ሰላም ልጆች እንዴት ናችሁ? ትምህርትስ ጥሩ ነው? ጎበዞች። ሰሞኑን ደግሞ ትምህርት የለም አይደል? ትክክል ብላችኋል! በዓል ስለሆነ ትምህርት ቤትም ከዓርብ ጀምሮ ዝግ ነው። ለመሆኑ ከጓደኞቻችሁ ጋር እንኳን አደረሳችሁ ተባብላችኋል? አዎን! በዓል ሲሆን እንዲሁም ሰዎች ደስ ባላቸው ጊዜ ሁሉ እንኳን አደረሳችሁ እንዲሁም እንኳን ደስ አላችሁ ማለት ተገቢ ነው። ለመሆኑ ልጆች አብልጣችሁ የምትወዱት በዓል አለ?
አዲስ ዓመት? የገና በዓል? መውሊድ? በአገራችን በርካታ ብሔራዊ እንዲሁም ሃይማኖታዊ በዓላት ይከበራሉ። ከእነዚህ በዓላት ውስጥ ከላይ ከተጠቀሱት ውጪ ምን ያህሉን ታውቃላችሁ? ብዙዉን መጥራት እንደምትችሉ አልጠራጠርም። አንዳንድ በዓላት ደግሞ በአገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበሩ ናቸው። ለምሳሌ ዛሬ የሚከበረው ፋሲካ ወይም ትንሣኤ በዓል የክርስትና እምነት ተከታዮች ባሉበት ሁሉ በድምቀት የሚከበር በዓል ነው።
በዓሉ እንዴት እንደሚከበር ልገራችሁ። በመጀመሪያ ግን ፋሲካ ለምን ይከበራል? ፋሲካ ለክርስትና መሠረት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ የሚታሰብበት በዓል ነው። ይህም ደግሞ በክርስትና እጅግ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ጉዳይ በመሆኑ፤ በዓሉም በዚያው ልክ በክብደትና በድምቀት ነው የሚከናወነው። እንደምታውቁት ደግሞ በአገራችን የፋሲካ በዓል ሲከበር ሃይማኖታዊም ባህላዊም ይዘቱን ጠብቆ ነው።
በዓሉ ከመከበሩ ቀደም ብሎ አርባ ቀን ጾም አለ፤ ቅዳሜና ዕሁድን ሳይጨምር ማለት ነው። ቅዳሜና ዕሁድ ሲጨመሩ በድምሩ 55 ቀናት በጾም ያልፋል ማለት ነው። ሰምታችሁ ከሆነ ይህ ጾም ሁዳዴ ወይም ዐቢይ ጾም ይባላል። ጾም ብቻ ሳይሆን ጸሎትና መሰል ሃይማኖታዊ ክዋኔዎችም አብረውት አሉ።
ፋሲካ በብዙ የዓለማችን ክፍሎች፤ ክርስቲያኖች ባሉበት ሁሉ በድምቀት ይከበራል። በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና እንዲሁም በካቶሊክ ሃይማኖቶችም የተለያዩ ባህላዊ ስርዓቶች ይካተቱበታል። ከአገራችን ውጪ ፋሲካ በድምቀት የሚከበርባቸው ከተሞች እነማን እንደሆኑ ታውቁ ይሆን? ኤርትራ፣ ግብፅ፣ ሩስያ፣ በርካታ የአሜሪካ ግዛቶች እንዲሁም ሌሎችም በርካታ ከተሞች ይጠቀሳሉ።
ከእነዚህ በተጨማሪ አንዷ ኢየሩሳሌም ከተማ ናት። በኢየሩሳሌም በሺዎች የሚቆጠሩ ክርስትያኖች በአብያተ ክርስትያናት ውስጥና ዙሪያ ሆነው በፋሲካ ዋዜማ ወይም ሌሊት ላይ ጧፍ እያበሩ ትንሣኤውን ያስባሉ። በነገራችን ላይ ክርስትና ብሔራዊ ሃይማኖት ሆኖ በሚያገለግልባቸው አገራት ፋሲካ እንደ ብሔራዊ በዓል እንደሚቆጠር ታውቃላችሁ?
በዓሉ ሁሌም ዕሁድ ቀን ቢውልም፤ ማግስቱን ሰኞን ጨምሮ የቀን መቁጠሪያቸው የሚዘጋና ማግስቱን ራሱ እንደ በዓል የሚቆጥሩ አገራት አሉ። ከፋሲካ ሁለት ቀን በፊት ያለው ስቅለት ወይም ስግደት የሚካሄድበት ቀን በተመሳሳይ በብዙ በዓሉን በሚያከብሩ አገራት ሥራ የሌለበትና ብዙ ድርጅቶች ዝግ የሚሆኑበት ነው።
ዴንማርክ፣ አይስላንድ እና ኖርዌይ በተባሉ አገራት ደግሞ ከዓርብ ዋዜማ ሐሙስ ዕለትም ሙሉ ቀን አልያም በግማሽ ቀን በዓል ሆኖ ስለሚቆጠር ተቋማት ይዘጋሉ። ከዚያ በተረፈ ደግሞ አንዳንድ አገራት ላይ ወቅቱም ይለያያል። ለምሳሌ አውስትራሊያ በተባለችው አገር ፋሲካ የሚውልበት ወቅት ሰብል ምርት የሚሰበሰብበት ጊዜ ነው። ይሁንና በዓሉን ግን ከሌሎች ምሥራቅ አገራት ካሉ የክርስትና እምነት ተከታዮች ጋር በሚመሳሰል ሁናቴ ያከብራሉ።
በነገራችን ላይ በአውሮፓውያኑ Easter eggs /የፋሲካ ዕንቁላሎች/ የሚባል ለበዓሉ ድምቀትና በምሳሌነት ዕንቁላልን የሚጠቀሙበት ስርዓት አላቸው። በጥንት ዘመን ዕንቁላል የአዲስ ሕይወት ተምሳሌት ስለሆነም ነው። በክርስትና ደግሞ ትንሣኤ ለክርስትና እምነት መሠረቱ ነው። ስለሆነም ሁለቱን በማመሳሰል ያቀርባሉ ማለት ነው።
በፊት በነበረው ስርዓትም የተቀቀሉ ዕንቁላሎችን ቀለም በመቀባት ነበር የሚጠቀሙት። አሁን ላይ ታድያ ሁሉም ቦታ እውነተኛ ዕንቁላል አይጠቀሙም። ይልቁንም በውስጡ ጣፋጭ ከረሜላ የያዘ የዕንቁላል ቅርጽ ያለው ፕላስቲክ ያቀርባሉ ወይም የዕንቁላል ቅርጽ ያላቸው ቸኮላቶችን ይሰጣሉ። ለልጆችም ይህ ደስ የሚያሰኝ የበዓሉ አንድ ስርዓት ነው።
ሌላው ደግሞ በልጆች ፊልሞች ላይ ዓይታችሁ ከሆነ ወይም ከሰማችሁ Easter Bunny ኢስተር በኒ የምትባል የፋሲካ ምልክት የሆነች ጥንቸል አለች። እርሷም ልክ ለገና በዓል፤ የገና አባት እንደሚባሉት በፋሲካ ስጦታ ትሰጣለች የምትባል ናት። ብዙ ጊዜም የተለያየ ቀለም የተቀቡትን ዕቁላሎች አልያም ጣፋጮች የምትሰጠው እርሷ መሆኗን ብዙ ሕፃናትና ልጆች ያምናሉ።
ከዚህም ሌላ በተለይ በሩስያ አገሪቱ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በተገኙበት ነው በዓሉ የሚከበረው። ብዙውንም ጊዜ ሃይማኖታዊ ስርዓቱ የሚበዛ ሲሆን ከዚያ በተረፈ ሰዉ ወደየቤቱ ሲመለስ ጾሙን ይፈታል፤ ደስታም ይሆናል። በእኛም አገር ፋሲካ በዓል እንዴት እንደሚከበር ታውቃላችሁ አይደለ?
ገና ከሳምንት በፊት ከሚከበረው ሆሣዕና ወይም የዘንባባ በዓል ይጀምራል። ሳምንቱም ሰሞነ ሕማማት ተብሎ ከትንሣኤ በፊት ነበሩትንና ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳለፋቸው ሁሉ የሚታሰብበት ነው። ልክ ዓርብ ላይ ስቅለት ሲሆን፤ በዕለቱም በየአብያተ ክርስትያናቱ ክርስትያናት ተሰብስበው ይሰግዳሉ። ቀጥሎም ቅዳሜን አልፎ ዕሁድ ትንሣኤ ወይም ፋሲካ ስለሚሆን እኩለ ሌሊት ላይ ክርስትያኖች በቤተክርስትያን ሆነው ሻማና ጧፍ ያበራሉ፣ ‹ተነስቷል› እያሉም ይዘምራሉ። ከዚያም ቤታቸው ሲገቡ ቤት ያፈራውን ጾም መፍቻ በጋራ ይመገባሉ ማለት ነው።
ደስ ይላል አይደለ? ዛሬ ፋሲካ ስለሆነ ይህን አነሳን እንጂ የተለያዩ በዓላትም የየራሳቸው ስርዓት አላቸው። ልክ እንዲሁ ሁሉን በየጊዜአቸው እንነግራችኋለን እሺ!። ብቻ ግን በዓልን እንዲህ ባለ መልኩ ስናሳልፍ የተቸገሩትን ማሰብና መርዳት እንደሚያስፈልግ አትረሱም አይደለ? እኛ ደስ ሲለን ሌሎችም ደስታችንን እንዲካፈሉን ማድረግ ተገቢ ነው። ጎበዝ ልጆች! በበዓሉና በዕረፍት ተዘናግታችሁ ትምህርታችሁን ችላ እንዳትሉ እሺ! መልካም በዓል!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 20 ቀን 2011 ዓ.ም
ሊድያ ተስፋዬ