ለብዙ ወራት ተሰውሮ የነበረው ወፈፌው ይልቃል አዲሴ ሰማይ የአህያ ሆድ ሲመስል ተነስቶ በሰፈራችን ከሚገኘው ዋርካ ስር ቆሞ ይጮሃል። ሰዓቱ የሰፈራችን ሰዎች ወደ «በተስኪያን» የሚሄዱበት ነው። በእኛ ሰፈር ያሉ ሰዎች በሙሉ በተስኪያን ሳይሄዱ አስቀድመው ምንም አይነት ስራ አይጀምሩም። ዛሬ ግን ወፈፌው ይልቃል አዲሴ ከብዙ የአርምሞ ቀናት በኋላ መጮህ ስለጀመረ በሰፈራችን የሚገኙ ሰዎች ሁሉ በተስኪያን የሚገኘውን ቡራኬ ትተው የይልቃ አዲሴን ንግግር ለማዳመጥ ተቻኩለው ወደ ዋርካው ስር ተሰባሰቡ። ሰዎች በመሰባሰብ ላይ እያሉ ይልቃል አዲሴም…
አስበን እንስራ ለነገም እንዲሆን፣
ይሁን ይሁን ብለን የማይሆን እንዳይሆን።
« አለ አንዳርጌ መስፍን » እያለ ደጋግሞ ያምቧርቅ ነበር።
የሰፈራችን ሰዎች ወደ ዋርካው ተሰባስበው ቦታቸውን መያዛቸውን ከተመለከተ በኋላ ይልቃል አዲሴ ራሱን ለንግግር እያዘጋጀ እህ ..እህ… ብሎ ጉሮሮውን ጠራረገ። ንግግሩንም እንዲህ ሲል ጀመረ ……አሁን አሁን በሰፈራችንም ሆነ በእድራችን በሰፊው እየተንሰራፋ የመጣ እና የእድራችንን ህልውና ሊያጠፋ የተቃረበ ክፉ ወረርሽኝ ተከስቷል። ይህ ወረርሽኝ አለመደማመጥ ነው ! በኃይማኖት አለመደማመጥ፣ በፖለቲካ አለመደማመጥ፣ በእድር እና በሌሎች ሁነቶች አለመደማመጥ።
የሰፈራችን እና እድራችን ነዋሪዎች፣ መሪዎች እንዲሁም የተፎካካሪ ኃይሎች በመደማመጥ እና በመነጋገር ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ ሁሉን ነገር በግብታዊነት እና በትዕቢት ለማስፈጸም ሲፋተጉ ይስተዋላሉ። ይህ ፈጽሞ ልክ አይደለም።
እንደእኛ ሰፈር እና እድር ተሞክሮ ከዚህ ቀደም በሰፈራችን እና በእድራችን ተከስተው ከነበሩ አያሌ ችግሮች መካከል አንዳቸውም በጉልበት ሲፈቱ አላየናቸውም። አጋጥመውን የነበሩ ችግሮቻችንን በጉልበት ለመፍታት በሄድንባቸው ዘመናት ሰፈራችን እና እድራችን እጅግ አስቻጋሪ የሆነ ሁለተናዊ ቀውስ ገጥሟቸው እንደነበር ታሪክ ፍንተው አድርጎ ያሳየናል። በነገራችን ላይ የዓለም ተሞክሮም የሚየሳየው ይህንኑ ሃቅ ነው።
የዓለም ታሪክ በግልጽ እንደሚያሳየን በአንድ አገር ላይ ችግር በተፈጠረ ወቅት የተፈጠረውን ችግር በውይይት እና በጥበብ የፈቱ መሪዎች እና ተፎካካሪዎች እንዲሁም ህዝቦች በትልቁ አትርፈዋል። በአንጻሩ ግብዝ የሆኑ መሪዎች እና ተፎካካሪዎች እንዲሁም ህዝቦች የተፈጠሩ ችግሮችን ሁሉ በጉልበት ለመፍታት ሄደው ያጋጠማቸው ኪሳራ የሚታወቅ ነው።
ሰዎች ከሰዎች ጋር በሚያደርጉት ሁለንተናዊ መስተጋብር ሰው ናቸውና በመካከላቸው የፍላጎቶች አለመጣጣም ይከሰታል። እነኝህ የፍላጎቶች አለመጣጣም በግብተኝነት ለመፍታት የሞከሩ ኃይላት በሚፈጥሩት ፍትጊያ የሰውን ህይወት ከመቅጠፍ ውጭ አንድም ቀን መፍትሔ ሲያመጡ አላየናቸውም። የአንደኛው እና የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተመልከቱ ፤ መሪዎች እና ፖለቲከኞች በነበራቸው መስተጋብር የፍላጎቶች አለመጣጣም ተከሰተ። የተከሰተውን ችግር በውይይት ከመፍታት ይልቅ ልባቸውን ከግመል ሻኛ በላይ አሳብጠው «ይዋጣልን» አሉ። አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ጦር ሰበቁ ። ዘግናኝ ጦርነቶችን አካሄዱ። በጦርነቱ ህዝባቸውን አስፈጁ።
ሶቅራጥስ ‹‹ቁጣ የሚያሸነፍህ እንደሆነ ክፋት ቅን ሃሳብህን ለውጦ የራሱ ተከታይ እና ተገዢ ትሆን ዘንድ ማርኮሃልና ራስህን ከሰው ወገን አትቁጠረው። ›› ይላል። እውነት ነው፤ ቀና ሀሳብን ማፍለቅ ካልቻልን እና የሚፈጠሩ ችግሮችን በመስማማትና በውይይት መፍታት የማንችል ከሆነ ራሳችንን እንደ ሰው መቁጠር አይገባንም። በእኛ ሰፈር ያሉ ሰዎች፣ የዕድር መሪዎች እና ተፎካካሪዎች ከሶቅራጥስ ሀሳብ ተነስተን ብንገመግማቸው ሰዎች ናቸው ለማለት እንቸገራለን።
በሰፈራችን እና በእድራችን የሚከሰቱ ማናቸውም አይነት ችግሮችን የውጭ ሰው ሳይሰማ በጓዳችን ተወያይተን ከመፍታት ይልቅ ይዋጣልን ማለትን ስንመርጥ ይስተዋላል። በተለይ እድር እና ሰፈራችንን የምትመሩ እንዲሁም ለመምራት የምትፎካከሩ ኃይሎች እኛን ለመምራት ከፈለጋችሁ በመጀመሪያ ደረጃ የመሪዎች «ሀሁ» የሆነውን ራስን መግዛት እና መቆጣጠር ተለማመዱ። ራስን መግዛት እና መቆጣጠር የሚችል ሰው የሚፈጠሩ ችግሮችን በንግግር እና በውይይት ለመፍታት አያዳግተውምና። ራስን መግዛት እና መቆጣጠር መቻል በግብዞች የሚፈጠሩ የጥፋት ሰደድ እሳቶችን የሚያጠፋ ሁነኛ መድኃኒት ነው።
ነገር ግን ራስህን ከፍተኛ ሰገነት ላይ በማስቀመጥ የሰዎችን ሀሳብ እና መብት በመደፍጠጥ በአንድ ማህበረሰብ የሚፈጠሩ ችግሮችን በጉልበት ለመፍታት መጣር ትርፉ ውርደት ነው። የበርካታ አገራት ታሪክ የሚያሳየን ይህንኑ ሀቅ ነው።
እደግመዋለሁ ! አሁን ላይ በሰፈራችን እና በእድራችን እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በጥበብ፣ በመነጋገር እንዲሁም በመወያየት ከመፍታት ይልቅ በግብታዊነት እና በጉልበት ለመፍታት ሲሞከር ይታያል። ልማትን ለተጠማ ሰፈር እና እድር መገፋፋት እና መገዳደልን መምረጥ፤ በጠራራ ፀሐይ የመንገድ ላይ መብራት የማብራት ያህል እርባና የሌለው ተግባር ነው።
ወፈፌው ይልቃል አዲሴ ይህን ንግግር እያደረገ እያለ ሁሉም የሰፈራችን ሰዎች ጸጥ እረጭ ብለው እያዳመጡ ነበር። ነገር ግን ሁሌም ሳይፈቀድለት የሚናገረው አብሿሙ ክንፈ ጉደታ በይልቃል አዲሴ ንግግር ላይ ተደርቦ የይልቃል አዲሴን ንግግር አቋረጠው።
ባለፈው እንደነገርኳችሁ የሰፈራችን ሰዎች ክንፈ ጉደታን አብሿም ይበሉት እንጂ ክንፈ ጉደታ የእውነት አብሾ መጠጣቱን በእርግጠኝነት መናገር የሚችል ሰው የለም። የይልቃል አዲሴን ንግግር የአቋረጠው አብሿሙ ክንፈ ጉደታ «ይልቃል አዲሴ ያደረጋቸው ንግግሮች በሙሉ እውነታ አላቸው። እኔም ከሱ ሃሳብ ላይ የምጨምረው አለኝ» አለና ንግግሩን እንዲህ ሲል ጀመረ ….
እርስ በርስ የማይስማማ ህዝብ ለውጭ ጠላት አመቺ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። የእኛ ሰፈር እና እድር ደግሞ በርካታ የውጭ ጠላቶች አድፍጠው የሚመለከቱት መሆኑ ይታወቃል። ታዲያ ይህ እየታወቀ ስለምን በመነጋገር እና በውይይት ችግሮቻችን መፍታት ተሳነን ? ፈላስፎች እንዲህ ይላሉ፤ ብልህ እና አስተዋይ ሰው ለዘመኑ የሚስማማውን ነገር ያውቃል። ስለራሱም ያስተውላል። አንደበቱ ክፉ ከመናገር ይቆጠባል። እኛ ግን ብልሃት ጎድሎን ለዘመኑ የማይመጥን እና ወቅቱ ከሚፈልጋቸው አስተሳሰቦች ጋር የተጣረሱ አካሄዶችን እየመረጥን ነው። ከዚህ አንጻር የእኛ ሰፈር ሰዎች፣ መሪዎች እና ተፎካካሪዎች የት ላይ ነን ? ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ።
በዓሉ ግርማ በጉልህ በሚታወቅበት መጽሐፉ በኦሮማይ እንዲህ ይላል ….«የአሮጌው ሙጣጭ የአዲሱ ትውልድ የበኩር ልጅ ነው። » እውነቱን ነው ! በ1950ዎቹ እና 60ዎቹ በውጭ አገር እና በእኛ ሰፈር መካነ -አእምሮ የተማሩ ሰዎች የእነ ማርክስ እና ሌኒንን የፖለቲካ ንድፈ ሐሳብ ጭልጥ አድርገው ጠጥተው እና ተግተው ግራ ዘመም ሳይሆኑ «ግራ ዘመም » ሆነው የበርካታ ሰዎችን ህይወት አስነጠቁን። የእነሱ ርዝራዥ እና ሙጣጭ ደግሞ የአሁኑ የሰፈራችን የበሕር /በኩር/ ልጅ ሆነው እየበጠበጡን ነው። ሁሉ ነገራችንን የቁም ሲኦል እያደረጉብን ነው።
ፈረንጆች እንዲህ ይላሉ… የሰው ሁሉ ወዳጅ የአንድ ሰው ወዳጅ እንኳን መሆን አይችልም። እውነታቸውን ነው ! የ1950ዎቹ እና 60ዎቹ ሙጣጭ ዘውጌ ማርክሲስቶች፤ የአሁኑ ፖለቲካል ኢኮኖሚ የበኩር ልጆች አንድ እና መተኪያ የሌለውን ወንድማቸውን እየገፉ፤ የእድራችን እና የሰፈራችን ታሪካዊ ጠላት ከሆኑ ኃይሎች ጋር በጊዜያዊ ጥቅም ተደልልው ሳንባችንን አጋጥመን በአንድ አንፍንጫ እንተንፍስ ሲሉ ይስተዋላሉ። ይሁን እንጂ በጊዜያዊ ጥቅም የተገዛ ጓደኛ ችግር በገጠመህ ጊዜ አብሮህ እንደማይቆም እሙን ነው።
ጠቢባን እንደሚሉት፤ ጊዜ አግኝቶ ሳለ አለሁልህ ማለትን ለማያውቅ ጊዜው ሲያልፍበት አለሁልህ የሚለው አይገኝም። ይህ አባበል 1950ዎቹ እና 60ዎቹ ሙጣጭ ዘውጌ ማርክሲስቶች የተባለ ይመስለኛል። ልማት ለተጠማው እድራችን እና ሰፈራችን በተማሩት ሙያ እና ስልጣን አሁኑኑ መድረስ ካልቻሉ እነሱ እክል በገጠማቸው ጊዜ አብሯቸው የሚቆም ይጠፋል። ህይወት በጋሬጣ የተሞላችና አንድ ቀን እነሱን የህይወት ጋሬጣ ማጋጠሙ አይቀርም። ያኔ አንድ ሰው እንኳን አብሯቸው አይቆምም። ለዚህ መድሃኒቱ አሁኑኑ ለሁለንተናዊ ጥቅም በጋራ በመቆም እና በመደማመጥ የሚያገጥሙ ችሮችን መፍታት ብቻ እና ብቸኛው አማራጭ ነው።
የ1950ዎቹ እና 60ዎቹ ዘውጌ ማርክሲስቶችን ስመለከት «ለውሃቤ ዝናም ማየ ክልእዎ፤ ለዝናብ ጌታ ውሃ ነሱት» የሚለው የሊቃውንት ንግግርን ያስታውሰኛል። የምስራቋ ኮከብ የ1950ዎቹ እና 60ዎቹ ልጆቿን ለነገ ችግሬ ይደርሱልኛል ብላ ዛሬ ላይ የምትባለው ሳይኖራት ከሀብታም ልጆች እኩል አስተማረቻቸው። ነገር ግን «ዝናብ ለሰጠ ጌታ ውሃ ነሱት» እንዳሉት ሊቃውንት ሳይኖራት ያስታማረቻቸውን እናታቸውን መርዳት ባይችሉ እንኳን እንደነሱ ተሞላቀው ያልተማሩ ልጆቿን በዘውግ አቧድነው ባያባሏቸው ጥሩ ነበር።
ፈላስፋዎቹ እንደሚሉት፤ ሰዎችን ፍጹም ጥሩ ሊያስብሉ የሚችሉ አራት ባህሪያት አሉ። እነሱም ማስተዋል፣ መስጠት፣ መልካም ጠባይ እና ምኞትና ፍላጎትን ማሸነፍ ናቸው። እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባ ነገር አለ። በእነኝህ ፍጹም ሊያስብሉ በሚችሉ አራት ባህሪያት ውስጥ ቅንነት እና ችግሮች ሲያጋጥሙ በውይይት መፍታትን በውስጣቸው የያዙትን እናገኛለን። እዚህ ላይ የእኛ ሰፈር እና እድር መሪዎች እና ተፎካካሪዎች የት ላይ ናቸው ብሎ መጠየቁ ተገቢ ይመስለኛል።
በነገራችን ላይ በውይይት የማያምኑ ሰዎች በትንሽ ድል ራሳቸውን የሚኮፍሱ ግብዞች፣ አብዝተው የሚቸኩሉ እና ማስተዋል የተሳናቸው ናቸው። ፈላስፎችም ለተስፋ ፈተናው እና እንቅፋቱ መቸኮል ነው ይላሉ። ጠንቃቆች እና በውይይት የሚያምኑ ሰዎች ማንኛውንም ውሳኔ ሲወስኑ አይቸኩሉም። ምክንያቱም የነገ ተስፋቸው እንዲበላሽ አይፈልጉምና።
«በነገራችን ላይ በውይይት የማያምኑ ግብዞች ውይይትን በዋናነት የሚጠሉበት እና ጦርነትን እንደ አማራጭ የሚጠቀሙት ቀናተኛ ስለሆኑ እና አማራጭ የምፍትሔ ሃሳብ ማቅረብ ስለማይችሉ ነው። ለዚያም ነው ፈላስፎች ልጄ ከቅናት ተጠበቅ፤ ተጠንቀቅ ቅናት የመለያያት በር ናትና ብለው የሚያስተምሩት ።»ብሎ ወደ መቀመጫው ተመለሰ።
አብሿሙ ክንፈ ጉደታ ንግግሩን ሲጨርስ ወፈፌው ይልቃል አዲሴ ንግግሩን ከአቆመበት ቀጠለ ….
ለመፍትሔ የሚደረጉ ንግግሮች እና ውይይቶች ከአሽሙር የጸዱ እና ቀጥተኛ መሆን አለባቸው። በውይይት መካከል አሽሙር ወይም ሽሙጥን መጠቀም ወደአልተፈለገ አቅጣጫ ይወስደናል። ይህንን በምሳሌ ላሳያችሁ አንድ እግሩ ላይ የተፈጥሮ ጉዳት ያለበት፤ መራመድ የማይችል እና በመቀመጫው እየተንኳተተ የሚሄድ ሰው ነብር። አንድ ቀን ልብስ ለማሰፋት ወደ ልብስ ሰፊዎች ሱቅ አቀና። ለኮት የሚሆን ልብስም አስቀደደ። ልብስ ሰፊው መራመድ ለማይችለው ሰው በቀነ ቀጠሮ ኮት ሰፍቶ እንደሚጠብቀው ነግሮት ተሰነባበቱ። ልብስ ያስቀደደው እና መራመድ የማይችለው ሰውየም በተቀጠረበት ቀን ሂዶ የተሰፋውን ልብስ ለሙከራ አጠለቀ። ልብስ ሰፊውም የሰፋትን ኮት ያደነቀ አስመስሎ በአሽሙር ወይ ኮቲት! ወይ ኮቲት! እያለ ተሳለቀ። ልብስ ያሰፋውን ሰውየ በእግርህ መራመድ የማትችል ኮታታ ነህ በማለት ሰደበው። ቅኔው የገባው ሰውየም ከልብስ ሰፊው ጋር የነበረው መልካም ግንኙነት ተቋጨ። ሊቃውንት «ህይወት ወሞት ውስተ እደ ልሳን፤ ህይወትም ሞትም በአፍ ይመጣሉ። » ማለታቸው ለዚህ አይደል?
ይልቃል አዲሴ ንግግሩን ቀጥሎ… የእኛ ሰፈር ሰዎችን፣ ንቃተ ህሊና እና ውስጠ ህሊና ምን በላው ? ሲል ጠየቀ። ይህ በእንዲህ እንዳለ አብሿሙ ክንፈ ጉደታ ንቃተ ህሊና እና ውስጠ ህሊና ልዩነቱ ምንድን ነው? ሲል ጠየቀ።
ወፈፌው ይልቃል አዲሴ የተጠየቀውን ሲያብራራ፤ ንቃተ ህሊና ማለት የማሰብ ችሎታ ነው። ነገሮችን መቀበል ወይም ውድቅ ማድረግ ይችላል። ውስጠ ህሊና ግን የሚሰጠውን መቀበል ብቻ ነው። ውስጠ ህሊና እንደ መረጃ ማዕከል ነው።
አሸናፊ ሆነን መውጣት እንድንችል እና ሁልጊዜም በታሪክ በጥሩ ተምሳሌትነት ለመጠቀስ ከተፈለገ ንቃተ ህሊናችንን አወንታዊ ልምዶችን እንዲያዳብር እናለማምደው። ንቃተ ህሊናችን አወንታዊ ልማዶችን ማዳበር ከቻለ ደግሞ ውስጠ ህሊናችን በጎ ነገሮችን ስሊሚያስቀምጥ ክፉ ተግባራትን ከመፈጸም እንታቀባለን። በነገራችን ላይ ሰዎች ፍላጎቱ ካላቸው አወንታዊ ልምዶችን በየትኛውም እድሜ ላይ መጀመር ይችላሉ። ለእዚህ አባባል በርካታ ማሳያዎች ቢኖሩም ካለን ጊዜ አንጻር አንዱን ብቻ ነጥለን እንመለክት። ለምሳሌ አንድ ሰው በወጣትነት ዘመኑ ለንቃተ ህሊናው መጥፎ ነገሮችን እየነገረ እና እየመገበ በርካታ ወንጀሎችን ሊፈጽም ይችላል። ነገር ግን እድሜው ሲገፋ እና ቆርቦ ሲመነኩስ ግን ንቃተ ህሊና በበጎ ነገር ስለሚሞላ፤ በጎ ነገሮችን እያደረገ ለአእምሮው እና ለፈጣሪው ለመገዛት ሲጥር እንመለከታለን።
ስለሆነም ንቃተ ህሊናችንን በበጎ አስተሳሰቦች ሞልተን በጎ ተግባራትን ለማድረግ በየትኛውም የእድሜ ዘመናችን ላይ መጀመር እንደሚቻል ሁሉም ሰው ሊገነዘብ ይገባል። በማንኛውም ሁኔታ ችግሮችን በኃይል ከመፍታት ይልቅ በቅንነት ለመወያየት ቅድሚያ እንስጥ።
በመጨረሻ «ሐንካስ በአግረ ዕውር ሖረ፤ ዕውርኒ በዐይነ ሐንካስ ነጸረ ወበክልዔሆሙ ወይንየ ተመዝበረ …. አንካሳ በእውሩ እግረ ሄደ፤ እውሩ በአንካሰው ዐይን አየ » እንዳሉት ሊቃውን በሰፈራችን እና በእድራችን የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ወደሚፈለገው የእድገት ጎዳና ለመግባት ዐይን ያለው እግር ይሸከም፤ እግር የሌለውም ዐይን ከሌለው ትክሻ ላይ ተቀምጦ ዐይን የሌለውን ይምራ። እንደዚህ ተደጋግፍን መኖር ይጠበቅብናል። ለዚህ ሁሉ ግን መደማመጥ መቅደም አለበት ብሎ ንግሩን ሲጨርስ የሰፈራችን ሰዎች በጭብጨባ አጀቡት። ስብሰባውም በዚሁ ተቋጨ።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12/2015