ልጅነት
በመሀል አዲስ አበባ አራዳ ጊዮርጊስ ግርጌ መወለዷ ከኪነጥበብ እንድትዛመድ ሰበብ ሆኗል።ልጅ ሳለች በሰፈራቸው ካሉ መደዳ ጠጅ ቤቶች በአንዱ ጎራ ማለት ልምዷ ነበር።እንዲህ ማድረጓ ለጠጅ አምሮቷ ‹‹ፉት›› ልትል አልነበረም።በየቀኑ በዚህ ስፍራ በምታየው ዘፈንና ጭፈራ ተማርካ እንጂ፡፡
ሜሪ አርምዴ ዘወትር ከምትረግጠው ጠጅ ቤት በደረሰች ቁጥር የዘመኑን ዝነኞች ንጋቷ ከልካይን፣ ባፈና ወልዴና ጥሩ ብርቄን ታያቸዋለች።እነሱ የዛኔ በጥሩ ድምጽና ውዝዋዜያቸው የታወቁ ነበሩ።ታዲያ ሜሪ እንደሌሎች በአድናቆት ብቻ አልቆመችም።በመጋረጃ ተከልላ እያየች እነሱን ለመመሰል ታንጎራጉራለች፡፡
በወቅቱ የውስጧን ፍላጎት ያዩ በስሟ እያቆላመጡ፣ እንድትዘፍንላቸው አነሳሷት። ሜሪ ደስ እያላት መዝፈን፣ ማንጎራጎሩን ያዘች።የልዩ ድምፅዋ ለዛና ጣዕም ጆሮ ገብ መሆኑ አልቀረም።አድማጭ፣ አድናቂዋ በረከተ።ጊዜው ወራሪው የኢጣልያ ጦር መላ አገሪቱን የተቆጣጠረበት ነበር።ይህ ክፉ አጋጣሚም ሜሪን ለስደት ሊዳርጋት ግድ ሆነ። ሁለት ዓመታትንም ‹‹ፋቄ›› ከተባለ አገር ቆየች።ጥቂት ቆይቶ የኢጣልያ መንግስት ለመነኮሳት፣ ሴቶችና ህፃናት ወደ አገር ቤት የመመለስ ዕድሉን ሰጠ፡፡
የጠጅ ቤቱ ዜማ
ሜሪ አዲስ አበባ ደርሳ ከቀድሞ ሰፈሯ አራዳ ተቀላቀለች።ውላ አድራም ትወድ፣ ትናፍቀው ወደነበረው ጠጅ ቤት መለስ ቀለስ አለች።ይህን ያስተዋሉ ዘመዶቿ እንደሴት ወግ እንድትፈትል፣ እንደትሰፋ ሙያን፣ እንድትማር ወተወቷት።እሷ ግን ቃላቸውን ባለመስማት ‹‹አሻፈረኝ›› አለች።ማንጎራጎር መዝፈኑንም ቀጠለች፡፡
ወዳጅ ዘመድ በሜሪ ጉዳይ ጥብቅ ምክር ያዘ።ድርጊት ባህርይዋ የሚበጅ አልሆነምና ነጋ ጠባ ውግዘትና ግርፊያዋ በዛ።ሜሪ ፈጽሞ አልሰማችም፣ አልታረመችም።ውሎ ማምሻዋ ከጠጅ ቤቱ ሆነ።እያደር ሁኔታዋ ለሌሎች ልጆች ስጋት መሆኑ ታመነበት።በእሷ ጉዳይ ቤተዘመድ ለምክር ተቀመጠ። ሚሲዮኖች ዘንድ ገብታ እንድትማር ተወሰነባት፡፡
ሜሪ በውሳኔው መሰረት ከሚሲዮኖቹ ገብታ ትምህርቷን ጀመረች።አልተመቻትም።ሁኔታዋ ‹‹ድመት መንኩሳ … ›› ይሉት አይነት ሆነ።እዛም መዝፈኗን ቀጠለች።ይህ ልማዷ የግቢውን መነኮሳትና መምህራን በእጅጉ አስቆጣ። አሁንም በሜሪ ላይ ተመሳሳይ ውሳኔ ሊተላለፍ ግድ ሆነ።ድርጊቷ ለሌሎች እንደማይበጅ ታምኖበት ከትምህርት ቤቱ እንድትባረር ሆነ፡፡
የሜሪ ቤተሰቦች በንዴት ጦፉ።በተቃራኒው የእሷ አንጀቷ ቅቤ ጠጣ። ይህ ደስታ ግን ብዙ አልቆየም። የትምህርት ቤቱ አስተዳደር ዳግም ተለምነው ወደ ትምህርት ገበታዋ ተመለሰች።ተማሪዎች ቀለማቸው ላይ ሲያተኩሩ ሜሪ በሀሳብ ጠጅ ቤት እየነጎደች ማንጎራጎሯን ቀጠለች።
ይህ ድርጊቷ የትምህርት ቤቱን አስተዳዳሪ ትዕግስት አሟጠጠ። መነኩሴው ከማዘን አልፈው በእጅጉ ተበሳጩ። ሁለተኛ ዓይኗን ማየት እንደማይሹም አሳወቁ።ከግቢው ሲያባርሯት አፍታ አልቆዩም።አሁን የሜሪ ዕጣ ፋንታ ግልጽ ሆነ።ብዙ አልቆየችም።ትምህርት የጠላ እግሯ ከጠጅ ቤቶቹ መንደር አደረሳት። እዛው ገብታ ከተመች።የአራዳ ጠጪዎች ሜሪን እያዳነቁ ግጥም ይሰጧት ያዙ።የልቧ ሞላ።በጎርናና ድምጽዋ ግጥሙን በዜማ እያዋዛች ተመልካቾች አበዛች፡፡
ዳንስና ፋሽን
የአራዳ ጊዮርጊስ ቆይታዋ ከአንዲት ፀጉረ ልውጥ ሴት አገናኛት።ሴትዬዋ የውጭ አገር ዜጋ ፈረንሳዊት ናት።ከሜሪ ለመግባባት አልተቸገረችም።የዘመኑን አለባበስና ለየት ያሉ የባዶ እግር ዳንሶች አስተማረቻት።ሁኔታው ለብዙዎች አልተመቸም።በተለይ የልብሱ ጉዳይ ተመልካቹን አስቆጣ።ልብሱ ከተለመደው የተለየ ነበርና በዳንሱ ላይ ያየው ሁሉ ‹‹ጉድ›› እያለ አነወረው፡፡
ውሎ አድሮ ፈረንሳይቷ ሙሉ ንብረቷን ለሜሪ አበርክታ ወደ አገሯ በረረች። ሜሪ እሷን ከሸኘች በኋላ በአካባቢው አንድ ትልቅ ቪላ ቤት በውድ ዋጋ ተከራየች።ሀሳቧ ዳንስና ሙዚቃውን እንዳሻት ልትወጣበት ነበር።ዕቅዷ ፈጥኖ አልተሳካም። ለሙያው የቀረቡ ዘመናዊ ሴቶች ለማግኘት ተቸገረች።መላ አላጣችም።‹‹ከሰል ተራ›› ከሚባል ሰፈር ዘልቃ አማተረች።ዓይኖቿ ክራር ይዘው በየጠላ ቤቱ ከሚዞሩ ቆንጆ ሴቶች ላይ አረፉ።ቀረብ ብላ የውስጥ ሀሳቧን ነገረቻቸው።ብዙዎቹ ዘመናዊ ልብስ የላቸውምና ለዕለት እንጀራቸው ሰግተው ‹‹እምቢኝ›› አሏት፡፡
እሷ ግን ‹‹አይዟችሁ ልብስና ጌጥ ከእኔ ዘንድ አለ።ቤቴ ፈረንጁና መኳንንቱ የሚጋፋበት ነው፣ ትለወጣላችሁ፣ ታድጋላችሁ›› ስትል ማሳመኑን ቀጠለች።ጥቂቶች ጆሮ ሰጧት። የተወሰኑትን መርጣ በጸጉር ስራና፣ በዳንስ አሰለጠነቻቸው።ጸጉራቸውን ተኩሳ፣ ዓይናቸውን ኩላ አሳመረቻቸው።ሴቶቹ በአለባበስና በጸጉራቸው የተለዩ ሆኑ። አድናቂያቸው በረከተ።
ሜሪ በተከራየችው ዳንስ ቤት ለዓይን ብርቅ የሆኑ ሴቶችን ይዛ ስራ ጀመረች።ደንበኞች ጎረፉላት፤ ገበያዋ ደራ።ታዋቂ ሰዎች፣ መኳንንቶች ቤቷን ጎበኙት።ባለ ክራሯ ሜሪ ዕለት በዕለት እውቅናዋ ጨመረ፣ ስሟ ገነነ።
ቅዳሜና ዕሁድ የሜሪ አርምዴ ቤት በእንግዶች ይጨናነቃል፤ በጨዋታ መሀል ጠብ ቢፈጠር፣ አምባጓሮ ቢነሳ የሚከላከሉ ሰባት ጠንካራ ዘቦች ቀጥራለች። ምሽት ሶስት ሰዓት የቤቱ ሙዚቃና ዳንስ በመብራት ደምቆ ይጀምራል።በአለባበሳቸው የተለዩትን ሴቶች ለማየት ደንበኞች ይጋፋሉ፡፡
በጡት ማስያዣና በውስጥ ሱሪ ብቻ የሚታዩት ዳንሰኞች ዓይን ይስባሉ። ታንጎ፣ ቫልስ፣ ቬርዱሉና፣ ማዙካ፣ በተባሉ ዳንሶች ቤቱ ይደምቃል።ውስኪው፣ ቢራው፣ አልኮሉ ይጠጣል። ሴቶቹ ከሚወርደው ዋና ውስኪ እንዲጠጡ አይፈቀድላቸውም። ጋባዥ ሲኖር በጠብታ ውስኪ የተበረዘው ሻይ በዘዴ በጠርሙስ ይቀርብና የውስኪው ሂሳብ ይቆረጣል፡፡
ቬርዱሉና የተባለው ዳንስ ጥንዶች በአረንጓዴ መብራት፣ በለስላሳ ሙዚቃ ተቃቅፈው የሚደንሱት ነው።ማዙካ ደግሞ በወርቅና በአልማዝ፣ በውስኪና ሻምፓኝ እየተወራረዱ የሚጫወቱት ነው።በዚህ ውርርድ ሜሪ ጭምር ዳኛ ሆና ጨዋታውን ትመራለች፡፡
በዳንስ ቤቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ቀይ መብራትን ያስተዋወቀች ሜሪ አርምዴ ነች። ሜሪ በዳንስ ቤቷ ስራዋን ቀጠለች። ውሎ አድሮ ግን ማዘጋጃ ቤት ድርጊቷን ተቃወመ። የጡት ማስያዣና የውስጥ ሱሪ ዳንስ እንዲቆም ሲል ጥብቅ ትዕዛዝ ደረሳት።
ይህ ሲሰማ ገበያዋ ተቀዛቀዘ። ደንበኞች እግራቸው ራቀ።ሜሪ ግን ስራውን አላቆመችም። በረዥም ቀሚስና በስስ ሸሚዝ ዳንሱን አስቀጠለችው።እንደቀድሞው ገበያዋ አልደራም። ውሎ አድሮ ከእሷ ያዩ ሌሎች የቀይ መብራት ዳንስ ቤቶችን ከፈቱ።የእሷ ቤት በሁካታና ድብድብ ይታወቅ ጀመር። ስሞታው፣ ወቀሳው በዛባት።ስራዋን ለመተው ወሰነች። ሰራተኞቿን ሸኝታ ቤቷን ዘጋች፡፡
ጸጉርን በካውያ
ከቀጠረቻቸው አብዛኞቹ እያየቻቸው ሕይወታቸው ተለውጧል።ቀድሞ ከየጣሳ ቤቱ ያመጣቻቸው ሴቶች ከእሷ ወጥተው የራሳቸውን መጠጥ ቤት ከፍተዋል፣ ቪላ ቤቶች ሰርተዋል።ሜሪ ለኑሮዋ ሌሎች አማራጮች ፈለገች።ዕድሜ ለፈረንሳይቷ ጓደኛዋ በሌሎች ፈጽሞ ያልተሞከረ ሙያ አስተምራታለች። ውስጧ መፍትሄውን ሹክ አላት።በሀሳቧ የዘመኑን ሴቶች ጸጉር ቃኘች።የአብዛኞቹ ጸጉር በወጉ አይያዝም።አንዳንዶች ደግሞ ‹‹አምበሬ ጭቃ›› የተባለን ቅባት ለጉደው በአበሻ ሚዶ እያበጠሩ አንሶላ የሚያበላሹ ናቸው፡፡
ሜሪ ልማዳቸውን ነቅፋ ስራዋን ለማስተዋወቅ ፈለገች።ክራሯን አንስታ፣ ግጥም ደረደረችና እንዲህ ስትል አቀነቀነች፡፡
ያሰራሽው አልጋ ወፍራም አጣና ነው፣
ያነጠፍሽው ፍራሽ የሱሉልታ ሳር ነው፣
እግርሽ ከታጠበ ሰባት አመቱ ነው፡፡
የፀጉርሽ አቧራ ዓይኔን ሊያጠፋው ነው፡፡
ይህ ግጥም የዘመኑን ሴቶች ብቻ ሳይሆን ሥራዋን በስፋት አስተዋወቀ።አንዷ የሌላዋን ጸጉር እያየች መከተሏ ደንበኞቿን አበራከተ።ያላቸው እየከፈሉ የሌላቸው ደግሞ በዱቤ መተኮስ ያዙ።ልክ እንደዳንሱና ቀይ መብራቱ ሁሉ የጸጉር ተኩስ ሥራ በሜሪ አርምዴ እጆች መተዋወቅ ጀመረ።ሜሪ የባለጎፈሬዎችን ጸጉር ጭምር አሳምራ ትከረክም፣ ታስውብ ነበር።ከዚሁ ጎንም ‹‹በርሞሌ ›› የሚባለውን ሽቶ ትሸጣለች፡፡
ደሞዝተኛዋ ሜሪ
በወቅቱ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ለድምጻውያንና መሰል ከያኒዎች ስልጠና ይሰጥ ነበር።በዋነኛነት ትምህርቱን የሚሰጡት ካፒቴን ናልባንድያን ታዲያ የሜሪን ሙያዊ እገዛ ፈልገው ጥሪ አቀረቡላት።ሜሪ በቲያትር ቤቱ ተቀጥራ የዳንስና የአልባሳት ዲዛይን ባለሙያ ሆነች፡፡
ከጥቂት ቆይታ በኋላ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቲያትር ቤት ተዛውራ መስራት ያዘች።በወቅቱ ቴዎድሮስ የተባለው ቲያትር ሲሰራ የሹሩባውን ጌጥ፣ ሀኒባል ሲሰራ ደግሞ የአልባሳቱን ዝግጅት የከወነችው ሜሪ ነበረች።ዘጠኝ ዓመታትን በቲያትር ቤቱ ስትቆይ ለአገልግሎቷ አበልና የደሞዝ ለውጥ አልነበራትም።እንዲህ መሆኑ ደግሞ ከልብ አስከፋት፣ አስኮረፋት፡፡
ሜሪ ከአንድ እንግሊዛዊ ጋር ለረጅም ዓመታት የዘለቀ ትዳር ነበራት።በኋላ ግን ያቺ ፈረንሳዊት ባልንጀራዋ ድንገት ጅቡቲ ይዛት መሄዷ ሰበብ ሆኖ ትዳሯ ፈረሰ።ሜሪ ምንግዜም የባለቤቷን መልካምነት አትክድም።ትዳሯን ‹‹አልፈልግም›› ባለችው ጊዜ በርከት ያለ ገንዘብ ሰጥቷት ነበር።ከጅቡቲ የዓመታት ቆይታ በኋላ አዲስ አበባ ስትመለስ በእጇ ባለው ብር የሙሽራ ልብስ /ቬሎ/ እየሰራች ማከራየት ጀመረች።አሁንም ይህን ዘመናዊ ቪሎ ለከተማው ያስተዋወቀች የመጀመሪያዋ ሰው ሜሪ አርምዴ ሆነች፡፡
ሜሪ አርምዴን እናውቃታለን የሚሉ የአንድ እግሯን ማንከስ ያስታውሳሉ።እሷም ብትሆን እንዲህ የመሆኗን ምክንያት ፈጽሞ አትዘነጋም።በዘመኑ ከመሀል ከተማ እስከ ገፈርሳ የብስክሌት ውድድር ይካሄድ ነበር።
አንድ ቀን ሜሪ ከውድድር መልስ ትልቅ ግብዣ አዘጋጀች።የዳጉሳ ጠላ አስጠምቃም በቤቷ እንግዶችን ጠራች።ሜሪ መዝናናት መጫወት ትወዳለች።ሰው አጠገቧ ሲኖር ደስ ይላታል።የዛን ዕለትም ጠላውን ጭው አድርጋ በላዩ የአበሻ አረቄ ጠጣችበት በሀሳቧ የዕለቱን ውድድር መለስ ብላ ትቃኝ ነበር።ሞቅታው ወደስካር ተለወጠ።በዚህ ብቻ አልቆመችም።በድንገት ብድግ አለችና ከብስክሌቷ ኮርቻ ፊጥ ብላ መክነፍ ጀመረች።የጠጣችው የዳጉሳ ጠላና አረቄ ፈጥኖ ሥራውን ጀመረ።ሜሪ ርቃ ሳትርቅ ከብስክሌቷ ተፈናጥራ ወደቀች።አንድ እግሯ ከብስክሌቱ ተንጠልጥሎ ቀረ።ሰዎች ደርሰው ሲያነሷት አንድ እግሯ ክፉኛ ተጎድቶ ነበር። ለመታከም ሀኪም ቤት ገባች የቁርጭምጭሚቷ ጅማት ተበጥሶ ነበርና ህመሟ አልሽር አለ።
ሀኪሞች እግሯ እንዲቆረጥ ወሰኑ። ቤተሰቦቿ ‹‹እምቢኝ›› አሉና በቤት አስተኝተው ጠቦት ሙክቱን እያረዱ ጠገኗት። ሜሪ ቆማ ለመራመድ ሞከረች። ለዳንስ እንደእንዝርት ከሚሾሩት እግሮቿ አንደኛው እንዳኮረፈ ነበርና ያስነክሳት ጀመር፡፡
ሜሪ በክራር ድርድሯ፣ ተፈጥሮ በቸራት ጎርናና ድምፅዋና በአነጋጋሪ ግጥሞቿ ትታወቃለች። ችሎታዋ የመጣው ግን ተምራና ፊደል ቆጥራ አልነበረም። ከፈጣሪ በተሰጣት ጸጋ እንጂ። ሜሪ ልጅ ሳለች አንዳንድ ዘፋኞች የሚሉትን ግጥም ከስር እየለቀመች መልሳ ትለው ነበር።በየመጠጥ ቤቱ ስትሰራም እንደ አዝማሪ ግጥም መቀበል ልምዷ እንደነበር ታስታውሳለች። ግጥሙን ክክራሯ ስታዛምድ ደግሞ ዓይንና ጆሮን ትስባለች። አድናቂዎቿ ተከታዮቿ ይበዛሉ፡፡
ፍቅር እንደገና
በአንድ ወቅት ሜሪ ሀይለኛ ፍቅር ያዛት።ሰውዬው ቀድሞ ወዳጇ ነበር። አጋጣሚ በትንሽ ጉዳይ ቢቀያየሙ ቤቷን እርግፍ አድርጎ ተወው። ይሄኔ የሜሪ ፍቅር አገረሸ። ጠዋት ማታ ደጅ ደጁን እያየች ናፈቀች፣ ተሰቃየች፤ ሰውዬው ይህን ቢያውቅ እግሩን ሰበሰበ። ሜሪ በእጅጉ ባሰባት።በኋላ ነገሩ ሁሉ ይነዳት፣ ያበሽቃት ጀመር።ጥቂት ቆይታ ግን ብታገኘው በጩቤ እንደምትወጋው ማስወራት ጀመረች፡፡ ይህን የሰማው ወዳጇ ይባስ ብሎ ሰፈሩን ለቆ ጠፋ።ናፍቆት ትዝታው የባሰባት ሜሪ ክራሯን አንስታ እንዲህ ስትል አዜመች፡፡
አልሰድበውም ነበር አላኮርፍም ነበር፣
እንዲህ መለየቱን አውቄው በነበር፡፡
አውላላ ሜዳ ላይ ይመታል ዕንቅፋት፣
ተለያይቶ መቅረት በአንድ ቀን ጥፋት፡፡
ሜሪ የዚህ ወዳጇን ፍቅር እንድትረሳ ለታቦታት ተስላ ነበር።ደግነቱ ስለቷ ተሰማ።ከእሱ በኋላ ፍቅር ይሉት ይዟት አያውቅም፡፡ ሜሪ ከድምጻዊነቷ ባሻገር ለአገሯ ዘመናዊነትን ቀድማ ያስተዋቀቀች ናት።በጸጉር ተኩስ፣ በሙሽራ ቬሎ፣ በቀይ መብራት ዳንስና በሌሎችም ስሟ ደምቆ ይጠራል።ይህን ሁሉ ትከውን እንጂ ሕይወቷ እንደነበረው አልቀጠለም።እያደር ብኩን ሆነች፣ ድህነት አጠቃት።ክብር ዝናዋም ቀረ።መኖሪያዋ ከአንዲት አነስተኛ ደሳሳ ቤት ሆነ።ልጄ፣ እናት አባቴ፣ ባሌና ትዳሬ ከምትላት ክራሯ በቀር የተረፋት አልነበረም፡፡
ሜሪና ማርያም አኬቫ
ሜሪ በአንድ ወቅት ከደቡብ አፍሪካዊቷ ታዋቂ ዘፋኝ ማርያም አኬቫ ጋር ድንገት ተገናኘች።ይህ የሆነው በአጋጣሚ ነበር።በአፍሪካ አገራት የነበሩ ኢትዮጵያውያን ስለሜሪ አርምዴ ለአኬቫ አዳንቀው ነግረዋት ኖሯል።ስለ ዝነኝነቷና ታዋቂነቷ።መልካቸው ስለመመሳሰሉ ጭምር።እንዲህ ይበሉ እንጂ ሜሪ ‹‹ድሀ ነኝ›› ብላ ገንዘብ እንድትቀበላት ፈልገው ነበር።
በዕለቱ ማርያም አኬቫን ጨምሮ ሌሎች ታዋቂዎች በጋዜጠኞች እየተመሩ ከደሳሳ ጎጆዋ በራፍ ደረሱ።ማርያ ሜሪን እያየች ‹‹ቤትሽ እዚህ ነው?›› ስትል ጠየቀቻት። ሜሪ ደነገጠች፣ አፈረች፣ በእሷ ድህነት አገሯን ማስነሳት አልፈለገችም። ቀልጠፍ ብላ የእሷ ቤት በድሉ ህንጻ የሚባለው ፎቅ እንደሆነና እዚህ ሰራተኛዋ ታማ ልትጠይቃት መምጣቷን ለአስተርጓሚዋ ተናገረች።ያልታመመችው ሴት በውሸት ታቃስት ነበር።አኬቫ ሀምሳ ዶላር አንስታ ሰጠቻት።ሜሪ በሚስጥር ብሩን አቀብላ ቤቷ ልትጋብዛት ከእንግዳዋ ቀጠሮ ያዘች፡፡
የገባችበት ጉዳይ አስጨናቂ ቢሆንም እውነታውን አልቅሳ የነገረቻቸው አንድ ሰው ግብዣውን ችለው፣ መኪና አዘጋጅተው፣ ቤቱን ፈቅደው የልቧን ሞሉላት።ሜሪ በቤታቸው የእሷን ፎቶግራፍ ሰቀለች።በራት ልብሷ አምራም እንደቤቷ ሽር ጉድ አለች።ዝናዋን ይዛ፣ ስጦታ አበርክታ የአገሯን ስም ጠበቀች። ታዋቂዋን ማርያን አኬቫን በክብር አስተናግዳ ሸኘች፡፡
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2015