ምህረት ሞገስ
በቅርብ የተጀማመሩ ከጥቂቶቹ በስተቀር በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች የክልል ከተሞች እንዲሁም በአገሪቱ የግንባታ መጓተትም ሆነ መቆምን ማየት ከተለመደ ዓመታት ተቆጥረዋል። አንድ ግንባታ በሁለት ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ ከአስር ዓመት በላይ መፍጀቱ አስገራሚ አይሆንም። የጥራት ጉዳይም በተመሳሳይ መልኩ ተለምዷል። ይህ ለምን ሆነ? እነዚህን ችግሮች ለማቃለል ምን እየተሠራ ነው? ስንል የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ነገዎን ጠይቀን እንደሚከተለው ምላሻቸውን ይዘን ቀርበናል። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን መቼ ተቋቋመ? ሲቋቋም ዓላማው ምን ነበር? ከሚለው ጀምረን ወደ መሠረታዊ ጥያቄዎቻችን እናምራ?
አቶ መስፍን፡- የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን አሁን ያለውን ስም ይዞ የተቋቋመው በ2014 ዓ.ም ነው። የመንግስት አስፈፃሚ ተቋማትን እንደገና ለማቋቋም በወጣው በአዋጅ ቁጥር 1263 የተቋቋመ ነው። ከዛ በፊት በለውጡ ማግስት አዋጅ 1079 ንዑስ 97 እንደዚሁ የመንግስት አስፈፃሚ አካላትን ለማዋቀር የወጣ አዋጅ ነበር። በዚያን ጊዜ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ተብሎ እንደ አዲስ ተፈጥሮ ነበር። ከዛ በፊት ደግሞ ራሱን ችሎ በሚኒስቴር ደረጃ ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ተብሎም ነበር። እንደገና በአዋጅ 1079 ንዑስ 97 ባለስልጣን ሆኖ ራሱን ችሎ ወጣ።
ራሱን ችሎ የወጣበት ትልቁ ምክንያት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ያለዳኛ የሚካሄድ የእግር ኳስ ዓይነት ጨዋታ ስለነበር ነው። ያለዳኛ ቅድስ ጊዮርጊስ እና ቡና እግር ኳስ ቢጫወቱ አዲስ አበባ ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ቀውስ መገመት አያዳግትም። በኢንዱስትሪው ውስጥ የተሳካላቸው አገሮች ለዕድገታቸው ትልቁን ሚና የሚጫወትላቸው የኮንስትራክሽን ፖሊሲ፣ አዋጆች እና ስታንዳርዶች ላይ የተመሠረቱ ሆነው ኢንዱስትሪውን በመመራታቸው እና በመገራታቸው ነው።
ከለውጡ በፊት የነበረው የቁጥጥር ሥርዓት እጥረት ስለነበረበት፤ የኮንስትራክሽን ፖሊሲ ቢኖርም ቀውስ ውስጥ ነበርን። ከቀውሱ ለመውጣት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ቁጥጥር ባለስልጣን ተቋቋመ። በዚያን ጊዜ ሲቋቋም ዓላማው አሁን ከተቋቋመበት ዓላማ ብዙ የራቀ ባይሆንም የቁጥጥር መንገዱ ግን የተቆራረጠ ነበር። ለምሳሌ የኢነርጂ እና የውሃ ሥራዎች ቁጥጥር ሌላ ቦታ ነበር፤ መንገድ ደግሞ ሌላ ቦታ ነበር። ስለዚህ ሙሉ አልነበረም። በመሆኑም በ2014 ዓ.ም የሁለተኛው መንግስት ሥራ አስፈፃሚ ሲደራጅ፤ እነኚህ እጥረቶች ተቀርፈው ራሱን በቻለ እና ሰብሰብ ባለ መልኩ በስትራቴጂ እንዲመራ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ተቆጣጣሪ የነበረው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ሆነ።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ ተቋሙ በውስጡ በተለያዩ ተቋማት ስር የነበሩ ሥራዎች ያከናውናል ማለት ነው?
አቶ መስፍን፡- አዎ! ለምሳሌ በውሃ እና ኢነርጂ ሥር የነበሩ የቁጥጥር ሥራዎች ወደ እኛ መጥተዋል። በኢነርጂ ባለስልጣን ሥር የነበረው የሲቪል ኮንስትራክሽን ቁጥጥር ወደ እኛ መጥቷል። የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ተብሎ የነበረው ሙሉ ለሙሉ የአስተዳደር ስራውን እርሱ ቢሰራም የቁጥጥር ሥራውን የሚሠራው ይህ ተቋም ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ባለስልጣኑ ምንም እንኳ በአዲስ መልክ ቢቋቋምም ቀድሞም ሲሠራ ነበር። ምን ያህል ዓላማውን እያሳካ ነው?
አቶ መስፍን፡– አስቀድሜ ዓላማዎቹን ልዘርዝር። በአዲስ መልክ ከተቋቋመ ወዲህ አራት ዓላማዎች አሉት። አራቱም ዋነኛ ዓላማዎች መጨረሻቸው አንድን ግብ ማሳካት ነው። ግቡ ተወዳዳሪ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪን በቁጥጥር እየመሩና እየገሩ መፍጠር ነው። ይህንን ዋነኛ ዓላማ ለማሳካት አራት ንዑሳን ዓላማዎች አሉ። የመጀመሪያው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በጊዜ፣ በተያዘለት ዋጋና ጥራት የአካባቢ ደህንነትን ባረጋገጠ መንገድ መፈፀም አለመፈፀሙን መከታተል፣ መቆጣጠርና ማረም ነው።
ሁለተኛው ይህንን ሥራ ለማሰራት የሚያስችል በቂ ኮድ እና ስታንዳርድ ማዕቀፍ እንዲኖር ማድረግ ነው። እዚህ ላይ ኮድ እና ስታንዳርድ ያሰናዳል ማለት ነው። ሶስተኛው ኢንዱስትሪው ግብዓት ይኖረዋል። ግብዓቱ ደግሞ ከገበያ የሚገኝ ነው። ያንን የግብዓት ጥራት ማረጋገጥና በኢንዱስትሪው ውስጥ አልፎ የመጨረሻው ውጤት ማምጣት ነው። በዚህ ውስጥ ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ጠቀሜታ የሚውሉ መሠረተ ልማቶችን፤ ጥራት ማረጋገጥ ነው። የሕዝብና የአካባቢን ደህንነት ያረጋገጠ ሆኖ ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ ግባችን ነው።
አዲስ ዘመን፡- እነዚህ አላማዎች የሚሳኩት መቼ ነው?
አቶ መስፍን፡- በቀጣይ በትውልድ መካከል የሚሳኩ ናቸው። ሥራውም ሆነ ግቡ ውስን እና የሚቆም አይደለም፤ ዛሬ ያለው ፍላጎት ከአምስት ዓመት በኋላ ከሚመጣው ጋር የተለየ እና አዲስ ነው። ስለዚህ የሚመጡትን አዲስ ፍላጎቶች እየተከታተሉ፤ እነዚህን አራት አላማዎች ለማሳካት ይሠራል።
በጥያቄው ላይ የቀረበው አሁን ካለው ፍላጎት አንፃር ምን ያህል ተጉዛችኋል? ለሚለው ደግሞ አንደኛ እነዚህን አራት ሥራዎችን ለመስራት የተሰጠን ትልልቅ ኃላፊነቶች ሁለት ዘርፎችን የያዘ ነው። የመጀመሪያው ዘርፍ ውስጥ የሚመደበው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ኮድ እና ስታንዳርድ ፍሬም ወርክን ማዘጋጀት እና መኖር አለመኖሩን ማረጋገጥ ነው። የሌሉትን አዘጋጅቶ ወደ ሥራ ማስገባት፤ ያሉትን ግን መተግበር ይችላሉ፤ አይችሉም የሚለውን ማየት ነው።
ሁለተኛው በመጀመሪያው ዘርፍ ላይ የሚገኘው መረጃ ነው። በየቀኑ የሚመጡትን መረጃዎች አደራጅቶ መያዝ ነው። ያለውን ትግበራ እና መረጃዎችን ይዞ፤ አደራጅቶ ትንተና አካሂዶ ለፖሊሲ፣ ለደንብ እና መመሪያ ማሻሻያ ግብዓት የሚሆኑትን ማሰባሰብ ነው። እዚህ ሥር ኢንደስትሪው ውስጥ የሚገቡ ማንኛውም አካላት የሚገቡት ተመዝግበው ነው። የምዘና እና የብቃት ማረጋገጫው በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስትቲዩት የሚሠራ ሆኖ፤ ምዝገባውን የእኛ ተቋም እየሠራው ነው።
ሌላው በሁለተኛው ዘርፍ ውስጥ ያለው ደግሞ የቁጥጥር ሥራ ነው። የቁጥጥር ሥራ ውስጥ መጀመሪያ የሚመጣው እነኚህ የተዘጋጁ የመለኪያ (ስታንዳርድ) ማዕቀፎች ትግበራ ቁጥጥር ነው። የተገዢነት ኦዲት ቁጥጥርን የምንሰራው በአገሪቷ አወቃቀር መሠረት ነው። በፌዴራል ደረጃ የሚሠሩትን እኛ እንተገብራለን። በክልል ደረጃ ደግሞ የክልሎቹ አደረጃጀቶች ይተገብሩታል፤ በከተማ አስተዳደር በማዘጋጃ ቤቶች ደረጃ ደግሞ የሕንፃ ሹሞች ይተገብሩታል። እንደ አዲስ አበባ ያሉ ሰፊ ከተሞች ላይ ደግሞ በክፍለ ከተማ እና በወረዳ ያሉ አስፈፃሚዎች ይተገብሩታል።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን ነገር የምትተገብሩት እንዴት ነው?
አቶ መስፍን፡- አንደኛ በጥቆማ ኦዲት እናደርጋለን። ሁለተኛ በዕቅድ የተገዢነት ኦዲት ቁጥጥር ላይ ኮዶቹ እንዴት ተተገበሩ? የሚለውን እናያለን። የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ተጀምሮ የሚያልቅ፤ ቦታውን የሚቀይር እና በውል የሚፈፀም በመሆኑ ውዝግቦች ያጋጥማሉ። የእኛ ተቋም የኮንስትራክሽን ውዝግቦችን አማራጭ በማቅረብ ይፈታል። ይህ የሆነው ብዙ ፕሮጀክቶች የመዘግየታቸው ምክንያት አንዱ በውዝግብ እና በፍርድ ቤት ጊዜያቸው ስለሚበላ መሆኑ በመረጋገጡ ነው።
በተጨማሪነት ከከተሞች አስተዳደር ውጪ የሆኑ በፌዴራል የሚሠሩ ፕሮጀክቶች ለምሳሌ አገር አቋራጭ መንገድ እና የኃይል ማመንጫ ግድቦች የመሳሰሉት ከከተማ ውጪ በመሆናቸው የከተማ ህንፃ ሹም የሚቆጣጠራቸው አይደሉም። ይህን የቁጥጥር ሥራ የምናከናውነው እኛ ነን። ስለዚህ የፕሮጀክት ቁጥጥር እንሠራለን። የፕሮጀክት ቁጥጥር ስንሠራ በየቀኑ ሳይሆን የምንሰራው ወሳኝ በሆኑ ደረጃዎች ላይ ያሉትን መረጃዎች (ዳታዎች) መሠረት አድርገን በመያዝ ቁጥጥር እንደርጋለን።
አዲስ ዘመን፡- ምን ያህል ሠራችሁ?
አቶ መስፍን፡– መጀመሪያ በኮንስትራክሽን ሥራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን የነበርንበትን የሶስት ዓመት ታሪክ እናንሳ። ከዛ የአሁኑን የአንድ ዓመት ታሪክ እንዘርዝር። በሶስት ዓመት ውስጥ በዋናነት የንቅናቄ ሥራ ሠርተናል። ህግ ከማስፈፀም በፊት የሚመጣው አንዱ ህግን ለማሳወቅ ንቅናቄ መፍጠር ነው። ስለዚህ በተከታታይ ሶስት ዓመት በአምስት ክልሎች መድረኮችን በማዘጋጀት የሚመለከታቸው ባለድርሻዎችን አሳትፈናል። ያ ንቅናቄ በጣም ብዙ ግብዓት አምጥቶልናል። አንደኛው እታች ያሉ አደረጃጀቶች ከእኛ ሥርዓት አንፃር ያለው ምንድን ነው? የሚለውን ወስደናል። በሌላ በኩል ያሰብነውን ሥራ እና የእኛን ግብ ለማሳካት ወደ ሚመለከታቸው አድርሰናል።
አቅማችን አዲስ እንደተፈጠረ ተቋም በጣም ደካማ በመሆኑ የተወሰኑ ፕሮጀክቶችን ይዘን እያሳደግን እየሠራን ነው። በሶስቱ ዓመት መቶ በመቶ እየጨመርን ከ120 ፕሮጀክቶች በላይ አይተናል። ከ250 በላይ የህንፃ ፕሮጀክቶችን አይተናል። የውሃም ከ40 ፕሮጀክቶች በላይ አይተናል። ሌላው ትልቅ ስራ ሰርተን ውጤት አምጥተናል የምንለው ከ920 ፕሮጀክቶች በላይ ነበሩ። ከለውጡ በፊት ጀምሮ ያልተጠናቀቁ እና የቆዩ ነበሩ። ከ920ዎቹ ውስጥ 758ቱ የዩኒቨርሲቲ ፕሮጀክቶች ናቸው። እነዚህ ፕሮጀክቶች ቆመው ነበር። የቆሙበት ምክንያት ምንድን ነው በማለት መረጃ በመሰብሰብ እና ትልቅ ጉባኤ በማዘጋጀት አማካሪ፣ ተቋራጭ እና የፕሮጀክቱን ማናጀሮች አካትተን አወያይተናል።
ፕሮጀክቶቹ የተነሳሽነት እና የአዋጭነት ጥናት ሳይደረግላቸው በስሜት የተጀመሩ ናቸው። ስለዚህ በግንባታ ጊዜ ውዝግብ ይኖራል። ይህ ይቅር ይባላል፤ ወይም ያልነበረ ነገር ይጨመር ይባላል። በዚህ ጊዜ ውዝግብ ይፈጠራል። እንዲያውም ከእነዚህ ውስጥ ወደ 20 ፕሮጀክቶች 80 በመቶ ለውጥ ተደርጎባቸዋል። የአገራችን የኮንስትራክሽን ገበያ ዋጋ በፍጥነት እያደገ በመሆኑ የእዛ ሰለባ ሆነዋል። እንዲያውም ብዙዎቹ በፍርድ ቤት የተያዙ ናቸው።
በደንብ እንነጋገር ከተባለ፤ ብረት በ17 ብር ውል የታሰረባቸው ለውጡ ሲመጣ የብረቱ ዋጋ 120 ብር ደረሰ። ውል በገቡበት መጠን መሔድ አልቻሉም፤ ስለዚህ ይህንን አጥንተን መንግስት የዋጋ ንረቱን የሚያካክስበትን መንገድ እንፍጠር በማለት ሦስት ወር ተኩል የፈጀ ጥናት አደረግን። ለገንዘብ ሚኒስቴር አቀረብን። ገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ በጀት ስለሚፈልግ ጊዜ ወሰደ፤ በመንገዱ ዘርፍ ወደ 71 ቢሊየን ብር ተጨማሪ ጠየቀ። በሕንፃው ዘርፍ ደግሞ ወደ 24 ቢሊየን ብር ተጨማሪ ብር አስፈለገ። ስለዚህ መንግስት ባለው ቁርጠኝነት የገንዘብ ማሻሻያውን ፈቀደ።
ከዛ በኋላ በዚህ ትልቅ ሥራ ከ758 ፕሮጀክቶች ከ400 የማያንሱት ግንባታቸው የቀጠለ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ 240ዎቹ ተጠናቀዋል። አሁንም በተቋራጮች፣ በአማካሪዎች እና በሌሎችም ችግሮች ምክንያት አሁንም እያዘገሙ ያሉ አሉ። በእነዚህ ላይ ወደ ፊትም የምንሠራ ይሆናል።
በሌላ በኩል 18 ከተሞችን የተገዢነት የቁጥጥር ሥራ ሠርተናል። ሰፊ የኮድ እና ስታንዳርድ ትግበራ ክፍተቶች አሉ። ስለዚህ በሚቀጥለው የሶስት ዓመት ስትራቴጂ ውስጥ የምንተገብረው ይሆናል። ለምሳሌ ከአምስት ፎቅ በላይ መሠራት ያለበት በብረት መወጣጫ (ስካፎልድ) ነው። በእርግጥ በእንጨት መስራት ይቻላል። ነገር ግን በአሰራር ግድፈት ምክንያት የሠራተኞች ደህንነት አደጋ ላይ ስለሚወድቅ አዋጅ 624 ላይ በብረት መሆን አለበት ይላል። ይህ እየተፈፀመ ባለመሆኑ ስካፎልዶች ተንደው ሰዎች ላይ አደጋ ሲደርስ ይታያል።
ይህ ሲነሳ ማዘጋጃ ቤቶችም ሆኑ አማካሪዎች አዲሶቹን ስታንዳርድ እና ኮዶችን ከመጠቀም ይልቅ የሚጠቀሙት የድሮውን እንደሆነ ማረጋገጥ ይቻላል። ስለዚህ ግንዛቤ መፍጠር ይፈልጋል። ያለበለዚያ አስገዳጅ ማድረግ እና የህግ ተጠያቂነትን ማስፈን የግድ ነው። ጉዳዩ የባለቤት፣ የተቋራጭ እና የአማካሪ ብቻ ሳይሆን የህዝብ ጉዳይም ነው። አንድ ዶክተር ቢሳሳት አንድ ሰው ይሞታል። አንድ መሃንዲስ ግን ቢሳሳት የሚፈጀው ብዙ ሰው ነው። ስለዚህ ጉዳዩ ከባድ መሆኑ መታወቅ አለበት።
ሌላው የተቋሙ ውጤት የምንለው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን አላሠራ ያለው ምቹ ሁኔታዎችን የማይፈጥሩ የህግ ማዕቀፎችን ማሻሻል ነው። የአማካሪ፣ የተቋራጭ እና የማሽነሪ ምዝገባ እንዲሁም የፕሮጀክት ምዝገባ አልነበረም። አሁን ግን ጀምረናል። እንደዚህ ዓይነቶቹ ሥራዎች ከላይ የጠቀስኳቸውን ዓላማዎቻችንን ለማሳካት ከሚያስችሉ ጉዳዮች መካከል ናቸው።
ሌላው የዓሥር ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አለ። ይህ ዕቅድ በሶስት ዓመት የተከፋፈለ ሲሆን፤ አጠቃላይ ለኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከተሰጠው መሰረታዊ ሥራዎች ውስጥ አምስቱ የእዚህኛው ተቋም ሥራዎች ናቸው። በእርግጥ ከአምስቱ በተጨማሪ በጋራ ከሌሎች ተቋሞች ጋር ተመጋጋቢ የሚሆኑ ሥራዎችም አሉ። የተወሰኑት ደግሞ በኛ ብቻ የሚሠሩ አሉ። የመጀመሪያው የቁልፍ አፈፃፀም አመልካች፤ ተብለው ብዙ ሥራዎችን የሚይዙ መመዘኛዎች አሉ። ይህ የሙስና ግንዛቤ መለኪያ (ኢንዴክስ) ነው።
ባለድርሻ አካላት ብዙ በመሆናቸውና የሚቃረን ፍላጎት ያላቸው በመሆኑ በዓለምም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ለሙስና የተጋለጠ ነው። በተለይ የቁጥጥር ዘርፉ ደካማ የሆነበት አገር፤ ሙስናው ሰፊና ሥር የሰደደ ነው። በዚህ ኢትዮጵያም ትነሳለች። ይህንን መቀልበስ ከቻልን የኢንዱስትሪውን ገፅታ እናሻሽላለን። ለዚህ አገር አቀፍ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ እና የዓለም መመዘኛዎች አሉ። ስለዚህ ይህንን ገፅ መቀየር አስፈላጊ ነው። ሌላው የኮንስትራክሽን ዘርፉን ተወዳዳሪነት መጨመር ነው። በአገር ውስጥ ተወዳዳሪ ሊሆኑ ይችላሉ። ከአገር ውጪም ተወዳዳሪ ሊሆኑ ይችላሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ የውጪዎቹ ወደ አገር ውስጥ መምጣታቸው በጣም ተለምዷል። ቻይናን አንዳንዶች የተዘዋዋሪ ቅኝ ግዛት እየተፈጠረ ነው እስከሚባል ድረስ በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ ስትሳተፍ ነበር።
ቻይናዎች መምጣታቸው ጥሩ ቢሆንም፤ መንግስት በህግ ማዕቀፍ ይህንን ኢንዱስትሪ ማብቃት እና ተወዳዳሪ አድርጎ የአገር ውስጥ ገበያን ድርሻ የመጨመር ኃላፊነት አለበት። በአገር ውስጥ ያለው የኮንስትራክሽን ገበያ ውስጥ ድርሻችንን መጨመር ተገቢ ነው። ሌላው ደግሞ በቀጣናው ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። ለእዚህ ዋነኛው ጉዳይ ቁጥጥር እና ስታንዳርድ ነው። ኬንያ ለመሔድ ቢሞከር መሰረታዊው ጥያቄ ስታንዳርድ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያውያን የኮንስትራክሽን ተዋናኞች በስታንዳርድ እንዲበቁ ማድረግ አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም።
አሁን ኢንዱስትሪው በተያዘለት ዋጋ እና ጥራት መጠን ደህንነቱ የተጠበቀ ምርት ያቀርባል? የሚል ጥያቄ ከቀረበ ከኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ አንፃር የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የሚሠራው የራሱ ድርሻ አለው። እኛ ደግሞ በቁጥጥር የምንሰራው የራሳችን ድርሻ አለን።
ሌላው ወሳኙ ከተያዘለት ጊዜ በላይ ምን ያህል ጊዜ ወሰደ የሚለው ነው። ለምሳሌ የሕዳሴው ግድብ የተያዘለት ጊዜ አምስት ዓመት ነው። ስለዚህ ጥያቄ የሚያስነሳው ኢንዱስትሪው ራሱ ጊዜውን ሲወስን ብቃት ነበረው? የሚለው ነው። እውነት የህዳሴው ግድብ በአምስት ዓመት ያልቃል ለማለት ይቻላል? ስንል ጠይቀን በደንብ ካሰላሰልነው ጊዜውን የገመትንበት መንገድ ጥራት አልነበረውም ማለት ነው። ስለዚህ አንደኛው የጊዜ ግምታችን ወደ እውነት የተጠጋ እንዲሆን ማድረግ ነው። አፈፃፀሙን በትክክል ገምተን በተያዘለት ጊዜ ውስጥ ይጨርሳል? የሚለውን በትክክል ማሻሻል ነው።
ሌላው በተገመተው ወጪ ልክ ይጠናቀቃል? ለምሳሌ የሕዳሴው ግድብ የተያዘለት ሰማኒያ ቢሊየን ብር ነው። በትክክል ኢንዱስትሪው የገመተበት መንገድ ወደ እውነት የቀረበ ነው? ሲባል ጥያቄ ውስጥ ይገባል፤ ምክንያቱም ግምት ለእውነት የቀረበ ነው። የዛሬ አስር ዓመት የዓለም ዋጋ ምን ያህል ይሆናል? ብሎ መገመት መቻል አለበት። ከአዝሚያሚያዎች ተነስቶ መገመት አለበት። በእኛ አገር አሰራር እና በእኛ አገር ገበያ ብቃት ያለው የመገመቻ ሥርዓትን መገንባት የግድ ነው። እርሱን ካረጋገጥን በኋላ ደግሞ የመገመት ብቃትን ማረጋገጥ ነው።
እናም በዛ ዋጋ የመጨረስ አቅምን መፍጠር ነው። እነኚህ አመልካቾች ናቸው። በእነዚህ አመልካቾች ውስጥ አስራ አንድ ጥናቶችን አስጠንተናል። በአገሪቷ የኮንስትራክሽን ኢንደስትሪ ስርዓት ባልያዘው የጊዜ ግምት ከ157 በመቶ በላይ መፋለሶች አሉ፤ የዋጋም ጉዳይ ከዚህ በላይ ነው። በተለይ አሁን ደግሞ ጠዋት እና ማታ የግብዓት ዋጋ በሚቀያየርበት ወቅት ከዛ በላይ ይሔዳል ማለት ነው። ስለዚህ ወደ ፊት ከዚህ ተነስተን የዋጋም ሆነ የጊዜ ግምት ሥርዓታችን በዚህ ያህል ተሻሽሏል እንላለን።
ከዓላማችን አንፃር ሲቃኝ፤ ሥራዎች ከዓላማችን ጋር የተያያዙ ናቸው። የሶስት ዓመቱን ገምግመን በፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ካሉት ዘርፎች የከተማ እና መሰረተ ልማት ከገቢዎች ቀጥሎ ያለ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። እንደተቋም ግን ስናይ በተለይ ከአሰራር እና ሙስናን ከመከላከል አንፃር በአፅንኦት መሥራት አለብን ብለናል። በአጠቃላይ ግን ሙስና ላይ፣ የአገር ውስጥ እና የቀጣናው ተወዳዳሪነት፣ የጊዜ እና የዋጋ ግምት ላይ እንሠራለን።
አዲስ ዘመን፡- በዋናነት ግን ግንባታዎች የሚዘገዩበት ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ መስፍን፡- ከምክንያቱ በፊት ባለድርሻ አካሉ ማን ነው? የሚለው በደንብ ማየት ይፈልጋል። ሁሉም የድርሻውን ማግኘት አለበት። ባለድርሻ አካላት የሚባሉት ብዙ ቢሆኑም ዋነኛዎቹ አራት ናቸው። አንደኛው የፕሮጀክቱ ባለቤት ነው። እርሱ ራሱ በሁለት ይከፈላል። የመጀመሪያው ገንዘቡን የሚበጅተው አለ። ለምሳሌ መንገዶችን ብናይ የዓለም ባንክ ነው። የዓለም ባንክ በአንዴ ገንዘቡን አይለቅም፤ በራሱ መስፈርት እየመዘነ ግንባታውን ሲያምንበት ገንዘቡን ይለቃል።
ሌላው የሥራው ባለቤት፣ ተቋራጩ እና አማካሪው አሉ። ሁሉም የየራሳቸው ሚና አላቸው። ከእነዚህ ውጪ የሆኑ ካለእነርሱ ግንባታው የማይሳካ፤ የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች አሉ። አቅራቢዎች፣ የማሽን አከራዮች፣ የፋይናንስ ተቋሞች፣ ዋስትና የሚሰጡ ኢንሹራንሶችም የየራሳቸው ሚና አላቸው። ለምሳሌ አቅራቢው ለኮንትራክተሩ ውል ገብቶ ካላቀረበ ተቋራጩ ሽባ ይሆናል።
በተጨማሪነት ደግሞ እንደእኛ ያሉ የመንግስት ተቋማት የቁጥጥር ባለድርሻዎች አሉ። ፈቃድ የሚሰጡ፣ የግንባታ አካላቶችን የሚቆጣጠሩ፣ የሚከታተሉ እና ኢንዱስትሪውን በፖሊሲ የሚመሩ አሉ። እነዚህ አራቱም የየራሳቸው ድርሻ አላቸው። ከጥያቄው አንፃር ሲታይ በፋይናንስ ችግር የቆሙ አሉ። ለምሳሌ ወደ አቃቂ ያለው መንገድ ፕሮጀክቱ ፋይናንሱን አቆመ። መንገዱ ወዴት ይሂድ? ውዝግቡን ጨርሶ ለመፍታት እስከ ዛሬ ቆየ። አሁን መተረቻ ሆኗል። ችግሩ ግን የፋይናንስ ነው።
ብዙዎቹ የመንግስት ሕንፃ ፕሮጀክቶች ዩኒቨርሲቲዎች የቆሙት በውዝግብ ነው። የይገባኛል ጥያቄዎች አሉ። አንደኛ የይገባኛል ችግር ምንጩ አማካሪ ነው። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከላይ እንዳልኩት አዋጭነቱ በደንብ ስለማይጠና ሌላ ያልነበረ ፍላጎት ይወለዳል። ግማሾቹ ወደ ፍርድ ቤት ይሔዳሉ። ለምሳሌ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ወደ አስራ አራት ህንፃ ከአስራ ሁለት ዓመት በላይ ዘግይቷል። ይህ የሆነው በፍርድ ቤት ምክንያት ነው። አንድ ብሎክ በትንሹ 500 ተማሪ ይይዝ ነበር ቢባል በአስራ አራት ሲባዛ በአስራ ሁለት ምን ያህል የአርሶአደር ልጆች ዕድል እንደተመናመነ ማሰብ ይቻላል። ስለዚህ በሚፈጠር ውዝግብ የመጡ ችግሮች ብዙ ናቸው።
ሌላው ደግሞ ከዋናው ኮንትራክተር ውጪ ያሉ ሌሎች ንዑሳን ኮንትራክተሮችን የተመለከተ ነው። የህንፃውን ሊፍት ኮንትራክተሩ ለንዑስ ኮንትራክተር ኮንትራት ይሰጣል። እንደገና ሊፍት ለማስመጣት ኤል.ሲ ይጠየቃል፤ ዶላር ያፈለጋል፤ የዶላር እጥረት ሁለቱንም ተቋራጮች ይይዛል። በተለይ ብዙ መንገዶች እና ትልልቅ ፕሮጀክቶች የቆሙት በውጭ ምንዛሬ ችግር ነው። ሌላው የቁጥጥር ችግርም አለ። በጊዜ ይህንን አስተካክሉ ስለማይባል መንግስትም ሆነ ፕሮጀክቱ ተጎጂ ይሆናሉ።
ለምሳሌ ወደ ፍርድ ቤት ከመሄድ ይልቅ ተቆጣጣሪው አማራጭ ሥርዓት ቢኖረው ወዲያው ችግሩ ይፈታ ነበር። ፍርድ ቤት ለማጣራት የሚወስደውን ጊዜ ያሳጥር ነበር። ስለዚህ በእነኚህ ባለድርሻዎች ያለው እጥረት በሙሉ ብዙ ፕሮጀክቶች እንዲቆሙ አድርጓል።
አዲስ ዘመን፡- ከላይ ቢጠቅሱትም በደንብ አብራሩልኝ። ምን ያህል ፕሮጀክቶች ቆሙ? በእናንተስ ምን ያህል ተጠናቀቁ?
አቶ መስፍን፡- 920 አካባቢ ናቸው። እነዚህን በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል። አንደኛው ከለውጡ በፊት የነበሩ እና ከለውጡ በኋላ ያሉ እንበላቸው። ከለውጡ በፊት የነበሩ በተለይ በሁለት ዓመት ይጠናቀቃሉ ተብለው የነበሩ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑት ተጠናቀዋል። አንዳንዶቹ በሲሚንቶና ብረት በግብአት እጥረት የተጓተቱ ናቸው። ይህ የዋጋ ማስተካከያ ስለተፈቀደ፤ እርሱን በስራ ላይ ያሉ አማካሪዎች እና ተቋራጮች ያሉበት ፈጥነው ወደ መጠናቀቅ ደርሰዋል። አሁንም ግን ጭቅጭቅ እና ውዝግብ ላይ ያሉ ተጓትተዋል። በእኛ ቁጥጥር ስር ያሉ ከ258 በላይ የሚሆኑት ግን ግብረመልስ ተሰጥቷቸው፤ የግብረ መልሱ ክትትል እየተደረገ ነው። 240ዎቹ ተጠናቀዋል። ይህ ትልቅ ስኬት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ግንባታዎቹ በጊዜ ባለመጠናቀቃቸው አገሪቱ ምን ያህል ተጎድታለች ይላሉ? ይህንን አስጠንታችኋል?
አቶ መስፍን፡– እውነቱን ለመናገር አላስጠናንም። ነገር ግን ካለው የዋጋ ንረት እና የዘገዩበትን ጊዜ ደምረን ስናያቸው በእርግጠኝነት ከተያዘው በጀት በላይ አስር እጥፍ እና ከዛ በላይ ጨምረዋል። ለምሳሌ ተቋሙ ያለበት እንፃ ለግንባታ ሲጀመር 400 ሚሊየን ብር ይፈጃል ተብሎ የተጠናቀቀው በዛው ብር አካባቢ ነው። ትንሽ ቢዘገይ ኖሮ ግን ከ4 ቢሊየን ብር በላይ ይፈጅ ነበር። ስለዚህ እነኚህ ፕሮጀክቶች ዘገዩ ቢባል አንዷን የብረትን ወጪ ስናይ በኪሎ በ17 ብር ሂሳብ የገቡ ውል የተያዘላቸው ናቸው። ዛሬ የብረት ዋጋ ወደ 140 ብር አካባቢ ደርሷል። ቢዘገይ መንግስት በዚህን ያህል ይከስራል ማለት ነው።
በእርግጥ መንግስት መሠረተ ልማት የሚገነባው ለማትረፍ አይደለም። ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማዋል ነው። ስለዚህ ብዙ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ቢጠናቀቁ ይኖራቸው የነበረ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የታቀደላቸውን ያህል ይሆን ነበር። መንገድ ከሆነ ከአርሶ አደሩ ጋር፣ ከማዕድን ጋር አጠቃላይ ከኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጋር ይያያዛል። ትምህርት ቤት ከሆነ ደግሞ ነገ ኢትዮጵያን ከሚረከብ ትውልድ ጋር የሚያያዝ ነው። የአንድ ኮንስትራክሽን መቋረጥ ጉዳቱ ብዙ ነው። ያስከተለውን ጉዳት በሚመለከት በሚቀጥለው ዓመት ለማስጠናት እንሞክራለን።
አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ እንደዚህ ተመሳሳይ ተደጋጋሚ እና ብዛት ያለው የግንባታ መቆም እንዳይኖር የቆሙትም ሙሉ ለሙሉ እንዲጠናቀቁ ምን እየተሠራ ነው?
አቶ መስፍን፡- መንግስት ሁለት አቅጣጫዎችን ይዟል። አንደኛው ፕሮጀክቶች በስሜት ዝም ብለው ወደ ሥራ እንዳይገቡ እና በስሌት እንዲሰራ አቅዷል። ያንን ስሌት ማን እንደሚሠራ ባለቤት ሰጥቷል። ለምሳሌ ለፕላን እና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር የተነሳሽነት ክፍሉን እና የአዋጭነት ጥናት ተካሂዶ ፕሮጀክቱ ከታመነበት ይፀድቃል። ፕሮጀክቱ ሲፀድቅ ተቋማችን ይመዘግባል። ወደ ዲዛይን ሲገባ እኛ ዲዛይኑን እንከታተላለን። ምክንያቱም መጨረሻ ላይ ፕሮጀክቱ ላይ ችግር የሚፈጠረው በቅድሚያ ዲዛይኑ ላይ ችግር ሲኖር ነው። ስለዚህ ዲዛይኑ በደንብ ይሠራል።
ሌላው በጨረታ ጊዜ የሚመጡ ሁለት ትልልቅ ጥፋቶች አሉ። በጨረታ ጊዜ አንደኛው ዋጋ ሰብሮ ይገባና መጨረስ ያቅተዋል። ስለዚህ በአነስተኛ ዋጋ የሆነበትን ምክንያት ዘርዝሮ ማስረዳት ይጠበቅበታል። ይህንን ሌላው ዓለምም የሚጠቀምበት ነው። ለምሳሌ የሲሚንቶ ዋጋ በገበያ ላይ 1ሺህ 200 ብር ሆኖ እርሱ በ200 ብር ገዝቼ እሰራለሁ ካለ ምን ሊያተርፍ ነው? ስለዚህ አይሰጥም። በዲዛይን ጊዜ ድብቅ ትርፍ ይኖረዋል ማለት ነው። በአርቴፊሻል ዋጋ ይተክልና በውዝግብ የሚበላውን ገንዘብ ያስባል።
የግዢ አዋጁ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ታይቶ ወደ ምክር ቤት ሄዷል። በአዋጅ እና በህግ የሚመለሱ አሉ። የሙስና ጉዳይ በጥብቅ ዲስፕሊን ከተመራና ወቅታዊ ውሳኔ ከተሰጠ እንደዚህ ዓይነት መዘግየቶች ዕድላቸው ትንሽ ይሆናል። ውዝግቦች ቁጥራቸው ያንሳል። ውዝግቦች ሲኖሩም አማራጭ ውዝግቦችን ለመፍታት በተቋማችን ራሱን የቻለ ይህንን ሥራ ብቻ የሚሠራ የሥራ ክፍል እየተደራጀ ነው። በቀጣይ ውዝግቦች እየተቀጩ የሚሄዱበት ሥርዓት ይኖራል። ይህ ደግሞ ያደጉት አገሮችም የተጠቀሙት ነው። ተቋራጮችም ሆኑ አማካሪዎች ክልል ላይ መጥፎ ሥራ ሰርተው የፌዴራልን ወይም ፌዴራል ላይ መጥፎ ሥራ ሰርተው ከክልል ክልል የሚንሸራሸሩበት ዕድል አይኖርም።
በስርዓት ዳኛ ኖሮ የሚጫወት ይጫወታል፤ መውጣት ያለበት ይወጣል። ቻይና እና ህንድም በዚሁ መልኩ ተመሳሳይ ነበር። ቻይና የኮንስትራክሽን ዕድገት በሶስት ተከፍሎ ሲታይ የመጀመሪያው ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ ነው። በኢትዮጵያም የ30 ዓመት ፍኖተ ካርታ (ሮድ ማፕ) ተዘጋጅቷል። ችግሮች የሚቀረፉት እና ወደ ትክክለኛው መስመር የሚገቡት በሁለተኛው ዘመን ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን የቀሩትን ለማጠናቀቅ ምን ዕቅድ ተይዟል?
አቶ መስፍን፡- አሁን መንግስት የያዘው አቅጣጫ ሁለት ነው። አንደኛው ፕሮጀክቶቹ ተለያይተው ይቀመጡ። ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ እና ቁርጠኝነት የሚያስፈልጋቸው በቅድሚያ ይለቁ የሚል ነው። ሌሎቹ ግን ለትንሽ ጊዜ ቆም ብለው በተለይ የበጀት ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት በሚችሉበት ጊዜ ይሠራሉ። አንዱ ይህ ነው። አዲሶቹ ግን እንደነዛኞቹ ሰለባ እንዳይሆኑ ቁጥጥር ስለሚደረግ ብዙ ችግር አያጋጥምም ብለን እናስባለን።
አዲስ ዘመን፡- መገለፅ ያለበት ቀረ የሚሉት ካለ ?
አቶ መስፍን፡- መገናኛ ብዙሃን እንደአራተኛ መንግስት የሚቆጠሩ ናቸው። ከጎናችን ሆነው ቁጥጥር ማድረግ አለባቸው። አንደኛው መሰል ተቋማትን መጠየቅና ሌሎችም ባለድርሻ አካላትን የፕሮጀክት ባለቤቶችን፣ ተቋራጮችን እና አማካሪዎችን እየፈለፈሉ ማጋለጥ ከቻላችሁ ህዝቡ ራሱ ጥራት፣ ዝርፊያም ሆነ ደህንነት ላይ ጠያቂ ከሆነ እና ከተባበረ ሙሉ ለሙሉ ውጤታማ መሆን ይቻላል። ስለዚህ መገናኛ ብዙሃን እንዲተባበሩን ጥሪዬን አቀርባለሁ። ቁጥጥር የአንድ አካል አይደለም። ህዝብም መተባበር አለበት። ህዝቡም ከተባበረ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን በማሳካት ውጤታማ እንሆናለን።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
አቶ መስፍን፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25/2015