አቶ ማስረሹ ፍቃድ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ግብር ከፋይ ናቸው። ሌላም ጊዜ እንደሚያደርጉት ሁሉ የግብር መክፈያ ወቅትን ጠብቀው ግብራቸውን ለመክፈል ወደ ቢሮው የሄዱበትን ቀን ያስታውሳሉ። ያን ዕለት የክፍያ አገልግሎቱ የሚሰጥበትን አሰራር ግን ወትሮ እንደሚያከናውኑት ሆኖ ሊያገኙት አልቻሉም፤ በዲጂታል ተቀይሯል።
አገልግሎቱን ለማግኘት የሚያስችላቸውን ቅጽ (ፎርም) እንዲሞሉ ተደረገ፤ ከዚያም በአጭር የጽሁፍ መልዕክት ማሳወቂያ ዘዴ በአጭር ጊዜ ውስጥ መረጃው ደረሳቸው፤ ምንም አይነት ምልልስ ሳያስፈልግ አስፈላጊው መረጃ በቅጽበጽ ተሞልቶ የተጠናቀቀና ክፍያውን በቴሌ ብር መፈጸም ቻሉ። በቴሌ ብር የክፍያ ሥርአት ግብራቸውን መክፈል መጀመራቸው የጊዜ ብክነትና ድካምን ማስቀረት እንደተቻለ ነው ማስረሹ የተናገሩት።
ቀደም ሲል የግብር ክፍያ ሥርአቱ ረጃጅም ሰልፎችን ጠብቆ የሚከናወን ከመሆኑ በተጨማሪ የክፍያ ሂደቱም ረጅም በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቅቆ ለመጨረስ አስቸጋሪና የቀናት ጊዜን የሚወስድ ነበር ያሉት አቶ ማስረሹ፤ በአጠቃላይ አሰራሩ እጅግ ኋላ ቀርና ግብር ከፋዩን የሚያሰለች እንደነበር ያስታውሳሉ።
አዲሱ በቴክኖሎጂ የታገዘ የአሰራር ሥርአት ይሄን ሁሉ ችግር ማስቀረቱንም አመልክተዋል። ጊዜ ሳይወስድ በደቂቃዎች ውስጥ አገልግሎት አግኝቶ ክፍያ መፈፀም እጅግ እንደሚያስደስት ይገልጻሉ። ይህን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ቴክኖሎጂ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፣ በተለይ ለቴክኖሎጂው መቆራረጥ እንቅፋት የሆኑትን ተከታትሎ ማስወገድ እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባሉ። አንዳንዴ ‹‹ሲስተም የለም›› የሚሉ ምክንያቶች አሁንም አንደሚሰጡና ይህም ተገቢ እንዳልሆነ ጠቁመዋል። ጊዜው ዘመናዊነትን እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፣ ይህን አሰራር አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ ሙና አሳየ በበኩላቸው ግብራቸውን ቢሮው በዘረጋው ዲጅታል ሲስተም ተጠቅመው በቴሌ ብር መክፈል መጀመራቸውን ይናገራሉ። ግብር ለመክፈል የግብር መክፈያ ማዕከላት ድረስ መሄድ አላስፈለጋቸውም፤ ባሉበት ሆነው ሞባይል ስልካቸውን ተጠቅመው በዲጅታል ሲስተም መክፈል እንደሚችሉ ካወቁ ጊዜ ጀምሮ ግብር ለመክፈል የሚያስፈልጓቸውን መስፈርቶች ካሟሉ በኋላ ግብር እንደሚከፍሉ ይገልጻሉ። ዲጂታል ዘዴን ተጠቅሞ ግብር ከመክፈል ባሻገር አሰራሩ የንግድ ፈቃዳቸውን በቀላሉ ለማደስ እንደረዳቸውም ጠቁመዋል።
ወይዘሮ ሙና በቀድሞው አሰራር ግብር ለመክፈል ከፍተኛ ጭንቀትና ውጣ ውረድ ይገጥም እንደነበር አስታወሰው ፤ እንግልቱና መጉላላቱ አሰልቺ ከመሆኑ የተነሳ የሚወሰደው ጊዜም ረጅም እንደነበረ ይገልጻሉ።‹‹ አዲሱ አሰራር ይህንን ሁሉ ችግር እንደቀረፈ ጠቅሰው፣ ጊዜንና ወጪን በመቆጠብ በቀላሉ ግብር ለመክፍል ይረዳል›› ይላሉ።
ዲጅታል ዘዴን ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል የሚሉት ወይዘሮ ሙና፤ እሳቸው የሚያውቋቸው የንግድ አጋራቸው በዲጂታል ሲስተሙ ተጠቅመው ለመክፈል ሲሞክሩ ሲስተሙ እንዳልተቀበላቸውም ጠቁመዋል። እነዚህ በዲጅታል አጠቃቀሙ ላይ የታዩ ችግሮችም ተፈትተው ዘመናዊ በሆነ መልኩ ቢሰራ የተሻለና የተቀላጠፈ አገልግሎት ማግኘት እንደሚቻል ነው ያስታወቁት።
የዘመናዊ አገልግሎት አሰጣጡን በተመለከተ የቢሮው የመረጃ ቴክኖሎጂ ልማትና አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ አብዱላዚዝ ካሊፋ እንደሚሉት፤ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ከ449ሺ በላይ ግብር ከፋዮችን የሚያስተዳድር ግብር ሰብሳቢ ተቋም ነው። የከተማ አስተዳደሩ ሙሉ ለሙሉ የሚያስተዳድራቸው ከ320ሺ በላይ የሚሆኑ የደረጃ ‹‹ሐ››ግብር ከፋዮች ናቸው። የእነዚህ ግብር ከፋዮች ቁጥር በጣም ከፍተኛ ነው። የተገልጋዩ መብዛት አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ከፍተኛ ክፍተት እንዲኖር አድርጎል።
ቀደም ሲል ተቋሙ ግብር ለማስተዳደር የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀም ነበር። ግብር ከፋዩ ብዛት ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ግን አገልግሎት አሰጣጡ ላይ የነበሩ በርካታ ተግዳሮቶች ተገልጋዩን ለእንግልት ሲዳርጉ ቆይተዋል። በመሆኑም ይህንን አሠራር ለመቀየር የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የአሰራር ለውጦች ለማምጣት ስትራቴጂ በመንደፍ ወደ ሥራ ተገብቷል።
በዚህም የግብር ከፋዩን ምልልስ ሊቀንሱ የሚችሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ሥራ ላይ መዋል መቻላቸውን ነው አቶ አብዱላዚዝ ያብራሩት። እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በየታክስ ማዕከላቱ ተበታትኖ የነበረውን አሠራር በአንድ ላይ በማስተሳሰር ግብር ከፋዩን በተሻለ መልኩ ማስተናገድ የሚቻልበት የአሠራር ዘዴ ሥራ ላይ ውሏል። ለግብር ከፋዩ አማራጭ የክፍያ ዘዴዎች በመፍጠር፣ ክፍያ ማሳወቂያና ክሊራንስ የሚወሰድበትን ዘዴ ማመቻቸት ተችሏል። በአዲሱ አሠራር ከ320ሺ በላይ የሆኑ ግብር ከፋዮችን በማስተናገድ ግብር ለመወሰን፣ ክፍያ ለማስከፈል እና ክሊራንስ ለመስጠት የሚችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
ግብር ከፋይ በግብር ማሳወቂያ ወቅት አገልግሎቶች ለማግኘት ወደ አምስት ጊዜያት ወደ ገቢዎች ቢሮ መመላለስ ይጠበቅበት ነበር። ግብሩን ለማወቅ፣ ግብሩን ለማስወሰን፣ ውሳኔ ይሰጠኝ ለማለት፣ በውሳኔው መሠረት ክፍያ ለመፈጸም እና ለከፈለበት ማረጋገጫ (ክሊራንስ) ለመውሰድ ወደ ተቋሙ መመላለስ ይጠበቅበታል። ይህንን ሁሉ ካጠናቀቀ በኋላ ደግሞ ንግድ ፈቃዱን ለማደስ ወደ ንግድ ቢሮ መሄድ የግድ ይለውም ነበር።:
አሁን የተዘረጋው የአሠራር ሥርዓት ግን እነዚህን ሁሉ ምልልሶች እና እንግልቶች ቀንሷል የሚሉት አቶ አብዱላዚዝ፤ አዲሱ የአሠራር ዘዴ (ሲስተም) ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመሆን የኦታስ (የኦንላየን ታክስ አውቶሜሽን)ንና የቴሌብር ሲስተምን በአንድ ላይ በማስተሳሰር ለግብር ከፋዩ በአጭር የስልክ መልዕክት እንዲደርሰው የማድረግ ሥራ መሥራቱን ጠቁመዋል። ግብር ከፋዩ ወደ ተቋሙ መምጣት ሳያስፈልገው በ7075 አጭር የስልክ መልዕክት ግብሩን ካለበት ሆኖ መክፈል ይችላል ሲሉ አብራርተዋል።
በአዲሱ አሠራር ግብር ከፋዩ የትኛውም ቦታ ላይ ሆኖ የሞባይል ስልኩን በመጠቀም ግብሩን መክፈል ይችላል ያሉት አቶ አብዱላዚዝ፤ በሌላ በኩል ግብር ከፋዩ ከገቢዎች ቢሮ የሚላክለትን ቁጥር በመያዝ በየትኛውም የንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በኩል ቀጥታ መክፈል የሚችልበት አማራጭም እንደተመቻቸ ጠቁመዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በአጭር የስልክ መልዕክት አማካይነት የግብር ውሳኔው ለግብር ከፋዩ የሚላክ ሲሆን፤ ክፍያውን ደግሞ በቴሌ ብርና በንግድ ባንክ አማራጮች አማካይነት መክፈል የሚችልበት የአሠራር ዘዴ ተዘርግቷል። በመጨረሻ ለግብር ከፋዩ ማረጋገጫ ደረሰኝ (ክሊራንስ) እንዲደርሰው ይደረጋል። ይህ ደግሞ ንግድ ፍቃዱን በቀጥታ ለማሳደስ ያስችለዋል።
በአዲሱ አሠራር መሠረት የግብር ከፋዩ ውሳኔ በ7075 አጭር የስልክ መልዕክት አማካይነት ወደ ተመዘገበው የስልክ ቁጥር ይልካል። ግብር ከፋዩም በቴሌ ብር *127# በመደወል ከሚመጡት አማራጮች ውስጥ ግብር የሚለውን በመምረጥ ከገቢዎች ቢሮ በአጭር የስልክ መልዕክት የተላከውን ቁጥር ካስገባ በኋላ የሚመጡለት መረጃዎች የራሱ መሆናቸውን አረጋግጦ ይሁንታውን አሳይቶ ግብሩን መክፈል ይችላል።
ይህ የአሠራር ዘዴ ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ የዋለው ከሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ ነው የሚሉት አቶ አብዱላዚዝ፤ ወደ ተቋሙ በመምጣት መስተናገድ ከሚጠበቅባቸው ግብር ከፋዮች መካከል ከ110ሺ በላይ የሚሆኑት በአዲሱ የአሠራር ዘዴ (ሲስተም) መስተናገዳቸውን አስታውቀዋል። የተቀሩት ግብር ከፋዮች በተለያዩ ምክንያቶች ወደ አሠራሩ እንዳልገቡም ገልጸዋል።
ቴክኖሎጂው ተቋሙ ባለው የሰው ኃይል ደንበኞቹን ለማስተናገድ ይቸገርበት የነበረውን ማስቀረቱን የገለጹት አቶ አብዱላዚዝ፤ አሠራሩን አጠናክሮ ለማስቀጠል ተደራሽ ባልሆኑ ቦታዎች ላይ መረጃና ስልጠና በመስጠት ሁሉም ግብር ከፋይ በዚህ ዘዴ ተጠቃሚ እንዲሆን ይደረጋል ይላሉ።
ግብር ከፋይ በሙሉ ወደ አዲሱ አሠራር ያልገባበት ዋንኛ ምክንያት አንዳንዱ ግብር ከፋይ አዲሱን ሲሰተም ስላልለመደው ከነባሩ አሠራር ቶሎ ያለመልቀቅ የሚታይበት በመሆኑ ነው አቶ አብዱላዚዝ የገለጹት። የአሠራር ሥርዓቱን በደንብ እስከሚለምድ ድረስ ወደ አዲሱ ሲስተም ስርዓት ለማስገባት በእጅጉ እንደሚቸገር ጠቁመው፤ ለዚህም ተከታታይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እንደሚሰራ አመላክተዋል።
‹‹ይህ አሠራር በግብር አሰባሰቡ ሂደት ከፍተኛ ውጤት የተገኘበት ነው›› ሲሉም አቶ አብዱላዚዝ ይገልገጻሉ፤ ተቋሙ የሚሰራው በውስን የሰው ኃይል መሆኑንም ጠቅሰው፣ በግብር አሰባሰብ ላይ ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል። በተጨማሪም ተቋሙ ሠራተኞች በየዕለቱ ግብር ከፋዩን በማስተናገድ ሥራ ላይ ብቻ ከሚጠመድ ሌላ ትልልቅ ሥራዎች ለመሥራት ያስችላል። የተቋሙን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት መፍትሔ ለማስቀመጥ የሚያስችል እድል የሚፈጥር ነው ይላሉ።
በሌላ በኩልም ለግብር ከፋዩ ጊዜውን፣ ገንዘቡንና ጉልበቱን እንደቆጠበለትም ነው የገለጹት። ግብር ከፋዩ ግብር ለመክፈል ያባክን የነበረውን ጊዜው ተቆጥቦ በንግድ ሥራ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ጠቅሰው፣ ግብር ከፋዩ አገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚያነሳውን ቅሬታ መፍታቱ በራሱ ትልቅ ውጤት መሆኑን ነው አቶ አብዱላዚዝ የሚገልጹት።
አሁን በተዘረጋው አሠራር ግብር ከፋዩ ወደ ተቋም መምጣት እንደማያስፈልገው ጠቅሰው፣ የመረጃ ለውጥ ያደረጉ ግብር ከፋዮች ቢሮ መምጣት እንደሚጠበቅባቸው አስታውቀዋል። እነዚህ ግብር ከፋዮች ወደ ቢሮ በመምጣት መረጃውን ወቅታዊ ማድረግ ወይም የተላከው መረጃ ትክክለኛ ካልሆነ ተቋሙ ዘንድ በመቅረብ እንዲያስተካክሉ የሚጠበቅባቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።
አሠራሩ የሚሰራው በገባለት መረጃ መሠረት ነው የሚሉት አቶ አብዱላዚዝ፤ በተለይ በውክልና በሚሰሩ ንግዶች ላይ የገባው መረጃና ያለው እውነታ ሊለያዩ እንደሚችሉም ጠቅሰው፣ ለአብነት መረጃውን ያስገባው ሰው እና አጭር የስልክ መልዕክቱ የሚደርሰው ሰው የተለያየ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ። በዚህ ጊዜ የመረጃ ጥራት ችግር በመኖሩ ውሳኔው እንደገና የሚወሰንበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል አመላክተዋል።
በሌላ በኩል በተቋሙ የስልክ መረጃ በሚሞላበት ጊዜ የቁጥር ስህተት ሊፈጸም እንደሚችል ጠቅሰው፣ በዚህ ጊዜ መልዕክቱ ለተሳሳተው ሰው ሊደርስ የሚችልበት አጋጣሚ ሊፈጠር እንደሚችል አልሸሸጉም። በተመሳሳይ ግብር ከፋዩ ደግሞ ስልኩን ቁጥሩን ሲያስመዘግብ በትክክል የማያስመዘግብ ሁኔታ በመኖሩ ያብራራሉ።
አቶ አብዱላዚዝ ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች መሠረት የመረጃ ጥራት ችግር ሊያጋጥም ይችላል ባይ ናቸው። ‹‹በዚህ አሠራር ሥርዓት መሠረታዊ ችግር የሆነው አንዱ የመረጃ (የዳታ) ጥራት ችግር ነው›› ያሉት አቶ አብዱላዚዝ፤ አሁን በተገኘው ልምድና ተሞክሮ የተሻሉ የአሠራር ዘዴዎችን ሥራ ላይ ለማዋል እንደሚሰራ ጠቁመዋል። የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ሙሉ ለሙሉ የሚያስተዳደራቸው የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮችን እንደሆነ የሚገልጹት አቶ አብዱላዚዝ፤ ሌሎች ግብር ከፋዮች የሚስተናገድበት የአሠራር ሥርዓት የተለየ መሆኑንና ከፌዴራል ገቢዎች ሚኒስቴር ጋር በጋራ የሚሰሩ ሥራዎች እንዳሉም ይናገራሉ።
በቀጣይም ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚሰጡ አገልግሎቶች ፈጣንና ቀልጣፋ የሚያደርጉ አሠራሮችን የመዘርጋቱ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚያስቀጥል የሚገልጹት አቶ አብዱላዚዝ፤ ዘመኑን የሚመጥን ቴክኖሎጂ በመጠቀም አገልግሎቶችን በየጊዜው ለማዘመን ትኩረት ተደርጎ ይሰራል ይላሉ። ግብር ከፋዩ ማህበረሰብም ይህንን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ተቋሙ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ላይ እምነት ማሳደር እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 24 ቀን 2015 ዓ.ም