‹‹ስም ከመቃብር በላይ ይውላል›› የሚባለው ዝም ብሎ አባባል ብቻ አይደለም፡፡ የሚናገረው ትልቅ መልዕክት ስላለ ነው፡፡ ከመቃብር በላይ የሚውለው ስም ከመቃብር በታች የሆነውን ሥጋ ሕያው ያደርገዋል፡፡ ‹‹ጀግና አይሞትም!›› የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ጀግና አይሞትም ሲባል በሥጋ ቢያርፍም በሥራው ሕያው መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡ ሕያው ነው ማለት በሠራው ሥራ ሌሎችን ያሰራል ማለት ነው፡፡ የዓድዋ ጀግኖቻችን ዛሬ በሕይወት የሉም። ሥራዎቻቸው ግን ዛሬም የጀግንነት ወኔ እንዲኖር አድርገዋል፡፡
በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን በጀግንነታቸው ስማቸው ከመቃብር በላይ ሆኖ ሕያው ካደረጋቸው ጀግኖች የዚህ ሳምንት ክስተት የሆነውን እናስታውሳለን፡፡
ይህ ሳምንት አንድ ታላቅ ጀግና ያስታውሰናል። በፋሽስት ጣሊያን ወረራ ጊዜ የአገራቸውን ነፃነት ለማስጠበቅ የተዋጉና በኢትዮጵያ የአርበኝነት ታሪክ ውስጥ ደማቅ ስም ያላቸው ጀግና ናቸው፡፡ ለዚህም ጀግንነታቸው ‹‹የበጋው መብረቅ›› የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቷቸዋል፡፡ የበጋ መብረቅ ልዩ ክስተት እንደማለት ነው፡፡
እኚህ ጀግና ሌተናል ጀኔራል ጃገማ ኬሎ ናቸው። ያረፉት ከስድስት ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ.ም ነው፡፡
ሌተናል ጀኔራል ጃገማ ኬሎ የተወለዱት ጥር 21 ቀን 1913 ዓ.ም በቀድሞው አጠራር በጅባትና ሜጫ አውራጃ፣ በደንዲ ወረዳ ዮብዶ በተባለ ስፍራ ነው። አባታቸው ኬሎ ገሮ (አባ ጃገማ) የሕፃኑ ጃጋማ መወለድ እጅግ ከፍ ያለ ደስታ አሳደረባቸው፡፡ ‹‹ … ለሰባ ዓመታት ሙሉ የጠበቅሁት አንበሳ ይህ ነው … የፈረሴን ስም ሰጥቼዋለሁ›› ብለው ‹‹ጃገማ›› ብለው ስም እንዳወጡለት ይነገራል፡፡
ሕጻኑ ጃጋማ በተወለደ በዓመቱ እናቱ ወይዘሮ ደላንዱ በአካባቢው ተከስቶ በነበረ በሽታ ምክንያት በመሞታቸው በአክስቱና በሞግዚት እንዲያድግ አባቱ ወሰኑ፡፡ አክስቱም ጃገማን ከወንድሙ ጋር ፀበል አስጠምቀው፤ ቄስ ቀጥረው ዳዊት እንዲማር አደረጉ። በ1923 ዓ.ም ደግሞ አባቱ ኬሎ ገሮ (አባ ጃገማ) አረፉ፡፡
ጃገማ ገና በለጋ እድሜው ‹‹አባቱ የመረጠው›› እየተባለ ለዳኝነት መቀመጥን፣ ፈረስ ግልቢያን፣ ጦር ውርወራን፣ ምክክቶሽን፣ ጋሻ አነጋገብን፣ ረሀብንና ውሃ ጥምን መቋቋምን፣ ውሃ ዋናን … እየተማረ በጥሩ ስነ ምግባር አደገ፡፡ በልጅነት ዘመኑ ስለቅድመ አያቱ ጎዳና ነሞ የጀግንነት ታሪክ በተደጋጋሚ ስለሰማ እርሱም እንደቅድመ አያቱ ጀግና መሆንን ያልም ነበር፡፡
ፋሺስት ኢጣሊያ በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ስትወር ጃገማ ገና በ15 ዓመቱ አርበኛ ሆኖ የፋሺስትን ጦር ለመፋለም ወሰነ፡፡ ከአጎቱ ልጅ አሰፋ አባ ዶዮ ጋር ወደ ጫካ ገቡ፡፡ እህቱና ወንድሞቹም ተከተሉት። ገበሬዎች፣ ወታደሮች፣ ሾፌሮች … ከጃገማ ጋር ተቀላቀሉ፡፡ አሰፋ አባ ዶዮን ጨምሮ መጀመሪያ ከጃገማ ጋር ለአርበኝነት የወጡ ብዙ ወጣቶች በቤተሰቦቻቸው ተግሳፅ አማካኝነት ከጫካ ወጥተው ወደ መንደራቸው ቢመለሱም ጃገማ ከእርሱ በእድሜም ሆነ በሌሎች ነገሮች የሚበልጡ በርካታ ሰዎችን በስሩ ማሰለፍ ቻለ፡፡
የጃጋማ አባት በአካባቢው ዘንድ ይወደዱና ይከበሩ ስለነበር የአካባቢው ሕዝብ በታዳጊው ጃገማ የሚመሩትን አርበኞች በልዩ ልዩ መንገዶች ያግዝ ነበር፡፡ አርበኞቹም በፋሺስት ጦር ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመሰንዘር ጦሩን መፈተን ጀመሩ። ፋሺስቶች ጥይት የሚጭኑባቸውን እንስሳት በመምታት ፋሺስቶችና ባንዳዎች ሲሸሹ አርበኞቹ መሳሪያና ጥይት እየሰበሰቡ ማከማቸት ቀጠሉ። ጣሊያኖችም ጃገማንና ተከታዮቹን ለመደምሰስ ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም፡፡
አርበኞቹ በጊንጪና አካባቢው በነበረው የፋሺስት ጦር ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት በመሰንዘራቸው ጣሊያኖች በጊንጪና በአካባቢው ጠንካራ ምሽግ ሰርተውና ጦራቸውን ጠምደው ተቀመጡ፡፡ ሐሮታና ጀልዱ የነበረው የጠላት ጦር ግንኙነት ፈጥሮ ስለነበር አርበኞቹ መተላለፊያ መስመሩን ለመቁረጥ ጥቃት ሰነዘሩ፡፡ ከጥቃቱ ባገኙት መሳሪያም ትጥቃቸውን አጠናከሩ፡፡ የጃገማ ተከታዮች ቁጥራቸው ጨመረ፡፡ ፋሺስቶች ተጨማሪ ምሽጎችን ለመገንባት ቢያስቡም ቀድመው በገነቧቸው ምሽጎች ውስጥም እንደልባቸው መንቀሳቀስ ሳይችሉ ቀሩ፡፡ አርበኞቹ በሚያዝያ ወር 1931 ዓ.ም ሐሮታና ጀልዱ የነበረውን የጠላት ጦር ግንኙነት ለመበጣጠስ የወሰዷቸው እርምጃዎች አዲስ አበባ ድረስ ተሰሙ፤ ብዙ የነፃነት ተዋጊዎችም እነጃገማ ያሉበት ድረስ ሄደው ተቀላቀሉ፡፡
በጃገማ የሚመራው የአርበኞች ጦር ምዕራብ ሸዋ በነበረው የኢጣሊያ ጦር ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት በመክፈት ብዙ ጉዳቶችን አደረሰበት፡፡ አርበኞቹ ድንገተኛ ጥቃቶችን ሰንዝሮ በፍጥነት ከአካባቢው በመሰወር የጠላት ጦር ጥይት እንዲያባክን በማድረግ፣ የአካባቢው ሰው ከፋሺስት ወታደሮችና ከባንዳዎች ላይ ጥይት እንዲገዛ በማስተባበርና ጥይት በጫኑ እንስሳት ላይ ጥቃት ፈፅሞ ጥይቱን በመውሰድ የመሳሪያ ክምችታቸውን ያጠናክሩ ነበር፡፡
በጥቅምት ወር 1933 ዓ.ም ጃገማን ለማጥቃት ወደ ሰንጎታ ተራራ የሄደው 350 የፋሺስት ጦር ጃገማ በሚመራቸው 17 አርበኞች ተሸነፈ፡፡ የጃገማ አርበኞች ብዙ የጠላት ወታደሮችን ገደሉ፤ ባንዳዎች የዘረፉትን ንብረት አስመለሱ፤ወታደሮችንና መሳሪያ ማረኩ፡፡ የጃገማ ጀግንነትም እየገዘፈ ሄደ። የአካባቢው ሕዝብም የጃገማን ጀግንነት ከቅድመ አያቱ ጀግንነት ጋር እያነፃፀረ በማውራት በጠላት ጦር ካምፕ ውስጥ ፍርሃቱ እንዲጨምር አደረገ። ወደ ወሊሶ ሄዶ በአካባቢው ከፋሺስት ጦር ጋር ሲዋጉ ወደነበሩት ወደ ደጃዝማች ገረሱ ዘንድ ሄደ፡፡ የፋሺስት ጦር በደጃዝማች ገረሱ ላይ ውጊያ ከፍቶ ስለነበር ጃገማም በውጊያው ላይ ተሳትፎ የማታ ማታ ድሉ የአርበኞቹ ሆነ፡፡ ደጃዝማች ገረሱም ‹‹ … አንተን የመሰለ ጀግና የወለደች እናት ትባረክ …›› ብለው ጃገማን አመሰገኑት፡፡
ጃገማ በአንድ ውጊያ ላይ የማረከውን የኢጣሊያ ወታደር እንዳይገደል አድርጎ ስለአርበኞቹ ኃይል እንዲሁም ስለፋሺስቶች ፈሪነትና አረመኔነት ከነገረው በኋላ ‹‹ከምርኮኝነት ነፃ የምትወጣው ለጥይት መግዣ የሚሆነኝን 10 ሺህ ሊሬ ከከፈላችሁኝ ብቻ ነው›› አለው፡፡ በአንድ ኢጣሊያዊ መልዕክተኛ አማካኝነት ጃገማ 10 ሺህ ሊሬ ተቀብሎ ምርኮኛውን ፈታው፡፡ ምርኮኛውም ወደ ጦር ሰፈሩ ሄዶ ስለጃገማ ጀግንነት ለአለቆቹ ሲነግራቸው ደስ ባለመሰኘታቸው ወደ ሌላ ስፍራ አዛውረውታል፡፡
ጃገማ በአርበኝነት ዘመኑ ከፈጸማቸው አኩሪ ገድሎች መካከል የፋሺስት ጦር ይመካበት የነበረው የአዲስ ዓለም ምሽግ ሰበራ ፈፅሞ የሚዘነጋ አይደለም። ጃገማ ደጃዝማች ገረሱን ለመርዳት ወደ ወሊሶ ሄዶ በነበረበት ወቅት ‹‹ … ጃገማ ያን የተመካከርንበትን ጉዳይ ጨርሻለሁና ዛሬ ነገ ሳትል ሰራዊትህን ይዘህ ቶሎ ና …›› የሚል መልዕክት ከስመ ጥሯ የውስጥ አርበኛ ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ ደረሰው፡፡ ጃገማም በፍጥነት ወደ አዲስ ዓለም አቅንቶ የምሽግ ሰበራው የጦር አዝማች ሆነ፡፡ ጥቃቱን አፈፃፀም የሚያሳይ መመሪያ ለባልደረቦቹ አስረድቶ የሥምሪት ትዕዛዞችን ሰጠ፡፡ ራሱ ምሽጉ ውስጥ ገብቶ ቦምብና ሌሎች መሳሪያዎችን ይዘው የነበሩ የፋሺስት ጦር ባለስልጣናትን ገድሎ የመሳሪያ ዝርፊያው እንዲፈጸም አደረገ፤ እስረኞችንም አስፈታ፡፡ በዘመቻው ላይ ከአርበኞቹ ወገን የሞቱት ሁለት ሰዎች ብቻ ነበሩ። ከጠላት ወገን ግን ከ100 በላይ ጣሊያናውያንና ጠባቂዎቻቸው ተገድለዋል፡፡
በመጋቢት ወር 1933 ዓ.ም ጃገማ የጭልሞን ምሽግ ከቦ በፋሺስት ጦር ላይ ተኩስ ከፈተ። ‹‹እጃችሁን ካልሰጣችሁ አንላቀቅም!›› የሚል መልዕክትም አስተላለፈ፡፡ ‹‹እንደራደርና እጅ እንሰጣለን›› ካሉ በኋላ አዘናግተው ሊያመልጡ ሲሉ ከአርበኞቹ ተኩስ ተከፈተባቸውና 13 የኢጣሊያ ወታደሮችና አንድ ሺህ 500 ባንዳዎች ተማረኩ፡፡ ጊንጪ በጃገማ አርበኞች ቁጥጥር ስር ዋለች፡፡ ወዲያውኑም ጃገማ የኢጣሊያ ጦር የሚተማመንበት የሐሮታ ምሽግ ላይ ጥቃት እንዲከፈት አዘዘ፡፡ የጠላት ጦር አንድ ጊዜ እየሸሸ፤ ሌላ ጊዜ እያጠቃ መፋለሙን ቀጠለ፡፡ በዚህ ጊዜ ጃገማ ብቻውን ሆኖ ቦታ እየቀያየረ መድፍ ሲተኩስ የፋሺስት ጦር ተስፋ ቆርጦ ለመጨረሻ ጊዜ ሸሸ፤ ከሞት የተረፈውም ተማረከ፡፡ የጃገማ ጦር በድል አዲስ ዓለም ገባ፡፡ ሆለታንም በቁጥጥሩ ስር አደረገ።
ከግንቦት 1934 ዓ.ም ጀምሮ ሆለታ ገነት ጦር ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በመግባት የውትድርና ስልጠና አጠናቆ የሻለቃነት ማዕረግ አገኘ፡፡ ከዚያም ለጥቂት ጊዜያት ያህል በአምቦና በቢሾፍቱ ተመድቦ አገልግሏል፡፡ ከዚያም በአምባላጌና በራያ አዘቦ በግዳጅ አፈፃፀም ላይ ባሳየው ብቃት በሜጀር ጀኔራል አበበ ዳምጠው ተመስክሮለት ሻለቃ ጃገማ የብርጌድ አዛዥ ሆኖ ተሾመ፡፡
በ1947 ዓ.ም የሌተናንት ኮሎኔልነት ማዕረግን አገኘ፡፡ የዩጎዝላቪያ ፕሬዝደንት የነበሩት ማርሻል ቲቶ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት የተደረገላቸውን የክብር ሰልፍ የመሩት ሌተናንት ኮሎኔል ጃገማ ነበሩ፡፡
በ1953 ዓ.ም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ወቅት የመፈንቅለ መንግሥቱን ሙከራ ለማክሸፍ ለጥቃት የተንቀሳቀሰው ኃይል አዛዥ ሌተናንት ኮሎኔል ጃገማ ኬሎ ነበሩ፡፡ በ1958 ዓ.ም የሜጀር ጀኔራልነት ማዕረግን አግኝተዋል፡፡ በ1965 ዓ.ም ደግሞ የብሔራዊ ጦር አዛዥ ሆነው ተሹመዋል፡፡
በፈረስ ስማቸው ‹‹አባ ዳማ›› የሚባሉት፣ ሌተናንት ጀኔራል ጃገማ አንድ ወንድና አምስት ሴት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ ጀግናው ሌተናንት ጀኔራል ጃገማ ኬሎ መጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ.ም አርፈው፣ ሥርዓተ ቀብራቸው ልክ በዛሬዋ ቀን እና በዛሬዋ ዕለት እሑድ ሚያዝያ 1 ቀን 2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 1 ቀን 2015 ዓ.ም