ስደትን በአዎንታዊ ጎኑ ስንመለከት ከድህነት አረንቋ ለማውጣት የሚወሰድ እርምጃ ቢሆንም፣ በአሉታዊ ጎኖች ያመዝናሉ። ወጣቶች ተሰደው በሚኖሩበት አገር ከሚደርስባቸው አሉታዊ ገጽታዎች መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው።
በግለሰብ ደረጃ፣ ወጣት ስደተኞች ከሚያጋጥማቸው ተግዳሮቶች መካከል ለስነ-ልቦናዊና፣ ለአካላዊ፣ ስሜታዊና ለአእምሮአዊ ችግሮች ይዳረጋሉ፣ በኢኮኖሚያዊ ዘርፍ እንዲሁም፤ የሞራል ውድቀት፣ የዕዳ ቀውስ፣ የሥራ ጫና በተለይም በቋንቋ ችግር ምክንያት የበለጠ ለችግር ይዳረጋሉ።
ስደት በቤተሰብ ውስጥ መከፋፈልን ያመጣል። ምክንያቱም ወጣቶች ትዳር ከመሰረቱ በኋላ ለስደት በሚዳረጉበት ወቅት ቤተሰብ ላይ መከፋፈል ይፈጥራል፣ በተለይም በትዳር ውስጥ ውዝግብ ያስከትላል፣ እስከ መለያየት ሊያደርስ ይችላል፣ አልፎ ተርፎም ሕጻናትን ለአደጋ ያጋልጣል፣ ይህ በብዙ ቤተሰብ ውስጥ ትልቅ ፈተና ሆኖ የሚታይ ሀቂ ነው፣ ምክንያቱም የቤተሰብ ኑሮ ለማሻሻል ሲባል የተወሰደ እርምጃ ቢሆንም በቤተሰብ መካከል ክፍተት ይፈጥራል።
ሰላማዊ ማህበራዊ ግንኙነቶችን ለማዳበር እና ለመጠበቅ ሁሉም አባላት በውይይት የሚሳተፉበት ተለዋዋጭ መዋቅራዊ ሂደትን ይጠይቃል። ማህበራዊ ውህደት ቁሳዊ የሆኑ ነገሮች በሚፈጥሩት ልዩነት፣ በራስ ወዳድነት፣ አግባብ ባልሆነ የደሞዝ ክፍያ ምክንያት ተገድቦ በኅብረተሰቡ አኗኗሪ ዘይቤ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ይህ ቢሆንም እንኳን በድህነት ተቆራምዶ ከመተያየት ሞትም ቢሆን መድፈር ይሻላል ያሉቱ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ወደ መካከለኛው ምስራቅ ይሰደዳሉ። ከእነዚህ መካከልም መቅደስ ደረጄ የተባለችው ወጣት አንዷ ናት። መቅደስ እንደ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ስደትን ምርጫዋ አድርጋ ለመሄድ ከተነሳች ሰነባብታለች።
የመቅደስ የጉዞ እቅድ
ሳቂታ ናት፤ ፈገግታ ከፊቷ የማይጠፋ አይነት ወጣት። ለቤተሰቦቿ የመጀመሪያ ልጅ ስለነበረች እንደ ቤት መብራት የቤተሰቡን ህይወት የምታደምቅ አይነት ልጅ። ይች ወጣት ምንም ነገር አደርጋ ቤተሰቧን ማስደሰት፤ የቤተሰቧን ችግር መቅረፍን ህልሟ ለማሳካት በተቻለት አቅም በሙሉ መስራት ያለባትን ስራ በሙሉ ትሰራለች። ስራ ባትሰራም ገንዘቡ በምትፈልገው ልክ የቤተሰቧን ኑሮ መሻሻል ባለመቻሏ የተነሳ አረብ አገር ሄዳ የተሻለ ገቢ ለማግኘት ታቅዳለች።
በዚህም ምክንያት እቁብ መጣል ተጨማሪ ስራ መስራት ገንዘብ ከዚህም ከዚያም ማፈላለግ ትጀምራለች። በዚህ ወቅት ደረጄ የተባለ ግለሰብ ታገኛለች፤ የምትፈልገውን ገንዘብ እንደሚሞላላትም ይነግራታል፡፡ ይህንኑ ታሳቢ አድርጋም ደላላ ታፈላልጋለች፡፡ በዚህ መሀል ሮባ በሪሶ የሚባል በህጋዊ መንገድ ወደ ዱባይ ወደ ውጭ አገር ይልካል ከተባለ ሰው ጋር ትገናኛለች።
ሰውየውም በህጋዊ መንገድ ወደ ዱባይ እንደሚልካት ገልጾላት በመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም አዳማ ከተማ ፓስፖርት ፎቶግራፍ እና ለጤና ምርመራ ብሎ ብር 6ሺ ብር ተቀብሏት ቪዛው ሲመጣ 20 ሺ ብር ትከፍያለሽ በማለት ይለያታል። ጥቂት ጊዜ ቆይቶ ይደውልላትና ቪዛሽ መጥቷል ገንዘቡን ይዘሽ ነይ ይላታል። ወጣቷም ከምትኖርበት ጅማ ዞን ሊሙ ኮሳ ወረዳ ወዳጅ ዘመዶቿን ተሰናብታ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ትመጣለች።
አዲስ አበባ ጀሞ 01 አካባቢ ከደላላው ጋር ተገናኝተው ከሌላ እንደ እሷ አረብ አገር ለመሄድ ቪዛ መጣልሽ ከተባለች ሶፊያ ገበየሁ ከተሰኘች ልጅ ጋር ወደ አዳማ ከተማ ወደ ራሱ መኖሪያ ቤት ይልካቸዋል። ከዛ በኋላ ለሥራ የመላክ ፍቃድ ሳይኖራት ወደ ዱባይ አገር እልካችኋለሁ ከምትል በድሪያ ኡመሬ አሚኖ ጋር ይገናኛሉ። ሴትየዋ በህጋዊ መንገድ ወደ ዱባይ አገር እንደምትልካት በማረጋገጥ ስታገኛቸው ምንም ሳትጠራጠር በጥሬ ገንዘብ 19 ሺ ብር ለፕሮሰስ ማስጨረሻ የሚሆን ብላ መቅደስ ለበድሪያ ትሰጣታለች።
በድርያም ብርን ከተቀበለች በኋላ ከሌሎች እንደ መቅደስ አረብ አገር ለመሄድ ከተዘጋጁ ሌሎች ወጣቶች ጋር አንድ ላይ በማድረግ ከአዳማ ከተማ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ይዛቸው መጥታ የካ ክፍለ ከተማ ላምበረት መናኸሪያ አካባቢ ለጊዜው ካልተያዘው ኡስማን አሊ ከሚባል ግለሰብ ጋር በመሆን አልጋ እንዲይዙ ታደርጋታለች፡፡
ሆኖም በዚህ መሃል በቀን 03/09/2014 ዓ.ም በድርያ በፖሊስ በቁጥጥር ስር ትውላለች፡፡ በፈፀመችው በህገ-ወጥ መንገድ ሰውን ለስራ ወደ ውጭ አገር መላክ ሙከራ ወንጀል ተከሳለች፡፡ እነ መቅደስም በባበዶ ጉጉት የለፉበትንና ከወዳጅ ዘመድ ፈላልገው ያገኙትን ገንዘብ አስረክበው ችግር ላይ ወደቁ።
በድሪያ ዑመሬ አማኖ
በድሪያ ዑመሬ አማኖ ለዓመታት አረብ አገር ኖራ የመጣች ሴት ናት። በአረብ አገር ከሰው ቤት ስራ እስከ ሰራተኞችን እየተቀበሉ ሰው ቤት እስከ ማሰማራት ድረስ ሰርታለች። ወደ አገሯ ከተመለሰች በኋላም ለሥራ የመላክ ፍቃድ ሳይኖራት ሰዎችን በህገ ወጥ መንገድ መላክን ዋነኛ ስራዋ አድርጋ ይዛዋለች።
በዚህም በርካቶችን በመላከ የብዙ ወጣቶች ህይወት የባህር ሲሳይ እንዲሆን አድርጋለች። በለስ ቀንቷቸውም ዱባይ የደረሱቱ ያለፈቃድ በመሄዳቸው የተነሳ እንግልቱ በዝቶባቸው ሌት ከቀን ያነባሉ። በድሪያ ግን በሌሎች ሰቆቃ ገንዘብ ማግኘትን ስራዬ ብላ ተያይዛዋለች። በዚህም ተግባሯ ለሥራ የመላክ ፍቃድ ሳይኖራት ወደ ዱባይ አገር እልካችኋለሁ በማለት ከ9 ግለሰቦች ገንዘብ በመቀበሏ ልትያዝ ችላለች።
ከፍትህ ሚንስቴር ድረገፅ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ ሰውን ለሥራ ለመላክ ፍቃድ ሳይኖራት በህጋዊ መንገድ ወደ ዱባይ አገር እንደምትልካቸው በማረጋገጥ ካልተያዙ ግብረ-አበሮቿ ጋር በመሆን ከግል ከተበዳዮች ያለአግባብ ገንዘብ ተቀብለሻል በማለት ክስ ተመስርቶባታል።
የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ
የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ላይ እንደተመለከተው በድሪያ ዑመሬ አማኖ የተባለችው ተከሳሽ ለጊዜው ካልተያዙ ግብረ-አበሮቿ ሮባ በሪሶ እና ኡስማን አሊ ጋር በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በመላ ሃሳቧ፣ በወንጀሉ ድርጊት እና በሚሰጠው ውጤት ሙሉ ተካፋይ የሆነች ናት፡፡
ወደ ውጭ አገር ሰውን ለሥራ ለመላክ ፍቃድ ሳይኖራት የግል ተበዳይ መቅደስ ደረጄ የተባለችው ለስራ ወደ ውጭ አገር መሄድ ስለምትፈልግ ሮባ በሪሶ የሚባል የተከሳሽ ግብረ-አበር በህጋዊ መንገድ ወደ ዱባይ እንደሚልካት ገልጾላት በመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም አዳማ ከተማ ፓስፖርት ፎቶግራፍ እና ለጤና ምርመራ ብሎ ብር 6ሺ ብር ተቀብሏታል፡፡
ቪዛው ሲመጣ 20 ሺ ብር ትከፍያለሽ ካላት በኋላ፣ ደውሎላት ቪዛሽ መጥቷል ገንዘቡን ይዘሽ ነይ ባላት መሰረት ከምትኖርበት ጅማ ዞን ሊሙ ኮሳ ወረዳ ወደ አዲስ አበባ ከተማ የመጣችና አዲስ አበባ ጀሞ 01 አካባቢ ተገናኝተው ከግል ተበዳይ ሶፊያ ገበየሁ ጋር ወደ አዳማ ከተማ ወደ ራሱ መኖሪያ ቤት የላካቸው ሲሆን፣ በኋላ ተከሳሿ በህጋዊ መንገድ ወደ ዱባይ አገር እንደምትልካት በማረጋገጥ ከተበዳይ በጥሬ ገንዘብ 19 ሺ ብር ለፕሮሰስ ማስጨረሻ የሚሆን ብላ በመቀበል ከሌሎች ተበዳዮች ጋር አንድ ላይ በማድረግ ከአዳማ ከተማ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ይዛቸው መጥታ የካ ክፍለ ከተማ ላምበረት መናኸሪያ አካባቢ ለጊዜው ካልተያዘው ኡስማን አሊ ከሚባል ግለሰብ ጋር በመሆን አልጋ እንዲይዙ ካደረገች በኋላ ሳትልካት በቀን 03/09/2014 ዓ.ም በቁጥጥር ስር የዋለች በመሆኑ በፈፀመችው በህገ-ወጥ መንገድ ሰውን ለስራ ወደ ውጭ አገር መላክ ሙከራ ወንጀል ተከሳለች፡፡
እንዲሁም ዐቃቤ ህግ በተደራራቢነት ባቀረባቸው ሌሎች 8 ክሶች ተከሳሿ ለጊዜው ካልተያዙ ከላይ ከተጠቀሱት ግብራበሮቿ ጋር በመሆን ሰሚራ ከሚል፣ ሁሴን መሀመድ፣ አብዱ ግርማ፣ ሱልጣን ኮቴ እና አሽሩ ከድር የተባሉ ተበዳዮችን ለስራ ወደ ውጭ አገር መሄድ ስለሚፈልጉ ሮባ በሪሶ የሚባል የተከሳሽ ግብረ-አበር በህጋዊ መንገድ ወደ ዱባይ እንደሚልካቸው በመግለፅ በመጋቢትና ሚያዝያ ወር 2014 ዓ.ም ሮባ በሪሶ የተባለውም የሚቀበሏቸውን ግብረ-አበሮቹን ያልተያዘው ኡስማን አሊ እና ተከሳሿን ልኮላቸው እነሱም ከተለያየ ቦታ ተነስተው የመጡትን ተበዳዮች ተቀብለዋቸው የካ ክ/ከተማ ላምበረት መናኽሪያ አካባቢ ወደሚገኝ ስሙ ባልታወቀ አልጋ ቤት ይዘዋቸው በመሄድ ተከሳሿ እና ያልተያዙ ግብረ-አበሮችም በህጋዊ መንገድ ወደ ዱባይ እንደሚልኳቸው በማረጋገጥ ለፕሮሰስ ማስጨረሻ የሚሆን ከሁሴን መሀመድ እና ሱልጣን ኮቴ ከያንዳንዳቸው 25 ሺ ብር ስትቀበል፣ አብዱ ግርማ
ከተባለው የግል ተበዳይ 30 ሺ ብር፣ ከአሽሩ ከድር ከተባለችው 20 እንዲሁም ሰሚራ ከሚል ከተባለችው 21 ሺ ብር በጠየቋቸው መሰረት ለተከሳሿ የሰጧት ሲሆን ተከሳሿ ሳትልካቸው በቀን 03/09/2014 ዓ.ም በቁጥጥር ስር የዋለች በመሆኑ በፈፀመችው በህገ-ወጥ መንገድ ሰውን ለስራ ወደ ውጭ አገር በመላክ ሙከራ ወንጀል ዐቃቤ ህግ ክስ መስርቶባታል፡፡
ዐቃቤ ህግ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀፅ 27(1)፣ 32 (1) (ሀ)፣ (ለ) እና በሰው የመነገድ እና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ 1178/2012 አንቀፅ 11(1) ን መሰረት በማድረግ ነው ክስ ያቀረበባት።
ውሳኔ
በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 14ኛ ወንጀል ችሎት የቀረበችው ተከሳሽ የተከሰሰችበት ክስ በችሎት ተነቦላት የክስ መቃወሚያ የለኝም ጥፋተኛም አይደለሁም ያለች ሲሆን አቃቤ ህግም ተከሳሿ ክዳ የተከራከረች በመሆኑ በጉዳዩ ላይ የሚያስረዱ የህግ ምስክሮቻችን ስላሉ ይሰሙልኝ በማለት 9 የሰው ምስክሮችን አቅርቦ ያሰማ ሲሆን የአቃቤ ህግ ምስክሮችና ማስረጃዎችም በተከሳሿ ላይ በክሱ መሰረት ያስረዱ በመሆኑ በቀረበባት ክስ መሰረት እንድትከላከል የመከላከያ ማስረጃ እንድታቀርብ ቀጠሮ በተሰጣት መሰረት የተከሳሿ ተከላካይ ጠበቃ የመከላከያ ምስክሮችን ከክፍለ አገር ፈልገው ማቅረብ እንዳልቻሉ ገልጸው ተከሳሽ የመከላከያ ማስረጃ ማቅረብ ስላልቻለች ትከላከል በተባለበችበት ድንጋጌ ስር ጥፋተኛ ነሽ ብሏታል፡፡
ፍርድ ቤቱም ተከሳሽን ያርማል ሌሎችንም ያስተምራል በሚል በ18 ዓመት ጽኑ እስራትና በ106 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንድትቀጣ ሲል ወስኖባታል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 30/2015