የባሕል አልባሳት የኢትዮጵያዊ ማንነት መለያ፣ የበዓላት ጊዜ መዋቢያና መደመቂያም ናቸው።በዓል በመጣ ቁጥር ኢትዮጵያውያን አምረውና ድምቀው እንዲታዩ ከሚያደርጉ፣ በዓልን በዓል ከሚያሰኙ ነገሮች መካከል የባሕል አልበሳት ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ።
ይህ ሁኔታ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ይበልጥ እየተጠናከረ መጥቷል።በአዘቦት ቀን እንኳን ሰዎች የባሕል አልባሳት ለብሰው ሲታዩ ዛሬ ደግሞ ቀኑ ምንድነው በዓል አለ እንዴ? ብሎ እስከመጠየቅ ተደርሷል።
የሠርግ ሥነ ሥርዓቶች፣ የጥምቀት በዓል ለባሕል አልባሳት ፍላጎት እየሰፋ መምጣት የራሳቸውን ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።የቤተሰብ አባላት፣ ጓደኛሞች፣ ወዘተ ተመሳሳይ የባሕል አልባሳት እያሠሩ የሚለብሱበት ሁኔታም ሌላው በባሕል አልባሳት መፈለግ አዎንታዊ ተጽዕኖ ያሳደረ ጉዳይ ነው።
ምስጋና ለፋሽን ኢንዱስትሪው ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አልባሳቱ ይበልጥ መዋብ ውስጥ ገብተዋል።አልባሳቱ በባሕላዊና በዘመናዊ መልኩ እንደ ለባሹ ፍላጎትና ምርጫ እየተሠሩ ለገበያ እንዲቀርቡ እየተደረገ ነው፤ተፈላጊነታቸውም በዚያው ልክ እየጨመረ ፤ከበዓላትም ውጪ እየተዘወተሩ ይገኛሉ።
በበዓላትም ቢሆን እንደ የበዓሉ አይነት፤ በዓሉን የሚመጥኑ የተለያየ አይነት የሀገር ባሕል ልብሶች ይለበሳሉ።ለአዲስ ዘመንና ለትንሳኤ በዓል የሚለበሱት አልባሳት በዓይነትም ሆነ በይዘት ይለያሉ።የአልባሳቱ ዓይነት በሸማቹ ፍላጎትና ምርጫ ላይ የሚመሠረት ቢሆንም በዲዛይን ተሠርተው ባማረ መልኩ ይቀርባሉ።ለዚህም ነው አሁን ላይ ባሕላዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ ባማረ ዲዛይን ተሠርተው ልበሱኝ! ልበሱኝ! የሚያሰኙ የባሕል አልባሳት እየተበራከቱ መምጣታቸው።
በዛሬው ፋሽን ዓምዳችን ስለ ባሕላዊ አልባሳት ማንሳት የወደድነው አልባሳቱ የዛሬው የትንሳኤ በዓል አልባሳቱ በስፋት የሚለበሱበት በመሆኑ አያይዘን ስለአልባሳት ጥቂት እንበል ብለን።ለእዚህም በበዓላት ተፈላጊ የሆኑ የሀገር ባሕል አልባሳት ገበያ ቅኝት አድርገናል፤ለባህል አልባሳት ልዩ ትርጉም የሚሰጡ የልብሱን አዘውታሪና ዲዛይነርም አነጋግረናል፡፡
ኤልሳቤጥ አበበ ትባላለች።ለበዓል የምትለብሰውን የሀገር ልብስ ለዲዛይነር መስጠቷን ሰሞኑን ነግራናለች። ኤልሳቤጥ የባሕል ልብስ መልበስ ትወዳለች፤ ከበዓላት ቀናት ውጪም በአዞቦት ቀናት ጭምር የባሕል ልብስ መልበስ ታዘወትራለች፡፡
‹‹እንኳንስ በበዓል ቀን ይቅርና በሌላም ጊዜ ምክንያት ፈልጌ ነው የሀገር ልብስ የምለብሰው›› የምትለው አልሳቤጥ፤ ቤተክርስቲያን፣ ወደ ተለያዩ ጥሪዎች እና የሥራ ቦታዎች ስትሄድ ሳይቀር የሀገር ልብስ መልበስ እንደሚያስደስታት ትናገራለች፡፡
ይሁን እንጂ አሁን ላይ ያለው የልብሶች ዋጋ መናር ለመልበስ አያስመኝም የምትለው አልሳቤጥ፤ እንደሌላ ጊዜ በየበዓሉ የሀገር ልብስ ማሠራት ቀርቶ በዓመት አንድ ጊዜ ለመልበስ እንኳን ዋጋው የማይቻልና ኪስ የሚጎዳ እየሆነ መምጣቱን ትገልጻለች።
አሁንም ለትንሳኤ በዓል የሀገር ልብስ ለማሠራት የፈለገችበት ዋነኛ ምክንያት ከበዓሉ በኋላ ሌላ ፕሮግራም ስላላት ለዚያም ጭምር አስባ እንጂ ዋጋው ተመጣጣኝ ሆኖ እንዳልሆነም ትገልጻለች።ልብሱን ያሠራችበት ዋጋ 8ሺ ብር ነው፤ ይህም በዋጋ ትንሹ እንደሆነ ነው የምትናገረው።ትንሹ ዋጋ ተብሎ የሚጠራው እንኳን የኅብረተሰቡን የመግዛት አቅም ያገናዘበ አይደለም በማለት ጠቁማለች፡፡
‹‹የሀገር ልብሶቻችን እኮ የኛ ናቸው፤ እኛ ለብሰን ካልደመቅንባቸውና ካለጌጥንባቸው ማን ሊያጌጥባቸው ይችላል›› ስትል ገልጻ፣ በበዓላት ጊዜም ሆነ በማንኛውም ጊዜ በልብሶቹ የሚደምቀው እና የሚያምረው ከኛ በላይ የለምም ነው የምትለው።ብዙ ሰዎች በሀገራቸው ልብስ መድመቅ እየፈለጉና እያማራቸው ከዋጋቸው አንጻር መልበስ አዳጋች እንደሆንባቸው ትገልጻለች።
ቀደም ሲል ሁሉም ሰው የሚፈልገው ዓይነት የሀገር ልብስ በሚችለው ዋጋ ሸምቶ መልበስ ይችል ነበር ።ለዚህ የአደባባይ በዓላቶቻችን ምስክር ናቸው የምትለው አልሳቤጥ፤ አሁን ላይ አብዛኛው ሰው ሽፎንና የቻይና ልብሶችን እየሸመተ መልበስ መጀመሩን ትገልጻለች።የሀገር ልብስ ሁሉም ሰው በሚፈልገው ዓይነት በተመጣጣኝ ዋጋ ሸምቶ ሊለብሰው የሚችል መሆን አለበት እንጂ ከሰው አቅም በላይ እንዳይለበስ መደረግ የለበትም ትላለች።
የወንዶችና የሴቶችን የባሕል አልባሳት ዲዛይን በማድረግ የምትታወቀው ዲዛይነር ቅድስት ወልዴ በበኩሏ፤ የደንበኛችን ፍላጎት መሠረት በማድረግ ልብሶቹን እንደምታዘጋጅ ትገልጻለች።ዲዛይነሯ ሁሉን ያማከሉ የተለያዩ የባሕል አልባሳትን ዲዛይን በማድረግና በመስፋት ለገበያ ታቀርባለች።
እንደየበዓሉ ሁኔታ ደንበኞች በሚፈልጓቸውና በሚመርጧቸው መጠን ልብሶችን እንደምታዘጋጅ የምትናገረው ዲዛይነር ቅድስት፤ በበዓል ጊዜያት ባሕላዊ ሆነው በሽመና የሚሠሩ ቀለል ያሉ ለባሕል የሚሆኑ ልብሶች ተመራጭ ናቸው ትላለች ።
በፋሲካ በዓልም ቀለል ያሉ ባሕሉን የጠበቁ ከባሕሉ ጋር አብረው የሚሄድ ጥለቶች እንዳሉም ትጠቁማለች፡፤ በተለይ አረንጓዴ ጥለት ያላቸው፣ ተጠልፈው ፤ተሰፍተውና ተሸምነው የሚለበሱ ጥበብ ነገሮች በዚህ በዓል እንደሚመረጡ ነው የጠቆመችው፡፡
‹‹የሀበሻ ቀሚስ ተፈላጊ ነው፤ ሰዎች የባሕል ልብስ መልበስ ይወዳሉ›› የምትለው ዲዛይነር ቅድስት፤ አሁን የአልባሳት ዋጋ መጨመር ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ ገበያውን እንዲቀዛቀዝ ማድረጉን እሷም ገልጻለች።
ልብሱን ለመሥራት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች መወደድ ዋጋውን ከፍ እንዲል ያደረገው መሆኑን ጠቅሳ፤ የዋጋው ውድነት ገበያ እንዲቀዛቀዝና ሸማቹ እንዳይገዛ ምክንያት እንደሆነም ነው ያመለከተችው።ከክር ጀምሮ ፣ለባለሙያ፣ ለሸማኔ ወዘተ. የሚከፈለው ክፍያ፤ ሁሉም ነገር ጨምሯል የምትለው ዲዛይነር ቅድስት፤ ይህ ልብሱ እንዲወደድ ችግር መፍጠሩን ጠቁማለች፡፡
የልብሶቹ ዋጋ እንደየልብሱ አይነት የተለያየ ቢሆንም ከትንሽ እስከ ትልቅ ድረስ ዋጋ የሚጠሩ ልብሶች እንዳሉም ጠቅሳ፣ ከ5ሺ ጀምሮ ከ20ሺ ብር በላይ የሚሸጡ ልብሶች እንዳሉም ታብራራለች።ዋጋው እንደየዲዛይኑና ጥበብ አይነት እንደሚለያይም ነው የተናገረችው፡፡
አብዛኛው ሸማች የሚፈልገው ባሕሉን የጠበቀውን ልብስ ነው የምትለው ቅድስት፤ ጥበቡ እንዳለ ሆኖ በዲዛይን ተደርጎ እንዲሠራ የሚፈልጉ እንዳሉም ትገልጻለች።እንደየሸማቱ ፍላጎት አልባሳቱ እንደሚዘጋጁም ትገልጻለች።ትልልቅ ሰዎች ባሕሉ እንዲጠበቅ ይፈልጋሉ፤ ወጣቶች ደግሞ በዲዛይን እንዲሠራ ይመርጣሉ የምትለው ዲዛይነር ቅድስት፣ የባሕል ልብስን በሁሉም እድሜ ደረጃ ያሉ ሰዎች የሚለብሱት በመሆኑ ሁሉን ያማከለ ሥራ እንደሚሠራ ነው የምትናገረው፡፡
‹‹የባሕል ልብሶችን በሚፈልጉት መልኩና ዲዛይን የሚያሠሩ ሰዎች ትዕዛዙን ቀደም ብለው ማዘዝ አለባቸው›› እንዳለባቸውም ዲዛይነር ቅድስት ታስገነዝባለች።ምክንያቱም የባሕል ልብስ ሥራው ከባድ መሆኑና ሸማኔ ለማዘዘ ቀን ስለሚፈልግ መሆኑን ትናገራለች፤፤ ከሁለት ወር በፊት በማሳወቅ የግድ መሆኑንም ነው ያመለከተችው።ሸማቶች ቀደም ብለው ቢያሳወቁ ጥሩ ነው ትላለች ፡፡
ዲዛይነር ቅድስት እንደምትለው፤ የባህል አልባሳትን የማዘጋጀቱ ሥራ ከዋጋ ንረቱ ጋር ተያይዞ ፈታኝ ሆኗል።የዋጋ ንረቱ ለሥራው እጅግ አዳጋች እየሆነ ነው ፤ በየጊዜው ዘርፉን የሚያዳክሙ አዳዲስ ነገሮች በየጊዜው ይፈጠራሉ፤ በዚህ የተነሳ ዘርፉን ለማሳደግ አልተቻለም፤ ገበያው የሚረጋጋበት መንገድ ቢፈጠር ገበያው ይረጋጋል ፤ ሁሉም በየአቅሙ የሚችለው ገዝቶ መልበስ ይችላል፡፡
ሙያው እንዲያድግ በማድረግ በዘርፉ ልቆ ለመውጣት ባለሙያው እንደፈለገ እንዲሠራ መድረግ አለበት የምትለው ዲዛይነር ቅድስት፤ ለዚህም በዋጋ ማረጋጋቱ ላይ መንግሥት ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቃለች።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 9 ቀን 2015 ዓ.ም