ወፈፌው ይልቃል አዲሴ ዛሬም እንደዚህ ቀደሙ በሌሊቱ ተነስቶ በሰፈራችን ከሚገኘው ዋርካ ስር ቆሞ ይጮሃል። «እለ ከርሦሙ አምለኮሙ ( እነሆድ አምላኩ)፤ ያሰባችሁት እኛን የመከፋፈል ሴራ መቼም አይሳካም» እያለ ያምቧርቃል። የይልቃል አዲሴን ጩኸት እንደ መጽሐፍ ማንበብ የጀመሩት የሰፈራችን እና የእድራችን ሰዎች የይልቃልን ንግግር ለመስማት በዋርካው ስር ተኮለኮሉ።
ይልቃል ንግግሩን የጀመረው … ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የእድራችንን እና የሰፈራችንን ህልውና የሚፈተተኑ ጋሬጣዎች እና እንቅፋቶችን በሰከነ እና በሰለጠነ መንገድ እየተነጋገርን እና እየተወያየን በመደማመጥ ከመፍታት ይልቅ ስሜታዊነታችን ጎልቶ እየወጣ እርስ በርስ ለመጠፋፋት ስንቋምጥ ይታያል። ይህን የሚመለከት ማንም የሰፈራችን እና የእድራችን አባል እውነት እኛ የአክሱም ስልጣኔ ወራሾች ፣ የላሊበላ የአጥንት ክፋዮች ፣ የሐረር ግንብ አናጺዎች ፣ የዓድዋ ድል ባለቤቶች የጥቁር ነጻነት ምሳሌዎች የሆኑ አባቶች ልጆች ነን ወይ ? ብሎ ራሱን መጠየቁ አይቀርም።
እኛ የምስራቋ ኮከብ ልጆች ያሉንን እምቅ ሀብቶች ተጠቅምን የጋራ የሆነችውን ሀገራችንን አበልጽገን ፤ በሀገራችን መበልጸግ ውስጥ ደግሞ ራሳችንን አዘምነን እና አጎልብተን በተደላደለ የእድገት ጎዳና ከመራማድ ይልቅ እርግማን መሰል ተጣብቶ የማይለቅ ፈውስ የሌለው በሽታ ዞን የተለያዩ ሰበቦችን እየፈጠርን እርስ በርስ መነቋቆሩን ስራዬ ብለን ይዘነዋል።
ይህ እርስ በርስ የመጠላላፍ ልማዳችን በተለይም ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ እየተባባሰ የመጣ ቢሆንም አሁን ላይ ደግሞ የሚታየው የእርስ በርስ መጠላለፍ አስፈሪ ደረጃ ላይ የደረሰ ይመስላል። የእርስ በርስ መጠላለፉን ከዳር ቆሞ የሚመለከት ሰው «እነዚህ የጦቢያ ልጆች ከድህነታችሁ እና ከኋላ ቀርነታቸው የሚላቀቁት የእርስ በርስ ግጭት በማካሄድ ነው የተባሉ ይመስላሉ» ማለቱ የማይቀር ነው።
የምስራቋ ኮከብ ምን ጎድሏት ነው ልጆቿ እንዲህ የምትባሉት? ተብለን ብንጠየቅ በእርግጠኝነት ይህ ነው የሚባል ሁነኛ መልስ የለንም። አንዳንድ በክፉ የነዋይ እና የስልጣን ልክፍት የተመረዙ ጽንፈኛ ብሔርተኞችና ኃይማኖተኞች የግጭታቸውን መንስኤ ከብሔር እና ከሃይማኖት ጋር እንደሚያቆራኙት ሳይታለም የተፈታ የአደባባይ ሚስጥር ነው።
እውነት እኛ የምስራቋ ኮከብ ልጆች የቸገረን በብሔር እና በሃይማኖት ጉዳይ አጀንዳ እየፈጠሩ መነታረክ ነው? አይደለም! የስልጣን ጥመኞች እና ጽንፈኞች በብሔር እና በሃይማኖትን ሽፋን አድርጋችሁ የራሳችሁን ገንዘብ ማግበስበስ ስለምትፈልጉ እንጂ።
በነገራችን ላይ ሃይማኖትን ሽፋንን እያደረጉ ሕዝብና ሕዝብን ማባላት በእኛ እድር እና ሰፈር እንዲሁም በውጩ አለም አሁን የተጀመረ አይደለም ። በውጭ በሚገኙ ሰፈሮች እና ድሮች የሆነውን ትተን የእኛን ሰፈር እና እድር የመካከለኛውን ዘመን ታሪክ ብቻ እንኳን ነጥለን ብንመለከት ዘመኑ ሃይማኖትን ሽፋን ባደረጉ ጦርነቶች የተሞላ ሆኖ እናገኘዋለን።
በመካከለኛው ዘመን የዘይላ ወደብን ተከትሎ የደራ ገበያ ነበር። የኢኮኖሚ ፍሰቱም ለጉድ ነበር። በመሆኑም በዘይላ ወደብ የገበያ መስመር የሚካሄደውን የንግድ ልውውጥ ለመቆጣጠር እና በብቸኝነት ለማስተዳደር በመፈለግ የክርስቲያኑ መንግስት (The Christian highland kingdom) እና የእስላም ሱልጣኖች Muslim sultanates) ግጭት ውስጥ ገቡ ።ምክንያቱም የኢኮኖሚ የበላይነት ያለው አካል ሁሉንም ነገር መቆጣጠር እንደሚቻል የአደባባይ ሚስጥር ነውና።
ጤናማ ያልሆነ የኢኮኖሚ ወድድር ውስጥ በመግባታቸው የተጋጩት እነኚህ ሁለት አካላት የሰፈራችን እና የእድራችንን ሰዎች ስስ ብልት ሃይማኖት መሆኑን ስለሚያውቁ ጉዳዩን ከኢኮኖሚያዊ ጉዳይ መሆኑን ደብቀው የሃይማኖት ሽፋን ሰጡት። ይሄው ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገው ጦርነት መላ ሰፈራችንን እና እድራችንን አመሰ።
«….. ሲጣሉ የሚጎዳው ሳሩ ነው» እንዲሉ ግጭቱን ከጠመቁት አካላት በላይ ሰፈራችንን እና እድራችንን ሰዎች እጅጉን በከፋ ደረጃ በጦርነቱ ተጎዱ። የውጭ ኃይሎችም ሰፈራችንን እና እድራችንን እንደፈለጉ ያለማንም ከልካይ እንዲፈነጩ እድል ሰጠ። የሰፈራችንን እና እድራችንን አደረጃጀቶች አይሆኑ ሆነው ተጎሳቆሉ።
ያ ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገው ጤናማ ያልሆነ የኢኮኖሚ ወድድርም እስካሁን ድረስ ጠባሳው እንደ ክፉ መንፈስ ከላያችን ላይ ተጣብቆ አልለቅ ብሎ የሰፈራችን እና እድራችን ሰዎች በሌሎች ሀገር የሚያዩት ስልጣኔ እንደ ውሃ ጠምቷቸው ሳያገኙት እነሆ እስከዛሬ በችጋር ጠኔ ውስጥ እንዲመላለሱ አድርጓቸዋል።
ዛሬም ላይ ከቀደሙት የአባቶቻችን ስህተት መማር ያቃተው ይህ ትውልድም ሀገራችንን ወደ አልተገባ ቅርቃር ውስጥ ለመክተት እየኳተነ ይገኛል። በተለይም በ1950ዎቹ በምዕራባዊያን አነሳሽነት፤ በሰፈራችን ከሚገኘው መካነ- አእምሮ ተማሪዎች አድራጊ ፈጣሪነት የተጀመረውን የጽንፈኛ ብሔርተኞች የብሔርተኝነት ጥያቄ አሁን ላይ አድማሱን አስፍቶ የመላው ሰፈራችን እና እድራችን የሀገሪቱ የህልውና አብይ ፈተና ሆኖ መጥቷል።
እውነት እንነገጋር ከተባለ አሁን ላይ የሰፈራችን እና የእድራችን ነዋሪዎች አብይ ጥያቄ የዳቦ እና የዳቦ ብቻ እንጂ የብሔር አልነበረም። ነገር ግን የነዋይ እና የስልጣን ጥቅማችሁን በብሔር ፖለቲካ ለመሳካት የፈለጉ ኃይላት ጽንፈኝነት የተጠናወተውን የብሔርን ጥያቄ ሀገርን በሚያወድም ጣፋጭ በመርዝ በመለወስ ዋነኛ የፖለቲካ መጨዋቻ ካርድ አድርገውታል።
በነገራችን ላይ ጽንፈኛ ብሔርተኝነትን የፖለቲካ መጫዎቻ ካርድ አድርጋችሁ የምትጠቀሙ ኃይላት ሰፈራችን እና እድራችን እየተጎዱ እናንተ የምትተርፉ መስሎ ከታያችሁ ተሳስታችኋል። ሰፈራችን እና እድራችን የሚያቃጥል እሳት ሁሉ እናንተንም እንደሚያቃጥል ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለባችሁም።
ብሔርን የመጫወቻ ካርድ ላደረጋችሁ ጽንፈኛ ብሔርተኞች አንድ ጥያቄ አለኝ…. እውነት ብሔራችሁን የምትወዱ ከሆነ፤ አርቆ ማሰቢያ አእምሮ አለኝ ካላችሁ እና ሕዝባችሁን የምትወዱ ከሆነ ሁሉንም ተውትና መጀመሪያ የምትጮሁለትን ብሔር የዳቦ ጥያቄ ብቻ መልሱ! በተለያየ ምክንያት የተፈናቀሉ፤ የታረዙ፤ የተጎሳቆሉ፤ የተራቡ፤ የተጠሙ ሰዎችን አለንልህ በሉት፤ድረሱለት።
እየማላችሁ እና እየተገዘታችሁ የምትጮሁለትን ብሔር የዳቦ ጥያቄ ከመለሳችሁ እውነትም ለብሔራችሁ የምጮሁ እውነተኛ ታጋይ መሆናችሁን ታሳዩናላችሁ። ነገር ግን ማድረግ አትችሉም። ይህን ስል በአመክንዮ እንጂ እንዲሁ በግብዝነት ስላለመሆኑ በርካታ መረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል። ወፈፌው ይልቃል አዲሴ ይህን እየተናገረ እያለ ሁሉም የሰፈራችን ሰዎች ጸጥ እረጭ ብለው እያዳመጡ ነበር። ነገር ግን ሁሌም ሳይፈቀድለት የሚናገረው አብሿሙ ከንፈ ጉደታ በይልቃል አዲሴ ንግግር ላይ ተደርቦ የይልቃል አዲሴን ንግግር አቋረጠው።
የሰፈራችን ሰዎች ክንፈ ጉደታን አብሿም ይበሉት እንጂ ክንፈ ጉደታ የእውነት አብሾ መጠጣቱን በእርግጠኝነት መናገር የሚችል ሰው የለም። የይልቃል አዲሴን ንግር የአቋረጠው አብሿሙ ከንፈ ጉደታ «ይልቃል አዲሴ የተናገረችው በሙሉ እውነታ አላቸው። እኔም ከሱ ሃሳብ ላይ የምጨምረው ነገር አለኝ» አለና ንግግሩን እንዲህ ሲል ጀመረ …. ፈላስፎች እንዲህ ይላሉ ፤ አምስት ነገሮችን ያሉበት ሰው ነፍሱ እጅጉን ይጎዳል። እነኚህም ሽማግሌዎችን መሸንገል (ማታለል)፣ አዋቂዎችን መናቅ ፣ ሰዎችን ማዋረድ ፣ ለማይረባ ነገር መታገስ እና ልብ ያሻውን መከተል ናቸው።
አሁን ላይ በእኛ ሀገር የሚገኙ ጽንፈኛ ብሔርተኞችም አምስቱን የክፉት መንፈስ የተጠናወታቸው ናቸው ብሎ ማጋነን አይሆንም። እንዴውም ያንሳቸዋል። ምንም መደባበቅ አያስፈልግም ! በተፎካካሪ ቡድኖችም ሆነ በእድራችን እና በሰፋራችን አስተዳዳሪዎች ያሉ ጽነፈኛ ብሔርተኞች አታላዮች፤ አዋቂዎችን የሚንቁ፣ ሰዎችን በመዋረድ ራሳቸውን ከፍ ለማድረግ የሚሞክሩ፣ መታጋስ ያለባቸውን እና መታገስ የሌለባቸውን ጠንቅቀው የማያውቁ፣ ሺህ ሕዝብ ቢሞት እና ቢፈናቀል ልባቸውን ያሻውን ከማድረግ የማይመለሱ ናቸው ።
አሁን ላይ በሰፈራችን እና በእድራችን በትክክል የሚታየው ትልቁ በሽታ ይህ ነው። ባይሆንማ ኖሮ በሰፈራችን እና በእድራችን እየታየ ያለው የርሃብ እና መፈናቀል ችግር ባልተፈጠረ ነበር። «የሚገርመው እኮ » አለ አብሿሙ ከንፈ ጉደታ፤ በእኛ ሰፈር እና እድር የሚገኙ ጽንፈኛ ብሔርተኞች ብሔር ማለት ምን ማለት ነው ተብለው ቢጠየቁ የተጠየቁትን ጥያቄ ከቋንቋ ጋር ብቻ የሚያገኛኙ ገልቱዎች ናቸው።
ስለብሔር በስፋት ለዓለም ህዝብ ያስረዱት እነማርክስ እንደሚናገሩት አንድ ማህበረሰብ ብሔር ለመባል ስድስት ነገሮችን ማሟላት ይጠበቅበታል። አንደኛው ብሔር ማለት በዘር ወይም በጎሳ የተደራጀ ሳይሆን በታሪክ የተቀናጀ ማህበረሰብ ነው። በሁለተኛነት አንድ ማህበረሰብ ብሔር ሊባል የሚችለው አንድ ማኅበረሰብ በአጋጣሚ ወይም በጊዜያዊ ሁኔታ የተሳሰረ የሕዝብ ክምችት ሳይሆን ለዘመናት ማንነቱን የጸና ማኅበረሰብ ሲሆን ነው። ሶስተኛው ቋንቋ ነው። አራተኛው ደግሞ ኢኮኖሚ ነው።
አምስተኛው አንድን ማኅበረሰብ ብሔር ሊያስብል የሚያስችለው ዓብይ ጉዳይ አንድ ማኅበረሰብ ተመሳሳይ ስነ ልቦና እና ታሪክ ሲኖረው ነው። ስድስተኛው እና መጨረሻው አንድን ማኅበረሰብ ብሔር ሊያስብል የሚችለው አብይ ጉዳይ ራሱን የቻለ ሀገር (sovereign state ) ሲኖረው ነው። ከዚህ አንጻር ሲታይ በምስራቋ ኮከብ ውስጥ ብሔር ተብሎ ሊፈረጅ የሚችል አንድም ማኅበረሰብ የለም። «ነገር ግን የእኛ ሰፈር እና እድር ውስጥ የሚገኙ ጽንፈኛ ብሔርተኞች ብሔረ የሚለውን ሰፊ ጽንሰ ሃሳብ ከቋንቋ ጋር ብቻ እያገናኙ ሲያውኩን እየታዩ ነው።» ብሎ ወደ መቀመጫው ተመለሰ።
አብሿሙ ክንፈ ጉደታ ንግግሩን ሲጨርስ ወፈፌው ይልቃል አዲሴ ንግግሩን ከአቆመበት ቀጠለ…. አፍላጦን የተባለውን ፈላስፋ «የአህጉሮች ደህንነት በምን ይታወቃል?» ቢሉት «አዋቂዎቻቸው ቢነግሱ እና የነገሱ ነገስታቶችም ቢጠበቡ (ብልሆች እና አስተዋዮች ) ቢሆኑነዋ» ብሎ መለሰ ይባላል ። እውነት ነው ! አሁን ላይ በእድራችን እና በሰፈራችን እየተስተዋለ ያለው ትርምስምስ መንስኤው የዚህ ፈላስፋ መለስ ይሆናል።
አሁን አሁን በሰፈራችን እና እድራችን በሚገኙ አንዳንድ ጽንፈኛ ብሔርተኛ አስተዳዳሪዎች ከዚህም ከዚያም የሚወረወሩ አስተያያቶች ከጥበብ ይልቅ በትዕቢት እና ጽነፈኝነት የታጨቁ ሆነው ይታያሉ። ይህ ደግሞ ፈላስፋ አፍላጦን «የአህጉሮች ደህንነት በምን ይታወቃል?» ተብሎ ለተጠየቀው ጥያቄ የሰጠው መልስ ሲያልፍም እንዳልነካቸው ሁነኛ ማሳ ነው።
አሁን ላይ በምስራቋ ኮከብ እንደሚታየው ነባራዊ ሁኔታ አንዳንድ የሰፈራችን እና እድራችን መሪዎች አስተዋይ እና በጥበብ የተሞሉ ቢሆኑ ኖሮ ሰፈራችንን እና እድራችንን ሰዎች ኮሽ ሳይል ማስተዳደር ይችሉ ነበር። ሰፈራችንን እና እድራችንን ከመርህ ውጭ ለመምራት ያልተገባ የፖለቲካ ሸቀጣቸውን እየሸቀጡ ሸብ ረብ ማለት የሚቀናቸው ግብዞችም መሆናቸውንም በተደጋጋሚ አሳይተውናል። ከሰሞኑ በተወካዮች ምክር ቤት ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳባቸው ግለሰቦች የእነኚህ ሰዎች ሁነኛ አመላካች ናቸው። የተጣለባቸውን ኃላፊነት ትተው የሕዝብን ገንዘብ ሲሰርቁ እንደነበር ተነግሯል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተለይ አንዳንድ ጽንፈኛ ብሔርተኛ አስተዳዳሪዎች በትዕቢት ተውጠው እርስ በርስ የሚለዋወጧቸው ሃሳቦች እጅጉን መናናቅ የሚታይባቸው ከመሆናቸውም ባለፈ ሰፈራችንን እና እድራችንን ወደተጠሙት የልማት ጎዳና የሚወስዱ አይደሉም። እውነት ለመናገር ትዕቢት የትም አያደርሰን። ይህንን በአንድ ምሳሌ ላሳያችሁ፤ በአንድ ወቅት የምስራቋ ኮከብ ንጉስ የነበሩ አንድ መሪ በሀገራቸው እዚያም እዚህም ከሚነሱ የሕዝብ አመጾች ጋር በተያያዘ አንድ ጋዜጠኛ ጋር ቃለ ምልልስ ያደርጋሉ። ንጉሱም ለተጠየቁት ጥያቄ እንዲህ ሲሉ መለሱ ……
«ስለአመጽ አንጨነቅም ወይም ከሚገባው በላይ አያሳስበንም እንዲህ አይነት አጋጣሚዎች በአንድ ሀገር ታሪክ ውስጥ ዘወትር የሚከሰቱ ናቸው። ሁልጊዜም የሚንቀሳቀስ የሚብላላ ነገር አለ። የትም ቦታ የስልጣን ጥመኞች አሉ። ተንኮለኞች አሉ፤ በእነሱ ላይ በድፍረት እና በቁርጠኝነት እርምጃ መውሰድ ብቻ ነው አማራጩ። ከማመንታት፣ ከደካማነት ወይም ከሚጋጩ ስሜቶች መጠንቀቅ ያስፈልጋል፤ ወደ ሽንፈት ይመራሉና። እኛ ራሳችን ከዚህ ወጥመድ ውስጥ ገብተን አናውቅም። ኃይል በኃይል ነው መመለስ ያለበት።» እኚህ ንጉስም በሰፋራቸው የተነሳውን የሕዘብ ጥያቄ ወደ ጎን ትተው የሕዝቡን ብሶት ለማፈን ሲሞክሩ ባለሰቡት ጊዜ አይሆኑ ሆነው እና ተዋርደው ከዙፋናቸው ተነሱ።
በመጨረሻም የእድራችን እና የሰፈራችን ዋና አስተዳዳሪ መልዕክት ነበር የሚጠበቀው። እሳቸውም የሚያምረውን ድምጻቸውን ለማውጣት ጉሮሯቸውን ሳሉና ንግግራቸውን ጀመሩ። ከዚህም ከዚያም በጥበብ ያልታሹ ንግግሮች በሚያደርጉ እና እርምጃዎችን በሚወስዱ ጽንፈኞች ላይ አሁኑኑ የእርምት እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል። ነገር ግን የእውነት እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን በአፋዊ ሰላም እና ጸጥታ እንዲሁም የልማት እንቅስቃሴዎች ከውስጥ የሚታፈኑ ከሆነ ዛሬ ላይ ሰፈራችን እና እድራችን ሰላም ሆነን ቢመስለንም ነገ የሚገጥመን ችግር ግን እጅጉን የተወሳሰበ እና መራራ መሰዋትነት የሚያስከፍል ይሆናል።
የተፈጠሩ ችግሮችን ምክንያቶች በመለየት እና በጠረጴዛ ዙሪያ ተወያይቶ መፍትሄ በማፈላላግ በሰፈራችን እና በእድራችን የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ማስቀጠል ያስፈልጋል። በጽንፈኝነት ከሰሜን እና ከደቡብ ዋልታዎች ላይ የቆማችሁ ጽንፈኛ ብሔርተኞች እየሄዳችሁብት ሰፈር እና እድራችንን የሚያፈርስ ተግባር ነው። ስለሆነም በጽንፈኝነት ከሰሜን እና ከደቡብ ዋልታዎች ላይ መቆሙን ትታችሁ ዛሬውኑ ሳይረፍድ ኑና ስለእናታችን እድገት እና ብልጽግና ሀሳብ እናዋጣ መልዕክቴ ነው። ሰላም !!! ብሎ ንግግሩን ሲጨርሱ የሰፈራችን ሰዎች በጭብጨባ አጀቧቸው። ስብሰባውም በዚሁ ተቋጨ።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2015