ለዚህ ጽሑፍ ይህንን ርእስ በስያሜነት ስንሰጥ ብዙ አስበንበታል። እናስብ ዘንድ ያደረገን ደግሞ “ማ ይቅደም?” የሚለው ሲሆን፣ ሄዶ ሄዶ እንደምንመለከተው “ቆሻሻ” የመሪነት ስፍራውን ይዟል። የዚህ ምክንያቱ ብዙ የሚያነጋግር ቢሆንም ለጊዜው ትተነው እንለፍና “ቆሻሻ እና እኛ”ን ወደተመለከተው ጉዳያችን እንገስግስ። “ከአፍሪካ የመጀመሪያው …” የሚለው ጎልቶ በሚቀነቀንባት፤ አንድም ቦታ “ከአፍሪካ ቀዳሚዋ …” ተብሎ በገለልተኞች ባልተረጋገጠላት አዲስ አበባ ማሳያም እንቆዝም።
እንደ መግቢያ
አለማችን በአመት በአማካይ 2.01 ቢሊዮን ቶን ደረቅ ቆሻሻን “ታመርታለች”። ከዚህ ውስጥ 33 በመቶ የሚሆነው ለሰውና አካባቢ ጠንቅ በሆነ ሁኔታ ነው የሚወገደው። እንዲሁም፣ አለማችን በአማካይ በቀን 0.74 ኪሎግራም (ይህ ከ0.11 እስከ 4.54 ኪሎግራም ድረስ የሚሄድ ነው) ቆሻሻን ትታቀፋለች። ይህንን የሚነግረን በ2018 የተደረገ አለም አቀፍ ጥናት ነው። “ከዚህ ውስጥ የእኛ ድርሻ ስንት ይሆን?” ለሚለው “እኛ እዚህ ውስጥ ምንም ድርሻ የለንም” የሚል መልስ እንደማይኖረው ሁሉ፣ ለዚህ ጥያቄም እስካሁን የተሰጠ ምላሽ የለም።
“አንድ ምርት ከአሁን በኋላ የማይጠቅም ወይም የተመረተበት ተመሳሳይ ተግባር ከሌለው ቆሻሻ ይሆናል፡፡” የሚለውን ይዘን ወደ ፍተሻ ስንገባ፤ በአለማችን በየአመቱ 380 ሚሊዮን ቶን ፕላስቲክ ይመረታል። ከዚህ ውስጥ 8 ሚሊዮን ቶን የሚሆነው (plastic waste) ወደ አደባባይና ውቅያኖሶች ይጣላል የሚለውን እናገኛለን።
በአለም ላይ ያለው የቆሻሻ መጠን በየጊዜው ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አይታይም። በ2050 አለማችን ቆሻሻዋ (Waste generation) ከ70 ፐርሰንት በላይ የሚጨምር ሲሆን፣ ከ3.4 ቢሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ የቆሻሻ መጠንም ልታስተናግድ ከወዲሁ ዝግጅቷን እያጠናቀቀች መሆኗን የwww.statista.com “Global waste generation – statistics & facts” በሚል ርእስ ያወጣው መረጃ ያመለክታል። ለዚህ የሚዳርጓትን ምክንያቶችም የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የከተሜነት መስፋፋት፣ እንዲሁም የሰዎች የሸቀጦች ግብይትና የሱቅ ሸመታ እየጨመረ መሄድና ልማድ (የአኗኗር ዘይቤ) መሆን በማለት ይዘረዝራቸዋል። እንዲሁም፣ የሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ቆሻሻን የማስተናገድና አገልግሎት የመስጠት (waste treatment and disposal services) አቅምና ፍላጎታቸው ቀሽም መሆኑንም ሳይሰስት የዘረዘረ ሲሆን፤ እኛም ሳንሰስት እዚህ ደግመነዋል።
እንደ ጥናቱ ዳሰሳ ከሆነ በየአመቱ በሚሊዮን ቶኖች የሚቆጠር ቆሻሻ ወደ አለማችን የሚጣል ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከ20 በመቶ በታች የሚሆነው ብቻ ነው በእንደገና ጭፍለቃ ወደ ሌላ ምርት ተቀይሮ አገልግሎት የሚሰጠው። ሌላው፣ እኛ “ቆሼ” እንደምንለው አይነት ስፍራ (landfill sites) እየተወሰደ ነው የሚጣለው። በኋላስ? በኋላማ፣ ቆሼ እኛ ላይ ያደረሰውን ማስታወስ ነዋ።
የቆሻሻ ጉዳይ የዘመኑ አደገኛ ጉዳይ መሆኑን የሚገልፀው ይህ ጥናት አለማችንን በሁለት የቆሻሻ ጎራዎች ከፍሎ የሚያይ ሲሆን፣ እነሱንም ደሃና ሀብታም አገራት ሲሆኑ ሀብታሞቹ አገራት ከደሃዎቹ የበለጠ ቆሻሻ ቢያመርቱም ቆሻሻን የማስተናገድ ልምድ ያላቸው በመሆኑ በቀላሉ የሚያስወግዱት መሆኑን ይገልፃል። (worldatlas.comም ጉዳዩን በአገራት በታትኖ የሚያብራራ ሲሆን፣ ድረ-ገጹን መጎብኘቱ ለተሻለ ግንዛቤ ያግዛል ብለን እናምናለን።)
የአካባቢ ብክለትን ከፕላስቲክ አኳያ (plastic pollution statistics) የሚመለከተውና (በሴፕቴምበር 21፣ 2021 ጥናቱ) ወቅታዊ መረጃን ለህዝብ ተደራሽ የሚያደግውና “በ2050 በአለማችን 937 ሚሊዮን ቶን የፕላስቲክ ምርቶች ይኖራሉ፤ በአሁኑ ሰአት በአለማችን ካሉት የፕላስቲክ ምርቶች ከ90 በመቶ በላይ የሆኑት ሪሳይክል አይደረጉም” የሚለው ድርጅት እንደሚነግረን ከሆነ በአለማችን 8.3 ሚሊዮን ቶን ፕላስቲክ በአለማችን የሚገኝ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 6.3 ቢሊዮን ቶን የሚሆነው ለሰው ልጅ ጤና ጠንቅ በሆነ መልኩ የሚገኝ ነው። እንደዚሁ ጥናት ከሆነ፣ በ2050 በአለም ላይ በሚገኙ ውቅያኖሶች ሁሉ ከአሳዎች ቁጥር ይልቅ የተጣሉ ፕላስቲኮች ቁጥር በበርካታ እጥፎች የሚበልጥ ይሆናል። ጉድ በል ጎንደር አለ።
በአመት 42 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ፕላስቲክ የምታመርተው አሜሪካ ሳትቀር፣ 1 ሚሊዮን ቶን ያህሉን ወደ ውቅያኖሶች በመጣል ለችግሩ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገች ትገኛለች። ጉድ በል በጌምድር ይሏል ይሄኔ ነው። (እኛ 101ኛውን የፕላስቲክ ውሃ አምራች ፋብሪካን በቅርቡ ስለማስመረቃችን እንጂ ሌሎች፣ እዚህ እየተነጋገርንባቸው ያሉ መረጃዎችን በተመለከተ የነገረን ባለመኖሩ ስለ ሰው ጉድ (ባለቅኔው “ምናልባት ቢያስፏጨው …) እንዳለው፣ ቢያስፏጨን በማለት) ማውራቱን መርጠናል።)
በቆሻሻ ብዛትና ብክለት ፊሊፒንስን 1ኛ፣ ኢንዶዥያን 2ኛ፣ ብራዚልን 3ኛ . . . ያደረገው የ2023 ጥናት ወደ እኛ አልመጣም እንጂ ቢመጣ ኖሮ የፊሊፒንስን ቦታ ለኢትዮጵያ አይሰጥም ማለት አይቻልም ነበር። (በ2021 በተደረገ ጥናት፣ በአመት 540,000 ቶን ፕላስቲክ የምታመርተው ኖርዌ ከ97 በመቶ በላይ ሪሳይክል በማድረግ አለምን እየመራችና Norway the highest recycling country for plastic. እየተባለላት ይገኛል።) በ2022 ጀርመን 66.1% የሚሆነውን በዳግም ጭፍለቃ መልሳ ወደ ስራ በማስገባት ከአለም 1ኛ በመሆን አለምን እጁን ከንፈሩ ላይ አስጭናለች። ኢትዮጵያ እንዲህ የሚባልላትን ጊዜ መናፈቅ ይቻላልን?? ከተቻለስ፣ መቼ??፡፡
እንደሚታወቀው ቆሻሻ እና እኛ የተለያየንበትን ጊዜ መናገር እጅጉን ይከብዳል። “መች ተገናኝተን የምናውቀውን ነው . . .?” የሚል አስተያየት እንደማይነሳው ሁሉ፣ “መች ተለያይተን የምናውቀውን ነው . . .?” የሚል አስተያየትም ሊያስነሳ ይችላል። ለማንኛውም ክርክሩ መሬት ያለውን እውነታ አይፍቀውም እና ወደ ተነሳንበት እንሂድ።
ያገለገሉና ማገልገል ያቆሙ የቤት እቃዎችን ከቤት ማስወገድ በማይሆንላት አገር፤ ያገለገሉ ፕላስቲክ ጠርሙሶችና ሌሎች ለአዲስ ገበያ ፍለጋ በይፋ ወደ ክፍለ አገራት (ለዛው፣ ለፈረደበት የገጠር ሕዝብ) የሚላኩባት ብቸኛ አገር ኢትዮጵያ . . .፤ በቆሻሻ የተነሳ የበርካቶች ሕይወት የተነጠቀባት አገር ብትኖር ኢትዮጵያ ስትሆን፣ ከከተሞችም አዲስ አበባ ነች። “ታዲያ ምን ትምህርት ወሰደች?” ብሎ የሚጠይቅ ካለም መልሱ የሚሆነው “ምንም” ነው። ምንም . . .። በመሆኑም ዝናም ጠብ ባለ ቁጥር ከየቱቦው እየተግተለተለ የሚወጣው የቆሻሻ በየአይነቱ አይን ያስቆረጥማል ብቻ ሳይሆን አፍንጫ ሳይቀር ያሰንጋል።
በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ዘነበወርቅ፣ ጉልት፣ ቀጫ ሰፈር፣ ሰማኒያ አራት፣ ቻይና ካምፕ፣ ቆሬ፣ ጉድ ሼፐርድ፣ ወድቆ የተነሳ፣ ገብረክርስቶስ፣ ጎንደር ሰፈር፣ ፈረንሳይ ሰፈር፣ ሀምዛ ማህበር፣ ቄሶች ሰፈርና በመሳሰሉ መንደሮች (ሄኖክ በመጣጥፉ እንደዘረዘረልን) ወደ ተከበበውና (ለቆሼ ራስጌውን የሰጠው ጉድ ሼፐርድም ሆነ በደርግ የመጨረሻ ሰዓት በምሪት የተዘረጋው እንደ ሀምዛ ማህበር እና ቄሶች ሰፈር ያለው ማህበር ቤት ሕገወጥ መንደር ሳይሆን በከተማችን ከሚገኙ ቀደምት ሰፈሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው) ቆሼ እሚባለው አካባቢ የደረሰውን የከፋ አደጋ (ቅዳሜ ምሽት መጋቢት 2/2009 ዓ.ም.)፤ በአደጋው ምክንያትም የሞቱትን ሰዎች እና የወደመውን ንብረት ማንም አይረሳውም።
በብዙ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ቆሼን የኑሮ መሰረት አድርጎ ሲኖር ቻይና ቀለበት መንገድን ሲሰራ ከተፈጠረው የስራ እድል ውጪ አዳችም ህይወቱን የሚደጉምበት የኑሮ መሰረት ያልታሰበለት ነበር፡፡ ይሄ የሶስት መንግሥት ድምር ውጤት ዛሬ “ቆሼ ተደርምሶ ወገኖቻችን አለቁ” ለሚለው መራር ዜና አበቃን በማለት የትውልድ ስፍራው ዘነበ ወርቅ አካባቢ የሆነው፣ የድሬ ቲዩቡ ሔኖክ ስዩም ማስነበቡ የሚታወስ ነው፡፡ እንግዲህ፣ እያወራንለት ያለው አጅሬ ቆሻሻ መጠነ ጥፋቱ ታሪካዊና እዚህ ድረስ ነው ማለት ነው።
ቆሼ በወቅቱም “ወይ ቆሼ ምግባችንም ሞታችንም አንተው ትሆን” ተብሎለት በነበረው ስፍራ ላይ የደረሰው አሳዛኝ እልቂት ምክንያቱ የቆሻሻ ተራራ መናድ መሆኑ ቢታወቅም ለቆሻሻው ተራራ መናድ ምክንያቱ ምን እንደ ሆነ ግን በወቅቱ ግልፅ የሆነና በህጋዊ ምንጭነት ሊጠቀስ የሚችል መልስ የተሰጠበት አጋጣሚ አልነበረም።
በወቅቱ “በአደጋው የሞቱ ሰዎች ቁጥር ዛሬም 113 እንደሆነና ፍለጋውም እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ የአደጋውን መንስዔ እስከዛሬ ማወቅ እንዳልተቻለ ገልፀው ይሔንን የሚያጣራ እና የሚያጠና ቡድን ከሀገርና ከውጭ ሀገር ባለሙያዎች” መዋቀሩን የከተማው መስተዳድር ቢነግረንም ምን ላይ እንደ ደረሰ እስካሁን ያወቅነው ምንም ነገር የለም።
ይህ እንግዲህ የቆሻሻ እና የእኛን ታሪካዊ ዝምድና የኋሊት ለማስታወስ የተደረገ መንደርደር ሲሆን ወደ አሁናችን ስንመጣ ደግሞ የሚከተለውን እናገኛለን። የዛሬዋ ኢትዮጵያ፣ በተለይም ከተሞቿ ከወትሮው ለየት ከሚሉባትና “ይበል” ከሚያሰኙ ተግባራት መካከል የፅዳት ስራዎች ይገኙበታል።
መንግሥት ጥሩ ስራ ሰርቷል ካልን ልንጠቅስለት ከሚገቡት ተግባራቱ መካከል የአካባቢ ፅዳት ስራዎችን ባለቤት ኖሯቸው እንዲሰሩ ማድረጉ ይመስለኛል። አዎ፣ ዛሬ በየትኛውም የአዲስ አበባ አካባቢ፣ ሰፈርና መንደር በፅዳት ሰራተኞች አማካኝነት የፅዳት ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። ድሮ እዛና እዚህ በተቀመጡ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳዎች አማካኝነት ብቻ ይሰበሰብና ወደ ቆሼ ይጣል የነበረው የመዲናዋ ቆሻሻ ዛሬ በየመንደርና ሰፈሩ እለት በእለት እየተጠረገ፣ በማዳበሪያም እየተሰበሰበና እየተሞላ ወደ’ሚሄድበት እየሄደ ይገኛል። የግሉ ዘርፍ ተሰማርቶ ቆሻሾችን ሲያነሳ እየተመለከትን ነው። አስፓልቶች እየተጠረጉ ናቸው። ችግር ያለው ግን ሌላ ነገር ነው።
ከላይ ያልነው እንዳለ ሆኖ ችግር የሚለው ነገር የፅዳት ሰራተኞች ቤት ለቤት እየሄዱ፣ በር እያንኳኩ “የቆሻሻ ያለህ” በሚሉበት በዚህ ዘመን፣ ሰፈርና አካባቢያችንን እናፅዳ ተብሎ ወደ ስራ በተወጣበት በዚህ ወቅት፣ የመንግስት በጀት ተመድቦና የሰው ኃይል ተሰማርቶ ቆሻሻ ከየአካባቢው በሚመነጥርበት በአሁኑ ሰአት፤ የግል ባለሀብቶች ሳይቀሩ በፅዳት ስራዎች ላይ ኢንቨስት ማድረግ በጀመሩበት 21ኛ ክፍለ ዘመን የቤትና የአካባቢ ቆሻሾችን በእነዚህ አካላት አማካኝነት ማስወገድ ሲገባቸው በየቱቦውና መንገዱ፣ የፅዳት ሰራተኞች ከሄዱ በኋላ በያገኙበት የሚጥሉ ሰዎች የመኖራቸው ጉዳይ ነው።
ጉዳዩን ጥያቄያዊ እናድርገውና ለምንድን ነው ሰዎች በየቱቦው፣ በየመንገዱ፣ በየአጥሩ . . . ላይ ቆሻሻ የሚጥሉትና አካባቢያቸውን ላልተፈለገ ጉስቁልና የሚዳርጉት? ለምንድን ነው በማዳበሪያ አድርገው ለፅዳት ሰራተኞች ምቹ አድርገው በመጠበቅ አካባቢያቸውን ደህንነቱ የተጠበቀ የመኖሪያ ስፍራ የማያደርጉት? የምን ልክፍት ነው? ሳይቸግር ጤፍ ብድር ውስጥ በመግባት ለጤና ጠንቅ በሆኑ ተግባራት ላይ የሚጠመዱት? ብለን ብንጠይቅ የምናገኘው መልስ ምን ይሆን?
ይህንን አባባል መሬት አውርዶ ለማየት ከተፈለገ ትንሽ ዝናብ ጠብ ሲል የአዲስ አበባ መንገዶችን ማየት ነው። ጎርፍ አግተልትሎ የሚያወጣው የቆሻሻ አይነት አለን? የፌስታል፣ የጫት እንጨቱ፣ የሀይላንድ (ፕላስቲክ ጠርሙሱ) መአት ተቆጥሮ ያልቃል? ምን የማይታይ የቆሻሻ አይነት (ኦርጋኒኩም (ከህያዋን የመጡ ለምሳሌ – ቅጠሎች፣ ቅርንጫፎች፣ የፍራፍሬ እና የእንቁላል ቅርፊቶች፣ የእንስሳት አጥንቶች፣ ወዘተ)፣ ኦርጋኒክ ያልሆነውም አለ? ምንስ አይነት የማይለቀቅ ሽንት ቤት አለ? ምንም የለም።
ሌላስ?
ሌላ ጉድ (ጉድ የሚገልፀው ከሆነ) ለማየት የሚፈልግ ካለ በአካባቢው ከሚገኝ አንድ ትንሽ ዘለግ ያለ ፎቅ ይፈልግና እዛ ላይ ወጥቶ ቁልቁል ይመልከት። በቃ፣ መሬት ላይ የድንጋይ እጥረት የተፈጠረበት ምክንያት እስኪገለፅለት ድረስ የእኛና የቆሻሻ ታሪካዊ ትስስር እስከበቃው ይወጣለታል። ለመሆኑ፣ ጣሪያችን ቆርቆሮ ነው፣ ወይስ ቆሻሻና ድንጋይ??
የዚህ ሁሉ ችግር ዋናው መዘዝ ግዴለሽነትና ከቆሻሻ ጋር አብሮ የመኖር ልምድ መኖር ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው። ባይሆን ኖሮ የፅዳት ሰራተኞች በየ በር ላይ እየመጡ “የቆሻሻ ያለህ”፣ “ቆሻሻ አውጡ” ሲሉ አውጥቶ ለእነሱ ማስረከብ ባልከበደም ነበር። ቆሻሻውን ወስዶ በየመንገዱ ዳር ዳር እተቀመጡት ማዳበሪያዎች ውስጥ መክተት ባላስቸገረም ነበር። ሌላው ሁሉ ቢቀር እንኳን ለፅዳት ሰራተኞቹ ምቹ የሆኑ ቦታዎች ላይ ወስዶ ማስቀመጥም እንደ ነውር ባልተቆጠረም ነበር።
“ሁሉም ሰፈሩን ቢያፀዳ ፓሪስ በአንድ ቀን ትፀዳ ነበር” የሚለው እድሜ ጠገብ አባባል ለአዲስ አበባም ሆነ ሌሎች ከተሞች ይሰራል እኮ። በፓሪስ አስታኮ ተነገረ እንጂ አገልግሎቱ ሁሉንም ማስተማር ነው። ሁሉም ከተሞች ፅድት ብለው ማየት ነው። ከተሞች ሁሉ ለሰው ልጆች ጤናና አጠቃላይ ህይወት ምቹ ይሆኑ ዘንድ መሻት ነው። ስለዚህ ለፓሪስ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ይሰራልና ሁሉም ሰፈሩን ቢያፀዳ . . .
ዛሬ ስልጣኔ ከሚለካባቸው ጉዳዮች አንዱ ፅዳት ነው። ፅድት ያለ አካባቢ የመኖር መብትም የሰዎች የሰብአዊ መብት አካል ከሆነም ቆይቷል። ባይሆን ኖሮ ደቡብ አፍሪካዊቷ ኬፕታዎን ከአህጉሪቷ ፅድት ያለች ከተማ ተብላ 1ኛ ባልወጣች፤ የታንዛኒያዋ ስቶን ታዎን (Stone Town)ም ባልተከተለች፤ የሞሮኮዋ ማራካሽም ባልሰለሰች ነበር። እነዚህና ሌሎች የአፍሪካ ከተሞች ይህንን ማእረግ ሊጎናፀፉ የቻሉት በነዋሪዎቻቸው አፍቃሬ ፅዳትና ስራዎቻቸው አማካኝነት ነውና አዲስ አበባ ለዚህ የምትታደልበትን ዘመን መናፍቅ እንደማያሰኝ ከወዲሁ መናገር ይቻላል።
ሳይንሳዊ አወጋገድ
እስካሁን ያወራነው ስለ ቀላሉና ማንኛችንም ልናደርገው ስለምንችለው የቆሻሻ አወጋገድ ስርአትና የአካባቢ ንፅህና አጠባበቅ ዘዴ ሲሆን፣ ሳይንሳዊውን ስንመለከት ደግሞ የሚከተለው ሆኖ እናገኘዋለን።
ቀደም ሲል ጠቃሚ ሕይወታቸውን ያገኙ እና ዓላማቸውን ያሟሉ ምርቶች፤ ወይም ቅሪቶች የሚሄዱባቸው በርካታ መንገዶች አሏቸው፡፡ የመጀመሪያው ለመቅበር ወደ ቆሻሻ መጣያ ቦታ መሄድ ነው፡፡ ሁለተኛው የድምፅ መጠን መያዙን ለማቆም በማቃጠያ መሳሪያ ውስጥ መቃጠል ሲሆን የመጨረሻው ደግሞ በምርቶቹ የሕይወት ዑደት ውስጥ እንደገና እንዲካተት፤ እንደገና ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል፡፡ ከዚህ አኳያ የአገራት ልምድ ምን ይመስላል?
“የዲ.ሲ. የህዝብ አገልግሎት ሥራዎች መምሪያ (DPW) የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ አስተዳደር ቆሻሻ እና ሪሳይክል የሚደረጉ ስብስቦችን፣ የንጽህና አጠባበቅ ትምህርትና አፈጻጸሞች፣ ያረጁ ምልክቶችን ማስወገድ፣ የህዝብ ቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች፣ የረገፉ ቅጠላ ቅጠሎችን መሰብሰብ እና የውስጥ መንገድና አስፋልት ጠረጋዎችን የሚያካትቱ ስራዎችን በየቀኑ የሚያከናውን” መሆኑን “ለጠቅላላ እውቀት”ና ልምድ ልውውጥ በማሰብ እዚህ ልንጠቅሰው ወደድን። በጃን. 13 2023 የተለቀቀ ጥናት በፕላስቲክ ቆሻሻ አስተዳደር በpay-to-dispose rubbish policy የምትመራው.ስዊዘርላንድ ከአለም 1ኛ መውጣቷን ማስነበቡንም እንደዛው። ቸር እንሰንብት!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5/2015