በፈረንጆቹ አዲሱ ወር የመጀመሪያዎቹ ቀናት ከተደረጉት የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮች መካከል አንዱ የደቡብ ኮሪያው ዴጉ የማራቶን ውድድር ነው። ከ5 ኪሎ ሜትር እስከ ማራቶን ባሉ ርቀቶች የተለያዩ ፉክክሮችን የሚያስተናግደው ይህ የጎዳና ላይ ሩጫ ለ13ኛ ጊዜ ከትናንት በስቲያ ሲካሄድ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የተለመደ ድላቸውን ማጣጣም ችለዋል።
በዓለም አትሌቲክስ የብር ደረጃ የተሰጠው ይህ ውድድር 15ሺ561 ሯጮችን ያሳተፈ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል ከ12 ሀገራት የተወጣጡ አትሌቶች ተካፍለውበታል። በሁለቱም ጾታዎች በተካሄደው የአርባ ሁለት ኪሎ ሜትር ውድድርም ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች አሸናፊዎች መሆን ችለዋል።
በወንዶች አሸናፊ የሆነው አትሌት ሚልኬሳ መንገሻ አሳማኝ በሆነ ብቃት ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶችን በማስከተል ቀዳሚ ሆኖ መግባት ችሏል። ባለፉት ቅርብ ዓመታት በመም ውድድሮች የሚታወቀው ወጣቱ አትሌት ፊቱን ወደ ጎዳና ላይ ውድድሮች ካዞረ ወዲህ የዴጉ ማራቶን ድሉ በትልቁ የሚጠቀስ ሆኗል። አትሌት ሚልኬሳ እአአ በ2019 አህሩስ ላይ በተካሄደው የዓለም ሀገር አቋራጭ ቻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት እንደነበረም የሚታወስ ነው። ይህ ወጣት አትሌት ከተፎካካሪዎቹ በአንድ ደቂቃ ቀድሞ ድሉን ያጣጣመ ሲሆን፣ ርቀቱን የሸፈነበት ሰዓትም 2:06:49 ሆኖ ተመዝግቦለታል። በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ለሁለት ዓመታት የተሰረዘው የዴጉ ማራቶን ባለፈው ዓመት በድጋሚ ወደ ውድድር ሲመለስ በኢትዮጵያዊ አትሌት አሸናፊነት ነበር የተጠናቀቀው።
ዘንድሮ በድጋሚ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች አሸናፊ በሆኑበት ሩጫም ኬንያዊው አትሌት ስታንሊ ኪፕሮቲች ሚልኬሳን ተከትሎ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። ቀዳሚ ሆኖ ካጠናቀቀው አትሌት በአንድ ደቂቃ ዘግይቶ ውድድሩን የፈፀመው ኪፕሮቲች የገባበት ሰዓት 2:07:00 ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፤ ኤርትራዊው ብርሃኔ ጸጋይ ደግሞ 2:07:21 በሆነ ሰዓት ውድድሩን በሶስተኝነት ማጠናቀቅ ችሏል። በሴቶች በኩል ደግሞ አትሌት አያንቱ አበራ የሀገሯን ልጅ በማስከተል ውድድሯን በአሸናፊነት አጠናቃለች። አትሌቷ 2:25:44 በሆነ ሰዓት ስትገባ፤ አትሌት መዲና ደሜ ሁለት ደቂቃዎችን ዘግይታ 2:27:27 በሆነ ሰዓት ውድድሯን ጨርሳለች። ኬንያዊቷ አትሌት ጃኔት ጊቹምቢ ደግሞ ሶስተኛውን ደረጃ ይዛለች።
ከዴጉ ማራቶን በተጨማሪ በሳምንቱ መጨረሻ በተለያዩ የዓለም ከተሞች በርካታ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮች የተካሄዱ ሲሆን፤ በአብዛኛዎቹ የተካፈሉት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ውጤታማ ሆነዋል። በአውሮፓ ከሚካሄዱ ማራቶኖች መካከል በጥንታዊነቱ ተጠቃሽ በሆነው የፓሪስ ማራቶን አትሌት አበጀ አያና አሸናፊ ሆኗል። ወጣቱ አትሌት በጎዳና ላይ ሩጫ ልምድ ያለውንና በዚህ ማራቶን ለአሸናፊነት ቅድመ ግምት ካገኙት መካከል አንዱ የሆነውን የሀገሩን ልጅ በማስከተልም ነው ውድድሩን የፈጸመው። በግማሽ ማራቶን ሩጫዎች በተለይ የሚታወቀው አትሌቱ ርቀቱን በአሸናፊነት ለመደምደምም 2:07:15 የሆነ ሰዓት ነው የፈጀበት።
ጠንካራ በነበረው ፉክክር በሰከንዶች ብቻ ተቀድሞ አሸናፊነትን ለጥቂት ያጣው ደግሞ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ጉዬ አዶላ ነው። በቫሌንሺና በበርሊን ማራቶኖች የሚታወቀው አትሌቱ ለአሸናፊነት ያደረገው ብርቱ ጥረት በ20 ሰከንዶች ብቻ የዘገየ ሲሆን፤ አትሌቱ በርቀቱ ካለው ምርጥ ሰዓት ደግሞ በደቂቃዎች ዘግይቷል። እሱን ተከትሎም ኬንያዊው አትሌት ጆስፋት ቦይት በ2:07:40 ሰዓት ሶስተኛ በመሆን ገብቷል። በተመሳሳይ ጠንካራ ፉክክር በታየበት የሴቶች ሩጫም ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች አታለል አንሙት፣ ፍቅርተ ወረታ እና የሺ ቸኮለ ኬንያዊቷን ሄላ ኪፕሮፕን እጅግ ጠባብ በሆነ ልዩነት ተከትለው በመግባት ከሁለት እስከ አራት ያለውን ደረጃ መያዝ ችለዋል።
በቻይና የዚመን ማራቶንም በተመሳሳይ ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች ስኬታማ ሲሆኑ፤ መሰረት አበባየሁ በሴቶች አሸናፊ ልትሆን ችላለች። አትሌቷ 2:24:42 በሆነ ሰዓት ርቀቱን ስትሸፍን ተከትላት ከገባችው አትሌት የአንድ ደቂቃ ልዩነት በመፍጠር ነው። 35ሺ ሯጮች በተካፈሉበት በዚህ ውድድር ኬንያዊቷ ግላዲስ ቼሲር ሁለተኛ ስትሆን፤ በሰከንዶች ብቻ ብልጫ የተያዘባት ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ጉተኒ ሾኔ ሶስተኛ ደረጃን መያዝ ችላለች። በወንዶች በኩል አሸናፊነቱን የተቀዳጀው ኬንያዊው አትሌት ፊሊሞን ኪፕቹምባ ኢትዮጵያዊው አትሌት ፈተና ሆኖበት ነበር። በ15 ሰከንዶች ብቻ ተቀድሞ ፉክክሩን በሁለተኝነት ያጠናቀቀው አትሌት ሌንጮ ተስፋዬ 2:08:29 የሆነ ሰዓት ማስመዝገብ ችሏል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2015