ኢትዮጵያ በአላት አቅም የኃይል አቅርቦትን ለዜጎቿ ተዳራሽ ለማድረግ ሰፊ ስራዎችን ስትሰራ ቆይታለች። ነባር የመብራት መስመሮች እድሳት፤ እንዲሁም፣ የአዳዲስ መስመሮች ዝርጋታ በስፋት ተከናውኗል። በዚህም የኤሌክትሪክ ኃይል ተዳራሽ ባልሆነባቸው የተለያዩ የገጠር መንደሮች ጭምር ይሄንን የኃይል አቅርቦት ለመድረስ ጥረት ተደርጎ ብዙ ዜጎች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል::
ነገር ግን ዜጎች፣ በተለይም የከተማ ነዋሪዎች፣ በዚህ ጉዳይ ያላቸውን ቅሬታ በተደጋጋሚ ያነሳሉ። ተደራሽነቱ ፍትሃዊ አይደለም፤ ይህ ነው ሊባል በማይችል ሁኔታ አቅርቦቱ ይቋረጣል፤ እና መሰል ጥያቄዎችን ያነሳሉ:: ይህም፣ የዜጎች ሕዝባዊ አገልግሎትን የማግኘት ሰብዓዊ መብት፣ በመላ ሀገሪቱ የአገልጋይ ተቋሙ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ ቆይቷል። ለዚህም በተለያዩ ጊዜያት ለጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት የተለያየ ምላሽ ሲሰጥ ኖሯል። ዛሬም ድረስ ግን ችግሩ አልተቀረፈም:: በአዲስ አበባ ደግሞ ችግሩ በስፋት ይስተዋላል፤ ተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥም የእለት ተእለት ገጠመኝ ነው። ይህም ነዋሪዎችን ለዘርፈ ብዙ ችግሮች ሲዳርጋቸው ይታያል::
ወይዘሮ ለምለም አፈወርቅ (ስማቸው የተቀየረ) በአዲስ አበባ፣ በተለምዶ “ጀሞ አንድ” ተብሎ የሚጠራው ኮንደሚኒየም ሰፈር ነዋሪ ናቸው። እሳቸው እንደሚናገሩት፤ እነሱ አካባቢ ያለው የመቆራረጥ ችግር ብቻም አይደለም። አንድ ጊዜ ከጠፋ አይመለስም። አንድ ሙሉ ቀን ወይም ለሁለት ቀናት ሳይመጣ ይቆያል። በዚህም እየተጋፈጥን ያለው ችግር ብዙ ነው:: በዚህ ጊዜ ደግሞ መብራት ብርሃን ከመስጠት ባለፈ አገልግሎቱ ዘርፈ ብዙ ነው:: ይህንን ሁሉም ሰው ያውቃል። ድርጅቱም ያውቃል። አብስለን ለመመገብ፣ እንጀራ ለመስራት ተዘጋጅተህ ይጠፋል። መብራት ያለመኖሩ ወይም መቆራረጡ ይሄንን ሁሉ ኪሳራ ነው እያመጣብን ያለው። በዛሬ ኑሮ ውድነት ደግሞ አስበው።
ሌላዋ ያነጋገርናቸው ቅሬታ አቅራቢ የዚሁ ኮንደሚኒየም ሰፈር ነዋሪ ናቸው። እንደ እሳቸው ብሶት አዘል ማብራሪያ የችግሩ ጫና ይበረታል፤ ከአቅም በላይም እየሆነ ነው። ይህ እንደለ ሆኖ፣ በችግሩ ምክንያት ቤት መስራት ሳይቻል ይቀርና ከውጭ ለመግዛት ሌላ አማራጭ ሲፈለግ፣ በአካባቢው በአጠቃላይ መብራት ስለማይኖር፣ እንጀራ በብርህ ለመግዛት ስታማትር ድሮ የሚሸጥበት ቦታ ሁሉ አይኖርም። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የእንጀራ ሻጮቹ ሳይሆን፣ እነርሱም ጋር ኃይል መቆራረጥ መኖሩ ነው።
ሌላው ደግሞ ትንሽ ዝናብ ጠብ ባለ ቁጥር መብራት የመቋረጡና ችግር የመፈጠሩ ጉዳይ ነው። መብራት ሲጠፋ፣ ቅድመ ጥንቃቄ እንዳናደርግ ሳይነገረን ነው እልም የሚለው። ይሄ ትልቅ ችግር ሆኖብን ነው ያለው::
ከላይ በቀረቡት የኃይል ተጠቃሚዎች ቅሬታ መነሻነት “የመብራት መቆራረጥ ዛሬም ችግር ሆኖ ዘልቋል። እስከ ዛሬ ከተለመደው ምላሽ ውጭስ የተሻለ መፍትሔ ነው የሚባልስ አለ ወይ?” ሲል አዲስ ዘመን ለሚመለከተው አካል ጥያቄ አቅርቦ የነበረ ሲሆን፤ የአዲስ አበባ ከተማ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ገበየሁ ሊካሳ ምላሽ ሰጥተዋል።
የተለመደ መልስ ለሕዝብ አንሰጥም የሚሉት ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ገበየሁ ሊካሳ፣ የኃይል መቆራረጡን በተመለከተ ከመነሻው ለማስረዳት የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ደካማ ነበር። 1990ዎቹ ላይ 400 ሜጋ ዋት ኃይል ነው የነበረን። ስለዚህ መንግስት እስትራቴጂካሊ ለኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ቅድሚያ ሰጥቶ፣ ከፍተኛ ፋይናንስ መድቦ ብዙ ስራዎችን ሰርቷል። ከየትኛውም ሴክተር በበለጠ ኤሌክትሪክ ላይ ነው ሀብት የፈሰሰው። በዚህም አሁን ያለን የኃይል ማመንጫ አምስት ሺህ ሜጋ ዋት ደርሷል። ይህ ከሁለት አመት በኋላ አስር ሺህ ሜጋ ዋት ይደርሳል። ይህ ከእኛም ተርፎ ለጎረቤት ሀገራት የሚተርፍ ነው የሚሆነው:: በዛው ልክ በማከፋፈያ ከተሞች አካባቢ ያለው የማከፋፈያ ኔትዎርክ አልተሰራም። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ቅድሚያ ለኃይል ግንባታ በመሰጠቱ ነው። ወደ ከተሞች አካባቢ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በተጠናከረ ሁኔታ እየሰራን ነው ብለዋል::
በአዲስ አበባ ሁለት ምዕራፎች ያሉት ፕሮጀክት ተጠናቋል። በአጠቃላይ ሁለት ሺህ አንድ መቶ ኪሎ ሜትር የመካከለኛ ቮልቴጅ፣ አምስት ሺህ ኪሎ ሜትር የዝቅተኛ ቮልቴጅ፤ እንዲሁም፣ አስር ሺህ አምስት መቶ የማከፋፈያ ትራንስፎርመሮች አሉ። እነዚህ ያረጁ ናቸው። ሌላ ነገር ብናወራ ጥቅም ስለሌለው ወይም ደግሞ ይህንን ኔትዎርክ በሙሉ በአንድ እና በሁለት አመት በማሻሻል እናጠናቅቅ ቢባል የማይቻል ስለሆነ ከእውነት ውጭ እንሆናለን። ፋይናንስ ከማግኘት ጋርም ሆነ መሬት ላይ ከመተግበር ጋር ቀደም ሲል የሰራናቸው የማሻሻያ ስራዎች ቢኖሩም፤ ቀደም ሲል የባቡር መስመር ሲዘረጋ የኃይል መስመሮቹን በጣጥሷቸዋል። በዚህ ምክንያት ነው በ2011 ዓ.ም ከአሮጌ ኔትዎርክ የጀመርነው። ይህንን የምናገረው ለምን ከዛ በፊት አልተሰራም ያልከውን ለማስረዳት ያህል ነው።
አንደኛ በኃይል ግንባታ ላይ ቅድሚያ ስለተሰጠ ነው:: ሁለተኛ ከ2003 እስከ 2011 ድረስ በሜቴክ ኮንስትራክሽን ምክንያት የዕቃ አቅርቦት እጥረት በመኖሩ ነው። ቃል በቃል ለመናገር ያረጀ ኔትዎርክ ነው የነበረው።
2011 ዓ.ም ላይ ይህን ሁለት ሺህ አንድ መቶ ኪሎ ሜትር የመካከለኛ ቮልቴጅ፣ አምስት ሺህ ኪሎ ሜትር የዝቅተኛ ቮልቴጅ፤ እንዲሁም፣ አስር ሺህ አምስት መቶ የማከፋፈያ ትራንስፎርመሮችን ስትራቴጂ በመቅረፅ፣ በአራት ምዕራፎች ተደራሽ ለማድረግ ፕሮጀክት ተነደፈ። የመጀመሪያው ፕሮጀክት “የስምንቱ ከተሞች ፕሮጀክት” ይባላል። 2011 ዓ.ም ላይ ተጀምሮ 2013 ዓ.ም ላይ ነው ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀው። ይህ ፕሮጀክት የክልል ዋና ዋና ከተሞችን እና አዲስ አበባን የሚያጠቃልል ነው::
በዚህ ስራ አዲስ አበባ ላይ 40 ኪሎ ሜትር መካከለኛ ቮልቴጅ፣ 412 ኪሎ ሜትር የዝቅተኛ ቮልቴጅ፣ 82 የማከፋፈያ ትራንስፎርመሮች እና 15 ማስተላለፊያ ጣቢያ (switching station) ነው የተሻሻለው። ሁለተኛው ምዕራፍ በ2012 ዓ.ም ተጀምሮ 2014 ዓ.ም ላይ ተጠናቀቀ። በዚህ ደግሞ 725 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ ቮልቴጅ፣ 400 ኪሎ ሜትር የዝቅተኛ ቮልቴጅ፣ 400 አገዥ የማከፋፈያ ትራንስፎርመር እና 73 switching station በዋናነት ተሰራ። ተመርቆም አገልግሎት መስጠት ጀምሯል::
ሶስተኛው ምዕራፍ ባለፈው በጀት አመት ነው የተጀመረው። በዚህ በጀት አመት መጨረሻ ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቅ ነበር። በተለያየ ምክንያት በኮረና፣ በኮንቴነር እጥረት ሳይጠናቃቅ ቆይቷል። በዚህ ስራ ደግሞ 733 ኪሎ ሜትር መካከለኛ ቮልቴጅ፣ 400 ኪሎ ሜትር የዝቅተኛ ቮልቴጅ፣ 258 አጋዥ የማከፋፈያ ትራንስፎርመሮች፤ ሰብ ስቴሽኖች እና የመቆጣጠሪያ ጣቢያን ጨምሮ አሁን እየተሰራ ነው የሚገኘው። 2016 ዓ.ም ላይ ይጠናቀቃል::
የዚህ ስትራቴጂክ ዕቅድ አራተኛው እና የመጨረሻው ምዕራፍ ደግሞ 600 ኪሎ ሜትር መካከለኛ ቮልቴጅ፣ ቀሪውን በሙሉ ማለት ነው፣ 2000 የማከፋፈያ ትራንስፎርመሮች አሉት። 2017 ዓ.ም ላይ ይጠናቀቃል። የአማካሪ ቅጥር እና የጨረታ ሂደት ተጀምሯል:: ይሄን ስራ ስትራቴጂ ነድፈን በትክክል እየተመራ ነው የሚገኘው:: ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ስራ ነው እየተሰራ ያለው። ለምሳሌ የመስመር ዝርጋታው በመሬት ስር ይካሄደል። በኮንክሪት ምሰሶ ነው የሚሰራው፣ ሽፍን ሽቦ ነው የምንጠቀመው። ይህ የኃይል መቆራረጡን ይቀርፋል:: በዚህ ሂደት በተጠናከረ ሁኔታ አሮጌውን ኔትዎርክ ለመቀየር በስፋት እየሰራን ነው ብለዋል::
ወይዘሮ ለምለም ሁሉም ቦታ ሲጠፋ ይሄ በቂ በሆነ ምክንያት የሆነ ነው። እንደ ሀገር ያለ ችግር ነው ተብሎ መቀበል እንዳይቻል አንድ ሰፈር፣ አስፋልት ተሻግሮ፣ ማዶ መብራት ይኖራል። እዚህ ጋር ደግሞ አይኖርም። “ይህ ለምን ይሆናል?” ተብሎ ቢጠየቅም ምላሽ የሚሰጥ ማንም የለም ይላሉ::
ዶ/ር ገበየሁ በበኩላቸው ይሄ የሚሆነው አንደኛው ትራንስፎርመር ለተወሰነ ደንበኛ ነው አገልግሎት የሚሰጠው። እሱ ላይ ችግር ሲፈጠር ያ ሰፈር መብራት ያጣል። ሄደን እስክንጠግን ድረስ በዛ መስመር ብልሽት ካለው መስመሩ አገልግሎት አይሰጥም። ሌላው ግን ያገኛል። እናም በዚህ ምክንያት በኔትዎርኩ ነባራዊ ሁኔታ የሚፈጠር ችግር እንጂ ልዩነት ለመፍጠር ታስቦ የተሰራ ስራ አይደለም:: በአካል ሄደን አይተናል። ማሻሻያ ያደረግንባቸው መስመሮች በሰሞኑ የአየር ሁኔታ እንኳ አልተጎዱም። በዚህ ደረጃ፣ እስትራክቸርድ በሆነ ፌዝ፣ በተጠናከረ መልኩ እየሰራን ነው። ግን ስንሰራ ችግሮች ያጋጥሙናል። የከተማው ማስተር ፕላን አሁን እየተተገበረ ነው። “እነዛን ኔትዎርኮች አንሱ” የሚል ይመጣል። እነርሱን እናነሳለን።
ከሌሎች የመሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት ጋር በቅንጅት የመስራት ችግር ስለመኖሩ፤ ይሄንን ችግር ለመቅረፍስ ምን እየሰሩ እንደሆነ ጠይቀናቸው ዶ/ር ገበየሁ ሲመልሱ፤
አዲስ አበባ አዲስ ማስተር ፕላን አለው። እንደገና ፈርሰው የሚሰሩ፣ በጣም አሮጌ ሰፈሮች አሉ። ጎን ለጎን መሰረተ ልማት እየተስፋፋ ነው:: በእነዚህ አካባቢዎች ደግሞ ቴሌ ስራ አለው። ውሃም አለው፤ መብራትም አለው። እነዚህ ካልተቀናጁ ስራው በአግባቡ ሊመራ አይችልም። በምንም ተዓምር።
ከአዲሱ የመንግስት ርፎርም በፊት፣ አዳዲስ በሚሰሩ መንገዶች ላይ በሙሉ ከ2006 እና 2007 ዓ.ም ጀምሮ ችግሩ በስፋት ነበር። አሁን ቅንጅቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል። አሁን የመሰረተ ልማት ቅንጅት የሚባል ተቋም አለ። በዚህ መልኩ በተሰራው ስራ ለውጥ ተይቷል:: ይሁን እንጂ፣ በብዙ ምክንያት በአንድ ምሽት ችግሩን መቅረፍ ደግሞ አይቻልም::
ወይዘሪት ብዙነሽ አለሙ በአዲስ አበባ በአንድ አካባቢ በፈጣን ምግብ አቅርቦት ቢዝነስ ስራ ላይ የተሰማራች ወጣት ናት። እርሷ እንደምትናገረው፤ የመብራት መቆራረጥ በእጅጉ እየተፈታተናት ይገኛል። አለ ስትል የለም። “ደንበኛ መጥቶ ምግብ እያበሰልኩ ይጠፋል። የጀመርኩትን ምግብ ለመጨረስ ደግሞ ከሰል በማያዋጣኝ ዋጋ ገዝቼ ካቀጣጠልኩኝ በኋላ መብራቱ ይመጣል። እንደገና ደግሞ ተመልሶ ይጠፋል። በዚህ ምክንያት ደንበኛም ይሰለቻል። ሌላ አማራጭ ወደ መፈለግ ይሄዳል። ይሄ ፈተና ሆኖብኛል። በተጨማሪም በዚህ የኃይል መቆራረጥ ምክንያት የማብሰያ ስቶቬ ተቃጥሎብኝ ያውቃል። ቤት ተከራይተን ነው ስራችንን የምንሰራው። በየወሩ ለመብራቱም እንከፍላለን። ይሄም በሚሰራው ስራ ውጤታማ እንዳልሆን እያደረገኝ ነው:: በዘላቂነት ችግሩን መፍታት ለምን እንደማይቻል አይገባኝም” ስትልም የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ትገልፃለች።
እንደ ዶ/ር ገበየሁ ማብራሪያ ከሆነ ዘላቂ መፍትሔው የሚገኘው ቅድም በጠቀስኩት አራተኛው ምዕራፍ፣ 2017 ዓ.ም ላይ በሚጠናቀቀው ፕሮጀክት ነው። ይሄ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ያግዘናል:: ሰሞኑን የተከሰተው የኃይል መቆራረጥ ደግሞ ካልተጠበቀው የአየር ሁኔታ የመጣ ነው:: ሁለተኛው እና ትልቁ ችግር አራቱንም ምዕራፎች ስንሰራ አሮጌውን መስመር በአንድ መንገድ ላይ ትተን በሌላው አይደለም የምንሰራው። ኮሪደር የለም። ከተማ ውስጥ እያጠፋን ነው ሌላውን የምንሰራው። በዚህ ምክንያት ኮንክሪት ተክለን እስኪደርቅ እንጠብቃለን። ኢንሱሌተር እናሰራለን። ያኔም ይጠፋል። እና ለዚህ ፕሮጀክት ማስፈፀም ሲባል የሚጠፋው ኤሌክትሪክ ነው የሚበዛው።
ማሳወቅን በተመለከተም “ሳይነግሩን ነው የሚያጠፉት” የተባለው ስህተት ነው:: የመስመር ማሻሻያ ስራ ሲኖር በሁሉም የሚዲያ አማራጮች ለኅብረተሰቡ እናሳውቃለን” በማለት መልሰዋል::
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን መጋቢት 26 ቀን 2015 ዓ.ም