በኢንዱስትሪ መነኻሪያነታቸው ከሚታወቁት የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል ‹‹የበረሃዋ ገነት›› ድሬዳዋ አንዷ ነች።ድሬዳዋ የነዋሪዎቿ እንግዳ ተቀባይነትና አስደናቂ ኅብር ለኢንቨስትመንት ሥራ ምቹና ተመራጭ አድርጓታል።በማምረቻ ዘርፍ (Manufacturing Sector) የተሻለ የኢንቨስትመንት አቅምና ምቹ ሁኔታ ያላት ‹‹የኢንዱስትሪ ኮሪደር›› የሆነችው ድሬዳዋ ከተማ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ፣ በኢንቨስትመንት ዘርፍ እያደረገች ባለችው መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ትርጉም ያለው ውጤት እያስመዘገበች እንደሆነ ይነገርላታል።
ኢንቨስትመንት በድሬዳዋ
የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመርን ተከትላ የተቆረቆረችው ድሬዳዋ፣ በንግድ ማሳለጫነቷ ተጠቃሽ ከተማ ናት።ይሁን እንጂ ይህ የንግድ መነኻሪያነቷ ተቀዛቅዞ ቆይቷል።ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ድሬዳዋ ቀደም ሲል ወደምትታወቅበት የንግድ መነኻሪያነቷ ለመመለስ ጥረት እያደረገች ትገኛለች።
የዚህ ጥረቷ ማሳያ ከሆኑ ተግባራት መካከል አንዱ ከተማዋ በኢንቨስትመንት ዘርፍ እያደረገችው ያለው እንቅስቃሴ ነው።የከተማዋን የኢንቨስትመንት ዘርፍ ችግሮች በመፍታት የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለመጨመር ዘርፉ በቦርድ እንዲመራ ተደርጓል።ይህም ሁሉም የኢንቨስትመንት ዘርፍ ጉዳዮች በቦርዱ እየታዩ የዘርፉ ችግሮችም ሆኑ የባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች ፈጣንና የተደራጀ ምላሽ እንዲያገኙ ለማድረግ ታስቦ የተወሰደ እርምጃ ነው።
በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የኢንቨስትመንት ጥናትና ፕሮሞሽን ቡድን መሪ አቶ አበራ መንግሥቱ እንደሚናገሩት፣ በድሬዳዋ ከተማ ያለው የኢንቨስትመንት ዘርፍ እንቅስቃሴ አበረታች ለውጦችን እያስመዘገበ ይገኛል። ከተማዋ ባለፉት ስምንት ወራት በኢንቨስትመንት ዘርፍ ጥሩ አፈፃፀም ማስመዝገብ የቻለች ሲሆን፤ የከተማዋ የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ በስምንት ወራት ውስጥ ብቻ ለ262 አዳዲስ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት እቅድ ይዞ ተንቀሳቅሷል።
ከዚህ ውስጥም ለ245 ባለሀብቶች የኢንቨስ ትመንት ፈቃድ መስጠት የተቻለ ሲሆን፣ ፈቃድ ከወሰዱት ባለሀብቶች መካከል 23 ማኅበራት ይገኙበታል።እነዚህ አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱ ባለሀብቶችም ከ20 ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማስመዝገብ ችለዋል።ባለሀብቶቹ የሚሰማሩባቸው ዘርፎች አገልግሎት (173)፣ ማምረቻ (62) እና ግብርና (10) ናቸው።የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ ወደ ሥራ ሲገቡ ከ21ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል፤ ከዚህ ውስጥም 10 ሺ የሚሆኑት የቋሚ የሥራ እድል ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
አዲስ ፈቃድ ከተሰጣቸው የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መካከል ስድስቱ ግንባታ አጠናቅቀው የምርት እና አገልግሎት የጀመሩ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ ደግሞ በግንባታ፣ በማሽን ተከላና በሌሎች የትግበራ ደረጃዎች ላይ እንደሚገኙ አቶ አበራ አስረድተዋል፡፡
በመሰረተ ልማት አቅርቦት ረገድም ከተማዋ የተሻለ የመሰረተ ልማት አቅርቦትን እውን በማድረግ የባለሀብቶችን ፍሰት ለመጨመር ጥረት ማድረጓን የጠቀሱት አቶ አበራ፤ 202 ሄክታር ስፋት ያለው የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ መንደር የራሱ የኃይል ማከፋፈያ ያለው መሆኑንና ከከተማው የኃይል አቅርቦት ጋር የሚገናኝ ባለመሆኑ የኃይል መቆራራጥ ስጋት አለመኖሩን ገልጸዋል።ባለሀብቶችም ለዚህ ጥሩ የሆነ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ጥሩ ዕይታ እንዳላቸው ምስክርነታቸውን መስጠታቸውን አቶ አበራ እንደሚገልጹ ይናገራሉ።የኢንዱስትሪ መንደሩ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ቀደም ሲል በተደጋጋሚ እየተቆራረጠ በኢንቨስትመንት ተቋማት ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሲያሳድር ለነበረው የኃይል አቅርቦት ችግር አስተማማኝ መፍትሄ የሰጠ የመሰረተ ልማት አቅርቦት እንደመሆነም ይናገራሉ።
የኢንዱስትሪ መንደሩ የውስጥ ለውስጥ ጥርጊያ መንገድም በቀጣይ የሚሻሻሉ ክፍሎች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ መንገዱ በጥሩ ይዞታ ላይ የሚገኝ ነው።ድሬዳዋ እምቅ የሆነ የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት ያላት በመሆኗ እንዲሁም ከከተማዋ የውሃ አቅርቦት ውስጥ ለኢንቨስትመንት የተመደበ ውሃ በመኖሩ፣ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የውሃ አቅርቦት ችግር አያጋጥማቸውም።
ባለሀብቶችን ለማበረታታት የሚተገበረው የአሰራር ስርዓት በአገር አቀፍ ደረጃ የተዘጋጀ ህጋዊ ማዕቀፍ እንዳለው ይታወቃል።በዚህ ረገድ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርም ህጋዊ ማዕቀፎቹን መሰረት በማድረግ ወደ ከተማዋ የሚገቡ ባለሀብቶችን ለማበረታታት የሚያስችሉ አሰራሮችን ተግባራዊ ያደርጋል።
እንደ አቶ አበራ ገለፃ፣ ለባለሀብቶች የሚሰ ጠው የአንድ መስኮት አገልግሎት ባለሀብቶች ለፕሮጀክቶቻቸው አስፈላጊ የሆኑ የግብዓቶችን ሲጠይቁ በቀላሉ ማቅረብና በፍጥነት ምላሽ ማግኘት ያስችላል።ይህ አሰራር ቀደም ሲል የሀብት (የጊዜና የገንዘብ) ብክነት ያስከትል የነበረውን የሥራ ሂደት የለወጠና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት አስችሏል።በአገር አቀፍ ደረጃ የሚተገበረውን የማበረታቻ መመሪያ መሰረት አድርገው የሚፈፀሙት መሬት ከሊዝ ነፃ የማቅረብ፣ ቀልጣፋ አሰራሮችን የማመቻቸትና ሌሎች ተግባራት ባለሀብቶችን የማበረታቻ እርምጃዎች አካል ናቸው።
የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ካሏቸው ፋይዳዎች መካከል አንዱ ፕሮጀክቶቹ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሚከናወኑባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረጋቸው ነው።በዚህ ረገድ በድሬዳዋ ከተማ ውስጥ የሚከናወኑ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የከተማዋንና የአካባቢውን ህብረተሰብ በተለያዩ መንገዶች ተጠቃሚ ያደርጋሉ፡፡
ባለሀብቶች ወደ ከተማዋ ሲገቡ በተለያዩ መንገዶች የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።ከእነዚህ መካከል አንዱ የሥራ እድል ፈጠራ ነው።የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ ለበርካታ የከተማዋና የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ እድል ፈጥረዋል።ነዋሪው ከሥራ እድል በተጨማሪ በምርትና አገልግሎት አቅርቦት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በገበያ እድል ተጠቃሚ እንዲሆን ይጠበቃል።ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ሥራዎቻቸውን በሚሰሩባቸው አካባቢዎች የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ተግባራትን ስለሚያከናውኑ የአካባቢው ኅብረተሰብ በዚህ ተግባር በኩልም ተጠቃሚ ይሆናል።ይህ የማኅበረሰቡ ተጠቃሚነት ማኅበረሰቡ ለኢንቨስትመንት ፕሮ ጀክቶች አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረው አድርጓል።
የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና እና የከተማዋ ኢንቨስትመንት
አገራት የወጪና ገቢ ንግዳቸውን ለማቀላጠፍና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰታቸውን ለማሳደግ ብሎም አጠቃላይ ምጣኔ ሀብታዊ እድገታቸውን ለማሻሻል ከሚተገብሯቸው አሰራሮች መካከል አንዱ ነፃ የንግድ ቀጠናዎችን (Free Trade Zones) ማቋቋም ነው።
ነፃ የንግድ ቀጠና ‹‹ልዩ የኢኮኖሚ ቀጠና›› (Special Economic Zones) የሚባሉት የንግድና ኢንቨስትመንት መከወኛ ስፍራዎች አካል ሲሆን እሴት የሚጨምሩ የምርት፣ የሎጂስቲክስ፣ የፋይናንስ አቅርቦትና መሰል ተግባራትና አገልግሎቶች የሚከናወንበት ቦታ ነው።በዚህ ስፍራ ምርቶችን ከማምረት በተጨማሪ አስመጪና ላኪዎች ዕቃዎችን ወደ አገር ውስጥ በማምጣት በቀጠናው ውስጥ የሚያከማቹበት፣ የሚያቀነባብሩበት እንዲሁም መልሰው ለውጭ ገበያዎች የሚያቀርቡበት እንዲሁም ሒደቱን ለማሳለጥ ቀልጣፋ የሆነ የሎጂስቲክስ አገልግሎት የሚቀርብበትም ነው።የተቀናጁ የፋይናንስና የምክር አገልግሎቶችም ይሰጥበታል።
ነፃ የንግድ ቀጠና ኢንቨስትመንትን የሚጨምር፣ አዳዲስ የሥራ ዕድሎች ለመፍጠር የሚያግዝ፣ ቢሮክራሲያዊ የአሰራር ውጣ ውረዶችን የሚቀንስ አማራጭ እንደሆነ ይነገራል።ይህ ቀጣና የንግድ እንቅፋቶች የሌሉበት እንዲሁም ቀረጥና ግብር ያነሰበት የንግድና ኢንቨስትመንት ማሳለጫ አካባቢ እንደሆነም ይገለፃል።በነፃ የንግድ ቀጠናዎች ውስጥ የሚተገበሩ ህጋዊ አሰራሮች በሌሎቹ አካባቢዎች ከሚተገበሩት ጋር ሲነፃፀሩ የላሉና አንፃራዊ ነፃነትን የሚያጎናጽፉ ናቸው።
ይህን ታሳቢ በማድረግም የኢትዮጵያን የወጪና ገቢ ንግድ በማቀላጠፍና የኢንቨስትመንት ፍሰቱን በመጨመር ለአገራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት ተስፋ የተጣለበት የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና (Dire Dawa Free Trade Zone)፣ ነሐሴ 8 ቀን 2014 ዓ.ም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ ሥራ እንደጀመረ ይታወሳል።
በድሬዳዋ የሚገኘውን የኢንዱስትሪ ፓርክና ደረቅ ወደብን ከዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት፣ ከባቡርና ከመንገድ ትራንስፖርት ጋር በማቀናጀት እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ የባንክና የጉምሩክ አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ ወደ አገልግሎት እንዲገባ ለማድረግ የሚያስችሉት ተግባራት ሲከናወኑ ከቆዩ በኋላ ሥራ እንዲጀምር የተደረገው ነፃ የንግድ ቀጠናው፤ ለበርካታ ዓመታት ከነፃ የንግድ ቀጠና አሰራር ርቆ ለኖረው የኢትዮጵያ ንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ እድገት ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው ተገልጿል።
ቀደም ሲል የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ የነበረው የአሁኑ የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና፣ ከአገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴና የሎጂስቲክስ አቅም መጎልበት ጋር ተያይዞ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ወደ ነፃ ንግድ ቀጠናነት እንዲሸጋገር ተደርጓል።ነፃ የንግድ ቀጠናው በመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው በ150 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን አራት ሺ ሄክታር መሬት የማስፋፈፊያ ቦታ ተዘጋጅቶለታል።
አቶ አበራ እንደሚሉት፣ ድሬዳዋ በንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የላቀ አፈፃፀም እንድታስመዘግብ ከሚያስችሏት መልካም እድሎችና ግብዓቶች መካከል አንዱና ዋናው የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ነው።በአሁኑ ወቅት በርካታ ባለሀብቶች በነፃ የንግድ ቀጠናው ለመሰማራት ፍላጎት እያሳዩ ነው።ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ የባለሀብቶች ፍሰት እየታየ ነው።ነፃ የንግድ ቀጠናው ወደ ከተማዋ የሚገባውን የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር ትልቅ አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።
ቀልጣፋና ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ በመፍጠር በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ለመሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማስተናገድ ዘርፈ ብዙ ዝግጅቶች እንደሚያስፈልጉ አይካድም።በዚህ ረገድ የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ለባለሀብቶች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ የነፃ ንግድ ቀጠናው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሚል ኢብራሂም ቀደም ሲል ለኢትዮጵያ ፕሬስ ደርጅት ገልፀው ነበር።
እርሳቸው እንዳሉት፤ የነፃ ንግድ ቀጠናውን መቋቋም ተከትሎ እየጨመረ የመጣውን የባለሀብቶች ፍሰት በብቃት በማስተናገድ ነፃ የንግድ ቀጠናውን ውጤታማ ለማድረግና አገራዊ ተጠቃሚነት እውን እንዲሆን የባለሀብቱን ፍሰት የሚመጥን አገልግሎት ለማቅረብ እየተሰራ ነው።ነፃ የንግድ ቀጠናው መቋቋሙን ተከትሎ የባለሀብቶች ፍሰት እየጨመረ በመምጣቱ የንግድ ቀጠናው ብዙ ዝግጅቶችን እያደረገ ነው።የሥራ መመሪያዎችና ደንቦች ተዘጋጅተዋል።በነፃ የንግድ ቀጠናው ውስጥ የማምረቻ፣ የሎጂስቲክስና የመጋዘን (Warehouse) አገልግሎቶች ይሰጣሉ።የንግድ ቀጠናውን የአገልግሎት አቅም፣ እየጨመረ ከመጣው የባለሀብቶች ፍሰት ጋር ለማጣጣም መሬትን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ ነው።
የኢንቨስትመንት መሰናክሎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች
ድሬዳዋ በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ መልካም አፈፃፀምን እያሳየች ብትሆንም በዚህ አፈፃፀሟ ላይ መሰናክል የሚፈጥሩ ተግዳሮቶች አልታጡም።ከእነዚህ መሰናክሎች መካከል በባለሀብቶች በኩል የሚስተዋሉት ፈጥኖ ወደ ሥራ ያለመግባት ችግር እና ለኢንቨስትመንት ተግባር የወሰዱትን መሬት አጥሮ ማስቀመጥና ሌላ ማስተላላፍ ይጠቀሳሉ።ችግሮቹን ለመፍታት ባለፉት ሦስት ዓመታት በተሰሩ ሥራዎች ጥሩ መሻሻሎች ታይተዋል።
በመንግሥት በኩል የሚታዩት ለባለሀብቶች የሚደረጉ ድጋፎችን እስከታችኛው የፕሮጀክቶቹ አፈፃፀም ድረስ በመውሰድ ድጋፎቹንና ክትትሎቹን በሚፈለገው ያለመፈፀም እና ጥፋት በሚያጠፉ አካላት ላይ ፈጥኖ እርምጃ ያለመውሰድ ክፍተቶችም ሌሎች የዘርፉ ችግሮች እንደሆኑ አቶ አበራ ይገልፃሉ፡፡
‹‹ድሬዳዋ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚኖራትን ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ በመለየት ረገድ ቀዳሚው ተግባር ከተማዋ ያላትን የኢንቨስትመንት አቅም መለየት ነው›› የሚሉት አቶ አበራ፣ ይህን ታሳቢ ያደረገ የኢንቨስትመንት ልማት እንደሚከናወን ያስረዳሉ።
‹‹ወደ ድሬዳዋ የሚገቡ ባለሀብቶች ከተማዋን፣ ነዋሪውንና አገርን የሚጠቅሙትና እነርሱም ውጤታማ የሚሆኑት በየትኛው ዘርፍ ቢሰማሩ ነው?›› ለሚለው ወሳኝ ጥያቄ አጥጋቢና ትክለኛ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል።በዚህ ረገድ ድሬዳዋ ዋናው የኢንቨስትመንት አቅሟ የማምረቻው ዘርፍ (Manufacturing Sector) ነው።
ከተማዋም ‹‹የኢንዱስትሪ ኮሪደር›› ተብላ ትታወቃለች።የከተማ አስተዳደሩ የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት አቅም ልየታ ሥራ (Project Profile) ሲያከናውን አብዛኞቹ የማምረቻ ዘርፉ ላይ ያተኮሩ ናቸው።ቀደም ሲል የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ የነበረውና የአሁኑ የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ውስጥ 4185 ሄክታር መሬት ለባለሀብቶች መዘጋጀቱም አምራች ዘርፉን ለማስፋፋት ያለውን ፍላጎት ያመለክታል።
ስለሆነም የድሬዳዋ ኢንቨስትመንት ዋናው የትኩረት አቅጣጫ የማምረቻው ዘርፍ ነው።የከተማ አስተዳደሩም ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ያለው በዚሁ ዘርፍ ላይ ነው።የኢንቨስትመንት አዋጁም (አዋጅ 1180/2012) ለማምረቻ ዘርፉ ትኩረት የሚሰጥ በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴም በአዋጁ መሰረት የተቃኘ ነው፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2015