ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ከሚያስገኙ ምርቶች አንዱ የወርቅ ምርት መሆኑ ይታወቃል። ሀገሪቱ ወርቅ የምታመርተው በአነስተኛ እና ልዩ አነስተኛ የወርቅ አምራች ማህበራት/ በባህላዊ መንገድ/ እና በኩባንያዎች ነው። አብዛኛው የወርቅ ምርት የሚመረተው ግን በአነስተኛና ልዩ አነስተኛ በሚል በሚታወቁት ባህላዊ የወርቅ አምራች ማህበራት በኩል ነው።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ይህን የሀገሪቱን የወርቅ ምርት አምራቾቹን የሚያበረታታ ዋጋ በማስቀመጥ ይገዛል። ባንኩ ካለፈው ሰኔ 16 ቀን 2014 አንስቶ ከአለም ገበያ 35 በመቶ ጭማሪ ያለው ዋጋ በመስጠት ወርቅ ሲረከብ እንደነበርም ከወራት በፊት የወጣ የባንኩ መረጃ ያመለክታል። ያንን ተከትሎም አበረታች ሊባል የሚችል የወርቅ አቅርቦት ወደ ብሄራዊ ባንክ ሲገባ እንደነበር ጠቁሟል። ይሁንና ከአነስተኛ ወርቅ አምራቾች ወደ ባንኩ መግባት ያለበት ወርቅ መጠን እያሽቆለቆለ መሆኑን በተያዘው 2015 በጀት አመት መግለጹ ይታወሳል። ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ እየተስፋፋ የመጣው የወርቅ ህገወጥ ግብይት መሆኑ ተጠቁሟል።
ወርቅ በከፍተኛ ሁኔታ ከሚመረትባቸው ክልሎች ውስጥ አንዱ የጋምቤላ ክልል ነው። በክልሉ እስከ አንድ መቶ ኪሎ ግራም ወርቅ በወር ይመረት እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። በወርቅ ላይ የተፈጠረውን ህገወጥ ግብይት፣ ፍለጋና ማምረት ተከትሎ ይህ አሀዝ ወደ ስድስት ኪሎ የወረደበት ሁኔታ እንደነበርም አዲስ ዘመን ጋዜጣ በታህሳስ ወር ይዞት የወጣው ዘገባ ያመለክታል።
ዘገባው እንዳመለከተው፤ በማዕድን ሚኒስቴር የሚመራ የተቀናጀ የማዕድን ቁጥጥር ኦፕሬሽን ቡድን በክልሉ ዲማ ወረዳ ከጥቅምት ወር አንስቶ የተሰማራው ይህ ቡድን ባደረገው ቁጥጥር ከአካባቢው በጥቅምት ወር 2015ዓም 10 ኪሎግራም፣ በህዳር ወር 2015ዓም 18 ኪሎግራም ወርቅ ብሄራዊ ባንክ እንዲገባ ማድረግ ተችሏል። ከአካባቢው መስከረም ወር ላይ ብሄራዊ ባንክ የገባው የወርቅ መጠን ግን ስድስት ኪሎ ግራም ብቻ እንደነበርና ቁጥጥሩ ከተጠናከረ በኋላ መጠኑ መጨመሩ ተጠቁሟል። ቡድኑ ባደረገው ኦፕሬሽን በኮንትሮባንድ የወርቅ ዝውውር የተጠረጠሩ 11 ግለሰቦች በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸውም እንደነበርም ተገልጸል።
የፌዴራል መንግሥትም ይህን ህገወጥ ተግባር ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተጠናከረ ስራ እያከናወነ ይገኛል። በማእድን ዘርፉ በተለይ በወርቅ ማምረትና ግብይት ላይ እየተፈጸመ ያለውን ህገወጥ ድርጊት ለመቆጣጠር የፌዴራል መንግሥት ከማእድን ሚኒስቴር፣ ወርቅ ከሚመረትባቸው ክልሎች፣ ከፌዴራል ፖሊስና ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን ለመቆጣጠር እየሰራ ይገኛል። የቁጥጥር ሥራው በተደረገባቸው ክልሎች የሚገኙ በሕገወጥ መንገድ በወርቅ ፍለጋ፣ ማምረትና ግብይት ላይ ተሰማርተው በተገኙ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው።
በቅርቡም የፀና የጉዞ ሰነድ፣ የመግቢያ ቪዛ እንዲሁም የመኖሪያ ፍቃድ ሳይኖራቸው በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በጋምቤላ ክልል በወርቅና የተለያዩ ማዕድናት ፍለጋ ላይ የተሰማሩ 45 የውጭ ሀገር ዜጎችና ሦስት ኢትዮጵያውያን ከእነ ኤግዚቢታቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሀይል ያወጣው መግለጫ ያመለክታል ።
በወርቅ ማእድን ላይ ህገወጥ ተግባር እያከናወኑ የሚገኙ አካላትን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራው ከሚከናወንባቸው ክልሎች አንዱ የጋምቤላ ክልል ስለመሆኑ ከፍ ብሎ ከቀረበው መረጃ መረዳት ይቻላል። በክልሉ የውጭ ሀገር ዜጎች ጭምር ናቸው በህገ ወጥ የወርቅ ማእድን ፍለጋ፣ ማምረትና ግብይት ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የተገኙት።
በጋምቤላ ክልል በህገወጥ የወርቅ ግብይት ላይ የተሰማሩ አካላትን በመከላከልና በመቆጣጠር በኩል እየተከናወነ ስላለው ተግባር፣ እየተገኘ ስላለው ውጤትና በቀጣይ ሊተኮርባቸው በሚገባ ጉዳዮች ላይ ያነጋግርናቸው የጋምቤላ ክልል የማእድን ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊን ወይዘሮ አኳታ ቻም እንዳሉት፤ ክልሉ ትልቅ የወርቅ ማእድን አቅም አለው። በክልሉ ወርቅ በብዛት የሚመረት ቢሆንም፣ በህገወጥ የወርቅ ግብይት የተነሳ ከዚህ የወርቅ ምርት ሀገር ተጠቃሚ እንዳትሆን ታደርጋለች።
ከወርቅ ኮንትሮባንድ ግብይት እየተስፋፋ መምጣት ጋር በተያያዘ ክልሉ በእቅዱ መሰረት ወርቅ ወደ ብሄራዊ ባንክ ማስገባት እንዳልቻለ ኃላፊዋ ይናገራሉ። በ2015 በጀት ዓመት 1ሺ 700 ኪሎ ግራም ወርቅ ለማግኘት ታቅዶ እንደነበር ጠቅሰው፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 146 ነጥብ 4 ኪሎ ግራም ወርቅ ብቻ መገኘቱን አስታውቀዋል።
የዓመቱን እቅድ ለማሳካት የኮንትሮባንድ ንግድ ትልቅ እንቅፋት መሆኑንም አመልክተው፤ በከፋ ደረጃ ላይ የሚገኘው የወርቅ የኮንትሮባንድ ንግድ ወደ ብሄራዊ ባንክ መግባት ያለበትን ወርቅ ወደ ተለያዩ ቦታዎች በመውሰድ ክልሉ ከወርቅ ማግኘት የሚገባውን ገቢ እንዳያገኝ ሲያደርግ መቆየቱን ይጠቁማሉ ።
እንደ ክልል የወርቅ ኮንትሮባንድ ጉዳይ በጣም ከአቅማችን በላይ እየሆነ መጥቶ ነበር የሚሉት ኃላፊዋ፤ እነዚህን ሕገወጥ ተግባሮች ለመቆጣጠር መንግሥት እርምጃ መውስድ ከጀመረ በኋላ መሻሻሎች እየታዩ መምጣታቸውንም ነው ያመለከቱት።
‹‹እንደኛ ክልል በወርቅ ግብይት ላይ ብቻ ሳይሆን በወርቅ አምራቾች ላይም እርምጃ ተወስዷል›› የሚሉት ኃላፊዋ፤ ግብይት ላይ የተሰማሩ አካላት የሚሰበሰቡትን የወርቅ ምርት በትክክል ወደ ባንክ እያስገቡ እንዳልሆነ ተናግረዋል፤ በወርቅ ግብይት ላይ ከተሰማሩት መካከል 36 በሚሆኑት ላይ እርምጃ መወሰዱንም አስታውቀዋል። አሁን በግብይቱ ላይ እንዲሰሩ የተፈቀዳላቸው ሁለት ብቻ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በፌዴራል መንግሥት በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት ከፌዴራል እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ካሉ አካላት ተውጣጥቶ በተቋቋመው ግብረ ኃይል አማካይነት በወሰደው እርምጃ በተለይ በክልሉ በህገወጥ ድርጊት የተሰማሩ የውጭ ሀገር ዜጎች እና ተባባሪዎቻቸውን ለመቆጣጠር በተከናወኑ ተግባሮች ትልቅ ለውጥ ማምጣት መቻሉን አስታውቀዋል። ህገወጥ ተግባሩን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚካሄደው የተጠናከረ ፍተሻ መሻሻሎች እየታዩ በየወሩ የሚገኘው የወርቅ መጠንም ጭማሪ እያሳየ መምጣቱን ኃላፊዋ አስታውቀዋል።
በዚህም ባለፈው የካቲት ወር 22 ኪሎ ግራም ወርቅ መገኘቱን ወይዘሮ አኳታ ጠቅሰው፤ በመጋቢት ወር የአምስት ኪሎ ግራም ጭማሪ በማሳየት 27 ኪሎ ግራም ወርቅ ማግኘት ተችሏል ብለዋል። የወርቅ ምርት ህገወጥ ግብይትን በመቆጣጠር የተከናወነው ተግባር በተጠናከረ መልኩ ከቀጠለ የበለጠ ለውጥ በማምጣት ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል ነው ኃላፊዋ የሚናገሩት ።
የማዕድን ዘርፉ ከተሰራበት ብዙ ገቢ እንደሚያስገኝ የጠቆሙት ኃላፊዋ፤ ባለፈው ዓመት ብዙ ወርቅ በማስገባት ብዙ ገቢም አግኝተናል ነው ያሉት። ዘንድሮ ምንም እንኳን እቅዱን ማሳካት ባንችልም የተገኘው የገቢ መጠን ግን ብዙ ነው ሲሉ ተናግረው፣ በተለይ ትልቅ የወርቅ አቅም ካለበት ዲማ በተለያየ መንገድ ብዙ ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።
በክልሉ ከፌዴራል ጀምሮ እስከታች ባሉ የፀጥታ አካላት ደረጃ የተዋቀሩ ኮሚቴዎች እንዳሉ የጠቆሙት ኃላፊዋ፤ ኮሚቴዎቹ በወርቅ ላይ የሚያደርጉትን የቁጥጥር ሥራ በማጠናከር ባደረጉት ፍተሻ ወርቅ የደበቁ አካላት መገኘታቸውን ጠቁመዋል። በእነዚህ አካላት ላይ እርምጃ የመውስዱ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ነው የተናገሩት።
በሕገወጥ መንገድ በወርቅ ማምረትና ፋለጋ ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላትም ተጠያቂ እንዲሆኑ በሚያስችል መልኩ እየተሰራ መሆኑን አመላክተው፤ በመከላከልና መቆጣጠር ስራው የተሰማራው አካል ሥራውን አጠናክሮ ከቀጠለ በቀጣይም ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል ሲሉ ጠቁመዋል።
‹‹ በወርቅ ማምረትና ፍለጋ ላይ የተሰማሩ አካላት ወርቅ የማንም ሀብት አይደለም፤ የሀገሪቷ ሀብት ነው›› ብለው ማሰብ አለባቸው ያሉት ኃላፊዋ፣ ወርቅ የሀገሪቷ ሀብት እስከሆነ ድረስ እያንዳንዱ አካል ይህን የሀገር ሀብት ከህገወጦች የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ሊያውቅ ይገባል ይላሉ። በወርቅ ማምረትና ፍለጋ የተሰማሩ አካላትም ግንዛቤ በደንብ ሊኖራቸው እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት። ህገወጦች ግን ግንዛቤ እያላቸው ሆን ብለው ሕገወጥ ድርጊት ይፈጽማሉ ሲሉ አስታውቀዋል።
እየተወሰደ ባለው እርምጃና በሚፈጠረው ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ የሚፈለገው ውጤት የማይመጣበት ሁኔታ እንደማይኖር የጠቆሙት ኃላፊዋ ፤ ሕብረተሰቡም እንዲሁ ወርቅ የራሴ ሀብት ነው ብሎ ሀብቱን እንዲጠብቅና እንዲንከባከብ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል ።
በአነስተኛ የወርቅ አምራች ማህበራት በኩል ክፍተቶች ይስተዋላሉ ሲሉ ኃላፊዋ ይጠቁማሉ። እነዚህ አምራች ማህበራት የተሟላ አቅም ስለሌላቸው ከሌሎች ባለሀብቶች ጋር የሚሰሩባቸው ሁኔታዎች አሉ፤ አብረው ከሚሰራቸው ባለሀብቶች መካከል አንዳንዶቹ ደግሞ ከውጭ ሀገር ዜጎች ጋር ውል በመግባት የሚሰሩበት ሁኔታ ይታያል፤ እነዚህ የውጭ ሀገር ዜጎች ደግሞ ወርቁን ሕገወጥ በሆነ መልኩ በማዘዋወር ሕገወጥነት እንዲስፋፋ እያደረጉ ይገኛሉ።
በወርቅ ማምረት ሥራ መስማራት ያለባቸው አቅም ያላቸው ማህበራት ብቻ መሆን እንዳለባቸውም ይገልጻሉ። አሁን በአነስተኛ የወርቅ አምራች ማህበራት በኩል ችግሮች እየተፈጠሩ መሆናቸውንም ጠቅሰው፤ ዋንኛው ችግር ካለአቅማቸው ወርቅ ማምረት ሥራ ላይ መሰማራታቸው መሆኑን ይጠቅሳሉ። ማህበራቱ በትክክል ሥራቸውን መሥራት የሚፈልጉ ከሆነ አቅማቸውን መሠረት ባደረገ መልኩ በመስራት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ እንደሚደረግም ነው ያስገነዘቡት።
‹‹ባለፈው ወር በህገወጦቹ ላይ እርምጃ ሲጀመር የወርቅ ምርት ሳይኖር ቀርቶ አልነበረም፤ የወርቅ ምርት ነበር›› የሚሉት ኃላፊዋ፤ እነዚህ አካላት ያመረቱትን ወርቅ በትክክል ወደ ባንክ ባለማስገባታቸው ነው ችግሩ የተፈጠረው ይላሉ። በዚህ ምክንያት በወርቅ ምርት ላይ ችግር መፈጠሩን ይጠቅሳሉ።
በእነዚህ በሕገ ወጥ መልኩ ወርቅ እንዲዘዋወር ባደረጉ የውጭ ሀገር ዜጎች ላይ እርምጃ እንደተወሰደው ሁሉ በቀጣይም በሌሎች ሕገወጦች ላይ እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል። አሁን በፌዴራል መንግሥት እየተወሰደ ባለ እርምጃ እንደ ጋምቤላ ክልል ጥሩ ለውጦች ተመዝግበዋል ብለዋል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ አሁን ላይ ክልሉ ከማእድናት አኳያ በዋናነት የሚያመርተው ወርቅ ነው። ሌሎች ማዕድናትን ማምረት ግን ገና አልተጀመረም። የወርቅ ማምረት ሥራው እንዲሰፋና ጥሩ ምርት እንዲገኝ ለማድረግ መንግሥት በያዘው አቋም መሰረት ክትትልና ቁጥጥሩን አጠናክሮ መቀጠል አለበት።
ወርቅ ማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ አምራቾችም የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ይኖርባቸዋል፤ ይህን ማድረግ ከቻሉ በህገወጥ የወርቅ ግብይት፣ ፍለጋና ማምረት ላይ የተሰማሩ ህገወጦችን በመቆጣጠር ለውጥ ማምጣት ይቻላል ይላሉ። መንግሥት ክትትል ቁጥጥር የማያደርግ ከሆነ አምራቹም የሚጠበቅበትን ግዴታ መወጣት ካልቻለ ለውጥ ማምጣት አይቻልም። ሁለቱም የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነትና ግዴታ በአግባቡ መወጣት አለባቸው ሲሉ ያስገነዝባሉ።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20/2015