ከአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ዙሪያ ነዋሪዎች አቤቱታ ጋር በተያያዘ ከአቤቱታ አቅራቢዎች እና ከሰነዶች የተገኙ የተለያዩ ማስረጃዎች፤ እንዲሁም ከተለያዩ የቢሮ ኃላፊዎች የተገኙ ምላሾች ተካተው ለአንባቢያን ፍርድ በሚያመች መልኩ እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 6፣ በተለምዶ አዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ዙሪያ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚገኙ ከ65 በላይ የሚሆኑ አባወራዎች «በራሳችን ወጪ እና መሬት ላይ የሠራነው፣ እንዲሁም ከ60 ዓመት በላይ የኖርንበት ቤታችን ምክንያቱ በውል ባልታወቀ ሁኔታ ‘ቤቱ የመንግሥት ስለሆነ ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ጋር የቀበሌ ቤት ኪራይ ውል ተዋዋሉ’ ተብለን ተገደናል። በራሳችን መሬት እና ወጪ ሠርተን ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በኖርንበት ቤት፤ ሕግ ባለበት አገር፣ እንዴት ከአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ጋር የኪራይ ውል ተዋዋሉ እንባላለን? የኢትዮጵያ ሕዝብም መንግሥት ለሕዝብ እንዲያገለግሉ ባስቀመጣቸው ሹመኞች እየደረሰብን ያለውን በደል ተመልክቶ ይፈረደን» ሲሉ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አቤት ብለዋል።
በአዋጅ ቁጥር 47/67 ትርፍ ቤት የተወረሰባቸው አቤቱታ አቅራቢ
እማሆይ አፀደ ረታ ይባላሉ፤ አሁን ላይ ውዝግብ የተነሳበትን ቤት በራሳቸው የገንዘብ እና የጉልበት ወጪ እንደሠሩት፤ በቤቱም ከአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ እየኖሩበት እንደሚገኙ ይናገራሉ።
እንደ እማሆይ አፀደ ገለጻ፣ በ1967 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 47/67 የደርግ መንግሥት ትርፍ ቤቶችን ሲወርስ ከአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ማዶ በሚገኘው፣ ቀበሌ 58 እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የነበረ አንድ ቤታቸውን ተወርሰዋል። ቤታቸው ሲወረስ «በአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ዙሪያ ከሚገኘው እና በቀበሌ 58 ከሚገኘው ቤት የትኛው ቢወረስ ይመርጣሉ?» ብሎ መንግሥት እንደጠየቃቸው የሚናገሩት ወይዘሮ አፀደ፣ እርሳቸውም በቀበሌ 58 የሚገኘው ቤት ተወርሶ በአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ዙሪያ የሚገኘው ቤት እንዲተውላቸው ማድረጋቸውን ያስረዳሉ። ለዚህ በምክንያትነት ያነሱት ደግሞ በአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ዙሪያ የሚገኘው ቤታቸው ለባለቤታቸው ሥራ ቅርብ መሆኑን ነው።
የተወረሰው ቤት እስካሁንም ድረስ በቤቶች አስተዳደር ሥር እንደሚገኝ የጠቆሙት እማሆይ አፀደ፤ ስለተወረሰው ቤታቸው የሚያስረዳ ሰነድ እንዳላቸውም አመልክተዋል። የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም ይህንኑ እውነት አረጋግጧል።
ይሁን እንጂ በራሰቸው የገንዘብ እና የጉልበት ወጪ የሠሩትን ቤት በ2002 ዓ.ም አንድ የወረዳ 6 አመራር በማን አለብኝነት ከአሠራር ውጪ «ቤቱ የመንግሥት ስለሆነ የቤት ኪራይ ውል ከመንግሥት ጋር ተዋዋሉ» ብሎ ማስገደዱን ይናገራሉ። ይህም ልክ ያልሆነ እና ሕጋዊ መሠረት የሌለው ነው ያሉት እማሆይ አፀደ፣ በተፈጠረው ችግርም ቤታቸውን ማደስ ባለመቻላቸው አሁን ላይ በእርጅና ዘመናቸው ለከፍተኛ ችግር ተዳርገው እንደሚገኙ ተናግረዋል። በመሆኑም መንግሥት የደረሰባቸውን ችግር ተመልክቶ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
ሌላኛዋ አቤቱታ አቅራቢ ወይዘሮ እህተ ፍርሼ ይባለሉ። የ80 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ ናቸው። በአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ለ26 ዓመታት በቋሚነት እና ቁጥሩን በውል ለማያስታውሱት በርካታ ዓመታት ደግሞ በጊዜአዊነት ማገልገላቸውን ይናገራሉ።
እንደ ወይዘሮ እህተ ገለጻ፣ በአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ሲቀጠሩ የወር ደመወዛቸው አንድ ብር ከአስር ሳንቲም ነበር። የሚያገኟት ገንዘብ ትንሽ ብትሆንም ከሥራ መልስ ወገባቸውን የሚያሳርፉበት ቤት ያስፈልጋቸው ስለነበር ከሚያገኟት ደመወዛቸው ቀንሰው አሁን ላይ ውዝግብ የተነሳበትን ቤት ሠሩ።
እንደ ወይዘሮ እህተ ገለጻ፣ አሁን ያሉበት ቦታ ላይ ከኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ኖረውበታል። የደርግ መንግሥት 47/67 ዓዋጅን ከማወጁ በፊት በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ሁለት ቤቶች ነበሯቸው። በአዋጁ መነሻነት አንዱ ቤታቸው በመንግሥት ተወሰደባቸው። አንደኛው ቤት በአዋጅ ቁጥር 47/67 መሠረት ሲወረስ የትኛው ቤት በራሳቸው ይዞታ እንዲቀርላቸው እንደሚፈልጉ መንግሥት ጠይቋቸው እንደነበርና እርሳቸውም ለሥራ ቅርበት ሲሉ በአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ዙሪያ የሚገኘውን ቤት መምረጣቸውን ይናገራሉ። የተወረሰው ቤታቸውም በድሮው ቀበሌ 58 የሚገኝ ሲሆን እስከዛሬም ድረስ የአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር በባለቤትነት እያስተዳደረው እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ቀበሌ 58 የነበረው ቤት ከመወረሱ በፊት የተመሩበት እና ቤቱን በአዋጁ መሠረት ለመንግሥት ያስረከቡት ሰነድ በእጃቸው እንደሚገኝ የተናገሩት ወይዘሮ እህተ ፍርሼ፣ ሰነዶቹንም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ማቅረብ ችለዋል።
ከሰነዶች የተገኙ ማስረጃዎች
ከሰነዶች የተገኙ ማስረጃዎች በርካታ በመሆናቸው ሁሉንም ማቅረብ አይቻልም። ይሁንና የኢትዮጵያ ሕዝብ ግራ ቀኙን አይቶ ይፈርድ ዘንድ ያስችሉታል ያልናቸውን ሰነዶች መርጠን በዚህ ጽሑፍ አካተናል።
ሰነድ አንድ፡- አቤቱታ አቅራቢዎቹ ቤቶች የመንግሥት ስለሆኑ የኪራይ ውል ተዋዋሉ ተብለው መነገሩን ተከትሎ አቤቱታ አቅራቢዎች ችግራቸው እንዲፈታ ለአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር አቤት ይላሉ። የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደርም ስለጉዳዩ ለማጣራት በቁጥር አቃ/ቃ/ክ/ከ/ቤ/ል/ማኔ በቀን 07/01/2006 ለባለአደራ ቦርድ፣ ለፕራይቬታይዜሽን ኤጄንሲ፣ ለአቃቂ ቃሊቲ መሬት ልማት ማኔጅመንት እና ለአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ደብዳቤ ጻፈ። ለሁሉም መስሪያ ቤቶች የተጻፈው ደብዳቤ በአንድ ቁጥር እና ቀን ነው። ይህን ተከትሎ የባለአደራ ቦርድ፣ ፕራይቬታይዜሽን ኤጄንሲ እና የአቃቂ ቃሊቲ መሬት ልማት ማኔጅመንት አቤቱታ ስለተነሳባቸው ቤቶች የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ሲገልጹ፤ አዋሽ ቆዳ ፋብሪካም ለቤቶች ለተወሰኑ አመታት የመብራት እና የውሃ ወጪ ይችላቸው እንደነበር፤ ነገር ግን ስለቤቶች ምንነት እንደማያውቅ ለቤቶች አስተዳደር በደብዳቤ አሳወቀ።
ሁሉም መስሪያ ቤቶች ስለጉዳዩ እንደማያውቁ ይግለጹ እንጂ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ቤቶቹ የመንግሥት ናቸው ተብሎ ከመስሪያ ቤቶች እንደተገለጸ በማስመሰል ለአቤቱታ አቅራቢዎቹ ጥያቄ ምላሽ ሳይሰጥ ቀረ።
ሰነድ ሁለት፡- አቤቱታ ከአቀረቡት መካከል ለተወሰኑት ሰዎች ካርታ ተሠርቶ የተሰጣቸው ሲሆን፤ ለተወሰኑት ደግሞ የአፈር ግብር እንዲከፍሉ በማድረግ ሰነድ አልባ መብት እንዲፈጠርላቸው የማድረግ እንቅስቃሴዎች አሉ።
ሰነድ ሦስት፡- የተወሰኑ አቤቱታ አቅራቢዎች በአዋጅ ቁጥር 47/67 ትርፍ ቤት እንደተወሰደባቸው፤ አሁን ያሉበትና በአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ዙሪያ ሰፈር የሚገኘውን ቤት መርጠው እንደቀየሩ የሚያሳዩ ናቸው።
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የወረዳ 6 ዋና ሥራ አስፈጻሚ ምላሽ
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ የምርመራ ክፍል በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ፣ የወረዳ 6 ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑትን አቶ ቶፊቅ ከድርን በአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ዙሪያ ስለሚገኙ ቤቶች ምን ያውቃሉ? ሲል ጠይቆ ነበር። አቶ ቶፊቅም የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተውናል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቶፊቅ እንደገለጹት፣ ስለቤቶቹ የተወሰኑ ጉዳዮችን ቢያውቁም የተሟላ መረጃ ግን የላቸውም። ይሁን እንጂ፣ በእነዚህ ቤቶች የሚኖሩ ሰዎች ከወረዳው ማግኘት ያለባቸውን አገልግሎቶች እያገኙ አለመሆናቸውን ይገነዘባሉ። አሁን ላይ ነዋሪዎቹ ከወረዳው ማግኘት የነበረባቸውን እንደ ውሃ፣ መብራትም እና መሰል አገልግሎቶችን እያገኙ አይደለም። በዚህም ለከፋ ችግር ተዳርገዋል።
ከቤቶች ጋር ተያይዞ ቁርጥ ያለ ውሳኔ ባለመኖሩ የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ነዋሪዎች የተለያዩ አገልግሎቶችን ፈልገው ወደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ቢሮ በመጡ ጊዜ ከመንግሥት ማግኘት የሚገባቸውን የተለያዩ አገልግሎቶች ለመስጠት መቸገራቸውን አቶ ቶፊቅ ያስረዳሉ። አንዳንዴ ችግሩ በጣም የከፋ ሲሆን በሕግ የሚደገፍ ባይሆንም ነዋሪዎችን የንግድ ፈቃድ እንዲያመጡ በማድረግ አንዳንድ አገልግሎቶችን እየሰጡ እንደሚገኙም ነው የሚናገሩት። ነገር ግን ከመብራት እና ውሃ አገልግሎት ጋር ተያይዞ ሥራ አስፈጻሚው ላይ የሕግ ተጠያቂነት የሚያስከትል በመሆኑ እስካሁን ድረስ የተሟላ የመብራት እና ውሃ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ማድረግ አለመቻላቸውን አመላክተዋል። ይሁንና እንደ ዜጋ ነዋሪዎቹ የመብራት እና የውሃን አገልግሎትን ማግኘት እንዳለባቸው ያምናሉ።
ስለጉዳዩ ብዙ የማውቀው ነገር የለኝም ማለት ግን ስለጉዳዩ እያጣራሁ አይደለም ማለት አይደለም ያሉት አቶ ቶፊቅ፤ የተፈጠረውን ውዝግብ በዘላቂነት ለመፍታት ችግሩን ከሥሩ እየመረመሩ መሆናቸውን አመላክተዋል።
በ2014 ዓ.ም ከበላይ አካል በተላለፈ ትዕዛዝ ነዋሪዎችን የኪራይ ውል አዋውሏቸው ተብለው ትዕዛዝ ተላልፎላቸው እንደነበር የሚናገሩት አቶ ቶፊቅ፣ ይሁንና ጉዳዩ ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት ማጣራት ስለሚጠይቅ ችግሩን በይደር ለመያዝ መገደዳቸውን ገልጸዋል።
በአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ዙሪያ የሚገኙ ነዋሪዎች አሁን እየኖሩበት ባለው ቦታ ለረጅም ዓመታት ቆይተውበታል። በዚያ ቦታ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ትውልዶችን እንጂ መጀመሪያ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች አይገኙም። ስለሆነም ቦታቸው በሰነድ አልባ ታይቶ ወደ ሕጋዊነት መምጣት አለበት። በወረዳቸውም አሠራሩ እና መመሪያው በሚፈቅደው ልክ በርካታ ቤቶችን በሰነድ አልባ ሕጋዊ አድርገዋል። የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ነዋሪዎች ጉዳይም በሰነድ አልባ ወደ ሕጋዊ መስመር ቢገባ ለመንግሥት አሠራርም ሆነ ነዋሪዎቹ በሰላም ይኖሩ ዘንድ ምቹ መደላድል የሚፈጥር መሆኑን ያስረዳሉ።
እንደ እነዚህ ያሉ ቤቶች በሊዝ አዋጁም ሆነ ሰነድ አልባ በምንለው መንገድ ተላልፈውም ጭምር ሰነድ እንዲኖራቸው ቢደረግ እና ሰዎች እንዲጠቀሙበት መብት ቢፈጠር፤ እኔ እንደ ዜጋ ደስተኛ ነኝ። እንደ አንድ አመራርም የምደግፈው ጉዳይ ነው የሚሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፣ የክፍለ ከተማ ቤቶች ልማት ጽሕፈት ቤት ጽፎ በነበረው ደብዳቤ ተነስተን በደፈናው ቤቶችን ወደ መንግሥት ይግቡ ለማለት ሕጋዊ የሆነ የሕግ መሠረት ለመያዝ የሚያስቸግር መሆኑንም ተናግረዋል።
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ምላሽ
በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የምርመራ ክፍል ስለአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ዙሪያ ቤቶች ምን ያውቃሉ? ተብለው የተጠየቁት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዳኛው ገብረሚካኤል በበኩላቸው የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተውናል።
የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ሠራተኞች እና ቤቶቻቸውን በሚመለከት ቀደም ሲል ከነበሩ መረጃዎች እና ዶክሜንቶች መሠረት ተደርጎ ታሪካዊ አመጣጣቸው ቢገለጽ ስለቤቶቹ ምንነት የተሟላ እይታ እንዲኖረን ያደርጋል።
አሁን ላይ የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ተብሎ የሚጠራው ድርጅት በ1948 ዓ.ም በአርመን ዜጎች የተመሠረተ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ስሙም ዳር ማር ቆዳ ፋብሪካ ነበር። አርመኖች ፋብሪካውን ለመመስረት በማሰብ ፋብሪው የሚገኝበትን ቦታ በአካባቢው ይኖሩ ከነበሩ ባለእርስቶች ገዙ። ፋብሪካውንም ገነቡ።
በ1948 ዓ.ም ዳር ማር ቆዳ ፋብሪካ ተብሎ የተመሠረተው ድርጅት የደርግ መንግሥት መምጣቱን እና መወረሱን ተከትሎ በ1969 ዓ.ም የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ የሚል ስሜ ተሰጠው። ይህ በእንዲህ እንዳለ ድርጅቱ ለሠራተኞቹ በማሰብ በፋብሪካው አካባቢ ከእንጨት እና ከጭቃ የተሠራ ፎቅ መሰል ጂ ፕላስ ዋን ቤት ሠርቶ በመኖሪያ ቤትነት እንዲገለገሉበት አደረገ።
ቀንን ቀን ሲወልደው ለሠራተኞች መኖሪያ የተሠራው ቤት በእርጅና ምክንያት ፈራረሰ። የድርጅቱ ሠራተኞችም ለመኖር ይቸገሩ ጀመር። ይህን ተከትሎ ድርጅቱ ለሠራተኞች የሚሆን የጭቃ ቤት ለመሥራት በማሰብ ለበላይ መስሪያ ቤቱ ጥያቄ አቀረበ። በወቅቱ ለአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ የበላይ መስሪያ ቤት የነበረው ብሔራዊ ቆዳ እና ጫማ ድርጅት ነበር። የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ለብሔራዊ ቆዳ እና ጫማ ድርጅት የጭቃ ቤቶች ለሠራተኞች እንዲሠራላቸው ሲጠይቅ የዋጋ ግምቱንም ጭምር አስቀምጦ ነበር ጥያቄውን ያቀረበው። ጥያቄውም ተቀባይነት አግኝቶ ተፈቀደ። በዚህ መሠረት ለሠራተኞች በርካታ ቤቶች ተሠሩ። ሠራተኞችም እዚያው እየኖሩ ሥራቸውን ማከናወን ጀመሩ።
መጀመሪያ ላይ የጭቃ ቤት እንዲሠራላቸው ጠይቀው የነበሩት እና በብሔራዊ ቆዳ እና ጫማ ድርጅትም ቤት እንዲገነባላቸው ፍቃድ ያገኙት ሠራተኞች ቁጥር 48 እንደነበር አቶ ዳኛቸው ይናገራሉ።
ቤቶች ከተገነቡ በኋላ ቀጥሎ የመጣው የመብራት እና ውሃ ጥያቄ ነበር። ከዚህ ጋር ተያይዞ ድርጅቱ ለአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ፣ መሬት አስተዳደር አመልክቶ መብራት እና ውሃ ገባላቸው። መብራቱ ሲገባ ሙሉ ወጪ በድርጅቱ የተሸፈነ ቢሆንም ከሠራተኞች የሦስት ወር ደመወዝ የሚቆረጥ ነበር። ይህ የሆነው አዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ወደ ግል ተቋም ዙሮ ኢትዮ ሌዘር ኢንዱስትሪ በሚባልበት ወቅት ነው። በዚህ ጊዜ ነዋሪዎቹ በግላቸው የሚያስተዳድሩት መብራት እና ውሃ ተፈቀደላቸው። ይህ በእንዲህ እንዳለ የነዋሪዎቹ ቁጥርም ከ48 ወደ 59 አደገ። ቀጥሎም ወደ 61 ከፍ አለ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በ2002 ዓ.ም የቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በክፍለ ከተማው የቤቶች ቆጠራ አካሄደ። እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ክፍለ ከተማው በራሱ ተነሳሽነት የቤቶች ቆጠራ ያካሂድ እንጂ የቤት ቆጠራው አገራዊ አልነበረም። ይህን ተከትሎ በወረዳ 6 ውስጥ አዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ዙሪያ የሚገኙ ቤቶች በነዋሪዎችም ሆነ በመንግሥት ያልተመዘገቡ ሆነው ተገኙ ።
ይህን ተከትሎ እነዚህ ቤቶች ምን ይሁኑ የሚል ጥያቄ ተነሳ። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች አስተዳደር ንዑስ የሥራ ሂደትም ለእነዚህ ቤቶች ለምን የኪራይ ተመን አይወጣላቸውም? ሲል በቀን 22/2/ 2003 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማን ጠየቀ።
በዚህም ምክንያት በጥቅምት ወር 2003 ዓ.ም በክፍለ ከተማ ደረጃ ኮሚቴ ተዋቅሮ፣ የከራይ ግምት ተዘጋጅቶ ለአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ተላከ። የተላከውን የኪራይ ግምትም ተከትሎ ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕርጀክት ጽሕፈት ቤት በሚያዝያ 26 ቀን 2006 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ የቤቶች የኪራይ ግምቱ መጽደቁ ተገለጸ። በዚህ መሠረት ቤቶቹ በኪራይ እንዲተዳደሩ የክፍለ ከተማው ቤቶች አስተዳደር ታዘዘ። በተያያዘም፣ ስለቤቶቹ የሚቀየር ነገር ካለ ወደፊት ሊቀየር እንደሚችል በደብዳቤው ተመላክቷል።
ይህን ተከትሎ «የቤቶች አስተዳደር የወሰነው ውሳኔ ትክክል አይደለም» ሲሉ 61 ሰዎች ለተለያዩ መስሪያ ቤቶች አቤቱታ አቀረቡ። አቤቱታ ከቀረበላቸው መስሪያ ቤቶች መካከልም የአዲስ አባበ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት፣ የኮንስትራክሽን እና ቤቶች ልማት ቢሮ፣ የወረዳ 6 ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና የወረዳ 6 ቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት፤ እንዲሁም፣ የመሬት ልማት እና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ተጠቃሽ ናቸው።
አቤቱታ አቅራቢዎችም «ቤቱ ሲሠራ ቦታውን በስጦታ ከባለእርስቶች ወስደን በራሳችን የገንዘብ እና የጉልበት ወጪ ቤት ገንብተን እያለ፤ መብራት እና ውሃም በራሳችን ከፍለን አስገብተን እያለ መመሪያውን እና አሠራሩን ተከትሎ ቦታው ወደ ግል ይዞታ መቀየር አለበት እንጂ እንዴት በኪራይ እንዲተዳደር የኪራይ ተመን ይጣልበታል?» የሚል ጥያቄ ይዘው ነበር ሲከራከሩ የነበሩት።
ይሁን እንጂ የኪራይ ተመኑ በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ጸድቆ ለወረዳ 6 ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና ለወረዳ 6 ቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት፤ እንዲሁም፣ ለመሬት ልማት እና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ወደ ኪራይ እንዲገቡ የሚያዝዝ ደብዳቤ ተጽፎ ስለነበር ጉዳዩ አቤቱታ አቅራቢዎች በፈለጉት መልክ ሊፈታ አልቻለም። አቤቱታ አቅራቢዎቹ ችግራቸው ሳይፈታ በእንጥልጥል እስከዛሬ ድረስ ሊቆዩ ተገደዋል።
የአቤቱታ አቅራቢዎቹ ፍላጎት የመሬት ባለይዞታነት መብት እንዲፈጠርላቸው ሲሆን፣ የወረዳው እና የክፍለ ከተማው ቤቶች ፍላጎት ግን የወጣውን የኪራይ ተመን መሠረት አድርጎ ለማከራየት ነበር። ይሁንና የአቤቱታ አቅራቢዎቹ ጥያቄ የመሬት ባለይዞታነት ማረጋገጫ እንዲሰጣቸው የሚጠይቅ በመሆኑ የቤቶች አስተዳደር መሬት መስጠት እንደማይችል ገልጾ፤ የመሬት ባለይዞታነት ጥያቄአቸው ተፈጻሚነት እንዲኖረው ከፈለጉ ጉዳዩን ለቤቶች አስተዳደር ሳይሆን ለመሬት አስተዳደር ማቅረብ እንደሚገባቸው ምክረ ሀሳብ እንደሰጧቸው ተናግረዋል።
ዛሬም ቢሆን የመሬት ባለይዞታነት ጥያቄ የሚመለሰው በመሬት አስተዳደር እንጂ በቤቶች ልማት ጽሕፈት ቤት አለመሆኑን የገለጹት አቶ ዳኛቸው፤ የሰዎች ጥያቄ ምላሽ ያገኝ ዘንድ የቤቶች አስተዳደር የራሱን ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል። በቅርቡም የቤቶች አስተዳደር የሚደርስበትን ቁርጥ ያለ ውሳኔ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደሚያሳውቁ ገልጸዋል።
የቤቶች አስተዳደር ከመሬት ተነስቶ የቤት ኪራይ ግምት ይሰጣል ወይ? ይህንን አሠራርስ ሕጋዊ የሚያደርግ መመሪያ ወይም አሠራር አለ ወይ? ተብለው በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል የተጠየቁት አቶ ዳኛቸው የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል።
የተለያዩ መመሪያዎች በየጊዜው እየተሻሻሉ መጥተዋል። እኔ የማውቃቸው መመሪያዎች አንደኛው መመሪያ ቁጥር 4፣ 2009 ሲሆን፤ መመሪያ ቁጥር 5፣ 2011 ሁለተኛው፤ አሁን በቅርቡ የወጣው መመሪያ ቁጥር 6፤ 2015 ደግሞ ሦስተኛው ነው። በተዋረድ እነኝህ መመሪያዎች በየዕለቱ እየተለወጡ የመጡበት ሁኔታ አለ። ግን በአጋጣሚ ሆኖ እነኝህ ሁሉም መመሪያዎች ከኪራይ ተመን አወጣጥ እና ከቤት ቁጥር አሰጣጥ አኳያ ሲታይ በማንኛውም መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ወይም በግለሰብ የተሠሩ ቤቶች ወደ መንግሥት አስተዳደር ይግቡ ተብሎ ከታች፣ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክፍለ ከተማው በአስተዳደሩ ሲወሰን እና ወደ መንግሥት ቤትነት ሲቀየሩ የቤት ቁጥር የመስጠት፤ የኪራይ ተመን የማውጣት የቤቶች አስተዳደር ሥራ ይሆናል። ነገር ግን፣ በማንኛውም ሁኔታ የቤቶች አስተዳደር ከመሬት ተነስቶ የኪራይ ተመን ማውጣት አይችልም። እዚህ ላይ የአስተዳደሩ ውሳኔ የሚለውን በአጽኖት ማየት ይገባል። ነገር ግን፣ በማንኛውም ሁኔታ የበላይ መስሪያ ቤትም ቢሆን የቤቶችን ተመን አውጥቶ ወደ ኪራይ አስገቡት የማለት ሥልጣን የለውም።
ለምሳሌ አንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት፣ ለአንድ ለተወሰነ ፕሮጀክት፣ በአንድ አካባቢ ቤት ቢሠራ እና ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ቤቶቹን ለመንግሥት አስረክቦ ሊሄድ ይችላል። ለመንግሥት አስረክቦ ሲሄድ በመንግሥት በኩል የተረከበው አካል ለሕዝብ አገልግሎት እንዲውል ሲታሰብ የኪራይ ተመን ይወጣለታል።
አቤቱታ ካቀረቡት ሰዎች መካከል ለተወሰኑ ሰዎች ተለይቶ ካርታ ተሰጥቷቸዋል፤ ግማሾቹ ደግሞ የአፈር ግብር እየከፈሉ ይገኛሉ። ስለዚህ ምን ትላላችሁ ብለን የጠየቅናቸው አቶ ዳኛቸው ይህን ጉዳይ ለመሬት ማኔጅመንት እንዳቀረቡትና መሬት ማኔጅመንት ደግሞ ምንም ዓይነት ካርታ እንዳልሰጠ በደብዳቤ እንደተገለጸላቸው ተናግረዋል።
የእናንተ መስሪያ ቤት ስለቤቶቹ ለማጣራት ለባለ አደራ ቦርድ እና ለፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ደብዳቤ ጽፎ ነበር። ለደብዳቤአችሁ ምላሽ የሰጡት ከላይ የተጠቀሱት መስሪያ ቤቶች ስለቤቶቹ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል። ታዲያ እናንተ ከእነሱ መረጃ ካላገኛችሁ ቤቶችን የእኛ ናቸው ማለት ትችላላችሁ ወይ? ስንል አቶ ዳኛቸውን ጠይቀን ነበር። ከላይ የተጠቀሱት መስሪያ ቤቶች ውዝግብ የተነሳባቸውን ቤቶች የቤቶች አስተዳደር መሆናቸውን ከገለጹ ውዝግብ የተነሳባቸው የቤቶች አስተዳደር ናቸው ሊባሉ እንደማይችሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።
አሁንም ቢሆን ከቤቶች ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ችግር ሊፈታ የሚችለው በክፍለ ከተማው የመሬት አስተዳደር ነው ያሉት አቶ ዳኛቸው፤ ችግሩ መፍትሄ እስከሚገኝለት ድረስ መመሪያ እና አሠራርን ተከትለው ተባባሪ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
የጋዜጠኛው ትዝብት
ለቤቶቹ የኪራይ ተመን እንዲወጣ የተደረገው የ2002 ምርጫን ተከትሎ ነው። በዚህ ምርጫ አቤቱታ ከተነሳባቸው ቤቶች በአንዱ ይኖሩ የነበሩት አቶ አስራት አራርሳ የተባሉ ግለሰብ የምርጫ ታዛቢ ሆነው ይመረጣሉ። ይሁንና ምርጫው ተጠናቆ በምርጫ ሰነዱ ላይ ፊርማቸውን እንዲፈርሙ ሲጠየቁ ምርጫው ሕጋዊ ሂደቱን ስላልጠበቀ አልፈርምም ይላሉ። ይህን ተከትሎ በወረዳ ስድስት ይሠሩ የነበሩ አቶ ገብረሚካኤል የተባሉ ግለሰብ አንተ እኮ መጀመሪያውኑ የኦነግ ተላላኪ እንደሆንክ እናውቅ ነበር። ፊርማውን አልፈርምም ማለትህ የምትኖርበትን ቤት እንደሚያሳጣህ እንዳትረሳ ብሎ ይዝታል። ይህን ተከትሎ ዛቻው ውሎ ሳያድር ተግባራዊ ሆነ። አንድን ሰው ለመበቀል የተወረወረ ጦር 65 አባወራዎችን ወጋ። ይህ ከበርካታ ሰዎች ጠይቀን ያገኘነው መረጃ ነው።
ሌላውና ጋዜጠኛው መታዘብ የቻለው ደግሞ የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ድርጅት እራሱ ሕጋዊ ካርታ ያገኘው በ2006 ዓ.ም መሆኑን ነው። ድርጅቱ ከ2006 ዓ.ም በፊት ካርታ አልነበረውም። ይህ ሰነድ በማስረጃነት ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ቀርቧል። ሌላው ከድርጅቱ ጋር ተያይዞ በአዋጅ ቁጥር 47/67 መሠረት ሦስት ቤቶች መወረሳቸውን እና በአሁኑ ወቅት ከእነኝህ ሦስት ቤቶች አንዱ ተዘግቶ የሚገኝ ሲሆን፣ ቀሪዎቹን ሁለት ቤቶች ግን የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት እና ቻይናውያን በመኖሪያነት እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ ተመልክተናል።
የመጨረሻው ትዝብት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ዳይሬክተር እና በወረዳ 6 ዋና ሥራ አስፈጻሚ የተሰጠው ምላሽ ቤቶችን ለአቤቱታ አቅራቢዎች ለመመለስ አንድ እርምጃ ወደ ፊት የተጓዘ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ ዳኛቸው ገብረሚካኤልን እና በወረዳ 6 ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑትን አቶ ቶፊቅ ከድር አለማመስገን ንፉግነት ነው።
በቀጣይ በሚኖረን ዝግጅት የነዋሪዎችን አስተያየት እና አጠቃላይ ጉዳዩ የት ደረሰ የሚለውን የመጨረሻ ክፍል ይዘን እንቀርባለን።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን መጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ.ም