ሌላኛው የዚህ ሳምንት ክስተት በዚሁ በመጋቢት 24 ቀን የተከናወነው የዶክተር ዐቢይ በዓለ ሲመት ነው። የዶክተር ዐቢይ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት መምጣት የኢትዮጵያን የፖለቲካ እንቅስቃሴ አዲስ ድባብ አላበሰው። ‹‹ፖለቲካና ኤሌክትሪክን በሩቁ›› ይባል የነበረው ተቀየረ፡፡ መንግሥትን ለመቃወም ሰልፍ ይወጣባቸው የነበሩ አደባባዮች መንግሥትን ለመደገፍ በሚወጣ ሰልፈኛ ተጥለቀለቁ፡፡
ዶክተር ዓቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ማግስት ጀምሮ በተለያየ ዘርፍ ውስጥ የሚገኘውን የማኅበረሰብ ክፍል ማወያየት ጀመሩ፡፡ መምህራንን፣ የጤና ባለሙያዎችን፣ የኪነ ጥበብ ሰዎችን፣ ባለሀብቶችን… በየደረጃው ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል አወያይተዋል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች እየሄዱም ነዋሪውን አወያይተዋል፡፡
እንዲህ እንዲህ እያለ የቀጠለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጉዞ እዚህ ደርሶ እነሆ ዛሬ እየታወሰ ነው፡፡ በተለይም በበዓለ ሲመታቸው ቀን በፓርላማ ያደረጉት ንግግር ዛሬ ድረስ በተለያዩ ዓውዶች ይጠቀሳል፡፡ ይህን ታሪካዊ ንግግር እነሆ በሳምንቱ በታሪክ ዓምዳችን እናስታውሳችሁ!
የተከበሩ አፈ ጉባዔ
የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት
የተከበራችሁ የአገራችን ሕዝቦች
ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች
ክቡራትና ክቡራን!
ሀገራችን ኢትዮጵያ በመንግሥት አስተዳደር ሥርዓቷ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር በምታከናውንበት በዚህ ታሪካዊ ቀን በተከበረው ምክር ቤት ፊት ቀርቤ ይህን ንግግር ለማድረግ ስለበቃሁ የተሰማኝን ልዩ ክብር ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ ከሁሉ አስቀድሜ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገራችን ለተከሰተው ፖለቲካ አለመረጋጋት የመፍትሔ አካል ለመሆን፣ የሀገር ክብርና ብሔራዊ ጥቅም በተሻለ ሁኔታ በአዲስ አመራር ሊጠበቅ ይችላል ብለው በማሰብ፣ ለአሕጉራችን ምሳሌ በሆነ መልኩ ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው ላሸጋገሩት ለክቡር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከፍ ያለ አክብሮቴን እገልጻለሁ፡፡ በተመሳሳይ የመንግሥታዊ ሥልጣን ሽግግሩ ያለ እንከን እንዲከናወን ልዩ ሚና ሲጫወቱ ለቆዩት ሁሉ በመላው ሕዝባችን ስም ከልብ አመሠግናለሁ፡፡
ዕለቱ ለአገራችን ታሪካዊ ቀን ነው!
በታሪካችን በተለያዩ አጋጣሚዎች አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ የመጀመር ዕድሎችን አግኝተን ብዙዎቹን በወጉ ሳንጠቀምባቸው አምልጠውናል፡፡ አሁንም ይህ የሥልጣን ሽግግር አዲስ ምዕራፍ የምንጀምርበት ሌላ ታሪካዊ ዕድል ነው፡፡ በመሆኑም በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ልንጠቀምበት ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ ማህፀነ ለምለም ናት፡፡ ከፍ ባለ የአገር ፍቅር መንፈስ ሁሌም የሚተጉ ልጆችን አፍርታለች፡፡ ልጆቿም ወደ ቀድሞ ክብሯ እንድትመለስ፣ የሕዝቧ ሰላምና ፍትሕ እንዲጠበቅ፣ ብልጽግና ያለ አድልኦ ለመላው ዜጎች ይዳረስ ዘንድ አጥብቀው ይመኛሉ. . . ይደክማሉ፡፡ በአገር ውስጥና በውጭ ሆነው ስለአገር አንድነትና ሰላም፣ ስለፍትሕና እኩልነት እንዲሁም ስለብልፅግና ይጮሃሉ፣ ይሞግታሉ፣ ይሟገታሉ፡፡ ይህ የሥልጣን ሽግግር ሁለት ዓበይት እውነታዎችን የሚያመላክት ነው፡፡ ክስተቱ በአንድ በኩል በአገራችን ዘላቂ፣ የረተጋጋና ሁሉን አቀፍ የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መሠረት ስለመጣላችን ማሳያ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከጊዜው ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ሁኔታዎች ጋር እኩል የሚጓዝና በሕዝብ ፍላጎት የሚገዛ፣ ሕዝብን አለቃው አድርጎ የሚያገለግል ሥርዓት እየገነባን መሆኑን ያመለክታል፡፡
ወቅቱ ከስህተታችን ተምረን አገራችንን የምንክስበት ወቅት ነው
መሪ ድርጅታችን ኢሕአዴግ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመሩን አጥብቆ በመያዝ አገራችንን ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ ባስተዳደረበት ወቅት፣ በሁሉም መስክ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣ ሕገ መንግሥታዊና ፌዴራላዊ ሥርዓት ገንብቷል፡፡ ዓለም በአንድ በኩል በጥሞና፣ በአግራሞትና በጉጉት በሌላ በኩል ደግሞ በሥጋት እየተመለከተው ያለ ሀገራዊ ለውጥ ላይ እንገኛለን፡፡ ያሳካናቸው በርካታ ድሎች እንዳሉ ሁሉ በፍጥነት መቀረፍ የሚገባቸው በርካታ ጉድለቶች እንዳሉም እናምናለን። ከስህተቶቻችን ተምረን ወደፊት በመራመድ ማተኮር ያለብን ጉዳይ የተሻለች አገር ለሁላችንም በመገንባቱ ላይ ነው፡፡ ዋናው ቁም ነገር ሀገራችንን ከፍ ወዳለ ምዕራፍ ማሸጋገሩና አንድነቷን ጠብቃ የምትቆይበትን ሁኔታ በቀጣይነት እያረጋገጡ መሄዱ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ያስተማረን እውነታ በጊዜያዊ ችግሮች ተሸንፎ መውደቅን ሳይሆን፣ ፈተናዎችን ወደ ዕድልና መልካም አጋጣሚ ቀይሮ ድል መቀዳጀትን ነው፡፡
ትናንት አባቶቻችን በመተማ፣ በዓድዋና በማይጨውና በካራማራ አጥንታቸውን ከስክሰው የከበረ ደማቸውን አፍስሰው በክብርና በአንድነት ያቆዩዋት አገር አለችን፡፡ እኛ ዕድለኞች ነን፡፡ ውብ አገር አኩሪ ታሪክ አለን፡፡ እኛ መነሻችንን እናውቃለን፡፡ በርካታ ዘመናትን የሚሻገር ታሪክ ያለው ታላቅ ሕዝብ ነን፡፡ ኅብረታችንን ለዓለም ምሳሌ መሆን ይችላል፡፡ ጠላቶቻችንን አንበርክኳል። ሉዓላዊነታችንን ጠብቆ ዛሬ ላይ ከማድረሱም በላይ፣ ለሌሎች ሕዝቦችም የነፃነት ትግል አርዓያ ሆኗል፡፡
ማንነታችን እንዳይለያይ ሆኖ የተሰናሰለ፣ እንዳይነጣጠል ሆኖ የተገመደ፣ የተዋደደና የተዋሐደ ነው አማራው በካራማራ ለአገሩ ሉዓላዊነት ተሰውቶ የካራማራ አፈር ሆኖ ቀርቷል፡፡ ትግራዋይ በመተማ ከአገሬ በፊት አንገቴን ውሰዱ ብሎ የመተማ አፈር ሆኗል፡፡ ኦሮሞው በዓድዋ ተራሮች ላይ ስለአገሩ ደረቱን ሰጥቶ የሀገሩን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ከዓድዋ አፈር ተቀላቅሏል። ሱማሌ፣ ሲዳማው፣ ቤንሻንጉሉ፣ ወላይታው፣ ጋምቤላው፣ ጉራጌው፣ አፋሩ፣ ስልጤው፣ ከምባታው፣ ሐዲያውና ሌሎቹም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ በባድመ ከሀገሬ በፊት እኔን ብለው እንደወደቁ ከባድመ አፈር ጋር ተዋሕደዋል፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ አባት እንዳሉት እኛ ስንኖር ሰዎች፣ ስናልፍ ሀፈር፣ ስናልፍ አገር እንሆናለን፡፡ የየትኛውንም ኢትዮጵያዊ ክቡር ሥጋና ደም በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ አፈር ሆኖ ታገኙታላችሁ። ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያዊ እንሆናለን፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2015