ልጆች እንዴት ናችሁ፤ ትምህርት እንዴት ነው? መቼም ጥሩ ነው የሚል ምላሽ እንደሰጣችሁኝ አምናለሁ። ምክንያቱም እናንተ ጎበዝ ተማሪዎች ስለሆናችሁ የሚከብዳችሁ ነገር አይኖርም፡፡
ልጆች ዛሬ እንኳን አደረሳችሁ የሚያሰኝ ነገር ይዤላችሁ ቀርቤያለሁ፡፡ ምንድነው ካላችሁ ደግሞ እንደምታውቁት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከተጀመረ 12ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ በዚህ ውስጥ ደግሞ ብዙዎቻችሁ አሻራችሁን እንዳሳረፋችሁ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ምክንያቱም ይህ ግድብ የእናንተ ሀገር ተረካቢዎች ደስታ ነው፡፡ ሀገራችንን ከአደጉት ሀገራት ተርታ የሚያሰልፋትና ለእናንተም ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡
ልጆች በዓመታት ጉዞ ውስጥ ብዙ ነገሮች ይለዋወጣሉ።አንዱ በየጊዜው የሚኖረው የግድቡ የእድገት ሁኔታና ጥቅሙ ሲሆን፤ ለአብነት የባለፈው ዓመትን ብናነሳ የታላቁ የኢትዮጵያ ዓባይ ግድብ የኃይል ማመንጨት ሥራ ጀምሯል፡፡ ግድቡ ካሉት 13 ተርባይኖች መካከል አንዱ ተርባይንም ከተሳካ ተከላ እና ሙከራ በኋላ የመጀመሪያውን ኃይል ማመንጨት ችሏል። ተርባይኑ 375 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን፤ 13ቱም ተርባይኖች ግንባታቸው ሲጠናቀቅ በአጠቃላይ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ማመንጨት የሚችል ይሆናል፡፡ ይህም በአፍሪካ ውስጥ ትልቁ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ አመንጪ ያደርገዋል።
ዛሬስ ካላችሁ ደግሞ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት እንዳስታወቀው የግድቡ ግንባታ በአሁኑ ወቅት 90 በመቶ ደርሷል። ለዚህ ልማት መፋጠን መሠረቱ ደግሞ እናንተም ጭምር እንደሆናችሁ ማመን አለባችሁ፡፡ ምክንያቱም ከቤተሰቦቻችሁ አልፎ ለእናንተም ገንዘብ ተሰጥቷችሁ በትምህርት ቤታችሁ በኩል አበርክቶ እያደረጋችሁ ትገኛላችሁ፡፡ ለሀገር ልማት ሁሉም የቻለውን ማድረጉ ደግሞ በርካታ ጠቀሜታ አለው፡፡ አንዱ የሀገር ፍቅርን ያሰፋል፡፡ ሌላው ደግሞ የወደፊት እድልን ቀና ያደርጋል። በተለይ ለእናንተ ደግሞ ያለው ጥቅም ከፍ ይላል። ምክንያቱም እናንተ ሀገር ተረካቢዎች ናችሁ፡፡ የተሠራው ሀገር ላይ ስለምታርፉ ሁሉ ነገር ይደላደልላችኋል። ስለዚህም አሻራችሁን ማሳረፉ ላይ የበለጠ መበርታት አለባችሁ፡፡
ልጆች ይህንን ካረጋገጡት መካከል ለዛሬ ይዤላችሁ የቀረብኩት የደጃዝማች ወንድራድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ናቸው፡፡ በቻሉት ልክ አዋጥተው ሰሞኑን በሚደረገው የቦንድ ግዢ እንቅስቃሴ ላይ አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡ የቦንድ ግዢውን የፈጸሙት በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 አስተዳደር በመገኘት ሲሆን፤ ይህ ተግባራቸው ቀጣይነት እንደሚኖረውም ነግረውናል። መጀመሪያ ያነጋገርናቸው ተማሪዎች ሁለቱ እህትማማቾች ሲሆኑ፤ በእምነትና የሲና አይሳነው ይባላሉ፡፡ የቦንድ ግዢውን የሚፈጽሙት ከቤተሰባቸው ብር ተቀብለው ነው። በእምነት የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን የደረጃ ተማሪ ናት፡፡ በዚህም ብዙ ተማሪ ይከተላታል፡፡ መምህራንና የትምህርት ቤት ማኅበረሰቡም ይሰማታል።ስለዚህም እርሷ እያደረገች ሌሎችም ይህንን ተግባር እንዲፈጽሙ ታበረታታለች። ለተከታታይ ዓመታትም ይህንኑ ተግባሯን ስታከናውን እንደቆየች ነግራናለች፡፡ እኛ ስናገኛት ደግሞ ተማሪዎችን በመወከል የቦንድ ግዢውን ለመፈጸም የቦንድ ግዢ የሚፈጸምበት ቦታ ላይ ተገኝታለች፡፡
እህቷ የሲናም እንዲሁ ለተከታታይ ዓመታት በቦንድ ግዢ ከሚሳተፉ ተማሪዎች መካከል ናት፡፡ እርሷም እንደእህቷ በጣም ጎበዝ ተማሪ ስትሆን፤ የዘንድሮ የስምንተኛ ክፍል ተፈታኝ ናት፡፡ በዚህም ጠንክራ እየተማረች እንደሆነና ይህንን ጉብዝናዋን በሀገራዊ ተሳትፎ ጭምር እያስመሰከረች መቆየት እንደምትፈልግ አጫውታናለች፡፡ ሁልጊዜም ሌሎቹን በሚያበረታታ መልኩ ስለ ታላቁ ዓባይ ግድብ ጥቅም ትናገራለች፡፡ ቦንድ እንዲገዙም ጓደኞቿን ታበረታታለች፡፡ በዚህም የክፍል ጓደኞቿ ብቻ ሳይሆኑ ብዙዎችን ወደ ቦንድ ግዢ ስባለች፡፡
ሌላኛዋ ያነጋገርናት ልጅ የሰባተኛ ክፍል ተማሪዋ ፕሪንሲስ ችኔዱ ነች፡፡ እንደ እነየሲና ሁሉ ለዓመታት በቦንድ ግዢ የተሳተፈች ተማሪ ናት፡፡ አምናና ዘንድሮ የ1000 ብር የቦንድ ግዢ ፈጽማለች፡፡ በቀጣይም ይህንን አጠናክራ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗን ነግራናለች፡፡
ፕሪንሲስ ይህንን የምታደርገው በምክንያት እንደሆነ ታነሳለች፡፡ አንዱ ምክንያት ነው የምትለው የነገ ሀገር ተረካቢ መሆኗን ሲሆን፤ ለራሴ ስንቅ ማስቀመጥ ነውና ያለማቋረጥ የቦንድ ግዢውን አከናውናለሁ፡፡ በዚህ ደግሞ ቤተሰቦቼ ሳይቀሩ ደስተኞች ናቸው ትላለች፡፡
ሀገርን መውደድ በተግባር የሚተረጎም ነው፡፡ ከተግባሩ አንዱ ደግሞ በሀገር ልማት ላይ መሳተፍ ነው። እናም ይህንን በማድረጌ እኔም ደስተኛ ነኝ፡፡ መስጠትን፤ ሀገርን መውደድን እየተማርኩበትም ቀጥያለሁ፡፡ ስለዚህም ዛሬ ብቻ ሳይሆን ሁሌም ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ ‹‹ እኔ የታላቁ ዓባይ ግድብ አምባሳደር ነኝ›› ማለቴን አላቋርጥም ብላናለች፡፡ ልጆች እናንተስ ምን አላችሁ? እርግጠኛ ነኝ እኛም አምባሳደሮች ነን ብላችሁናል፡፡ ልክ ናችሁ አምባሳደር ሆናችሁ የነገ ተስፋችሁን አስተካክሉ፡፡ በሌላ ጉዳይ ሳምንት እስክንገናኝ ቸር ሰንብቱ፡፡
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2015