አዲስ ዘመን አዲስ ሆኖ ብቅ ካለበት ጊዜ ጀምሮ በየእለቱ ብዙ አዳዲስ ነገሮችን ለአንባቢዎች በማድረስ ዘመናትን ተሻግሯል። ዛሬም ድረስ ያለድካም የኢትዮጵያን ታሪክ እየሰነደ ዘልቋል። በእያንዳንዱ እርምጃው ምን ምን ጉዳዮችን ይዞ ወደ አንባቢ ይቀርብ ነበር ብለን ወደኋላ መለስ ብለን በአዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን እንዳስሳለን። 1960ዎቹ እና 70ዎቹ በጋዜጣው ለንባብ በቅተው ከነበሩ ጉዳዮች መካከል በኢትዮጵያ ከሐዳር አካባቢ ስለተገኘው የሰው ልጅ የቅሪት አካል፣ በኤርትራ ክፍለ ሀገር ስለወጣው ፖሊሲ፣ በዘመነ ደርግ የኢትዮጵያ የገንዘብ ኖቶች ቅያሪን አስመልክቶ ስለወጡ ተከታታይ ዘገባዎችን ጨምሮ እንዲሁም ከሕዝብ ወደ መንግሥትና ከሕዝብ ወደ ሕዝብ የጥያቄና የትዝብት አጀንዳዎችን ይዞ ከሚዘዋወረው ደብዳቤዎች ከተሰኘው ገጽ ላይ ቆንጠር በማድረግ አቅርበናል።
ከሐዳር አካባቢ የተገኘው የሰው አፅም 3.5 ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ አለው ተባለ
አዲስ አበባ (ኢ.ዜ.አ) በወሎ ክፍለ ሃገር በአውላ አውራጃ ሐዳር በሚባለው አካባቢ የተገኘው የሰው አፅም ቅሪት ሦስት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ ዓመት ዕድሜ እንዳለው ተረጋገጠ።
የአፅሙ ቅሪት ይህን ያህል ረጅም እድሜ እንዳለው የተረጋገጠው ለጥናታዊ ምርምር ወደ አሜሪካን ሃገር ተወስዶ በባለሙያዎች ጥናት ከተካሄደ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ትላንት ለብሔራዊ ሙዚየም በተሰጠበት ወቅት ነው።
ማክሰኞ ጥር 20 ቀን 1967 ዓ/ም
የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ የመን ግንኙነት በደም የተገነባ መሆኑ ተገለጠ
አዲስ አበባ -(ኢ.ዜ.አ) የኢትዮጵያ አብዮትና አንድነት ከአደጋ ለማዳን ጭቆናንና ብዝበዛን በመቃወምና የእብሪት ወረራን በመከላከል ለሶሻሊዝምና ለጭቁን መደቦች አሸናፊነት እንደ ኢትዮጵያ ሐቀኛ ልጆች ሁሉ የየመን ሕዝባዊት ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጀግኖችም ሕይወትን ያህል ከፍተኛ ዋጋ በመክፈላቸው የሁለቱ ወዳጅ አገሮች ግንኙነት በደም የተለሰነ መሆኑን ጓድ ብርጋዲየር ጄነራል ተስፋዬ ገ/ኪዳን የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ የቋሚ ኮሚቴ አባልና የሀገር መከላከያ ሚኒስትር ገለጡ። (አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 20 ቀን 1967 ዓ/ም)
ለኤርትራ ክፍለ ሀገር የወጣውን ፖሊሲ ውሳኔ የሚቀበሉት ታጋዮችና ጭቁኖች ናቸው
ወጣት ታጋይ ሣራ መኮንን ከአራት ዓመታት በላይ በኤርትራ በረሃ በትግል በነበረችበት ወቅት ስላስተዋለቻቸው ሁኔታዎች ሁለተኛው ክፍል ነው። ሣራ መኮንን በንግግሯ ውስጥ በአንክሮ ከገለጠቻቸው ነገሮች መካከል አንደኛው የኤርትራ ጭቁን ሕዝቦችና የተቀሩት የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች የተሳሰረ መሆኑን የሚያሳስብ ነው። ከዚህም ሌላ ሣራ መኮንን የኤርትራ ሐቀኛ ታጋዮች ከተቀሩት የኢትዮጵያ ታጋዮች ጋር ሆነው ለኤርትራ ክፍለ ሀገር በሳይንሳዊ ሶሻሊዝም የተረጋገጠ መፍትሔ ሊያስገኙ እንደሚችሉ ገልጣለች።
አልፈው የሰፊውን ጭቁን ሕዝቦች ችግር ለማስወገድ በረሃ ገብተው እንደነበር ካወሳች በኋላ፣ ከእንግዲህም ቢሆን ለጭቁን ኤርትራ ሕዝብ ሰላም የሚገኘው በአብዮታውያንና በጭቁን ሕዝቦች ጥረት እንጂ እንደ ኢ-ኤል-ኤፍና መሣዮቹ ባሉት የፔትሮ ዶላር ተገዢዎችና የለየላቸው አድኃሪያን እንደማይሆን ገልጣለች።
(አዲስ ዘመን እሁድ መስከረም 4 ቀን 1969 ዓ/ም)
የኢትዮጵያ ብር ኖት በቅርቡ ይለወጣል
ይህ የፊውዳልና የከበርቴ ሥርዓት ምልክትና ውክል ሆኖ የቆየው በኢትዮጵያ ብሮች ላይ የነበረው ምስል፣በመካሄድ ላይ በሚገኘው አብዮት(ተሐድሶ እንዲያገኝ በማድረግ) አዲስ የኢትዮጵያ ገንዘብ/ ብር ከጥቅምት 4 /1969ዓ/ም ጀምሮ ለሕዝብ ይወጣል።
ባንኮች ከጥቅምት 4-8 ኖቶችን ብቻ ይለውጣሉ
(ኢ.ዜ.አ)- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የአዲስ ባንክ ከነ ቅርንጫፎቻቸው ጭምር ከጥቅምት 4 ቀን እስከ 8 ቀን 1969ዓ/ም ድረስ ባሉት ቀናት ውስጥ የኖቶችን መለወጥ አገልግሎት ብቻ እንደሚያበረታቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ትናንት አስታወቀ።
ብሔራዊ ባንኩ በሰጠው ተጨማሪ ማብራሪያ፤ አብዛኛዎቹ ባንኮች ከጥቅምት 9 ቀን እስከ ጥቅምት 19 ቀን 1969 ዓ/ም ድረስ ከቀትር በፊት የኖቶች መለወጥ ተግባር ብቻ የሚያከናውኑ ሲሆን፤ ከቀትር በኋላ ደግሞ መደበኛውን የባንክ አገልግሎት ያበረክታሉ።
(አዲስ ዘመን እሁድ መስከረም 14 ቀን 1969 ዓ/ም)
አዲሶቹ የገንዘብ ኖቶች ሥራ ላይ መዋል ጀመሩ
ሕዝቡ ተደስቷል
ስለ ባንኮች አቋምና ስለ ገንዘብ ኖቶች መለወጥ በወጡት አዋጆችና ደንቦች መሠረት የሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕይወትና ገናናነት የሚያንጸባርቁት አዲሶቹ የብር ኖቶች ከትላንት ጥቅምት 4 ቀን 1969 ዓ/ም ጀምረው በመላ ኢትዮጵያ በአገልግሎት ላይ ውለዋል።
……………..
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በየክፍለ ሀገሩ ባሉት ቅርንጫፎች ገቢ ያደረገው ከሰሜናዊው ክፍል 15 ሚሊዮን፣ ከመካከለኛው 18.8፣ ከደቡባዊው ክፍል 7.5 ሚሊዮን፣ ከምዕራባዊው ክፍል 7.1 ሚሊዮን፣ ከምሥራቃዊው ክፍል 13.5 ብር እንደሆነም አቶ ለገሰ ጥቃሄር አስታውቀዋል።
በሕዝቡ እጅ፣ በድርጅቶች ዘንድ አለ ተብሎ የሚገመተውና በአዲሱ የገንዘብ ኖት በሦስት ወር ውስጥ መለወጥ የሚገባው ገንዘብ መጠን 62 ሚሊዮን ብር ያህል እንደሆነ ለዚሁም በጠቅላላው ተቋቁመው በሚገኙ 2062 የመለወጫ ጣቢያዎች የባንክ ሰራተኞች ሕዝቡን ለማስተናገድ ባላቸው ኃይል ተሰልፈዋል።
(አዲስ ዘመን ዓርብ ጥቅምት 5 ቀን 1969 ዓ/ም)
ከደብዳቤዎች
ለፀሐይዋ እርዳታ ነው?
በአዲስ አበባ ትላልቅ ጎዳናዎች ላይ ያሉት አንዳንድ መብራቶች ብዙ ጊዜ እንደማያቸው 24 ሰዓት ሙሉ ይበራሉ። ከምሽቱ 12 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ድረስ ጭለማ በመሆኑ መብራት ያስፈልጋል።
የቀኑ መብራት ደግሞ ለፀሐይዋ እርዳታ ነው? ከታዛቢ
(አዲስ ዘመን የካቲት 16 ቀን 1972 ዓ/ም)
ይታሰብበት
በወንጂ ሸዋ ሲኒማ ቤቶች ከሚታዩት ፊልሞች አብዛኛዎቹ ጆሊጃኪዝምን የሚያንጸባርቁ፣ ጎጂ ልማዶችን የሚያስፋፉ ናቸው። በተለይ አሁን የምርትና የባሕል እድገት ዘመቻ በምናካሄድበት ወቅት እነዚህን ትግል አዘናጊ ፊልሞች ማሳየቱ ተገቢ አይመስለኝም።
ይህ አይነቱ ጥቆማ ቀደም ሲልም በተደጋጋሚ የቀረበ ቢሆንም አሁንም እንዲታሰብበት ጥቆማ አቅርቤአለሁ።
ተማሪ ያደታ ገመዳ
(አዲስ ዘመን የካቲት 16 ቀን 1972ዓ/ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 17 ቀን 2015 ዓ.ም