በዛሬው ባለውለታዎቻችን ዓምዳችን ከስፖርቱ ዓለም ጎራ ብለን ኢትዮጵያዊው ብስክሌት ጋላቢና በዘርፉ ሀገሩን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስተዋወቀውን ገረመው ደንቦባን ይዘን ቀርበናል። ይህ የአገር ባለውለታ እንግዳችን የተወለደው ጣሊያን ኢትዮጵያን ከመውረሩ አንድ ዓመት በፊት አዲስ አበባ አንዋር መስጊድ ፊት ለፊት መዲና ሕንፃ የተሠራበት ቦታ መሆኑን በእርሱ ዙሪያ የተሰነዱ ጽሑፎች ያስረዳሉ።
ዕድሜው ለፊደል ቆጠራ እንደደረሰም ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን ግቢ ያስተምሩ በነበሩ ቄስ አማካኝነት የፊደል ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ፤ በቀድሞ ሥሙ ቀበና ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አሁን ኮከበ ጽብሐ እየተባለ በሚጠራው ትምህርት ቤት ገና በአሥር ዓመቱ እየተመላለሰ መማር መጀመሩንም ያመለክታሉ።
እንደመረጃው ገረመው ብስክሌት መንዳትና ማዘውተር የጀመረው ገና የሰባት ዓመት ልጅ እያለ ነው። የሚገርመው ግን በወቅቱ በእርሱ ጊዜ እንደዛሬው የልጅ ብስክሌት ባለመኖሩ ትላልቅና አጫጭር ብስክሌቶች ላይ እግሩን በፊላዮ (መሐሉ ላይ ያለው ብረት) እያሾለከ ካልሆነ በስተቀር ኮርቻው ላይ ተቀምጦ መንዳት አይችልም ነበር።
ወላጅ እናቱም ልጃቸው ለብስክሌት ያለውን ፍቅርና ችሎታ እንዲሁም የትምህርት ቤቱን ርቀት በሚገባ በመረዳታቸው በ30 ብር አዲስ ብስክሌት ገዝተው ሰጡት። ገረመው ታዲያ በጊዜውም የተሰማውን ስሜት አሁንም ድረስ መግለጽ እንደማይችል ቃለመጠይቅ በተደረገለት አጋጣሚ ሁሉ ሳያነሳው አያልፍም። እናት ልጃቸው በመንገድ ርቀት እንዳይጐዳባቸው ይህን ዘዴ ሲዘይዱ ልጃቸው በብስክሌት ሀገሩንና አህጉሩን በኦሎምፒክ ይወክላል ብለው ሊገምቱ ቀርቶ አስበውትም እንደማያውቁ ግልፅ ነው።
የነገውን አመርቂ ውጤት ከወዲሁ የተነበየችለት እድሉም በአዲሷና ብርቋ ብስክሌቱ ጓደኛውን ከኋላ እያፈናጠጠ ከአሜሪካ ግቢ ተነስቶ የአቡነ ጴጥሮስን ዳገት በቮላታ ፉት ብሎት ፒያሣን አቆራርጦ በራስ መኮንን አራት ኪሎ ገስግሶ ቀበና ቀዳማይ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤት በራፍ ላይ ከች ማለትን የዘወትር ፀሎት ያህል ተያያዘው። ይህም አነሰህ ብሎ ሌላ ምስኪን ጓደኛውን ከፊት ጨምሮ በጨቅላ ጡንቻው ሁለት ጓደኞቹን ይዞ መብረሩ ለጡንቻው መፈርጠም ዋንኛ መሠረት መሆኑንም የገባው ቆይቶ ነው። ከዕለት ወደ ዕለት ለዓመታት ጡንቻውንና ፍጥነቱን ያፈረጠመው ገጠመኙ ተባብረው ለመጀመሪያ ጊዜ በ1943 ዓ.ም በብስክሌት ውድድር እንዲቀርብ የልብ ልብ ሰጠው።
በውድድሩም የካበተ ልምድና ብስክሌት ካላቸው የጣሊያንና ግሪክ ተወዳዳሪዎች መሐል በዕድሜም ትንሹ ሆኖ ያገኘው የሰባተኛ ደረጃ ውጤት ይበል የሚያሰኝ ሆነለት። ያገኘው ውጤት ያስከተለለትን አድናቆት ተከትሎ ብስክሌት ልምምዱን አጠናክሮ ሲቀጥል ጉራጌዋ እናቱ ቆጮውን፣ ክትፎውን፣ ቡላውን እያቀረቡ ለውጤቱ መስመር ከጀርባው ያሉ ሁነኛ ሰው ሲደግፉት እንደነበርም ያነሳል። በ1945 ዓ.ም በአዲስ አበባ ውድድሩ በስፋት ተጀመረ። በአጭር ጊዜም ከእግር ኳሱ ቀጥሎ በርካታ ተመልካቾችንና ተሳታፊዎችን በመሳብ ብስክሌት ስፖርት ስሙ ገነነ።
በኢትዮጵያ ለብስክሌት ስፖርት መጀመር ፈር ቀዳጁ ፈረደ ካሣ የተባለ ሰው ነው። ፈረደ አሥመራ ከጣሊያን ብስክሌተኞች ጋር ሲወዳደር የቆየና ቀድሞ ኦርማ ጋራዥ ወይም አውራ ጐዳና ጋራዥ የሚሠራ ነበር። ፈረደ ጐላ በ1945 ዓ.ም ከታዋቂው የስፖርት ሰው ከክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ጋር በመነጋገር ባዘጋጀው ውድድር ገረመው ደንቦባ “ቢያጆ” በሚሰኝና ያውም በውሰት በተገኘ ብሰክሌት ለመወዳደር ተሰለፈ።
ከአርባ በላይም ተወዳዳሪ በተገኘበት ፉክክር ለመጀመሪያ ጊዜ አሸነፈ። በጊዜው የነበረው ውድድር ጥንካሬንና ፍጥነትን የሚጠይቅ ነበር። ገረመው ለመጀመሪያ ድሉ የተሸለመውን 25 ብር ለእናቱ አስረከበ። በወቅቱ ታዲያ ገንዘቡ የመግዛት አቅሙ ጠንካራ ስለነበር እናቱ በደስታ ምረቃቸውን አዥጎደጎዱለት። ለመጀመሪያ ጊዜ የታያቸውንም ራዕይ “ከፍ ያለ ቦታ ያድርስህ!” ሲሉ ተመኙለት።
ወጣቱ ብስክሌት ጋላቢ በተደጋጋሚም ታላላቆቹን ልምድ ያላቸውን ሚስተር ደቦስ፣ ሚዮጂ፣ ሲኖር ኮንቲ፣ ኡስማን መሐመድ፣ ኃይሉ በየነ፣ ጫላ ወርዶፋ የመሳሰሉትን በተደጋጋሚ በማሸነፍ ትኩስ፣ አዲስና ልዩ ኃይሉን አሣየ። “ከእኔ ወዲያ ማን?” የሚለው ወኔውም ልቡን ሙሉ አደረገለት። እነ አራዳ፣ ወልወል፣ ለገሀር፣ መቻል የመሳሰሉ ክለቦችም አዲሱንና ልዩ ስፖርተኛ የግላቸው ለማድረግ የተለያዩ ማባበያዎችና ተስፋ ቃሎች አጐረፉለት። በውድድር ጊዜ የሚያሳየው ብቃት ያስደሰታቸው በአቶ ፈረደ ካሣ የሚመራው ወልወል ቡድን መሪዎች የሚማርበት ትምህርት ቤት ድረስ በመሔድ ቮልሲክ የተሰኘች ብስክሌት ሸለሙት። በዚህ ማባበያ ተስቦም ክለቡን በመወከል ከ1945 ዓ.ም እስከ 1954 ዓ.ም ባሉት አሥር ተከታታይ ዓመታት የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ሆነ።
ገረመው ደንቦባ በሀገር ውስጥ የሚያሸንፈው ቀርቶ የሚፎካከረው በማጣቱ ደብዳቤ ጽፎ ያዘጋጅና ንጉሡ ለእረፍት ወደ ቢሾፍቱ የሚሄዱበትን ዕለት ሰንበት ጠብቆ መኪናቸው የሚያልፍበት አራተኛ ክፍለ ጦር (ሪቼ) ሆኖ በመጠበቅ መኪናቸው ሲያልፍ ተከትሎ የደብረዘይትን መንገድ ተያያዘው። ዱከም ሊደርሱ ጥቂት መቶ ሜትሮች ሲቀራቸው ፍጥነቱን ጨምሮ ንጉሡን የያዘው ተሽከርካሪ አጠገብ ሲደርስ ፖስታውን ከፍ አድርጐ አሳያቸው። ገረመው በወቅቱ ስሙ በብስክሌት ከመግነን አልፎ፡-
“ይሻልሻል …. ይሻልሻል
ገረመው ደንቦባ ይሻልሻል
ጥላሁን ገሠሠ ይሸኝሻል
አበበ ቢቂላ ያገባሻል።
ገረመው ደንቦባ ከዳረሽ
ጥላሁን ገሠሠ ከሸኘሽ
አበበ ቢቂላ ካገባሽ
ከሴቶቹ ሁሉ ብልጫ አለሽ….።” እየተባለ ከሌሎች ዕንቁ ዜጐች ጋር ሕዝባዊ ግጥም ተገጥሞ የተዘፈነለት ብቻ ሳይሆን ንጉሡ በሚያገኘው አስደሳች ውጤት በተደጋጋሚ የሸለሙት በመሆኑ ጠባቂዎቻቸው (ሮያል ጋርዱ) ከመኪናቸው አጠገብ ፔዳሉን በፍጥነት እየዘወረ የሚከተላቸውን ወጣት ስፖርተኛ ፍጥነትና ጉልበት እየተደነቁ ከመመልከት ውጪ አልተከላከሉትም። ንጉሡም መኪናው እንዲቆም አዘዙ። ጄኔራል መኮንን ደነቀም ፖስታውን ተቀብለው ለንጉሡ ሰጧቸው። ገረመው ደብዳቤውን አቀብሎ ከንጉሡ ፊት ለፊት ከብስክሌቱ ወርዶ በመቆም አቀረቀረ።
ንጉሡም ቁምጣ ያደረገውን ፈርጣማ ብስክሌተኛ በአድናቆት እየተመለከቱ “… ምንድነው የምትፈልገው አንተ ጐረምሳ….?” ሲሉ ይጠይቁታል። እሱም በተረጋጋና ፍፁም ጨዋነትና ሥነ-ምግባር ያሻውን ፀባይ እና ለንጉሡ የሚገባቸውን ክብር በሚገልጽ ከአንገቱ ጐንበስ ብሎ መሬት … መሬት እያየ … ከዓለም የብስክሌት ተወዳዳሪዎች ጋር መፎካከር እንደሚፈልግ ነገራቸው።
ንጉሡ ለአዳዲስ ነገሮችና ሀገራቸው በሁሉም መንገድ እንድትጠራላቸው ከፍተኛ ጉጉት ስለነበራቸው ፈጥነውም “… ከቻልክ እንፈቅዳለን…!” ሲሉ ይሁንታቸውን አረጋገጡለት። በጄኔራል መኮንን ደነቀ በኩልም ቀጠሮ ተያዘለት። ገሬም ብስክሌቱን ወደኋላ አዙሮ ደስታውን ለማካፈል ወደ አዲስ አበባ ሸመጠጠ። የቀጠሮው ቀን ደርሶም በ30 ብር የገዛውን ምርጥ የጣሊያን ሙሉ ልብስ ከነሰደርያውና ከረባቱ ግጥም አድርጐ ንጉሡ ፊት ቀረበ። ንጉሡም በስደት እያሉ ስለ ኦሎምፒክ ውድድር፣ ክብርና ዝና በሚገባ ያውቁ ስለነበር ሀገራቸው የምትካፈልበትን ቀን ያብሰለስሉ ስለነበር የቀረበላቸውን ጥያቄ በቸልታና አጉል ስሜት በሚል መልኩ ለመለወጥ ባለመፈለጋቸው የሚያስፈልገውን ሁሉ እንደሚያመቻቹለት ቃል ገብተው አሰናበቱት።
ንጉሡም ቃላቸውን ሳያጥፉ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጥቁር አፍሪካ ሀገራት መሐል ነፃነቷን እንዳስጠበቀች በ1949 ዓ.ም አውስትራሊያ የምታዘጋጀውን የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ለመካፈል ወደ ሜልቦርን ለመጓዝ ዝግጅቷን አጠናቀቀች። በዚህ አሰልጣኝ በሌለበት የብስክሌት ብሔራዊ ቡድናችን ውስጥ ነዋሪነቱን በቢሾፍቱ ያደረገው መንግሥቱ ንጉሤ፣ ተሰማ ሙሣ፣ አበበ ማሞ፣ መስፍን ተስፋዬና ፀሐየ ባሕታ ሲካተቱ፤ በማራቶን ባሻዬ ፈለቀና ገብሬ ብርቄ ተሰላፊዎች ነበሩ።
የኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድናችን ወደ አውስትሪሊያ ለመጓዝ ሲነሳ መንግሥት ያዘጋጀለት አውሮፕላን መቀመጫ የሌለው የቡና እና የቆዳ መጫኛ ዳኮታ ነበር። ይኸው በቀዳሚው ኢትዮጵያዊው ፓይለት ካፒቴን አለማየሁ ደስታ አብራሪነት ምድርን የለቀቀው አይሮፕላን ከሰባት ቀንና ሌሊት አሰልቺ እና አድካሚ ጉዞ በኋላ ሜልቦርን ሲደርስ ስፖርተኛው ያደረገው ልምምድ ከመበላሸቱም በላይ የሁሉም ክብደት ከሚገባው በላይ ቀነሰ።
በሜልቦርን ኦሎምፒክ ተዳክሞና ተሰላችቶ ብቻ ሳይሆን ከልምምድ ርቆ የቆየው የኢትዮጵያ ቡድን ከመቶ በላይ የብስክሌት ተወዳዳሪዎች በተካፈሉበት ገረመው 24ተኛ ሲወጣ ቀሪዎቹ 35ተኛ፣ 37ተኛ እና 42ተኛ በመውጣት በቡድን ባገኙት ውጤት መሠረት ከዓለም በደረጃ ሰንጠረዥ ላይ በዘጠነኛ ለመቀመጥ ቻሉ።
ይህም ውጤት እስካሁን ድረስ በሀገራችን ያልተሰበረ ሪከርድ ነው። ምናልባትም በአፍሪካ ቡድኑ ከአውስትራሊያ ሲመለስ የአውስትራሊያን ንጉሥ ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በስጦታ መልክ እንዲበረከትለት የሰጠውን አንድ ወንድና አንድ ሴት ካንጋሮ ይዞ መጣ። የኦሎምፒክ ቡድኑም ቤተ-መንግሥት ቀርቦ ካንጋሮዎቹን ለንጉሡ አስረከበ። ንጉሡም ለኦሎምፒክ ልዑኩ የደረት ኒሻን ሸልመዋል።
“በኦሎምፒኩ ጨዋታ በአጨራረስ ብልጠት ውጤቱን አሳልፎ የሰጠ” በሚል ርዕስ አውስትራሊያ የሚታተም ጋዜጣ ገረመው ከፊት ሲመራ የሚያሳየውን ፎቶ አትሞ በማውጣት ለዓለም አስተዋወቀው። ከኦሎምፒክ መልስም እስራኤል የተመሠረተችበትን ሰባተኛ የነፃነት ቀን ስታከብር የክብር ተወዳዳሪ እንዲሆንላት ባደረገችለት ጥሪ መሠረት ከዓለም ምርጥ በራሪዎች ጋር ተወዳድሮ ሰባተኛ ወጣ።
ከአራት ዓመት በኋላም 1952 ዓ.ም ጣሊያን በተዘጋጀው ኦሎምፒክ ገረመው ደንቦባ ተካፍሏል። በውድድሩም በከፍተኛ ፍጥነት በፊት እየመራ ባለበት ጊዜ ብልጠትና ልምዱ ያላቸው ተወዳዳሪዎች ከኋላ ደርሰው ጐማውን በመግጨት መንገዱን ስቶ ክፉኛ እንዲወድቅ በማድረጋቸው እጁ ተሰብሮ ለማቋረጥ ተገደደ። ከሮም በኋላ ገረመው ኦሎምፒክን የተካፈለው በተወዳዳሪነት ሳይሆን በአሰልጣኝነት ነው – 1960 ዓ.ም ጃፓን ቶኪዮ ላይ።
ገረመው ብስክሌት መወዳደሩን ቢያቆምም ነፍሱን ይማረውና እነ ዶን ጥላሁን ወልደሰንበት የመሰሉ በሞስኮ ኦሎምፒክ በፔሌግሬ (የቤት ውስጥ ውድድር) በመካፈል እስካሁን ከኢትዮጵያ ብቸኛ የሆነውን ጨምሮ በርካታ ብስክሌተኞችን አፍርቷል። የሚገርመው ደግሞ ካሉት 11 ልጆች ሶስቱ ወንዶችና አንዲት ሴት ልጁ የብስክሌት ተወዳዳሪና አፍቃሪ ነበሩ።
በአሰልጣኝነት ዘመኑም ናይጄሪያ፣ ሌጐስ በተዘጋጀው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ ወርቅ ይዞ ተመልሷል። ሁለ-ገቡ ገረመው በብስክሌትም ብቻ ሳይሆን በሀገር ቤት የደጋው መኪና እሽቅድድምም ቀደምት ታሪክን የጨበጠ ነው። አመለ ሸጋው ገረመው ደንቦባ የብስክሌት ውድድሮች በሚደረጉበት ስፍራ በመገኘት ብቻ ሳይሆን ተወዳዳሪዎች ከውጪ ውድድር ሲመለሱ በመቀበል፣ ልምዱን ማካፈል፣ የተለያዩ ኤሌክትሮኒክስና ፕሪንቲንግ ሚዲያዎች ለቃለ-ምልልስ ሲፈለጉት ፈጥኖ በመገኘት የካበተ ልምዱን፤ ምክሩን ያስተላልፋል። ለዚህ የሀገርና የሕዝብ ባለውለታ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከሁለት ዓመት በፊት ለገጣፎ የመሬት ስጦታ አበርክቶለታል።
የመጀመሪያው ኢትዮጵያ በተሳተፈችበት ሜልቦርን ኦሎምፒክ በብስክሌት ስፖርት ኢትዮጵያ ወክሎ በመሳተፍ እና ባንዲራዋን በኦሎምፒክ በመያዝ ቀዳሚ የሆነውና በቶኪዮ ኦሎምፒክም በዋና አሠልጣኝነት ቡድኑን በመምራት ከ30 በላይ ዋንጫ እና 32 ወርቅ ሜዳሊያ ማስመዝገብ የቻለው ይህ ድንቅ አትሌት በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ በ90 ዓመቱ ልክ የዛሬ ሁለት ወር በሞት ማጣታችን ይታወሳል። እኛም ይንን ድንቅ ኢትዮጵያዊ ብስክሌት ጋላቢ በእንዲህ መልኩ ልንዘክረው ወደድን።
ማሕሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 18 ቀን 2015 ዓ.ም