አዛውንቱ ዕድሜያቸው እየገፋ ነው። ከጥቂት ጊዚያት ወዲህ ደግሞ ድካምና ህመም ያንገላታቸው ይዟል። በእርጅና ምክንያት ቤት መዋል ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። ሁሌም ገና በጠዋቱ በሞት ያጧቸውን ሚስታቸውን እያሰቡ ይተክዛሉ። የዛሬን አያድርገውና በትዳራቸው ደስተኛ ሆነው ዓመታትን ዘልቀዋል። ባለቤታቸው ስድስት ህጻናት ልጆችን ትተው ባለፉ ጊዜ ግን ውስጣቸው በሐዘን ተጎዳ። አቶ መሀመድ ሌላ ትዳር መያዝ አላሰኛቸውም። ዓመታትን በብቸኝነት እየገፉ የሙት ልጆችን በጥንካሬ አሳደጉ።
አቶ መሀመድ ኑር እያደር በሐዘን የተሰበረ ልባቸው አገገመ። በልጆቻቸው ማደግና ቁምነገር መድረስም ደስተኛ መሆን ጀመሩ። ትዳር የያዙትን፣ ውጭ የሄዱትን፣ ሥራ የፈቱትን በእኩል እያዩ በሰላም ወጥተው መመለሳቸውን ተመኙ። እርሳቸው ሁሌም ለልጆቻቸው መልካም አባት ስለመሆናቸው የሚያውቋቸው ሁሉ ይመሰክራሉ። በተለይ ደግሞ ለትንሹና የመጨረሻው ልጃቸው ያሲን የተለየ ስሜት ይታይባቸዋል። ያሲን እናቱ ሲሞቱ ገና ጨቅላ ስለነበር የአባቱ ዐይኖች በተለየ ስስት ይቃኙታል። አቶ መሀመድ ሁሌም ካጠገባቸው እንዲርቅ አይፈልጉም።
ያሲን ማለት ለእርሳቸው የሙት ሚስታቸው የመጨረሻ ማስታወሻ ነው። በእርሱ ማንነት ውስጥ የቀድሞ ህይወታቸውን ያዩታል። በያሲን ልጅነት የልጅነት ትዳራቸውን ያስቡታል። እርሱ ፈጽሞ እንዲከፋና እንዲተክዝ አይሹም። አቶ መሀመድ አሁን ሰማንያ ዘጠኝ ዓመት ሆኗቸዋል። ይህ እድሜ ለእርሳቸው የማረፊያና የመጦሪያ ጊዜያቸው ነው። ሴቷ ልጃቸው በትዳር፣ ሌሎች ደግሞ በሥራ ምክንያት አብረዋቸው የሉም። ያሲን ግን እንደእርሳቸው ፍላጎት ሆኖ ዛሬም ከጎናቸው አልተለየም። በልጅነቱም ሆነ አሁን ከጎናቸው ባለመራቁ ደስተኛ ናቸው። ትዳር ይዞም ቢሆን አብሯቸው መኖሩና ወንድ ልጅ አሳቅፎ የልጅ ልጅ ማሳየቱ ሁሌም ያኮራቸዋል።
ያሲን በአባቱ ቤት መኖሩ ህይወትን አቅልሎለታል። እንደሌሎች እኩዮቹ ትዳር ሲይዝ በኪራይ ቤት አልተንገላታም። ባሻው ጊዜ ከፍቶ የሚገባበት ጎጆ አላጣምና ሚስትና ልጁን ይዞ በነጻነት ይኖራል። ይህ መሆኑ ለሽማግሌው አባቱ ደስታ መፍጠር ከጀመረ ሰንብቷል። አሁን ሁሌም የልጅ ልጃቸውን ራስ እየዳሰሱ፣ በሳቅና ለቅሶው ይመሰጣሉ። የጨቅላው ትንፋሽ ብርታታቸው ሆኗል። በእርሱ መኖር ህይወታቸው ይታደሳል። በእድሜያቸው ማምሻ ስላገኙት ጸጋም ፈጣሪያቸውን ደጋግመው ያመሰግናሉ። ያሲን እናቱን በልጅነቱ ቢያጣም የትምህርት ዕድል አልተነፈገውም። አባቱ እንደ እድሜ እኩዮቹ ሁሉ የፍላጎቱን አሟልተው አሳድገውታል።
የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በአግባቡ ተምሮ ሲያጠናቅቅ አባት በልጃቸው ተምሮ መለወጥ ተስፋ አደረጉ። ከፍ ሲል ግን የነበረው ጥንካሬ ሳስቶ መዋያው ካልባሌ ቦታ ሆነ። አስረኛ ክፍል ሲደርስ ደግሞ ትምህርቱን ከነአካቴው ትቶ መኪና መንዳት ተመኘ። ይህን ሙያ ሲያስብ የመጀመሪያ ዓለማው የታክሲ ሾፌር መሆን ነበር። በወቅቱ ጥሩ ገቢ ስለነበረው ደስተኛ ሆነ። ከጫትና ሲጋራው ተላምዶ ያሻውን ለማድረግም አጋጣሚውን አገኘ። የታክሲ ሥራው ጥሩ ገቢ ሲያስጨብጠው ኪሱን በገንዘብ አረጠበ። ይህኔ እንደአቅሙ የያዘውን ቆጥቦ እንደእኩዮቹ ለመታየት ሞከረ። እንዲህ መሆኑ ደግሞ የግራ ጉኑን እንዲያገኝና ጎጆ እንዲቀልስ ምክንያት ሆነው።
ሚስቱን ይዞበትዳር ለመኖር ባሰበ ጊዜም አዛውንት አባቱ አላሳፈሩትም። በእርሱ ቁምነገር መድረስ ተደስተው ከነሚስቱ ቤቱን «እነሆ» ሲሉ ፈቀዱለት። ያሲን ትዳር በያዘ ማግስት ታላቅ ወንድሙ ወደ ሳዑዲ ሊጓዝ ተሰናዳ። እሱም ለጉዞው የአቅሙን አበድሮና ለቪዛው የጎደለውን አሟልቶ ሸኘው። ወንድም ካሰበው ሲደርስ የያሲንን ውለታ አልዘነጋም። በኑሮ ሲደላደልም የቤቱን ጎዶሎ እየሞላ የአባቱን ምርቃት አገኘ። ያሲን ወንድሙ ሳዑዲ ሄዶ ሥራ ከጀመረ በኋላ ገንዘብ እንደላከለት ያውቃል። ይህ መሆኑ ብቻ ግን ለእርሱ በቂ ሆኖ አልተገኘም። ሁሌ እንደሚለውም የተበደረውን በሙሉ ጨርሶ አልከፈለውም። ይህንንም በየጊዜው በደወለ ቁጥር እያስታወሰ እንዲመልስለት ነግሮታል። ወንደሙም እሱ ዘንድ ምንም ቀሪ ገንዘብ እንደሌለው በማስረጃዎች እያጣቀሰ ሲገልጽለት ቆይቷል። በአንድ ወቅት ያሲን መተዳደሪያው ከነበረው የታክሲ ሥራ ድንገት ተሰናበተ። እንዲህ መሆኑ ደግሞ በቂ ገንዘብ ላልያዘው ወጣት ከባድ ፈተና ሆነ። የእርሱን እጅ አይተው የሚያድሩት ጨቅላ ልጁና ባለቤቱ መቸገራቸው አልቀረም። እንዲህ ሲሆን ግን አባት አልጨከኑም።
እርሱን ጨምሮ ሚስትና ልጁን ካላቸው ሁሉ እያካፈሉ፣ ከሚላክላቸው እየደጎሙ ክፉ ቀንን አሻገሩ። ወንድሙም ይህን በሰማ ጊዜ ለእጁ የሚበቃውን እየላከ የአቅሙን ሲረዳው ቆየ። አጋጣሚው ሰበብ የሆነለት ያሲን ግን በመጠጥ እየናወዘ ሰክሮ መግባትን ልምድ አደረገው። በሲጋራና በሺሻ ሱስ ራሱን ደብቆም የቤተሰቡን ሰላም ይነሳ ያዘ። ሁሌም ምሽት ሰክሮ በገባ ቁጥር ወንድሙ ተበድሮ አስቀረብኝ ስለሚለው ገንዘብ ያነሳሳል። ገንዘቡን ቢልክለት ከችግሩ መውጣት እንደሚችል እያሰበም ያማርራል።
መልሶ ሥራ ከጀመረም ወዲህ ይህን ጉዳይ በየምክንያቱ ማንሳቱን አልተወም። ያሲን እየተንገዳገደ ቤት ሲደርስ ከአልጋው ላይ የሚያያቸውን አባቱን መውቀስ ይጀምራል። ሁሌም የገንዝቡን ጉዳይ ከእርሳቸው ጋር አዛምዶም እንዲያስመልሱለት ያሳስባቸዋል። ውሎ አድሮ ጉዳዩን እንደ አዲስ አንስቶ ደጋግሞ ይጠይቃል። የአዛውንት አባቱ ምላሽ ግን ሁሌም ተመሳሳይና አንድ አይነት ነው። ገንዝቡ እንደሚመለስለት እያሳመኑ ማባበል። አሁን ያሲን ሥራ እየዋለ ቤተሰቡን ማስተዳደር ጀምሯል።
በቂ የሚባል ገቢ ቢኖረውም ሳውዲ ካለው ወንድሙ «ቀርቶብኛል» ስለሚለው ገንዘብ አልዘነጋም። ይህን ሲያስበ ደግሞ አሁንም አዛውንት አባቱን ተወቃሽ ያደርጋል። እሳቸው «መልስለት» ብለው ቢያዙት ወንድሙ እንደሚያደርገው እያሰበም ጥርሱን ይነክስባቸዋል። ይህ እልሁ ደግሞ በመጨቃ ጨቅ ብቻ አልቆመም። በሽማግሌው ላይ ቂም አሲይዞ ዛቻና ማስፈራራትን አስከተለ። አሁን የያሲን ባህርይ ከወትሮው ተለይቷል። ሰክሮ በገባ ቁጥር አዛውንቱን እየደበደበ «ገንዘቤን» እያለ መጮህ ጀምሯል።
አንዳንዴ ሽማግሌው ዱላው ሲበዛባቸው ወደጎረቤት ሸሽተው ይሄዳሉ። ነገሩን የረሳና የዘነጋው ሲመስላቸው ደግሞ ተመልሰው ይገባሉ። ይህን ጉዳይ የቅርብ ሰዎች ጭምር ጠንቅቀው ያውቁታል። አባት ግን ነገሩን ሸፋፍነው ምንም እንዳልተፈጠረ መናገርን ልምድ አድርገዋል ። ልጃቸው በየቀኑ እየደበደበ ቢያሰቃያቸውም ስለእርሱ ከማሰብና በስስት ከማየት በቀር በክፉ አይመልሱም። አንድ ጊዜ ደግሞ ከልጆቹ የመጀመሪያዋ በአባቷ ላይ ሰለሚለፈፀመው ድርጊት ሰምታ ከቤት ደረሰች።
ጉዳዩን ከጎረቤት በማጣራቷ ወንድሟን ከቤት ለማስወጣት ወስና ነበር። አባት ግን ይህንሲሰሙ «አይደረግም» ሲሉ ሞገቱ። ያሲን የመጨረሻ ልጅ በመሆኑ በስስት እንደሚያዩት ተናግረው ከቤት እንዳይወጣ ተከላከሉ። ልጃቸው በድብደባ ብዛት የቆሰለውን የአባቷን እግር ተመልክታ ወንድሟን በጥርጣሬ ጠየቀች። እሱ ግን የአልጋ ብረት እንደመታቸው ነግሮ ዋሻት። እሷም ያለምንም መፍትሄ እያዘነች ተመለሰች። ሳዑዲ ያለው ልጃቸው የአባቱን በደል ሰምቶ ጉዳዩን ከአንደበታቸው ለማጣራት ሞከረ።
አባት ግን የተባለው ሁሉ ውሸት መሆኑን ነግረው ሰላም መሆኑን መለሱለት። ያሲን ይህን በሰማ ጊዜ ለቀናት የተረጋጋ መሰለ። ውሎ አድሮ ግን የቀድሞው ባህሪይው አገርሽቶ አባቱን መደብደብ ቀጠለ። ወንድሙ አስቀርቶብኛል ስለሚለው ገንዘብ እርሳቸውን ተጠያቂ አድርጎም ያልበሉትን እንዲከፍሉ አሰቃያቸው። እሱ ዱላ ባነሳ ቁጥር የሸመገለ አካላቸው አያሳዝነውም። ድምጽ አልባ ጩኸታቸው አይረብሸውም። አዛውንቱ የሆዳቸውን ሀዘን በሚስጥር እንደያዙ ቀናትን በስቃይ ገፉ። ሁሌም ያሲን ለሚያቀርበው «ገንዘቤን አስመልስልኝ» ውትወታ ምላሻቸው ፈጽሞ አልተቀየረም። ዱላውን በይሁንታ እየተቀበሉ ስድቡን እንደልማድ ቆጥረው በዝምታ ሲብሰለሰሉ ቆዩ። አንዳንዴ በደላቸውን የሚያውቁ የቅርብ ጎረቤቶች ሊመክሯቸው ይሞክራሉ። እርሳቸው ግን በደላቸውን ውጠው ምንም እንዳልሆኑ ይመልሳሉ። በቤት ስልክ ሳዑዲ እየደወለ የሚጨቃጨቀው ያሲን ከአቅም በላይ አስወጥቷቸዋል። ነገሩን በሚስጥር ይዘውም ዕዳ ሲከፍሉ ቆይተዋል።
አሁን ያሲን በአዛውንት አባቱ ላይ የሚያሳርፈውን ዱላ አጥብቋል። በወጣ በገባ ቁጥር ጭቅጭቁ ብሶበታል። ምሽት ሰክሮ ሲገባ ያለምንም ገላጋይ ዱላውን ያነሳል። የተለመደውን ጥያቄ ሲያቀርብ ደግሞ ከእርሳቸው የሚያገኘው ተለምዷዊ ምላሽ ያበግነዋል። ይህኔ የጣለውን ዱላ እያነሳ ያለምንም ርህራሄ ይደበድባቸዋል። አባት የቆሰለ አካላቸውን እያሻሹ፣ የፈሰሰው እንባቸውን እያበሱ ስለነገው አዳራቸው ያስባሉ። ያም ሆኖ ግንማንም ስለሆነው ቢጠይቃቸው የልጃቸውን ክፉ አይናገሩም።
ሐምሌ 15 ቀን 2003 ዓ.ም ምሽቱ ገፍቷል። የሐምሌ ዝናብ ያስከተለው ቅዝቃዜ እንደቀጠለ ነው። የሰማንያ ዘጠኝ ዓመቱ አዛውንት ብርዱን ለመሸሽ ካልጋቸው ያረፉት ገና በጊዜ ነበር። እኩለሊቱ ተጋምሶ አካባቢው ጭር ቢልም ያሲን ወደቤቱ አልመጣም። ከለሊቱ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ግን የሽማግሌው በራፍ በከባድ ጡጫ ተንኳኳ። ማንነትቱን ጠንቅቃ ያወቀቸው ወይዘሮ ልጇን እንዳዘለች በሩን ተጣድፋ ከፈተች። ባለቤቷ ያሲን በስካር እየተንገዳገደ ከደጃፉ ቆሟል።
እሷን አልፎ ወደ ውስጥ እንደዘለቀ አባቱ ከአልጋቸው ጋደም ማለታቸውን አስተዋለ። ይህኔ ንዴቱ እንደገነፈለ ከዕንቅልፍ ቀሰቀሳቸው። በኑሮው መቸገሩን እያወሳም የተለመደውን ጥያቄ አነሳ። አባት በደከመ አንደበት «ልጄ እባክህ ገንዘቡን ይሰጥሀል » ሲሉ በትህትና መለሱለት። የሁልጊዜ ምላሻቸው እንዲህ መሆኑ ያበሸቀው። ያሲን በተኙበት መደብደቡን ቀጠለ። አባት እያለቀሱ እንዲተዋቸው ተማጸኑት። መስሚያ ጆሮ አልነበረውም። ጥቂት ቆይቶ ባለቤቱን ተጣራ። ባስቸኳይ ክብሪት እንድታመጣለትም ትዕዛዝ አስተላለፈ።
ሚስት የሚያደርገው ባይገባትም የተባለውን ላለመስጠት ከአይኑ ራቀች። እሱ ግን ወደመኝታ ቤት ዘልቆ በጄሪካን የተቀመጠውን ጋዝ ከፈተ። ወዲያው በወለሉና በአባቱ አካል እያርከፈከፈ ክብሪት ለኮሰበት። የጋዙ ሽታ ለአፍንጫዋ የደረሰው ሴት ተመልሳ ስትመጣ አቶ መሀመድ የለበሱት ቢጃማ በእሳት ተያይዞ እየጮሁ ደረሰች። አዛውንቱ ነፍስ ይዟቸው ወደሳሎኑ ሮጡ። ጠብቆ የተዘጋው በር ግን አልከፍት አላቸው። የእሳቱን በላያቸው መንደድ ያስተዋለችው ወይዘሮ ውሃ እየደፋች የድረሱልኝ ጩኸት አሰማች።
ጩኸቱን ሰምተው በግቢው የደረሱ ጎረቤቶች እሳቱን አይተው ሽማግሌውን ለመርዳት ፈጠኑ። በር ላይ ቆሞ የነበረው ያሲን ግን አልፈው እንዳይገቡ በእርግጫ እየመታ መለሳቸው።የእርሱን እርግጫ የተቋቋሙ ብርቱዎች በሩን አልፈው በሽማግሌው የሚነደውን እሳት ለማጥፋት ሞከሩ። ተጋግዘውም ወደጎረቤት አደረሷቸው። አቶ መሀመድ መላ ሰውነታቸው ተያይዞ ደም እየፈሰሳቸው «ልጄ አቃጠለኝ ውሃ፣ ውሃ ስጡኝ » እያሉ ነበር።
ሰዎቹ እርሳቸውን ተሸክመው ካወጡ በኋላ በቤቱ የነበረውን ቁሳቁስ ለማትረፍ ተረባረቡ። ጥቂት ቆይቶ ግን በርካታ ንብረት በእሳት ጋይቶ እንደወደመ አስተዋሉ። ለአስቸኳይ ህክምና የካቲት አስራሁለት ሆስፒታል የደረሱት አዛውንት በዕለቱ ተኝቶ የመታከም ዕድል አላገኙም። ጉዳታቸው ግን ውሎ የሚያሳድር አልነበረም። ወደ ባልቻ ሆስፒታል ተልከው ጥቂት ቀናትን በበዛ ጭንቀት አሳለፉ። ስቃያቸው የከፋ ህመማቸው የበረታ ሆነ። አቶ መሀመድ ከጥቂት ቀናት በኋላ ህይወታቸው ከማለፉ አስቀድሞ የሆነውን ሁሉ በቃላቸው አረጋገጡ። ታሪኩን የሰሙ የአብነት ሰፈር ነዋሪዎች ለልጃቸው የነበራቸውን ስስት እያስታወሰ በሬ ካራጁን ተረተ። ዝምተኝነታቸውንና ልጅ ለማሳደግ የከፈሉትን ዋጋ የሚያውቁም በደግነታቸው የተቀበሉትን ግፍና መከራ እያወሱ ከልብ ሲያዝኑ ከረሙ።
የፖሊስ ምርመራ በፖሊስ የምርመራ መዝገብ ቁጥር 047/04 የተከፈተው ፋይል ስለተፈፀመው የወንጀል ድርጊት ዕለታዊ ማስረጃዎችን ከትቧል። በመርማሪ ዋና ሳጂን ሰለሞን ወጋየሁ የሚመራው ቡድንም ከስፍራው ደርሶ ቴክኒካዊ ማስረጃዎችን ለይቷል።
በአካባቢው ያሉ ምስክሮችን ቃል በቃል አነጋግሮ በቂ ማስረጃዎችን ያሰፈረው ፖሊስ አቶ መሀመድ ከመሞታቸው በፊት ቃላቸውን ተቀብሎ የገዳይን ማንነት አረጋግጧል። በሟች የህክምና ውጤት የተገኘው መረጃም ግለሰቡ በደረሰባቸው ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ ምክንያት ለሞት መዳረጋቸውንና የነበረውን የጉዳት መጠን ለማወቅ ተችሏል። አሁን በበቂ ምስክሮች፣ በቴክኒካዊ ስልቶችና በህክምና ማስረጃዎች የተጠናከረው እማኝነት ለክስ በሚበቃ መልኩ ተደራጅቷል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 19/2011
መልካምሥራ አፈወርቅ