሱ ደግሞ እየጠበቃት:: ከሰላሳ ደቂቃ ቆይታ በኋላ በጣም አምራ ወደሳሎን መጣች::
‹ኢትዮጵያን መስለሻል! አላት በአገር ባህል ልብስ የደመቀ ሴትነቷን እያየ::
‹ኢትዮጵያ ምን አይነት ናት? ጠየቀችው::
‹ልክ እንዳንቺ ትሁትና ኩሩ› መለሰላት::
ስቃ ዝም አለች:: ሳቅና ዝምታ እሱን ካወቀች በኋላ የተዋሃዷት ማንነቶቿ ናቸው:: ነፍስ ከአቅሟ በላይ የሆነ መባረክ ሲጎበኛት አንድም በሳቅ አንድም በዝምታ የምታልፈው የሆነ ተፈጥሮ አላት ትላለች:: ግራ የሚገባት እሱ ፊት ነው:: የደስታ እና የኩራት ግራ መጋባት::
እሱም እንደ እሷ ነው:: እንዲህ እንደአሁኑ በፈገግታ ዝም ስትል ድንገት የሚወስደው ደራሽ ስሜት አለው:: ከእሷ ወደ እሱ ካልሆነ ከሌላ ወደ እሱ የማይጋባ የንቃት ስሜት:: አጠገቧ መሆን በህይወቱ ተመኝቶ ከሆኑለት ነገሮች በላይ ደስታ የሚሰጠው ነገር ነው:: በህይወቱ ድንገት ተከስተው ሙሉ ያደረጉትን ጸጋዎች ሲጠይቅ ጣቶቹ ወደ እሷ የሚቀሰሩ ናቸው::
‹ትህትናና ኩራት የአንድ ማንም የማይስተካከለው ማንነት ስያሜ ናቸው:: ሀይለ ስላሴ በአንድ ጋዜጠኛ ፊት ኢትዮጵያዊነትን ሲመልሱት ትህትናና ኩራት ነው ብለው ነው:: ኢትዮጰያዊነት ከዚ ውጪ በምንም ቢገለጽ ልክ አይሆንም:: አንቺም ያቺ ትሁትና ኩሩ የተባለችውን አገር ነሽ› ሲል ግንባሯን ሳማት::
ዓለም ላይ የእሷን ውበት የእሷን ሴትነት ለመግለጽ ከልቧ የማይጠፉ ውብ ቃላትን ሲጠቀም ታውቀዋለች:: በዘመኗ የሰማቻቸው ባስታወሰቻቸው ቁጥር ፈገግ የምትልባቸው ጥኡመ ወሬዎች ሴትነቷን ታከው ከእሱ አፍ የሰማቻቸው ናቸው::
በየቀኑ ከትላንት ሌላ ያደርጋታል:: የሰው ልጅ የቸገረው አንድ ነገር ቢኖር ከትላንት ሌላ መሆን ነው:: እሷ ግን በዚህ ሰው ሌላ ናት:: በሴትነቷ ውስጥ ማንም ያላደረገላትን የእንኳንም ሴት ሆንኩ ሞገስ ያጎናጸፋት እሱ ነው:: እንዳታስከፋው ተጠንቅቃ ነው የምትኖረው:: የህይወቷ ማብቂያ የእሱ አለመኖር እንደሆነ ድሮ ገና ነው የመለሰችው::
የሆነ ጊዜ ላይ ከአቅሟ በላይ በሆነ ፍቅሩና መልካምነቱ ዝም የምትለው ዝምታ አላት:: ይሄ ዝምታዋ ከእሱ ጋር ስትሆን ብቻ ነው የሚከጅላት:: በህይወቷ ብዙ ወንዶችን ታውቃለች አንዳቸውም የእሱን ያክል ሞገስ አልሰጡዋትም:: እንደምታፈቅረው ይሄን ብቻ ነው እርግጠኛ የሆነችው:: ከአንቺና እሱን ከማፍቀር በየቱ ነሽ እርግጠኛ ብትባል እሱን በማፍቀር ነው የምትለው:: ግን እንደምታፈቅረው አልነገረችውም:: ባልም ፍቅረኛም ወንድምም መሆን የሚችል ነው:: የሆነ ጊዜ ላይ በህይወቷ ባላወኩት ከምትለው ኤርሚያስ ጋር በተለያየች በሳምንቱ ነበር ከሳህሉ ጋር የተዋወቁት:: ያኔ ለእሷ ጥሩ ስሜት እንዳለው ነግሯት አብራው እንድትሆን ጠይቋት ነበር:: ምን እንዳለችው ስታስብ ዛሬም በዛ ተልካሻ መልሷ ትበሽቃለች:: ወንዶች ሁሉ አንድ እንደሆኑ በማሰብ ‹ይቅርታ ፍቅረኛ አለኝ፣ ፍቃድህ ከሆነ ወንድሜ ብቻ እንድትሆን እፈልጋለው› አለችው:: ይሄው ከዛን ጊዜ ወዲህ ወንድምና እህት ሆነው ይኖራሉ:: አንድ ቀን ግን የወንድምና የእህት ድንበራቸው ተጣሰ:: ዝም ብላ መጥታ ፊቱ ላይ አለቀሰችበት::
‹ምን ሆነሻል? አላት ሁሌም በሚታወሳት ማባበልና እቅፍ::
‹አንድ ነገር እጠይቅሀለው፣ የዛ ጥያቄ መልስ እኔ እንደምፈልገው ካልሆነ ዛሬ ብቻ ነው እንዲህ እንደአሁኑ ፊትህ ቆሜ የምታየኝ› አለችው ላመል ጥርጥር በሌለው እርግጠኝነት::
አስደነገጠችው:: ሁኔታዋ ሁሉ አዲስ ነበር:: ምንም ይሁን ከእሷ ፍላጎት ውጪ የሚሆን ፍላጎት እንደማይኖረው እርግጠኛ ነበር:: እንድትነግረው አይኗ ላይ ተንቀዋለለ::
‹ከዚህ በኋላ ከአንተ ጋር ወንድምና እህት መሆን በቅቶኛል..
‹ማለት? ካወቃት ጀምሮ እንደዛሬ አስደንግጣውና ግራ አጋብታው አታውቅም::
‹ማለት እማ ሚስትህ መሆን እፈልጋለው:: አሁኑኑ አገባሻለው ስትል ቃልህን ስጠኛ ያለበለዛ..
ባስታወሰው ቁጥር ለዘላለም የሚስቅበትን ወይም ደግሞ እንዴት ተጋባችሁ ብሎ ለሚጠይቃቸው ሁሉ የሚመልሰውን አስደናቂ መልስ ሰማ:: እሱ ነበር ግራ የሚያጋባት ዛሬ ገና እሱን ግራ በማጋባት ተሳካላት:: ምንም አላለም ተነስቶ አቀፋት:: እቅፉ ውስጥ እያለች አንድ ነገር ብቻ አላት ‹አንቺ ለአንድ ጊዜ አይደለም ለሁልጊዜም የተመኘኋት ሴት ነሽ:: በህይወት እስካለሁ ድረስ የምትኮሪበት ባልሽ ልሆን ቃሌን እሰጥሻለው› አላት::
በንግግሩ ተኮርኩራ ቀና ብላ አየችው:: መች ይሆን ከዚህ ሰው የክብር ትከሻ ላይ የምትወርደው? መች ይሆን ከፍቷትና አስከፍቷት የምታየው? የቃል ሰው ብቻ ቢሆን ገና ድሮ ትጠላው ነበር ግን አይደለም..ከቃሉ የበረታ በዝምታ የሚለጉም ግብር አለው:: ከዛን ቀን ጀምሮ እህቱ እያለች ይሰጣት የነበረውን ሁሉ በሚስትነት ይሰጣት ገባ:: ይገርማታል..ለሚስትና ለእህት አንድ አይነት የሆነ ወንድነት እሱጋ ነው ያስተዋለችው:: ያን ጊዜ ለፍቅር ስትጠይቀኝ ለምን አይሆንም እንዳልኩህ ሌላ ቀን እነግርሀለው:: ከዛ ቃሌ በኋላ የማልረባ ሴት እንደሆንኩ ሲሰማኝ ነበር ስትል ሀዘን ወረራት::
……….
ወደ እሱ ስትሄድ ወደማንም ባልተራመደችው ርምጃ ነው:: እሱን ስታስብ ማንንም ባላሰበችው ድንግል ሀሳብ ነው:: ራሷን አንድ ሳታስቀር ሰጥተዋለች:: ግን ግን ከእሷ የእሱ መሆን ይልቅ የእሱ የእሷ መሆን እንደሚበልጥ ያለመጠራጠር ታውቀዋለች::
ሲያፈቅራት ከዛሬ አልፎ ነው:: ከነገም ርቆ:: ሲያፈቅራት እስከሚመጣው ነው:: ሲያስባት ያለፈውንና የሚመጣውን ጨምሮ ነው:: ለእሷ የሚጠብ የወንድነት ሀሳብና ምናብ የለውም::
ዛሬ በሁለቱም ልብ ውስጥ እሱ ለእሷ እሷም ለእሱ የሆነ ደስታ አዘጋጅተዋል:: በሳቋ ውስጥ የምትበራ ዓለም አለችው:: በሳቁ ውስጥ የምትወግግ ምድር አለቻት:: ወደሆነ ቦታ ወስዶ ለዘላለም እንድታስበውና እንድታፈቅረው ያደርጋታል:: እጇን ይዞ ከተቀመጠችበት በቀስታ አስነሳት:: ይሄም ሌላ ማመስገኛዋ ነው:: ቃላት ብቻ አይደለም ከተግባር ጋር ባሏ የሆነ ወንድ ነው:: ዓለም ላይ አንድ መልካም ወንድ ተፈጥሮ እሱም ለእሷ የታደለ መሰላት:: እንዲህ ከመሆን ውጪ ምንም እንደማይሆን እሷ ብቻ ናት የምታውቀው::
ምን እንደምትሰጠው አታውቅም:: ብቻ የሆነ ነገሯን ልትሰጠው ተሰናድታለች:: ምኗን እንደሆነ ግን አታውቀውም:: ያልሰጠችው ምን እንዳላት እንጃ..ግን የሆነ ነገር ከጅላለች:: እስከዛሬ እሱ ነው የሚያስቃት:: ዛሬ ሌላ ልትሆንበት ሽታለች:: በፍለጋ ያገኘቻቸው እንኳንም ሚስትክ ሆንኩ፣ እንኳንም ባሌ ሆንክ የሚሉ የተመረጡ ቃላቶች በልቧ ሰሌዳ ላይ ጽፋለች:: ለመጀመሪያ ጊዜ ዝምታዋን ሽራ ታመሰግነዋለች:: ለመጀመሪያ ጊዜ በእንባ ተሞልታ ንጉሴ፣ ልኡሌ ትለዋለች..ይሄ ልትሰጠው ያሰበችው አዲስ ነገሯ ነው::
ምን እንዳሰበ የእሱን አታውቀውም:: ሁሉም ወደአዲስ አለም እንደወሰዳት ነው:: እጁን ወገበዋ ላይ ጣል አድርጎ ከቤት ወጡ:: የከሰዐት በኋላው ንፋስ አብረው ሲሆኑ ይቀናባቸዋል መሰለኝ መሰስ ብሎ መጥቶ መሀላቸው ገባ:: የውጪውን በር አልፈው ከመሀል አስፓልት ደረሱ..:: እንደጠቃቀፉ አጠገባቸው የቆመች ታክሲ ውስጥ ሰተት አሉ:: የድሮ ፍቅረኛዋን ኤርሚያስን ታክሲው ውስጥ አየችው:: በዛ ታክሲ ላለመሄድ አስባ ነበር:: ግን አልወረደችም:: አጠገቧ ያለውን ፍቅረኛዋን ጠበቅ አድርጋ ያዘችው::
በግምት አምስት ደቂቃ ነው የተጓዙት:: የተሳፈሩባት መኪና ከፊት ለፊት ከሚመጣ ከባድ መኪና ጋር ስትጋጭ በታሪክ አስከፊው የመኪና አደጋ እንደሚሆን ብዙዎች ገምተው ነበር:: በበነጋታው በማለዳ የትራፊክ ዜና ላይ በመዲናችን አዲስ አበባ በደረሰ የትራፊክ አደጋ አስር ሰዎች ሲሞቱ አንድ ሴትና አንድ ወንድ በህይወት ተርፈዋል ሲል ዘገበ::
ኤርምያስና ትውፊት:: የቀድሞ ፍቅረኛዋና እሷ::
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27/2015