የሰዎችን ቀልብ ከሚገዙና አዝናኝ የኪነ ጥበብ ዘውጎች ውስጥ አንዱ ሙዚቃ ነው። ሙዚቃ ከአዝናኝነቱ ባሻገር በርካታ ማህራበዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሌሎችም ሀገርኛ መልዕክቶች የሚተላለፉበት የጥበብ ዘርፍ ነው። በሙዚቃ ፍቅር፣ አንድነት ፣ መተሳሰብና አብሮነት ይሰበካል። በሙዚቃ የግል ስሜት፣ ደስታ፣ ፍቅር፣ አስተሳሰብ፣ ሃሳብ ያለገደብ ይገለፃል። በሙዚቃ የራስን ሁለንተናዊ ስሜት ከማንፀባረቅ ባለፈ የሌሎችንም ስሜት መኮርኮር፣ ማነሳሳት፣ ማነቃቃትና ማበረታታት ይቻላል። ለዛም ነው ሙዚቃ የአለም ቋንቋ ነው የሚባለው።
በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሙዚቃ ታሪክ ቀደምት ሙዚቀኞች በጊዜያቸው እንደየራሳቸው ቀለምና የአዘፋፈን ስልት በማቀንቀን የራሳቸውን የጥበብ አሻራ አስቀምጠዋል። የእነርሱን ፈለግ ተከትለውም በርካታ ተተኪ ሙዚቀኞች ተፈጥረዋል። እነርሱም በተራቸው አቀንቅነው የሚዚቃን ጥበብ ጥግ በራሳቸው መንገድ አሳይተዋል። አሁንም የዚህ ትውልድ ሙዚቀኞች በቀደምት የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ሙዚቃ ራሳቸውን ገርተው አያሌ የሙዚቃ ስራዎችን እንካችሁ ብለዋል።
ምንም እንኳን የዚህ ዘመን አብዛኛዎቹ ሙዚቀኞች በራሳቸው ነጠላ ዜማና ቀደምት የኢትዮጵያ ሙዚቃዎችን በራሳቸው መንገድ ዳግም ዘፍነው የአድማጫቸውን ቀልብ ለመሳብ ጥረት እያደረጉ ቢሆንም ከጥቂቶቹ በስተቀር እንደበፊቱ በራስ ሙሉ አልበም ሰርቶ አዳዲስ የሙዚቃ ስራዎችን ይዞ ብቅ ማለት ብርቅ እየሆነ የመጣ ይመስላል። ተተኪ ድምፃውያንን ለማፍራት የሚደረገው ጥረትም ያን ያህል አይደለም።
በእርግጥ ከአመታት በፊት ተጀምሮ ተቋረጠ እንጂ በኢትዮጵያ ቴሌቪዢን ሲተላለፍ የነበረው የኢትዮጵያ አይዶል የሙዚቃ ውድድር አዳዲስና ተተኪ ሙዚቀኞችን በማፍራት ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል። የኮካ ኮላ የሙዚቃ ባለተሰጥኦ ውድድርም በተመሳሳይ ተጀምሮ ተቋረጠ እንጂ እርሱም ቢሆን ሙዚቀኞችን በማፍራት በኩል የድርሻውን ተወጥቷል።
ቀደም ሲል ሲደረጉ የነበሩ የሙዚቃ ባለተሰጥኦ ውድድሮች ከተቋረጡ በኋላ ግን ከቅርብ አመታት ወዲህ እንደገና ወደ ቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለዋል። ለዚህም በፋና ቴሌቪዥን ‹‹የፋና ላምሮት›› የሙዚቀኞች ውድድር፤ መጀመሪያ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ኋላ ላይ ደግሞ በባላገሩ ቴሌቪዥን ‹‹የባላገሩ ምርጥ›› ወድድር ተጠቃሽ ናቸው።
በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያን አይድል የሙዚቀኞች ውድድር ከተቋረጠ ወዲህ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲህ አይነቱን ውድድር ‹‹ባላገሩ ምርጥ›› በሚል በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መጀመርና በሂደት ደግሞ በባላገሩ ቴሌቪዥን መቀጠል የተመልካቾችን ቀልብ በመሳብ ረገድ ትልቅ ድርሻ ወስዷል። በዚህ የሙዚቃ ባለተስጥኦዎች ውድድርም እንደነ ዳዊት ፅጌንና ኢሳያስን የመሰሉ በርካታ ወጣት ድምፃውያንን ማፍራት ተችሏል።
ባላገሩ ምርጥ የሙዚቃ ባለተሰጥኦዎች ውድድር ከተጀመረ ወዲህ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ የራሳቸውን አሻራ እያስቀመጡ ያሉ በርካታ አዳዲስ ድምፃውያንን እያፈለቀ ይገኛል። ሆኖም በኮቪድና በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት የዘንድሮው ውድድር ደብዝዟል። እንደከዚህ ቀደሙም በየክፍለሀገሩ ተዟዙሮ ባለተሰጥኦዎችን የመፈለግ እድልም አልነበረም። ውድድሩ ረጅም ጊዜ የፈጀውም በዚሁ ምክንያት ነው። በተቻለ አቅም ግን ባለተሰጥኦዎች ከየቦታው ተሰብስበው እንዲመጡና በውድድሩ እንዲሳተፉ በባላገሩ ቴሌቪዥን በኩል ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል።
የዘንድሮው የባላገሩ ምርጥ የባለተሰጥኦ ሙዚቀኞች የመጨረሻው መጀመሪያ ውድድር በባለፈው የትንሳኤ በአል በቦናንዛ ሆቴል በቀጥታ ስርጭት ተካሂዷል። በውድድሩም ካምፕ ገብተው ስልጠና ሲወስዱ ከቆዩት ሃያ ሰባት ተወዳዳሪዎች መካከል አስራ አምስቱ ተለይተው ስራቸውን አቅርበዋል። ከአስራ አምስቱ ውስጥ ለግማሽ ፍፃሜ ውድድር አላፊ የሆኑት አስር ምርጦች ታውቀዋል። አራት ተወዳዳሪዎች ደግሞ ከእድሜ በታች ሆነው በአስተሳሰባቸውና በሙዚቃ በሚያስተላልፉት መልዕክት በልዩ መልኩ ተመርጠው ለመጨረሻው ውድድር እንደሚቀርቡ ተረጋግጧል።
በሁለት ወር ጊዜያት ውስጥ ደግሞ ከአስሩ ባላገሩ ምርጥ ተወዳዳሪዎች ውስጥ አሸናፊዎቹ እንደሚለዩ ይጠበቃል። በውድድሩ የሚቀርቡ ተወዳዳሪዎች ምንም ልምድ የሌላቸውና ከዚህ በፊት ከሙዚቃ መሳሪያ ጋር ተገናኝተው የማያውቁ በመሆናቸው ብሎም በካምፕ ገብተው ስልጠና የሚወስዱ እንደመሆናቸው ውድድሩ ትንሽ ጊዜ ይፈጃል። ነገር ግን ደግሞ በዚህ ጊዜ ውስጥ ከምርጥ አስሮቹ ውስጥ በደምብ የተዘጋጁና ታሽተው የመጡ ተወዳዳሪዎች አሉ። በቀጣይ ከምርጥ አስሮቹ ውስጥ አሸናፊዎቹን ለመለየት ለዳኞች ፈታኝ የሚሆንበት ሁኔታም ተፈጥሯል። የተወዳዳሪዎች ችሎታም ተመሳሳይና ተቀራራቢ መሆኑ ተነግሯል።
የባላገሩ አስሩ ምርጥ ውድድር በቅርቡ የሚካሄድ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ የመጨረሻዎቹ ስድስቱ አሸናፊዎች በዳኞች ይለያሉ። ለመጨረሻው ውድድር የሚቀርቡትም ስድስቱ ተወዳዳሪዎች ናቸው። እነዚህን ውድድሮች ለማካሄድ ሁለት ወር ያስፈለገበትም ምክንያት በመሃል የተወዳዳሪዎቹን ማንነት ለተመልካች ማሳወቅ አስፈላጊ በመሆኑ ነው። ከዚህ ባለፈ ተወዳዳሪዎች ተመልካች አውቋቸው በአጭር የፅሁፍ መልዕክት እንዲመርጣቸው የሚቀሰቅሱበት የአየር ሰአት ጊዜ ለማመቻቸትም ጭምር ነው።
ለተወዳዳሪዎች የህዝብ ድምፅ የሚፈለግ ቢሆንም በባላገሩ ምርጥ ህዝብ ተወዳዳሪዎችን የሚመርጥበት መቶኛ ነጥብ አለ። ነገር ግን ተወዳዳሪዎች ይበልጥ የሚዳኙት በሙያተኞች ነው። ተወዳዳሪው የሚገኝበትን አካባቢ ወይም ብሄሩን ተከትሎ መምረጥ አይፈቀድም። ስለሆነም ህዝቡ ተወዳዳሪዎችን እንዲመርጥ 7544 አጭር የፅሁፍ መልእክት ተዘጋጅቷል።
በባላገሩ ምርጥ የሙዚቀኞች ባለተሰጥኦ ውድድር አሸናፊ ለሚሆኑ ተወዳዳሪዎች በጥቅሉ ስምንት ሚሊዮን ብር ተመድቧል። በወድድሩ አንደኛ የሚወጣውን ተወዳዳሪ ጊፍት ሪል እስቴት የሚሸልም ሲሆን ሁለተኛና ሶስተኛ የሚወጡትን ተወዳዳሪዎች ደግሞ ሌሎች ወድድሩን ስፖንሰር ማድረግ የሚፈልጉ ድርጅቶች እንዲሸልሙ ተጋብዘዋል።
ሽልማቱ ተወዳዳሪዎች ብዙ በደከሙበት ልክ እና እስከመጨረሻው ድረስ እንዲሄዱ ታላሚ ባደረገ መልኩ ተዘጋጅቷል። ተወዳዳሪዎች የተሻለ ቦታ ላይ ደርሰው ሀገራቸውንም ጭምር ሊያስጠሩ የሚያስችልም ጭምር ነው። በዚሁ መሰረት ከአንደኛ እስከ አራተኛ ደረጃ ይዘው የሚያጠናቅቁ ተወዳዳሪዎች ይሸለማሉ። ከአራተኛ እስከ አስረኛ ደረጃ ይዘው የሚያጠናቅቁ ተወዳዳሪዎችም በባዶ አይሸኙም።
በውድድሩ አንደኛ ሆኖ ለሚያጠናቅቅ ተወዳዳሪ የሶስት ሚሊዮን ብር ሽልማት ተዘጋጅቷል። ከዚህ ውስጥ ተወዳዳሪው አንድ ሚሊዮን ብሩን ለራሱ የሚወስድ ሲሆን ቀሪው ሁለት ሚሊዮን ብሩ በቀጣይ አልበም መስሪያ፣ ለዜማ፣ ግጥም ለስቱዲዮ ክፍያ ይውላል። ሁለተኛ ሆኖ የሚያጠናቅቀው ተወዳዳሪ ደግሞ ሁለት ሚሊዮን ብር ተሸላሚ ይሆናል። ከዚህ ውስጥ አምስት መቶ ሺ ብሩ ለራሱ ይደርሰዋል። ቀሪው አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሺ ብሩ ደግሞ በተመሳሳይ ለአልበም ስራ ይውላል። ሶስተኛው የውድድሩ አሸናፊ አንድ ሚሊዮን ብር ተሸላሚ ሲሆን ሁለት መቶ ሀምሳ ሺ ብሩ ለራሱ፤ ቀሪው ሰባት መቶ ሀምሳ ሺ ብሩ ደግሞ ለሙሉ አልበም ማሰሪያ ይሆናል።
የሶስቱም አሸናፊዎች ሙሉ አልበም በያሆ ኢንተርቴይመንት አማካኝነት ይሰራል። ከሀገር ውስጥ ጀምሮ በተለያዩ አውሮፓ ሀገራትና በአሜሪካ በተቀናጀና በውጪ ሀገር በሚገኙ ባለሙያዎች እገዛ አሸናፊዎች የኮንሰረት ስራዎችን እንዲያቀርቡ ይደረጋል። ከአራት እስከ አስር የሚወጡ ተወዳዳሪዎችም ሁለት ነጠላ ዘፈኖችን እንዲሰሩ ድጋፍ ይደረግላቸዋል።
በውድድሩ አንደኛና ሁለተኛ የወጡ ተወዳዳሪዎች ሙሉ የአልበም ኮንትራት ይፈርማሉ። ሶስተኛ የወጣው ተወዳዳሪም እንደ ሽልማቱ መጠን ታይቶ ሶስት ወይም አራት ነጠላ ዜማዎችን ይሰራል። ከአንድ እስከ አስር የወጡት ግን የጋራ ሙሉ አልበም ይሰራሉ። ይህም ከአራት እስከ አስር የወጡ ተወዳዳሪዎችን ለአድማጭ ተመልካች ለማስተዋወቅ ያግዛል።
ከዚህ በፊት በባላገሩ ምርጥ ውድድር ከአንድ እስከ ሶስት የወጡ ተወዳዳሪዎች ብቻ ይሸለሙ የነበረ ቢሆንም በዚህ ውድድር ግን ከአራት እስከ አስር ለወጡ ተወዳዳሪዎችም ለእያንዳንዳቸው የመቶ ሺ ብር ሽልማት ይበረከትላቸዋል። በዚሁ ውድድር አራት ልዩ ተሸላሚዎችም ይኖራሉ። ሶስት የተለያዩ ሙሉ አልበሞችም ከአንድ እስከ ሶስት በወጡ ተወዳዳሪዎች ይሰራሉ። እንደየዘፈኖቹ ጉልበት ታይቶም የሚሰሩ የተለያዩ የሙዚቃ ክሊፖችም ይኖራሉ።
የዚህ ወድድር ሽልማት ዋነኛ አላማውም ተወዳዳሪዎች ስለድምፃቸውና ስለስራቸው እንጂ ስለሌላው ጉዳይ እንዳይጨነቁ ነው። ዜማ ደራሲውንና ገጣሚውን አሰባስቦ፣ ስቱዲዮና ሙዚቃ አሬንጅመንት ዝግጁ አድርጎ የሚያሰራ ቡድን ተዋቅሯል። ለተወዳዳሪ የሚሰጣቸው ሽልማትም በዚሁ በሚዋቀረው ሙዚቃ ቀማሪ ቡድን በትንሽ ወጪ አልበማቸውን ለማሰራት ያስችላቸዋል። ለዛም አሸናፊዎች ከሚያገኙት ሽልማት ውስጥ የተወሰነው ነው ለአልበም ማሰሪያ የሚውለው።
ከዚህ በኋላም ከአልበሙ ሽያጭ አሸናፊው ሙዚቀኛ የሚያገኘው ገቢ ይኖራል። ከአልበሙ ስራ በኋላም አልበሙ እየተወደደ ከሄደ በኮንሰርት ስራዎች ከሙዚቀኛው ጋር በመስማማት ልዩ የክፍያ ኮንትራት ይኖራል።
የሙዚቃው ዘርፍ በተደጋጋሚ የተተኪነት ጥያቄ በሚቀርብበት በዚህ ጊዜ በሀገሪቱ ጦርነት፣ ግጭትና መፈናቀል ብሎም ሰላም በጠፋበት ወቅት እንዴት ይካሄዳል የሚል ሌላ ጥያቄ ይነሳበታል። ውድድሩን ለማዳከም የሚደረጉ ጥረቶችም ይስተዋላሉ። ነገር ግን ደግሞ በቀውስም ወቅት ቢሆን ሙዚቃ ሰላም በመስበክ፣ ህዝብን በማቀራረብና አንድ በማድረግ ረገድ ሚናዋ የጎላ ነው። እነ ጥላሁን ገሰሰ፣ መሃሙድ አህመድ፣ ብዙነሸ በቀለ፣ ሂሩት በቀለ፣ አለማየሁ እሸቴ፤ ከአሁኖቹ ደግሞ እነ ቴዎድሮስ ካሳሁን፣ ማዲንጎ አፈወርቅ፣ ታምራት ደስታና ሌሎችም ድምፃውያን ደግሞ ተተኪዎችን በማፍራቱ ሂደት የድርሻቸውን ተወጥተዋል።
እናም ተተኪ ድምፃውያን እየጠፋ በመጣበት በዚህ ጊዜ ባላገሩ ምርጥን የመሰሉና ሌሎች መሰል የሙዚቃ ባለተሰጥኦ ወድድሮች ተተኪ ድምፃውያንን በማፍራት ረገድ ሚናቸው የጎላ ነውና ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንጂ ሊኮስሱ አይገባም። የኢትዮጵያ አይድል ውድድር ሲጀመር እንኳን በርካታ የተረሱ የቀድሞ ሙዚቀኞች በተወዳዳሪዎች ታውሰዋል። የህዝቡም ጆሮ በምን ያህል ደረጃ ለሙዚቃ እንደተቃኘ ታይቷል። ስለዚህ በተሰጥኦ ውድድሮች የተተኪ ሙዚቀኞች ፍለጋ ተጠናክሮ ይቀጥል እንላለን።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19/2015