በ1960ዎቹ መባቻ የታተሙ ጋዜጦች ከዚህ ዘመን ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ናቸው። ለዛሬ ከመርጠናቸው ዘገባዎች መካከል በወቅቱ በማንአለብኝነት ሕግን የጣሰ ባለሥልጣን በገንዘብ ሲቀጣ፤ በአዲስ አበባ ዕድሮች ስለልማትና ስለ አካባቢ ፀጥታ መወያየታቸውና ሌሎችም ወጣ ያሉ ርዕሰ ጉዳዮች የያዙ ናቸው፡፡
ሕፃኑ ብረት ውጦ ሞተ
አዲስ አበባ፤ (ኢ-ዜ-አ) መስፍን ቸርነት የተባለ የ፭ ዓመት ሕፃን መስፍን ፳፫ ቀን ፲፱፻፷ አንዲት ቀለህ የምትመስል ብረት ውጦ መስከረም ፳፬ ቀን ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሆስፒታል ዶክተር ማይክ ኢቫኖቪች ኦፕራሲዮን ሲያደርጉት ሞተ፡፡
መስከረም ፳፫ ቀን ረቡዕ ከሰዓት በኋላ ‹‹ልጅዎ አንድ የፍሉቨር ቀለህ የሚመስል ብረት ውጧል ብለው ለአቶ ቸርነት እንደነገሩዋቸው፡፡ አቶ ቸርነት ወዲያውኑ ደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል ወስደው ሕፃኑን አስመረመሩት፡፡ የሆስፒታሉም ሠራተኞች ኤክስሬይ አንስተው የኤክስሬይ ፊልም በማሳየት ‹‹አንድ ድብልብል ነገር በሳምባው አጠገብ በሚገኘው ሥጋ ላይ ተለጥፏል አሏቸው፡፡ አባትየው ሕፃኑን በዚያኑ ዕለት ወደ ቀዳማዊ ኃለሥላሴ ሆስፒታል ወሰዱት፡፡
ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሆስፒታልም በድጋሚ ሕፃኑን ራጅ አንስተው ከላይ የተጠቀሰው ብረት በቀኝ ሳምባው በ፪ኛው ክፍል ላይ ተለጥፏል፡፡ እዚሁ አድሮ ነገ ኦፕራሲዮን እናደርገዋን በማለት ልጁን እዛው አሳደሩት በነጋታው መስከረም ፳፬ ቀን ሐሙስ ወደ ፭ ሰዓት ገደማ የአንገት በላይ ልዩ ዶክተር ማይክ ኢቫኖቪች ኦፕራሲዮን ካደረጉት በኋላ ሕፃኑ ሞተ፡፡
ወላጆቹ ሕፃኑ ኦፕራሲዮን እንዲሆን ሳይፈቅዱ በመቀደዱ በብርቱ ተቃውመዋል፡፡ ከዚህም በቀር ራጅ በታየ በማግስቱ ኦፕራሲዮን በመሆኑ ይህ አደጋ ሊደርስበት ቻለ በማለት ወላጆቹ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም አስረጂ የሚሆነን መጀመሪያ የመጣው ከችግሩ እንዲወገድ ነው፡፡ ይህ ሕፃን ቀለህ የሚመስል ብረት ውጧል፡፡ በኦፕራሲዮኑም የዋጠውን ብረት ዐይቻለሁ ፡፡ ቤተሰቦቹ ስለኦፕራሲዮኑ ባይፈርሙም ተግባብተናል፡፡ ዳሩ ግን በእኛ በኩል ችግር አለብን ፡፡ ይህም ማለት ለሕፃናት ኦፕራሲዮን በሚረዱ መሣሪያዎች በኩል ሆስፒታሉ የተሟላ አይደለም፡፡ ካሉ በኋላ ›› ባለን መሣሪያ ለመጠቀም ሞክሬ ነበረ፡፡ ዳሩ ግን የሕፃኑ ሕዋሳቶች ቀዳዳቸው ጠባብ ስለነበር መንጠቆው የተዋጠውን ብረት አልደረሰበትም ፡፡ በአጭሩ ለሕፃኑ ሞት ምክንያት ይህ ነው፡፡
ይሁንና በተቻለን መጠን ለማውጣት በሙከራ ላይ ሳለሁ የቀኝ ሳምባው ውስጣዊ ስሮች ፈነዱ በውስጡ የተቋጠረው አየር ወጥቶ ሳምባው ተጣበቀ፡፡ አየር እንዲያገኝ ቀዳዳ ባበጅለትም የሕፃን ሕዋሳት ከመሆኑ የተነሳ ሊቀበል ስላልቻለ ወዲያውኑ ሕይወቱ አለፈ፡፡›› ብለዋል፡፡
(መስከረም 27 ቀን 1960 ዓም የታተመው አዲስ ዘመን)
በጠላት ጊዜ የተጣለ ቦምብ በደብረ ማርቆስ ተገኘ
ደብረ ማርቆስ /ኢ.ዜ.አ/ በደብረ ማርቆስ ከተማ ውስጥ በጠላት ዘመን የተቀበረ አንድ የኤሮፕላን ፈንጂ ቦምብ ተገኝቷል፡፡ ቦምቡ የተገኘው ወደ ጥምቀተ ባህር የሚወስደው መንገድ ቦይ ሲቆፈር አፈሩ በወሀ ኃይል ከታጠበ በኋላ መሆኑ ታውቋል፡፡
ይህ አሁን የተገኘው ቦምብ ዓይነት ጠላት ከአኤሮፕላን ይሰደው የነበረ ዓነት መሆኑ ይነገራል። የአካባቢው ሰዎች እንደተናሩት ከሆነ በጠላት ወረራ ጊዜ ሁለት ቦምቦች በሰፈሩ ሲጣሉ አንደኛው ስለፈነዳ ጥቂት ቤቶች አቃጥሏል ይባላል፡፡ ይህ ሁለተኛው ቦምብ ግን ባመፈንዳቱ ለብዙ ዘመን በግልጥ ሲታይ ቆይቶ ባለመፈንዳቱ በአፈር ተሸፍኗል በማለት የአካባቢው ኗሪዎች ተናግረዋል፡፡
(ጥቅምት 6 ቀን 1960 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን)
ከወንጀለኞች የተገኘች አህያ በመጫናቸው ፫፻ ብር ተቀጡ
አሰላ /ኢ.ዜ.አ/ በአርባ ጉጉ አውራጃ የጉና ወረዳ ገዥ አቶ አድማሱ አበበ ከወንጀለኛ እጅ ተያዘችውን አህያ በገዛ ሥልጣናቸው እየጫኑ ስለተጠቀሙባት ፫፻ ብር እንዲቀጡ ተፈረዶባቸዋል፡፡
አቶ አድማሱ የወረዳውን ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ካለመቀበላቸውም በላይ ሊሠሩበት ከተፈቀደላቸው ሥልጣን ዘልለው በአህያይቱ ጉልበት ሲጠቀሙ መቆየታቸው ተገልጧል፡፡
ከዚህም ሌላ አቶ አድማሱ አህያይቱ ከአንድ ወንጀለኛ በፍርድ የተያዘች መሆኗን እያወቁ በኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በቁጥር ፬፻፳ እና ፬፻፵፪ የተደነገገውን ተላልፈዋል፡፡
በአህያዋ ጉልበት የተጠቀሙት የወረዳው ገዥ አቶ አድማሱ አበበ አርባ ጉጉ አውራጃ ፍርድ ቤት ተከሰው ከቀረቡ በኋላ ፫፻ ብር መቀጫ እንዲከፍሉ ፍርድ ቤቱ መወሰኑን የአውራጃው ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ድፋባቸው በንቲ ገለጡ፡፡ (ጥቅምት 6 ቀን 1960 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን)
የዕድር ወኪሎች ስለልማትና ፀጥታ ተወያዩ
አዲስ አበባ ኢ.ወ.ም/ በመስፍነ ሐረርና በአርበኞች መንገድ መካከል ለሚገኙ ፭ ሺህ ዕድርተኞች የተወከሉ የሰፈር ሽማግሌዎች ጳጉሜ ፭ ቀን እሁድ ከጧቱ ፫ ሰዓት በወይዘሮ ቀለመወርቅ ትምህርት ቤት ጠቅላላ ስብሰባ አድርገው ፤ስለሠፈራቸው ልማትና ፀጥታ ጥበቃ ተወያይተዋል፡፡
በስብሰባውም ላይ የአካባቢው ሠፈረተኞች ፤ የ፯ ዕድር አጠቃላይ ፕሬዚዳንት አቶ አማረ ሙላት በሠፈሩ ውስጥ የሚገጥመው የማኅበራዊ ኑሮ ችግር የሚወገድበትን የሠፈሩ አዛውንቶች በኅብረት ማስወገድ ያለባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ቀትሎም የዕድሮቹ ምክትል ፕሬዚዳት አቶ ፍስሐ ሀብተ ሥላሴ የአካባቢው ሕዝብ በኅብረት በመሥራት የቀበሌውን ንጽህናና ፀጥታ መጠበቅ ያለበት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በቀበሌው ሕዝብ በኩል ተወክለው የመጡት ሽማግሌዎቹም በየተራ ንግግር አድርገዋል፡፡ እንዲሁም የአካባቢው ንጽህናና ፀጥታ የሚጠበቅበትን በተለይም ለበዓሉ ሰሞን ያለፈቃድ ያልተመረመሩ ከብቶች እንዳይታረዱ ምክርና ማስጠንቀቂያ የሚሰጡ መሆናቸውን ተወያይተዋል፡፡
(መስከረም 1 ቀን 1960 ከወጣው አዲስ ዘመን)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2015