ኢትዮጵያ በበርካታ የታሪክ፣ የባህል፣ የአስተሳሰብ፣ የፎክሎርና የጥበብ እሴቶች የተገነባች አገር ነች። ከሦስት ሺህ ዘመናት በላይ ሕዝቦች የጋራ ማንነት ኖሯቸው አብሮነታቸው የጠነከረ እንዲሆን ያስቻሉ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሥርዓቶች ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገሩ እዚህ ደርሰዋል። ለዚህ ነው «ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ፣ የታሪክ፣ የተፈጥሮና የባህል መናገሻ» እንደሆነች የሚገለጸው።
ሕዝቦቿ በብዙ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች ተከብበውና ተዋድደው የሚኖሩ የፍቅርና የመከባበር ተምሳሌቶች እንደሆኑም ይነገራል። አገሪቱ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስከብሩ የራሷ የዘመን መቁጠሪያና ፊደል ያላት፤ በሌላው ዓለማት በማይገኙና ተወዳጅ በሆኑ በዓላት፣ አልባሳትና የአመጋገብ ሥርዓትም ትታወቃለች።
የፎክሎር ባለሙያው ዶክተር ዘላለም ተፈራ ግብረ ገብነት፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓት፣ ሰብዓዊነት የኢትዮጵያውያን መገለጫና አብሮ የመኖር ተምሳሌት መሆናቸውን ይጠቅሳሉ። «የባህል እሴቶቻችን በትውልድ መካከል የሚኖር ተግባቦትና የሚደረግ ቅብብሎሽ ምን መሆን አለበት?» ለሚለው ጉዳይ ምላሽ ሲሰጡም ሰው የመሆን ክብር፣ ከራስ ባሻገር ለሰው ቅድሚያ መስጠት እንደሆነ ይጠቅሳሉ።
በርካታ የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራንም ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ ከመሆኗ አንፃር የዚያኑ ያህል እጅግ ብዙና ህብርን የተላበሱ እሴቶችና የጋራ ማንነቶችም እንዳሏት በተደጋጋሚ ይገልፃሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሀገር ልማት ጥናት ኮሌጅ ዲን የሆኑትና በቱሪዝም ልማትና አስተዳደር፣ በቱሪዝም ምርቶችና ሌሎች መሰል ጉዳዮች ላይ በማስተማር፣ ከማስተዋወቅ አንፃርም ምርምርና ጥናት ለፖሊሲ ግብአቶች በማበርከት የሚታወቁት ዶክተር ተስፋዬ ዘለቀ የዚህ ሃሳብ ተጋሪ ናቸው። ዜጎች ከሃይማኖታቸው ከሚቀዱ የበዓል ሥርዓቶች የተገነባ ውብ ማንነት ከመላበሳቸውም ባሻገር፤ በመቻቻል ለዘመናት አብሮ በመኖር በዳበረው እሴት የተነሳ ሁሉም የሚጋሩት ባህልና ኢትዮጵያዊ ቀለምም እንዲሁ መገለጫው እንደሆነ ይናገራሉ። ከእርሳቸው በተጨማሪ ከላይ በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ምርምር ያደረጉ የማህበራዊ ዘርፍ ምሁራን ሃሳቡን በተጨባጭ ማስረጃ ያረጋግጡልናል።
እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ የአዲስ ዘመን መለወጫ እስኪበሰር ድረስ «ከመስከረም እስከ መስከረም» አያሌ ተወዳጅና በጉጉት የሚጠበቁ ክብረ በዓላት፤ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሥነ ሥርዓቶች ይካሄዳሉ። ከዘመን መለወጫ ወይም እንቁጣጣሽ እስከ «መስቀል»፣ ኢሬቻ፣ ጨምበላላ፣ ጥምቀት፣ ጊፋታ እና ሌሎችም በርካታ የማህበረሰቡን ባህላዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች የሚያሳዩ ተወዳጅ እሴቶች በድምቀት ይከበራሉ። ከውጪ ሆኖ ለሚመለከታቸው በሚያስቀኑና «የኔ በሆኑ» በሚያሰኙ ኢትዮጵያዊ ህብር ማንነቶች ዜጎች አብረው በጋራ ይደምቃሉ።
በመግቢያችን ላይ በምሁራን ከተገለጹት ኢትዮጵያዊ እሴቶች መካከልም በተያዘው የሚያዝያ ወር በክርስትና እምነት ተከታዮችና በእስልምና አማኞች ዘንድ የሚከበሩት «የትንሳኤና» እና «የረመዳን» ታላላቅ ሃይማኖታዊ በዓላት ይገኙበታል። ዛሬ በመላ ክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ እየተከበረ የሚገኘው የትንሳኤ በዓል በአገሪቱ ከሚከበሩ ተወዳጅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሥነሥርዓቶች ውስጥ አንዱ ነው።
በአሉ ሃይማኖታዊ ብቻም ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ባህላዊ እሴቶች በድምቀት የሚንጸባረቁበትም ነው። ይህ በዓል በባህሪው ለአንድ ቀን ብቻ የሚከበርም አይደለም ለአንድ ሳምንት በተለያዩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሥርዓቶች በድምቀት ይከበራል፡፡
የኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት በአብዛኛው ከባህላዊ ሥርዓቶች ጋር ከፍተኛ ትስስር አላቸው። የአመጋገብ፣ አለባበስ፣ መረዳዳት፣ ቤተሰባዊ አብሮነትና ፍቅር ከሃይማኖታዊ በዓላት ጋር ጥብቅ ቁርኝት አላቸው።
ለምሳሌ ያህል በዛሬው እለት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ እየተከበረ ከሚገኘው የእየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ወይም «የፋሲካ በዓል» ጋር የሚገናኙ አያሌ ባህላዊ ሥርዓቶች አሉ። በተለይ ይህ ክብረ በዓል ከመድረሱ አስቀድሞ የሃይማኖቱ ተከታዮች በእለቱ በድምቀት ለሚከወነው ሥርዓት የሚያደርጉት ዝግጅት በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ ልዩ ባህላዊ ውበትና ድምቀትን የሚፈጥር ነው።
የበዓል ወቅት የገበያ ሥርዓቱ ከምግብ፣ ባህላዊ መጠጥ ዝግጅት አለባበስና መሰል ጉድጉዶች ጋር ተሰናኝቶ የበዓሉ ድምቀት ብቻ ሳይሆኑ ለዘመናት ትውልድን ተሻግሮ የመጣ ባህላዊ እሴት የሆነ ሀብት ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን አብሮነትና ፍቅር በልዩ ሁኔታ ስፍራ አግኝተውና ከመቼውም ጊዜ በተለየ ደምቀው የሚታዩት «ፋሲካን» በመሰሉ በዓላት ወቅት ነው። የእምነቱ ተከታዮች ባይሆኑም አብሮ በመኖር በጉርብትና የፈጠሩት ህብረትና የመቻቻል ተምሳሌት ፈክቶ የሚወጣውም እንደ «ፋሲካ» በዓል ባሉት በዓላት ወቅቶች ነው።
በፋሲካ- የሹላሌና ጊጤ ጨዋታዎች
አቶ ክፍሌ ለገሰ በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ወሰን እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ላለፉት 23 ዓመታት ኖረዋል። ወደ ከተማዋ መጥተው ከባለቤታቸው ጋር መኖር ከመጀመራቸው በፊት በወጣትነታቸው የትንሳኤ በዓል በላሊበላ በሃይማኖታዊ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን በባህላዊ ሥርዓትም ጭምር ይከበር እንደነበር ያስታውሳሉ።
በበዓሉ ወቅት ከሚከናወኑት ድርጊቶች አንዱ፣ የአካባቢው ልጃገረዶች የሚጫወቱት ሹላሌ የተሰኘ ጨዋታ እንዱ መሆኑን ያስታውሳሉ። አሁንም አልፎ አልፎ ወደ ስፍራው ለቤተዘመድ ጥየቃ ሲያቀኑ ይህንን ጨዋታ እንደሚመለከቱት ይናገራሉ። እንደ አካባቢው ተወላጅ አገላለጽ፣ ሹላሌ ከትልቅ ዛፍ ላይ ጠፍር ታስሮ ልጃገረዷ በጠፍሩ ላይ ተቀምጣ የምትጫወተው ነው። ሌሎች እየገፏት እየዘፈኑ ዥዋዥዌውን ይጫወታሉ።
ግጥሙም የሚከተለውን ይዘት አለው… ‹‹ሽው ሽው ላሌ፤ እሰይ ለዓመት በዓሌ…›› «ታተይ ከቋቱ ላይ ያለው እንቁላል ድመት በላው አንቺ የት ሄደሽ? እኔማ ለገብርዬ ያን እሰጥ ብዬ»፤ አግባኝ ሳልለው አግብቶኝ ነጋዴ፤ ሲያበላኝ ከረመ ነጭ ጤፍ ከስንዴ›› እያሉ እንደሚጫወቱና በደስታ፤ አብሮ በመብላት፣ የተቸገረን በመርዳትና በፍፁም ሰላም ሹላሌ የተሰኘው ጨዋታ ከፋሲካ (ትንሣኤ) እስከ ዳግማይ ትንሣኤ ድረስ የሚቀጥል እንደሆነም ነግረውናል። ልጃገረዶቹ በጠፍር ላይ ሆነው መወዛወዛቸው አይሁዶች የኢየሱስ ክርስቶስን ጉዳይ በክስ አደባባይ ከሄሮድስ ወደ ጲላጦስ፣ ከጲላጦስ እንደገና ወደ ሄሮድስ የማመላለሳቸው ምሳሌ እንደሆነ ያስረዳሉ።
በተመሳሳይ ልክ እንደ ልጃገረዶቹ ሁሉ ወጣት ወንዶችም ተመሳሳይ ጨዋታ አላቸው። የላሊበላ ወንዶች የሚጫወቱት ደግሞ የጊጤ ጨዋታ እንደሚሰኝ እኚሁ የአካባቢው ተወላጅ ይነግሩናል። ስለዚህ ጨዋታ አቶ ክፍሌ እንዲህ በማለት ያስረዳሉ፤ ወንዶች ቁልቋል የሚባል ተክል ቆርጠው ግንዱን መሬት ቆፍረው ይተክሉታል። ከዚያ የሾለ አንካሴ ይዘው እሱን እየወረወሩ ይወጋሉ። ውድድር አለው በተራ በተራ ያሸነፈ ይጨበጨብለታል። ረቺው በተረቺው ላይ ተፈናጦ ይሄዳል። በአንካሴ ቁልቋሉን ይወጋል። ይኸው ጨዋታ ኢየሱስ በጦር የመወጋቱ ምሳሌ መሆኑ ይነገራል።
አክፋይና ትንሳኤ
ሌላው የፋሲካ ወይም «ትንሳኤ» በዓል ወቅት ዘርን፣ ቀለምን፣ የኢኮኖሚ ደረጃን ሳይለቅ የሚከናወን ባህላዊና ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው «አክፋይ» እየተባለ የሚታወቀው ሥርዓት የሚካሄድበትም ነው። በበዓሉ ሰሞን በተለይ ቤተሰብ የመሰረቱ ልጆች ልጆቻቸውን ይዘው አከፋይ ለወላጆቻቸው ይወስዳሉ፡፡ በዚህም አቅም የሚፈቅደውን ያህል ሙከት በግ ወይም መጠጥ ወይም ዳቦ፣ ወዘተ ወደ ቤተሰብ ይዞ በመሄድ ሲጫወቱ መዋል የተለመደ ነው፡፡
ወይዘሮ ቦጋለች ተሾመ የመርሐቤቴ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። የዘንድሮውን የትንሳኤ በዓል ከልጆቻቸው ጋር በአዲስ አበባ ለማክበር ወስነዋል። እርሳቸው እንደሚሉት፤ በሰሞነ ትንሳኤ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘት ያላቸው ልዩ ልዩ ሥነሥርዓቶች በኢትዮጵያውያን ዘንድ ይከናወናሉ። ከእነዚህ ውስጥ እሳቸው የሚያውቁትና በሚኖሩበት ወረዳ የሚካሄደው «የአክፋይ» ወይም አክፍለት ሥነሥርዓት ነው።
«በእኛ አካባቢ ትንሳኤን አክፋይ ይዞ ወደ ቤተሰብ በመሄድ ከሳምንት እስከ ሳምንት በደስታ እናሳልፈዋለን» የሚሉት ወይዘሮ ቦጋለች፤ ሁሉም እንዳቅሙ ወዳጅ ዘመዱን የሚጠይቅበት፣ ዝምድና የሚፈጠርበትና የሚጠናከርበትም እንደሆነ ይገልፃሉ።
በተለይ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ ልጆች ሲወለዱ «ክርስት አባትና እናት» በሚል ለቅርብ ወዳጅ የሚሰጡ መሆኑን አስታውሰው በዋናነት የክርስትና ልጅ የክርስትና አባት/እናቱን እቤቱ በመሄድ የሚጠይቅበትና እንኳን አደረሰህ የሚባባልበት መሆኑን ይገለፃሉ። በምላሹ የክርስትና አባት/እናት ልጆቻቸው በትንሳኤ ሰሞን ለጥየቃ ቤታቸው ሲመጡ ስጦታ እንደሚያዘጋጁ ይናገራሉ። ይህ ባህላዊ ሥርዓት በደም የማይተሳሰር ወዳጅን ዘመድ የማድረጊያ አንዱ መንገድ መሆኑንም ጠቅሰው፣ የትንሳኤ በዓልን መሠረት አድርጎ የሚከናወን መሆኑን ነግረውናል።
ኢትዮጵያዊ እሴቶች
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የፎክሎርና የአትሮፖሎጂ ክፍል እንደሰነደው በሰሜን ሸዋ ምንጃር አካባቢ ደግሞ የበዓሉ አከባበር በዕለተ ሐሙስ ይጀመራል፤ ይህ ዕለት ጉልባን፣ ዳቦና ጠላ ተዘጋጅቶ በመብላትና በመጠጣት ይታለፋል። በማግስቱ ደግሞ የስቅለት ወይም የስግደት ዕለት በዋናነት የአካባቢው ሽማግሌዎችና አዛውንቶች በመስገድ የሚሳተፉበት ዕለት ነው። ቅዳም ስዑር (የቅዳሜ ስዑር ዕለት) ማታ ዶሮ ይታረዳል። የዶሮ ወጥ የጾም መፍቺያ በመሆኑ የሚበላው ሌሊት ዶሮ ሲጮህ ሲሆን፣ በዚህ ሰዓት ከትንሽ እስከ ትልቅ ያሉ የቤተሰብ አባላት ከእንቅልፉ ተቀስቅሶ እንዲገድፍ ወይም ጾሙን እንዲፈታ በማድረግ ይሆናል።
በደቡብ ክልል ሸካ ዞን የሚገኙት ሸከቾዎችም ፋሲካን በራሳቸው ባህላዊ መለያ ያከብሩታል። በዓሉ ሐሙስ የሚጀምር ሲሆን ዕለቱ ‹‹ዳጲ ማዮ ማዮ›› ይባላል። ይህም የንፍሮ ቀን ማለት ሲሆን፣ ቀኑን በጾም በማሳለፍ ወደማታ የሚበላው ምግብ ንፍሮ ብቻ ነው። በሌሎች ቦታዎችም በጸሎተ ሐሙስም ጿሚዎቹ ጉልባንና ንፍሮ ቀምሰው እስከ ትንሣኤ ሌሊት ሳይመገቡ ያከፍላሉ። ባቄላ፣ ስንዴና ጥራጥሬ ተቀላቅሎበት የሚዘጋጅ የምግብ ዓይነት ጉልባን ነው። ዓርብ ስቅለት ከስግደት መልስም ጉልባን ይበላል፡፡ የኀዘን መግለጫ ሆኖ የተወከለ ነው።
ሚሻ ሚሾ-የፋሲካ ጨዋታ
በፋሲካ ወቅት ከሚከበሩ ባህላዊ ሥርዓቶች መካከል በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የምናገኘው «የሚሻ ሚሾ» በዓል ሌላው ባህላዊ ሥርዓት ነው። ይህ ሥርዓት ልዩ ልዩ መገለጫዎች እና ትርጉሞች አሉት፡፡ ይህንንም በጉዳዩ ላይ ጠለቅ ያለ እውቀት ያላቸው ምሁራን በመጽሐፋቸው ላይ ያሰፈሩትን ዳሰሳ ተመልክተን ይበልጥ ለመረዳት እንሞክር።
የፋሲካ በዓል ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዳግማይ ትንሣኤ እየተከበረ ይቆያል። የበዓሉ መንደርደርያ ጸሎተ ሐሙስ ሆኖ ማዕከሉን በተለይ በዓለ ስቅለትን ያደርጋል። ከበዓለ ስቅለት ባህላዊ መገለጫዎች አንዱ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚዘወተረው «ሚሻ ሙሾ» ነው። ይህንንም ባህላዊና ትውፊታዊ ሥርዓት ቀሲስ ሰሎሞን ወንድሙ መታፈሪያ «መዝገበ በረከት ዘሰሙን ቅድስት» በተሰኘውና ለንባብ በበቃው መጽሐፋቸው ዘርዘር አድርገው ማስረጃዎች እያጣቀሱ አቅርበውታል።
ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ወንዶች ሕፃናት «ሚሻ ሚሾ» እያሉ እየዘመሩ በየቤቱ እየዞሩ ዱቄት ይለምናሉ። በዓሉ በባህላዊ ሥርዓቱ በቂጣ ስለሚከበር የአይሁድ የቂጣ በዓልን ይመስላል። አለቃ ታየ ገብረ ማርያም በ1902 ዓ.ም በታተመው የትብብር ሥራቸው «ሚሻ ሚሾ» የሚለው ስያሜ የት መጣንም «ውሾ ውሾ» ከሚል እንደሆነ ያስረዳሉ።
ሕፃናት ከሐሙስ ጀምረው እስከ በዓለ ስቅለት ምሽት የሚሻ ሙሾን ዝማሬ እያሰሙ በየቤቱ በመዞር ዱቄት የሚያሰባስቡት ትውፊታዊ ክዋኔ አላቸው። ሕፃናቱ በየቤቱ ዱቄት ለመሰብሰብ ሲዞሩ በቀለማት ወይም በእሳት ተለብልቦ የተዥጎረጎረ ቀጭን ዘንግ ይይዛሉ። መሬቱን በዘንግ በመምታት ዱቄት እስኪሰጣቸው ድረስ በተለያዩ ግጥሞች የታጀበ ዝማሬ ያሰማሉ። ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘንግ መመታቱን ለመዘከር ነው። በዝማሬያቸውም…
ሙሻ ሙሾ ስለ ስቅለቱ
አይንፈጉኝ ከዱቄቱ።
ሚሻ ምሾ፣ ሆ ሚሻ ሙሾ
ሳይጋገር መሸ፣
እሜቴ ይውጡ ይውጡ ይበላዋል አይጡ፣
እሜቴ ይነሱ ፣ ይንበሳበሱ፣
ከቆምንበት፤ ቁንጫው ፈላበት፣
ስለ አቦ፤ ያደረ ዳቦ፣ ስለ ስቅለቱ፤ ዛቅ አድርገው ከዱቄቱ» በማለት ይዘምራሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን በርካታ ግጥሞችና የጨዋታ ዓይነቶችም እያዜሙ በዓሉን ታዳጊዎቹ ያከብሩታል። እኛም መልካም በዓል እንላለን፡፡
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8 ቀን 2015 ዓ.ም