መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በቱሪዝም ዘርፍ እንደ አገር ያለን ሀብት በርካታ ነው። ይህ ሃብት ሌሎች አገራት እንዳላቸው ከፍተኛ የነዳጅ ክምችት ሊታይ የሚችል ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት የተፈጥሮ፣ የባህል፣ ቅርስ፣ የፌስቲቫል፣ የታሪክና የአርኪዮሎጂ ሃብቶች ገና በሚፈለገው ልክ ያልለሙና በቀጥታ ወደ ህብረተሰቡ ኪስ ውስጥ ገብተው ምጣኔ ሃብቱን ማነቃቃት ደረጃ ላይ ያልደረሱ ናቸው። የቱሪዝም ሃብት በምጣኔ ሃብቱ ላይ ቀጥተኛ ተፅእኖ እንዲፈጥርና ህብረተሰቡን እንዲጠቅም በማድረግ በኩል በቅድሚያ ሃብቱን የመለየት፣ የማስተዋወቅና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለውጤቱ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
በምሳሌነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት በአዲስ አበባ ከተማ ከተገነቡት የቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል የእንጦጦ ፓርክን ብንመለከት ከግንባታው ቀደም ብሎ ጎብኚዎች ትኩረት የሚያደርጉት ዳግማዊ ሚኒሊክ ቤተመንግስትና የእንጦጦ ማሪያም ቤተክርስቲያን ላይ ነበር። አሁን ግን በተለይ የአገር ውስጥ ጎብኚዎች በዚያው አካባቢ በተገነባው የመዝናኛ ቦታዎች ላይ በብዛት እየተገኙ ናቸው። በአካባቢው በስፍራው ካሉ ታሪካዊ ቦታዎች በተጨማሪ የልማት ስራዎች በመከናወናቸው ህብረተሰቡን በቀጥታ መጥቀም እንደጀመረም የሚያሳይ ምሳሌ ነው።
የዝግጅት ክፍላችን በቱሪዝም ዘርፉ የሚከናወኑ ተግባሮች በቀጥታ ማህበረሰቡ ላይ ተፅእኖ እንዲኖራቸው ለማስቻል መከናወን ስላለባቸው ተግባራት ከቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲቲዩት የቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊና መምህር አቶ አብይ ንጉሴ ጋር ጥቂት ቆይታ አድርጎ ነበር።
“በእንጦጦ የመዝናኛ ፓርክ ውስጥ አዲስ የመስህብና የቱሪዝም መዳረሻ ከመፈጠሩም በተጨማሪ ለሥራ እድል ፈጠራው ትልቅ ድርሻ ወስዷል” የሚለው የቱሪዝም መምህሩ አብይ፤ በተመሳሳይ በከተማዋ የተገነቡትና ታድሰው ለእይታ የበቁት የቱሪዝም መዳረሻዎች ቱሪዝም ለኢኮኖሚው ያለውን ጉልህ አበርክቶ በምሳሌነት ማሳየት የቻሉ እንደሆኑ ይገልፃል። ይህ የሚያሳየው የመስህብ ስፍራዎች፣ የተፈጥሮ ሃብቶች፣ ቅርሶችና መሰል መዳረሻዎች የቱሪዝም ምርት መሆን ሲችሉና በገበያው ላይ ሲቀርቡ በማህበረሰቡ ላይ በቀጥታ የሚፈጥሩትን በጎ ውጤት ማየት እንድንችል ያደርገናል ይላል።
በዚህ መሰረት በቅርብ ግዜ ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እያገኙ የመጡ የቱሪዝም መዳረሻዎች (የጮቄ ተራራ ሙሉ ኢኮ ሎጅ፣ የአፋርና በአማራ ክልል የሚገኙ) በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት የሚታወቁ የመስህብ ስፍራዎችንም በተመሳሳይ መልኩ መንግሥት በልዩ ሁኔታ በመደገፍ ህብረተሰቡ ላይ ቀጥተኛ በጎ ተፅእኖ እንዲያመጡ መስራት እንደሚያስፈልግ መምህሩ አብይ ንጉሴ ይናገራል። በተለይ መንገድን የመሰሉ መሰረተ ልማቶች በአገር አቀፍ ደረጃ ሲሰሩ የተፈጥሮ፣ የባህልና የታሪክ ሃብቶች ያሉበትን አካባቢም ታሳቢ ባደረገ መልኩ መሰራት እንዳለባቸው በመግለፅም ዘርፉን የሚመራው የቱሪዝም ሚኒስቴርም ሆነ ተጠሪ ተቋማት ለተፈፃሚነቱ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ በምክረ ሃሳብ ደረጃ ያስቀምጣል።
“የመሰረተ ልማት በአግባቡ ከሰራን፣ ሃብቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስተዋወቅ ከቻልንና ወደ ቱሪዝም ምርትነት ከቀየርናቸው ሃብቶቻችን ‘የጋን ውስጥ መብራት’ አይሆኑም” የሚለው የቱሪዝም ትምህርት ክፍል ኃላፊውና መምህር አብይ ንጉሴ፤ የምጣኔ ሃብትን ጠቀሜታ ብቻ ሳይሆን ገፅታችንን ለመገንባት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጠቅሙን ይገልፃል። የመስህብ ሃብቱን ወደ ቱሪዝም ምርትነት ከተቀየረ በኋላም በቅርቡ “ልወቅሽ ኢትዮጵያ” በሚል የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን ለማነቃቃት በዓለም ዋንጫ ወቅት እንደተካሄደው ሁሉ የማስተዋወቅና የጉብኝት ልምድ እንዲመጣ የማበረታታት ሥራ መቀጠል እንደሚኖርበት ምክረ ሃሳቡን ይሰጣል።
ዛሬ ኢትዮጵያ ያለችበትን የምጣኔ ሃብት (ጂዲፒ) ደረጃ አይተን ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም የሚለው ምምህር አብይ ንጉሴ፤ ከ100 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ያላት ኢትዮጵያ የሳይንስ ሙዚየም፣ እንጦጦ ፓርክ፣ የገበታ ለአገር ፕሮጀክቶችና ሌሎችም የቱሪዝም መዳረሻ ልማት በአግባቡ ከሰራችና ወደ ምርትነት ከቀየረች ከዓለም አቀፍ ቱሪስቱ በላይ በአገር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ብቻ ተጠቅሞ ዘርፉን ማነቃቃትና የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ያስረዳል። ይህንን አቅምም ሳይውል ሳያድር መጠቀምና በጥንካሬ መስራት እንደሚያስፈልግ ነው የዘርፉ ምሁር የሚናገረው።
“የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ሥራዎችን ስንሰራ የምናወጣውን ከፍተኛ ወጪ መመልከት የለብንም” የሚለው መምህሩ፤ ከፍተኛ ወጪም ቢሆን ትክክለኛው ልማት ላይ ካዋልነው የቱሪዝም ዘርፉ በአጭር ግዜ ውስጥ ወጪዎችን የሚመልስና ተጨማሪ የአገር ሃብትን የሚፈጥር እንደሆነ ይናገራል። እንደ ምሳሌም ከፍተኛ ወጪ ተደርጎባቸው የተሰሩት የወዳጅነት ፓርክ፣ ቤተመንግስት፣ እንጦጦ ፓርክና መሰል የቅርብ ግዜ መዳረሻዎች በፍጥነት በብዙ ህዝብ እየተጎበኙና ገቢ እያስገቡ መሆናቸውን ልንረዳ ይገባል ይላል። በዚህ ምክንያት መልሶ የሚከፍለው የቱሪዝም ዘርፍ ላይ መዋለ ንዋይ ለማፍሰስ መንግሥትም ሆነ የግሉ ዘርፍ አንቀሳቃሾች ጥርጣሬ ውስጥ ሊገቡ እንደማይገባ ያስረዳል።
የማስተዋወቅና ገበያ ልማት
“የመስህብ ሃብቶቻችንን በማስተዋወቅ ረገድ ጥንቃቄ ልንወስድ ይገባል” የሚለው መምህሩ፤ ‘ከፈረሱ ጋሪው ቀደመ’ እንደሚባለው ብሂል እንዳይሆን ማስተዋል ያስፈልጋል ይላል። አንድን የመስህብ ስፍራ ስናስተዋውቅ ለአገር ውስጥም ሆነ ለዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ‘ቃል’ እየሰጠን መሆኑን አንስቶ አስፈላጊው የመሰረተ ልማት ሥራ ሳይሟላ፣ ሃብቱ በሚገባ ወደ ቱሪዝም ምርትነት ከመቀየሩ አስቀድሞ ማስታወቂያው ገንኖ እንግዶች ቢመጡ ገፅታን የሚያበላሽና ከውጤት ይልቅ አሉታዊው ተፅእኖ የጎላ እንደሚሆን ይናገራል።
በመሆኑም ሁሉንም መስፈርቶች አሟልቶ ወደ ማስተዋወቅ ሥራው መግባት አስፈላጊ መሆኑን ይመክራል። በተሟላ መልኩ የሚተገበር የቱሪዝም ሥራ ደግሞ ከዋና ዋናዎቹ የምጣኔ ሃብት አንቀሳቃሽ አንዱ ፈር የሚቀድ እንዲሆን ያስችላል የሚል እምነት አለው።
ከላይ ባነሳነው ምክንያት የገበያና ማስታወቂያ ልማት ከመሰረታዊ የመሰረተ ልማት ሥራ መቅደም እንደሌለበት የቱሪዝም ባለሙያው ምክረ ሃሳብ ይሰጣል። በሌላ መልኩም አንድ ዓለም አቀፍ ጎብኚም ሆነ የአገር ውስጥ ዜጎች ካሉበት ስፍራ ወደ መስህብ ስፍራዎች ሲያቀኑ ቆይታቸውን ማራዘም እንዲችሉ የሚገፋፉ አገልግሎቶችን (የደህንነት ጥበቃ፣ አልጋ፣ መፀዳጃ፣ ሬስቶራንትና ሌሎች የቱሪዝም ምርቶች) ማግኘት እንደሚገባቸው ይገልፃል።
በኢትዮጵያ የሚገኙ ለቱሪዝም መዳረሻ ምቹ የሆኑ ስፍራዎችና የታሪክ፣ የተፈጥሮ፣ ቅርስና መሰል ሃብት ያለባቸው አካባቢዎችን በስፋት ማስተዋወቅ የሚገባውና እንግዶችን መጋበዝ የሚያስፈልገው የተነሱት አስፈላጊ መሰረታውያን ከተሟሉ በኋላ አንደሆነ ይናገራል። በምሳሌነት ደብረ ሊባኖስን አንስቶም በዚያ የኢትዮ ጀርመን ሬስቶራንትና መሰል የአገልግሎት መስጫ በመኖሩ ተመራጭ እንደሆነ ያነሳል።
“ዘርፉን በሚመሩ የግሉም ሆነ የመንግሥት አካላት አሁን ላይ እየተዋወቁ ያሉ የኢትዮጵያ የመስህብ ሃብቶች ሁሉም ከላይ ያነሳነውን መስፈርት አሟልተዋል ማለት አይቻልም” የሚለው መምህሩ፤ የመሰረተ ልማት እና የመዳረሻ ልማት በበቂ ሁኔታ ያላቸው ቢኖሩም እንኳን ሁሉም እዛ ደረጃ ላይ ደርሰዋል ማለት አንደማይቻል ነው የገለጸው፡፡ ሃብቶቹ መኖራቸውን ግንዛቤ መፍጠርና ማሳወቅ ተገቢ ቢሆንም በቂ መሰረተ ልማት ሳይሟላ በተለይ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ወደዚያ አካባቢ መጋበዝ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ያነሳል።
የማህበረሰብ አቀፍ ሎጅ፣ መሰረተ ልማትና የምጣኔ ሃብት እድገት
የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ሲከናወን የአካባቢውን የተፈጥሮ፣ ባህልና መሰል ገፅታዎች በማያበላሽ መልኩ መሆን እንዳለበት የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ። ይህንን ሃሳብም በቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲቲዩት የቱሪዝም ዘርፍ የትምህርት ክፍል ኃላፊና መምህር አብይ ይጋራዋል።
“የማህበረሰብ አቀፍ ሎጅ የአካባቢው ነዋሪዎች ለመስህብ ሃብቶቹ የኔነት እንዲሰማቸው የሚያደርጉ ናቸው” የሚለው መምህር አብይ፤ ዜጎች በሃብቱ ላይ ‘የእኔነት’ ስሜት አሳደሩ ማለት መዳረሻውን ለመጠበቅና የእንግዶችን ደህንነት ለማረጋገጥ ሁነኛ መንገድ እንደሆነ ይናገራል። በተጨማሪ በዙሪያው ያለው ነዋሪው የመስህብ ስፍራውን ለመመልከት ከሚመጡ የአገር ውስጥም ጎብኚዎች ምጣኔ ሃብት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይናገራል። ከዚያ በላይ ግን የማህበረሰቡ ቱባ ባህል፣ አኗኗርና አጠቃላይ ማንነት ለማሳየትና ሳይበረዝ ለጎብኚዎች ለማቅረብ ምቹ አጋጣሚ እንደሆነ ይናገራል። በዚህ ምክንያት የማህበረሰብ አቀፍ ሎጆችን ማስፋት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው አያሌ መሆኑን ያስረዳል።
“ማህበረሰቡ በአካባቢው ላይ በሚካሄድ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ ተሳታፊ ካልሆነ አለመስማማት/ ‘antagonistic society’ /እንዲፈጠር ያደርጋል” የሚለው መምህር አብይ፤ ቀጥተኛ የምጣኔ ሃብት ተጠቃሚ ካልሆኑና ጥቅሙን ካልተረዱ የልማቱና የዘርፉ ተቃዋሚ እንደሚሆኑ ይናገራል። ከዚህ መነሻ የማህበረሰብ አቀፍ ሎጅና የቱሪዝም መዳረሻ ልማቶችን ማስፋፋት ይህንን አሉታዊ ተፅእኖ እንደሚያስቀርና ማህበረሰቡን የሃብቱ ተጠቃሚና ባለቤት እንደሚያደርግ ይናገራል። በመሆኑም በዚህ ንኡስ ዘርፍ ላይም መስራት ተገቢ መሆኑን ያሳስባል።
የሙያ ብቃትና የዘርፉ ማነቆዎች
የቱሪዝም ዘርፍ ከዋና ዋና የምጣኔ ሃብት ምሰሶዎች ውስጥ ተመድቦ በመንግሥት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል። የልማት፣ የገበያና ፕሮሞሽን በመስራት፣ አካታች ቱሪዝምን ተግባራዊ በማድረግ አሁን ካለበት ደረጃ ለማሻሻልና የታለመለትን ግብ ለማሳካት ደግሞ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማብቃት የሚጠይቅ ነው። በሆቴልና ሆስፒታሊቲ እንዲሁም በአገልግሎት ዘርፉ ላይ ብቁ ባለሙያዎች የማሰማራት ችግር እንዳለና የሙያው ባለቤት የሆኑትም የተግባር ሥራው ላይ ደካማ ውጤት እንደሚያስመዘግቡ አንዳንድ ባለሙያዎች ይናገራል። ይህንን ሃሳብ ያነሳንላቸው የማሰልጠኛ ኢንስቲቲዩቱ የቱሪዝም ዘርፍ ምምህርና ኃላፊ እንደሚከተለው ሃሳባቸውን ይሰነዝራል።
“ባለሙያዎችን ከማብቃት አንፃር ተግባራዊ ልምምድ ላይ አንዳንድ ጊዜ ትኩረት አለመስጠት ይታያል” የሚለው መምህር አብይ፤ ይሁን እንጂ በቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲቲዩት ቱሪዝምን በሚመለከት በሚሰጡ የትምህርት አይነቶች ላይ ተማሪዎች ጉዞ አድርገው “ትምህርታዊ ጉብኝት” የሚያደርጉበት እንደሆነ ይገልፃል። በተለይ በሆቴል ዘርፍ ወደ መስክ እየወጡ በተግባር ልምምድ የሚያደርጉበት አግባብ እንዳለ ይናገራል። መንግስት አሁን ለዘርፉ ከሰጠው ትኩረት አንፃር ኢንዱስትሪውን የማይጠቅም የትምህርት አይነት ተቋማት የሚሰጡ ከሆነ እንዲቀር አስገዳጅ አቋም መያዙን ጠቅሶ፤ ይህንን አይነት አመለካከትና ውሳኔ ላይ መድረሱ ተገቢና ብቁ ባለሙያን ለማፍራት በሚደረገው ሂደት ላይ ድጋፍ ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን አንስቷል።
በቱሪዝም የሙያ ስልጠና ላይ ከ40 በመቶ በላይ የሚሆነው ስልጠና የሚሰጠው “በትብብር ስልጠና” ማእቀፍ መሆኑን የሚያስረዳው መምህሩ፤ ይህን መሰል ተሞክሮ በሌሎች መሰል ማሰልጠኛዎች ጋር እየተስፋፋ መሄድ እንዳለበት ምክረ ሃሳባቸውን ይሰጣል። ይህን ተግባር ላይ ማዋል ከተቻለም መንግሥት እየተከተለ ያለውን ፖሊሲ ለመደገፍና የቱሪዝም ዘርፉ የአገሪቱ የምጣኔ ሃብት ምሰሶ እንዲሆን የማይተካ ሚና እንደሚጫወት ነግሮናል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15 ቀን 2015 ዓ.ም