ለ2023 የኮትዲቯር አፍሪካ ዋንጫ ሶስተኛና አራተኛ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎቹን ከጊኒ አቻው ጋር ሞሮኮ ላይ ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን(ዋልያዎቹ) አንድም ነጥብ ማግኘት ሳይችል ወደ አገሩ ተመልሷል። በዚህም ወደ አፍሪካ ዋንጫው የማለፍ እድሉ የጠበበ ሆኗል። የዋልያዎቹ አለቃ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከሁለቱ የጊኒ ጨዋታ ሽንፈቶች በኋላ እዚያው ሞሮኮ እያሉ መግለጫ መስጠታቸው የሚታወስ ሲሆን ወደ አገር ቤት ተመልሰው የሚሰጡት መግለጫም ተጠባቂ ነበር።
አሰልጣኝ ውበቱ ከፌዴሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን ጋር በመሆን ከትናንት በስቲያ በፌዴሬሽኑ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከጊኒ አቻቸው ጋር በነበራቸው የ180 ደቂቃ ጨዋታ ዙሪያ በሰጡት መግለጫም ዋልያዎቹ ላሳዩት ደካማ አቋም ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አንዱ ምክንያት መሆኑን በመግለፅ ወቀሳቸውን አቅርበዋል።
በሊጉ የሚታየው እንቅስቃሴ ቡድኑ ውስጥ ስላሳረፈው ጫና የተጠየቁት አሰልጣኝ ውበቱ “ሊጉም ይቋረጣል ወጥ የሆነ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ክለቦች ማነስ አይተናል፣ የተጨዋቾች ወጥ አቋም ማየት ላይ አስቸጋሪ ሆኖብናል፣ ሌሎች ሀገሮች ወጥ ብሔራዊ ቡድን አባላት ይኖራቸውና አንድ ሁለት ሊቀይሩ ይችላሉ እኛ ግን ሁለት አመት የሚቆዩ ወጥ ተጨዋቾች ማግኘት ተቸግረናል፣ በአጭር ቀናት ውስጥ መጫወት ጫና አለው ሜዳ በተመለከተ አሁንም ችግር ነው በመጥፎ ሜዳ ላይ የሚጫወቱ ወደ ጥሩ ሜዳ ሲመጡ ክፍተት ይፈጠራል፣ ይሄም አንድ ችግር ነው” በማለት የተናገሩ ሲሆን ከጊኒ ጋር በነበረው ጨዋታ ግን ከሜዳውና ከሊጉ ይልቅ ተጠያቂ የሚያደርጉት የራሳቸውን ቡድን ዝግጅት መሆኑን አስረድተዋል።
ዋሊያዎቹ ወደ ኮትዲቯር የአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ዕድላቸው መጥበቡን የገለፁት አሰልጣኝ ውበቱ፣ “ ከጊኒ ጋር ማሳካት የፈለግነውን ውጤት አላሳካንም፣ የመጀመሪያው ጨዋታ ደካማ አቋም አሳይተናል፣ ሁለተኛው በንጽጽር የተሻለ ነበር፣ ያም ሆኖ በተገኘው ውጤት መሰረት ወደ ኮትዲቯር የአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ዕድላችን ጠቧል” ሲሉ ተናግረዋል።
አሰልጣኙ እንደሚሉት “ከመጀመሪያው የኒጀር ጨዋታ ጀምሮ ቡድኑ ጥሩ መደላደል ላይ ነበር ማለት አይቻልም፣ በሁለቱ አመታት ውስጥ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ መገኘት በራሱ ስኬት ነው፣ እኛ እንደ አልጄሪያ ግብጽና ናይጄሪያ በየአፍሪካ ዋንጫው የምንገኝ አይደለንም እናም በሻምፒዮናው ላይ መገኘታችንን እንደ ስኬት እቆጥራለሁ፣ ውድድሩ ላይ ገብተን ያሳየነው ድክመት ግን መሻሻል አለበት። ስኬታማ ነኝ ብለው ያስባሉ ወይ? ተብ ለው ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡም፣ “ወደ ኮትዲቯር የአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ዕድላችን ጠቧል በቀጣይ ግብጽን ስንገጥም የምንችለውን እናደርጋለን ለወደ ፊትም ሽንፈት ቢገጥመን ዋናው ጉዳይ ከሽንፈት መነሳት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ቡድኑ እየተመራ ይስቁ ስለነበሩ ተጨዋቾች የተጠየቁት አሰልጣኙ “እንኳን ተጨዋቾቼ ማንም በቡድኑ ሽንፈት አይስቅም ለምን ሳቁ የሚለው ግን መታየትና መመርመር አለበት” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ውበቱ ከወራት በፊት ዋልያዎቹን በማሰልጠን እንዲቀጥሉ ተጨማሪ የሁለት አመት ኮንትራት ሲሰጣቸው ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ የማብቃት ኃላፊነት አብሮ እንደተሰጣቸው ይታወሳል። ይህ ካልሆነም አሰልጣኙ ከቡድኑ ጋር እንደሚለያዩ በርካቶች ጠብቀዋል። ዋልያዎቹ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የሚያልፉበት እድል ከጊኒው የደርሶ መልስ ጨዋታ በኋላ መጥበቡን ተከትሎ አሰልጣኝ ውበቱ ከቡድኑ ጋር ስለሚኖራቸው ስንብት አስበው ያውቃሉ ተብለው በመግለጫው የተጠየቁት ሲሆን “ቀሪ ኮንትራት አለኝ በድንገት ተነስቼ የምወስነው ነገር የለም፣ ከቀጣሪዎቼ ጋር መነጋገር ይኖርብኛል፣ ምንም የሚያስቸኩል ነገር የለም” ሲሉ መልሰዋል።
ከተጨዋቾቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄም፣ “የማስገባቸው ተጨዋቾች ደስ ሊላቸው የማይገቡት ደግሞ ቅር ሊላቸው ይችላል፣ ነገር ግን ሁሉም ለህግና ስርዓት ሊገዙ ይገባል፣ ከዚያ ውጭ በግሌ ከማንም ጋር ችግር የለብኝም “ በማለት መልስ ሰጥተዋል።
ፌዴሬሽኑ ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር ስላለው ውል ዝርዝር የተጠየቁት የፌዴሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን በበኩላቸው “ከአሰልጣኝ ውበቱ ጋር መነጋገራችን አይቀርም፣ ከአሰልጣኙ ጋር በነበረው ውል ዙሪያ የቱ ተሳካ ..? ምኑስ አልተሳካም የሚለውን የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አይቶ በቀጣይ ውሳኔ የሚሰጥበት ይሆናል፣ አሁን ላይ ግን ምንም መናገር አልችልም” ሲሉ ተናግረዋል።
በማጣሪያው በምድብ አራት ከግብጽ፣ ማላዊ እና ጊኒ ጋር የተደለደሉት ዋልያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ብቻ ይቀሩታል። ይህንን ተከትሎም አሰልጣኙ ከሽንፈት በኋላ እንዴት አገግሞ መመለስ ይቻላል የሚለው ላይ እንደሚያተኩሩ ጠቁመዋል።“ የአንድ ቀን መውደቅ የሁልጊዜ መገለጫ ተደርጎ መታየት የለበትም” የሚሉት አሰልጣኝ ውበቱ፣ እስካሁን የነበረው ስነልቦና መሰናክል ቢያገኘውም ከዚያ ስሜት መውጣት የግድ መሆኑን አስረድተዋል። ምናልባትም ቡድኑ ከውድድሩ ወጥቶ ሊሆን ይችላል ነገር ግን ከዚህ ቀደም እንደታዩ የከፉ ሽንፈቶች አይደሉም፡፡ በመሆኑም ቡድኑ በውድድር እስካለ ድረስ ለቀጣይ መታገል የግድ ነው፡፡ ቀጣይ ተጋጣሚዎቻችን በነጥብ የራቁን ቢሆንም አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ የግድ ነው፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መጋቢት 27/2015