በማዕድን ዘርፉ በተከናወኑ ተግባራት፣ ከልማቱና ከግብይቱ ጋር በተያያዘ ያጋጠሙ ክፍተቶችን በአጠቃላይ ወቅታዊ አገራዊ የማዕድን ኢንዱስትሪ ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ ማዕድን ሚኒስቴር በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የማዕድንና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ኮሚቴ ሪፖርት አቅርቦ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡
ሪፖርቱን ያቀረቡት የማዕድንና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የማዕድንና ነዳጅ ልማት ዘርፍ ቁጥጥር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊየን ማቲዎስ እንደገለጹት፤ ባለፉት ሶስት አራት ዓመታት በተደረገው ማሻሻያ በተለይ በ2013 እና 2014 ዓ.ም የተሻለ ውጤት ተገኝቷል፡፡ መንግሥት የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በማድረግ አጠቃላይ የተገኘ የወርቅ ምርት ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባና የተሻለ የውጭ ምንዛሪ እንዲገኝ አስችሎም ነበር፡፡
ከ2014 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ግን በተለይም የወርቅ ምርት በህገወጥ (ኮንትሮባንድ) መንገድ ከአገር እየወጣ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰው፤ በህገወጥ ድርጊቱ ላይ የአገር ውስጥም የውጭ ኃይሎችም መሰማራታቸውን ተናግረው፣ ህገወጥ ድርጊቱ በእጅጉ እየጨመረ መምጣቱንም ነው የጠቆሙት፡፡ በዚህ ግማሽ ዓመትም ይህ ህገወጥ ግብይት ጎልቶ መታየቱን ተናግረዋል፡፡ አቶ ሚሊዮን የችግሩ ምንጭና ችግሩን ለመፍታት የተሰራውን ሥራ አስመልክተው ሲያብራሩም፣ ህገወጥ ድርጊቱን የመቆጣጠሩን ስራ በየወሩ ከሚገመገሙ ስራዎች አንዱ በማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ከክልል አስተዳደሮችና ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በጋራ በመሆን ችግሩን ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይቶች ተካሂደዋል። በተለይም የወርቅ ልማቱ በስፋት በሚካሄድባቸውና ህገወጥነቱም በጎላባቸው ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ እንዲሁም ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች አመራሩን በማግኘት ችግሩን በማስረዳት እና የጋራ በማድረግ ስለሚቀረፍበት ሁኔታ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ አሁንም ከጠቅላይ ሚኒስትር ጸህፈት ቤት እንዲሁም ክልሎችን ከሚመለከቱ የጸጥታ መዋቅሮች ጋር በቅርበት ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ አጠቃላይ ውጤቱ ሲታይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች እንዳሉት በሚኒስትር መስሪያቤቱ በኩልም ታይቷል።
ይህን ተከትሎ የምርት መጨመር ቢኖርም በህገወጥ ንግድ መሥፋፋት የተነሳ በበጀት ዓመቱ ለማግኘት የታቀደውን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ግን እንዳልተቻለ ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያስታወቁት፤ ህገወጥነትን የሚያበረታቱ ጉዳዮች በመኖራቸውም ከማዕድን ሚኒስቴር ውጪ ከሚገኙት አካላት ጋር በቅንጅት መስራትን እንደሚጠይቅ አቶ ሚሊዮን ገልጸዋል።
አቶ ማቲዎስ በተለይ ብለው ካነሷቸው ችግሮች መካከል ፈቃድ ማስተዳደርን የሚመለከተው አንዱ ነው፡፡ የክልል መንግስታት ለባህላዊ የወርቅ አምራች ማህበራት ፍቃድ ሲሰጡ ፍቃዱን በአግባቡ ማስተዳደር የሚገባቸው መሆኑ ላይ እየሰሩ አለመሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰዋል፡፡ በወርቅ አምራች ማህበራት የተመረተ ወርቅ ገዝቶ ወርቁን ወደ ብሔራዊ ባንክ ከማቅረብ አንጻር በአፈጻጸም በኩል ሰፊ ችግር እየተስተዋለ ነው ይላሉ፡፡
ምን ያህል ማህበር፣ በየትኛው ክልል በየትኛው ወረዳ እንደሚገኝ፣ በቀን እና በወር አንድ ማህበር ምን ያህል እንደሚያመርት ይታወቃል፡፡ በመሆኑም አመራሩ ትኩረት ሰጥቶ አስተዳደራዊ ችግሩን ለመፍታት ከየክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር እየተሰራ ነው። ከዚህ አንጻር ክልሎች እርምጃ በመውሰድ ላይ ይገኛሉ። የውጭ አገራት ህገወጦችን በተመለከተ ምርቱን በተለያየ ማሽን በመጠቀም ካመረቱ በኋላ ወደ ብሔራዊ ባንክ ሳይሆን፣ አገርን በሚጎዳ መልኩ በህገወጥ መንገድ ወደ ውጭ ያሻግራሉ ያሉት አቶ ሚሊዮን፣ በዚህ ረገድም ከፌደራል ፖለስ፤ ከክልል የጸጥታ መዋቅር ጋር በተጠናከረ መልኩ ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል።
የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኘ ‹‹የአገራችንን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የማዕድን ዘርፉን አቅም መጠቀም ይገባል›› ብለዋል። በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በተለይ በወርቅ ላይ ያለውን ሕገወጥ ምርትና ግብይት ለመከላከል ለክልሎቹ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል። ለማእድን ዘርፉ ከአምስት ዓመታት በፊት ብዙም ትኩረት አልተሰጠውም ነበር ያሉት ኢንጂነር ሀብታሙ፣ ካባለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ግን ማዕድን አንዱ የኢኮኖሚ ምሰሶ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ወርቅ፣ ታንታለም፣ ሚቴን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ እና ሌሎች ማእድኖች በከፍተኛ ክምችት እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ የአገሪቷ የማዕድን ሀብት በተገቢ የመረጃ ቋት እንዳልተደራጀ ገልጸዋል። የሲሚንቶ ምርት በተመለከተም 14 ሚሊዮን ቶን የማምረት አቅም ቢኖርም 6 ሚሊዮን ቶን ብቻ እየተመረተ መሆኑን አስታውሰው፤ በቀጣይ በሲሚንቶ በኩል ያለውን አቅም ከመጠቀም አልፎ ወደ ውጭ ለመላክ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
ምርት ያቆሙትን ከማስጀመር ጎን ለጎን ከአንድ ዓመት በኋላ ምርት የሚጀምር ግዙፍ ሲሚንቶ ፋብሪካ በመቋቋም ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል። በፖታሽ ብቻ 351 ቢሊየን ሜትሪክ ኪዩብ ሀብት መኖሩን ገልፀው የማዕድን ፕሮጀክቶችን አቅም በሚገባ መገንባት ይገባል ብለዋል። ማዳበሪያ በአገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችል ከፍተኛ ሀብት መኖሩንና ኢትዮጵያ በዓመት ለማዳበሪያ ግዢ የምታወጣውን አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለማስቀረት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል። በተቋማት አቅም ግንባታ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሳይንስ ላቦራቶሪ ግንባታ ላይ በትኩረተ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የወርቅ ምርትን በተመለከተ ሚድሮክን የመሳሰሉ በፋብሪካ ደረጃ ሊያመርቱ የሚችሉ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ጠቁመው፣ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በአገር ደረጃ እስካሁን የነበረውን የወርቅ ምርት በአምስት እጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም ነው ያስታወቁት። እስካሁን በባህላዊ መንገድ በዓመት የሚመረተውን የወርቅ መጠን ፋብሪካዎቹ በአንድ ጊዜ ሊያመርቱ እንደሚችሉም አስታውቀዋል፡፡
ሚኒስትሩ በማዕድን ዘርፉ የሚታየውን ሌብነትና ሕገወጥነትን ለመከላከል ከየክልሎቹ ጋር ውይይት ከማድረግ ጀምሮ ተግባራዊ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማዕድንና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴም በዚሁ ወቅት በሰጠው ማሳሰቢያ በማዕድን ዘርፉ ያለውን ሕገወጥነትና ሌብነት ለመከላከል በቴክኖሎጂ የተደገፈ ጠንካራ የአሠራር ስርዓት እንደሚያስፈልግ ገልጿል።
የማዕድንና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር አማረች ባከሉ እንደገለፁት፤ የማዕድን ዘርፍ መንግሥት ለአገር ኢኮኖሚ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣሉ ተብለው ትኩረት ከሰጣቸው አምስት ዘርፎች አንዱ ነው። በመሆኑም አገራዊ የማዕድን ምርት በግልፅ አሠራር ካልተመራ አሁን የሚታየውን ሕገወጥነት ለመከላከል ያስቸግራል። የማዕድን ዘርፉ ለዜጎች ሰፊ የሥራ እድል በመፍጠር ከፍ ያለ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፣ ይህንንም ታሳቢ ያደረገ ሥራ መሰራት ይኖርበታል ነው ያሉት፡፡ በማዕድን ዘርፉ ትላልቅ ባለሀብቶችን ለመሣብም የተደራጀ ዳታ ቤዝ እንዲኖር ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
የማዕድን አምራች ኩባንያዎች የሚያመርቱትን ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ስለማቅረባቸው አስተማማኝና ዘመናዊ የአሰራር መዋቅር ሊኖር እንደሚገባም ሰብሳቢዋ አስታውቀዋል። የማዕድን ዘርፉ ለመንግሥትም ሆነ ለተቋሙ ፈተና ሆኗል ያሉት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፣ ይህ ችግር የአፍሪካ እና በማደግ ላይ የሚገኑ አገራት ፈተና መሆኑን ተናግረዋል።
‹‹የማዕድን ልማታችን በተገቢው አሰራር መመራት ካልተቻለ ለሙስና በር ይከፍታል፤ የውጭ ዜጎች ህገወጥነት ይስፋፋል፣ ተቋማት ይዳከማሉ፤ የህዝብና መንግሥት መለያየት ያስከትላል›› ሲሉም ሰብሳቢዋ አስገንዝበዋል፡፡ ፌዴራል ላይ ያለው ተቋም ወደ ክልሎች ወርዶ እንዳይሰራ የህግ ክፍተት መኖሩንም ጠቅሰው፣ በአዋጅ የታገዘ የፖሊሲ አቅጣጫ ከማስቀመጥ አንጻር መልካም ጅምሮች መኖራቸውንም ነው ያመለከቱት፡ ፡ ከታች ጀምሮ ያለውን ሌብነት ለማስቀረት ግልጽ እና ዘመናዊ አሰራር ሊኖር ይገባል ሲሉም አጽንዖት ሰጥተው አስታውቀዋል። ለዚህም ሀብቱ የሚዘረፍበት ህዝብና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
ማዕድን ሚኒስቴር ማዕድንን የማምረት ኃላፊነት ሲሰጠው ከማዕድን ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ የመፍትሄ ሀሳቦች የማቅረብ ኃላፊነት እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡ በማእድን ዘርፉ እየጨመረ የመጣው ዝርፍያ ለአገርም ለመንግስትም ለህዝብም የሚበጅ እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ ይህ ችግር እንዳይከሰት የሚያደርግ ግልጽ የአሰራር ሥርዓት ሊኖር እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።
በማእድን ዘርፉ በተለይ በወርቅ ማምረትና ግብይት ላይ እየተፈጸመ ያለውን ህገወጥ ድርጊት የፌዴራል መንግስት ከማእድን ሚኒስቴር፣ ወርቅ ከሚመረትባቸው ክልሎች፣ ከፌዴራል ፖሊስና ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን ለመቆጣጠር እየሰራ ይገኛል፡፡ በቅርቡም የብሄራዊ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል በሕገ-ወጥ የወርቅና የተለያዩ ማዕድናት ፍለጋና ማምረት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችንና ተባባሪዎቻቸውን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የኢዜአ ዘገባ አመልክቷል፡፡ በዚህ ህገወጥ ድርጊት ከተሰማሩት መካከልም በርካታ የውጭ ዜጎች ይገኙበታል፡፡
ዘገባው እንዳመለከተው፤ የፀና የጉዞ ሰነድ፣ የመግቢያ ቪዛ እንዲሁም የመኖሪያ ፍቃድ ሳይኖራቸው በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በጋምቤላ ክልል ወርቅና የተለያዩ ማዕድናት ፍለጋ ላይ የተሰማሩ 45 የውጭ አገር ዜጎችንና ሦስት ኢትዮጵያውያንን ከነ-ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ስር ውለው፣ ምርመራ እየተጣራባቸው ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የፀና የጉዞ ሰነድ፣ የመግቢያ ቪዛ እንዲሁም የመኖሪያ ፍቃድ ሳይኖራቸው በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በወርቅና የተለያዩ ማዕድናት ፍለጋ እንዲሁም ማምረት ስራ ላይ የተሰማሩ 47 የውጭ አገር ዜጎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ዘገባው አመልክቷል።
በተጨማሪም ዘጠኝ ኃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ማኅበራትና ሰባት ኢትዮጵያውያን ግለሰቦችን ከእነ-ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝም የጋራ ግብረ-ኃይሉ በላከው መግለጫ አስታውቋል። ህገወጦች አገራችን ከማዕድን ዘርፉ ተጠቃሚ እንዳትሆን ማዕድናትን በኮንትሮባንድ ከአገር እንደሚያወጡ ደርሼበታለሁ ያለው የጋራ ግብረ-ኃይሉ በህገ-ወጥ መንገድ በማዕድን ፍለጋ ላይ የተሰማሩ የውጭ አገር ዜጎች፣ ተባባሪ ኢትዮጵያውያን ግለሰቦችና ኃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ማኅበራት ላይ እያደረገ ያለው ጠንካራ ክትትል ከጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ባለፈ በሌሎች ክልሎችም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
በአገራችን የማዕድን ሃብት ላይ ያነጣጠረ ወንጀል በመፈፀም የተጠረጠሩ የውጭ አገር ዜጎች፣ ኢትዮጵያውያን ግለሰቦችና ኃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ማኅበራት ከነ-ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ሥር ሊውሉ የቻሉት በአካባቢው ኅብረተሰብ ጥቆማ መሠረት በተካሄደው ጠንካራ ክትትልና ኦፕሬሽን መሆኑም ተገልጿል። ኅብረተሰቡ ላደረገው ቀና ትብብር የላቀ ምስጋናውን ያቀረበው የጋራ ግብረ-ሃይሉ፣ ህብረተሰቡ በየትኛውም አካባቢ በአገራችን ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጸሙ መሰል የወንጀል ተግባራትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ጥቆማ በመስጠት የሚያደርገውን ትብብር እንዲያጠናክር ጥሪውን አቅርቧል።
ከዘገባው መረዳት እንደተቻለው ህገወጥ ድርጊቱ በወርቅ ህገወጥ ግብይት ላይ ብቻ የሚታይ አይደለም፤ በማእድናት ፍለጋ ፈቃድ ያልተሰጣቸው የውጭ ዜጎችና ተባባሪዎቻቸውም በማእድን ፍለጋና ማምረት ጭምር ተሰማርተው ተገኝተዋል፡፡ ችግሩ የሰፋ መሆኑን ከግብረ ኃይሉ መግለጫ መረዳት ይቻላል፡፡
መንግስት ህገወጥ ግብይቱን ለመቆጣጠር ግብረ ኃይል አቋቁሞ እየሰራ መሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል፤ የስራው ውጤት በተወሰነ መልኩም ቢሆን እየታየ መሆኑን ማእድን ሚኒስቴር ጠቁሟል፤ ግብረ ኃይሉ እነዚህን ህገወጦች በቁጥጥር ስር እንዳዋለ ሁሉ በህገወጥ የወርቅ ግብይት ውስጥም የተሰማሩትን አካላት ለመቆጣጠር የያዘውን ሰፊ ርብርብ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 13 ቀን 2015 ዓ.ም