እና ልቀጥልና ልጠይቅ፤ ለበዓል ስንት ሰው ነው ጋዜጣ የሚያነበው? ስንትም። በፊት በፊት የቤቱም ግድግዳ ሆነ ከሥጋ ቤት የሚገዛው ሥጋ በጋዜጣ ስለሚጠቀለሉ፤ ወድዶ ሳይሆን በግድም ሰው ለበዓልም ጭምር ንባብ አይለየውም። «ጋዜጣ መጠቅለያ ሆናችሁ» የሚሉንን ራሱ፤ «እሱም ቢሆን ማኅበራዊ አገልግሎት ነው። ደግሞም ከሥጋው ካላቀቁት በኋላ ነበብ የሚያደርጉ አሉ።» እል ነበር።
አይ ቲቪ! በቲቪ የመታየት ጥቅሙን እዩልኝ! አሁን በአዲስ ዘመን ዕለተ ሰንበት መዝናኛ አምድ ላይ ሆኜ «በዓልን ከእኛ ጋር ላሳለፈ አንድ አንድ ሙክት ዶሮ እሸልማለሁ» ብል ማን አቤት ይለኛል? አሃ! ሙክት ዶሮ የሚባል ነገር ስለሌለ አይደለም፤ መልዕክቱ የተጻፈው በጋዜጣ ስለሆነ ብቻ ነው። ቆይ እንጂ! እንኳን ለፋሲካ በዓል ሁላችንንም በደኅና አደረሰን፤ አደረሳችሁ፤ ዘነጋሁትኮ! ነገር ነገር ሲል እንዲህ ሰላምታም ያስረሳል እንዴ? ኧረ እንደምን ናችሁ?
ዛሬ ጋዜጣ ለጤና ጠንቅ ነው ተብሎ ከሥጋው መጠቅለያነት ሲቆጠብ፤ ዋስትና ያለው የቤት ቀለምም ገበያውን ተቀላቅሎ ጋዜጣ ከየግድግዳው ላይ ተለቅሞ ሲነሳ፤ እኛ በየት በኩል እንነበብ? ብቻ ችግር ነው! እናማ እኔም ለበዓል ቤቴ ተቀምጬ መቼስ ጋዜጣ አላነብምና ያንን የፈረደበትን የቴሌቪዥን መቆጣጠሪያ ልቡ እስኪጠፋ ስጠቀጥቀው እውላለሁ።
«ምነው አንዱ ጋር ብታደርጊው የኔ ልጅ! አቅበዘበዝሻቸውኮ!» ትለኛለች አያትየው። እንኳን በዓል ሆኖና እንዲሁም አንዱ ጣቢያ ላይ ረግተን አንቆይም። ያው አንዳንዴ መካከል ላይ ወሰድ የሚያደርጉ ርዕሰ ጉዳዮች ወይም ክዋኔዎች አይታጡምና እነርሱ ላይ አርፈን ዝም ስንል፤ «ጎሽ! ዛሬስ ሪሞቱም አረፈ!» ትላለች። ቴሌቪዥን መቆጣጠሪያው ያሳዝናታል ልበል!?
በእርግጥ እንኳን በዓውደ ዓመቱ አሁን ላይ እንዳልኳችሁ በአዘቦቱም መርጦ ማየት አስቸጋሪ ሆኗል። በ«ነፃነት» ላይ ሁሉም ገብቶ እየዋኘ፤ ጣቢያው ሁሉ ፖለቲካ ተንታኝና አስተንታኝ ስለሞላው አንዱን መርጦ መመልከት ይከብዳል። አንዳንድ ተንታኞችማ ቀጥሎ ምን ሊሉ እንደሚችሉ በትክክል ለማወቅ ምንም አልቀረንም። ለምሳሌ ተረቶችና ቀልዶች ሳይቀሩ ከመደገማቸው የተነሳ «ይህቺማ የእገሌ ተረት ናት!» ብለን አናውቅም!?
አጋነንኩት? ይሁንላቸው፤ መተንፈሱ ጥሩ ነው። ባይሆን የበዓሉ ዝግጅት ነገር ነው ግራ የሚያጋባው። «ቴሌቪዥንም ከእስር ተፈትቶ ነው ማለት ነው? ጣብያውም ፆም ይዞ ነበር እንዴ?» እስክንል ድረስ በበዓል ዝግጅት ነፃነት መንቦራጨቅ እናያለን። በመጀመሪያ ደረጃ «በዓልን ከእኛ ጋር» እያለ የሚጣራው ሁሉም ነው። አንዳቸው እንኳ ለበዓሉ ማግስት አስተርፈው የሚያቆዩልን ነገር የለም። ነገ የሚባል ቀን የሌለ ነው የሚመስለው።
የኪነጥበብ ባለሙያው፣ ጋዜጠኛው፣ የተዘነጋው ሰው፣ ባለስልጣኑ፣ ሙዚቀኛው፣ ገጠመኙ፣ ምግብ መብላት ውድድሩ፣ ወጥ መሥራት ፉክክሩ፣ ውድድሩ፣ ሩጫው… ኧረ ፋሲካ ቀጣይ ዓመትም አለ። አንዳንዴማ የኪነጥበብ ባለሙያውን ስብስብ አድርገው አንድ ዝግጅት ላይ ሲያውሉት፤ «በቀጣዩ በዓል የእነዚህን ሰዎች ምን ሊያቀርቡልን ይሆን?» ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል። የእናንተን ባላውቅም እኔ ግን እንደዚያ ብዬ አውቃለሁ። «ማን ቀረ?»
እምዬ ኢትዮጵያ ከተራራዎቿ፣ ከወንዞቿና ከፏፏቴዎቿ ቀጥሎ ያላት አንጡረ ሀብት «አርቲስቷ» ነው። ነጠላ ዜማ በነፍስ ወከፍ እንዲደርሰን አንድ አንድ ነጠላ በማውጣት ተግተው ቀን ከሌሊት የሚያቀነቅኑትም አርቲስት አይደለ የምንላቸው? እና አርቲስቶቻችን ቢቀርቡ… ቢቀረቡ… ቢቀርቡ ያልቃሉ?
እንዳትቀየሙኝ! ይህን ስል ለበጎ ዓላማ የሚንቀሳቀሱትን ለመውቀስ አይደለም። ሊመሰገኑ የሚገባቸው ብዙ የበዓል ዝግጅቶች እንዳሉ አውቃለሁ። በጎ የሠራውን ሳንሸልም አጠፋ ያልነውን ብቻ መውቀስም ለውጥ ያመጣል ማለት አይደለም፤ ይህንንም እረዳለሁ። ይሁንና ግን ሲበዛስ? አስራ ምናምን ሊደርሱ ጥቂት የተቃረቡት የቴሌቪዥን ስርጭቶቻችን ሁሉ አዲስ ነገር ሲታጣባቸውስ? በዓል ከእኛ ጋር ብለው ጋብዘውን ሄደን ሲያደክሙንስ?
በእርግጥ እንደ በዓል ሆድ፤ የበዓል ዓይንም ለመጥገብ ትንሽ ሳይበቃው አልቀረም። በፊት ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ወይም ኢቲቪ የቴሌቪዥኑ አንድያ ልጅ በነበረበት ጊዜ ዛሬ ላይ የታከቱን ዝግጅቶች ብርቅ ይሆኑ ነበር። ለካ ሁሉም ነገር ሲበዛ ነው ደስ የማይለው? ነፃነትም ሲበዛ ጥሩ እንዳይደለ፤ ትዕግስትም ሲበረክት «ኧረ በቃ!» እንደሚያስብለው ሁሉ፤ የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲበዛም «ኧረ በቃን!» ያሰኛል ለካ!
የበዓል ዝግጅቶች በእርግጥ ከበፊቱ አንጻር ሲታዩ ብዙ ለውጦችን አድርገዋል። በፊት አንድ እንግዳ ተጋብዞ ገጠመኙን ይናገራል፤ ጥያቄ ይጠየቃል። ነገሩ ሲጠናቀቅ ሙዚቃ ይጋበዛል፤ አጭር ድራማ ይታያል፤ ኮሜድያን ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ፤ ሲጨፈር ዝግጅቱ ያበቃል። አሁንስ?
አሁን ጥሩ ሆኖ አርቲስቶች ይጫወታሉ፣ ይሳሳቃሉ፣ ይዝናናሉ፣ ይወዳደራሉ። ቅናት አስመሰለብኝ? ብቻ ጥበባዊ ይዘቱና የፈጠራው ነገር እንደ ቀድሞው አይደለም። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በፊት ከቀረቡ የበዓል ዝግጅቶች መካከል ለትውስታ እየመረጠ የሚያቀርባቸውና አንዳንዴም በዕሁድ መዝናኛ ዝግጅት ላይ በ«ዝንቅ» የሚያሳያቸው ትዕይንቶች ከበዓላት ዝግጅቶች የተወሰዱ ናቸው።
እነዛ ዝግጅቶች ከአቅራቢዎቹም ይሁን ከርዕሰ ጉዳዩ፤ ብቻ ግን ሳይሻግቱ ዛሬ ድረስ እያሳቁ ሊታዩ ይችላሉ። «ከቀድሞው የቀድሞ ስርዓት ናፋቂ» ካላላችሁኝ፤ እነዚያ ዝግጅቶች ከአሁን የበለጠ ጥበባዊ ይዘትና ውበት ነበራቸው ብል አላፍርም። በእርግጥ የአሁን ላይ ዝግጅቶችም የራሳቸውን ቀለምና ልዩነት ይዘው አልመጡም ማለቴ አይደለም። ነገር ግን ተመሳሳይና አዲስ ነገር የማይገኝባቸው ሆነዋል። የጥበብ ፈጠራ አቅም የተረገጠም ይመስለኛል።
ማለቴ…ለምሳሌ አንድ ጣብያ «በዓልን ከእኛ ጋር» ብሎ፤ አበበ፣ ከበደና አበበች የተባሉ አርቲስቶችን ይዞ ይቀርባል። በአሁኑ በዓል ላይ እንጨት ተሸክመው ከሆነ በቀጣዩ ውሃ ይቅዱ ይላል ሌላው። ከዚያ በሚቀጥለው «ለበዓሉ ዝግጅት አርቲስቶቹ ምን እያደረጉ ይታዩ?» ይሆናል ጥያቄው። አያችሁ! አዲስ ነገር ከማሰብ ይልቅ ቀለል የሚለው መንገድ በቅርባችን እየታየን ነው። መዝናኛ ሲባልም ቀድሞ ትውስ የሚሉን የኪነጥበብ ባለሙያዎች ሆኑ ማለት ነው።
አዳዲስ ሃሳቦች ጠፍተው ወይም አሸናፊ መሆን የማይችሉ ሆነው አይሆንም። ነገር ግን የሰዉ ፍላጎት ምንድን ነው የሚለው ላይ ርግጠኛ መሆን ስላልተቻለ ይመስለኛል። አንዳንዴ የፊልም ዘርፉ አስቂኝ የፍቅር ፊልሞችን ብቻ እንደሚለቀውና በዚያ መሰረት የሕዝቡ ፍላጎትም ያ እየመሰለው እንደሚሳሳተው፤ በዚህም እንደዚያ እየሆነ ይመስለኛል።
እና አሁን ይህ ሁሉ ሲጠቃለል አሁንም ቅናት መስሎ ይሆን እያልኩ እያሰብኩ ነው። ብትሉም አልፈርድም! ስጀምር «በዓልን ከእኛ ጋር» የሚሉት በቲቪ እና በራድዮን ብቻ እንጂ በጋዜጣ ብንልም ለውጥ የለውም አልኩኝ። ከዚያ ደግሞ «አርቲስቶች ብቻ ለምን ይጋበዛሉ?» ያልኩኝ እስኪመስል ድረስ ደጋገምኳቸው። ደስ እንዳላችሁ! ብቻ ግን በበዓል ዝግጅቶቻችን ላይ ጥበብ ቢታከልበት፣ አዳዲስ ፈጠራ ቢጨመርበት የጥበብንም ኃይል ማሳየት ይቻላል ለማለት ነው። «ምን አገባሽ!» አትሉኝም መቼስ! ለማንኛውም መልካም የትንሣኤ በዓል። ሰላም!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 20 ቀን 2011 ዓ.ም
ሊድያ ተስፋዬ