ፈረስ በኢትዮጵያውያን ታሪክ ውስጥ ልዩ ቦታ ከሚሰጣቸው የጋማ እንስሳት መካከል ቀዳሚ ነው፡፡ ፈረስ ማለት ለኢትዮጵያውያን የጋማ ከብት ብቻ ሳይሆን መጓጓዣ፣ በበዓላት ጊዜ መዝናኛ፣ ለጦርነት ጊዜ ድምጽ አልባ ታንከኛም ጭምር ነው፡፡
ፈረስ በዘመናችን ተወዳጅና ብዙ ገንዘብ የሚፈስበት ስፖርትም ነው። በእርግጥ የፈረስ ስፖርት በኢትዮጵያም ቀደምት ዘመናዊ የስፖርት አይነቶች አንዱ ነው። ስፖርቱ የተጀመረው በዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት ሲሆን፤በወቅቱ ለጋሲዮን የሚባሉት (የፈረንሳይ፣ የጣሊያን፣ የእንግለዝና የአሜሪካን) ኤምባሲዎች በግቢያቸው ውስጥ ያዘወትሩት ነበር፡፡ ኤምባሲዎቹ ጃንሜዳ ላይ እርስበርስ ውድድር ሲያደርጉ ንጉሡ ተገኝተው ይመለከቱና ያበረታቱ ስለነበር ኢትዮጵያውን ፈረሰኞችም የባህል ስፖርትን እያከናወኑ ዘመናዊውን በመቅሰም በኋላ ሁለቱም አብሮ በጥምረት እየተከናወነ መቀጠል ችሏል፡፡
ስፖርቱ በንግሥት ዘውዲቱ ጊዜም በመስፋፋት በተደራጀ መልኩ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በ1950 ዓ.ም የፈረስ እሽቅድምድም ተብሎ ተቋቁሟል። በወቅቱ በንጉሡ ትዕዛዝ በባለሙያ ተጠንቶ በአዋጅ ተደግፎ የኢትዮጵያ ፈረስ እሽቅድምድም ተብሎ በመቋቋም ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ስፖርቱ ረጅም እድሜ ቢያስቆጥርም የመንግሥታት ለውጥን ተከትሎ ትኩረት በማጣቱ ተቀዛቅዞ ቆይቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የኢትዮጵያ ፈረስ አሶሴሽን ከሃገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን በመፍጠር ስፖርቱን ለማሳደግ የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ይህን ስፖርት ይበልጥ ለማሳደግ የአደረጃጀት ለውጥ በማስፈለጉ ከአሶሴሽን ወደ ፌዴሬሽን ደረጃ ለማሳደግ ሥራዎች መጀመራቸውን ታውቋል። የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ባወጣው የስፖርት ማኅበራት አደረጃጀት መመሪያ መሠረት አሶሴሽኑን ወደ ፌዴሬሽን ከፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን የኢትዮጵያ ፈረስ ስፖርት አሶሴሽን አስታውቋል። ይህንን ለማድረግም በተለያዩ ክልሎች ስፖርቱን የሚመሩ አደረጃጀቶችን ለመመሥረት ጥረት እየተደረገ ነው። ለዚህም የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቱን ከአሶሴሽኑ የተገኘው መረጃ ያሳያል። በዚህም መሠረት በአምስትና ስድስት ክልሎች ስፖርቱን የሚመሩ ፌዴሬሽኖችን በማደራጀት ወደ ፌዴሬሽን ደረጃ ለማሳደግ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።
ስፖርቱን ወደ ክልሎች ለማስፋፋት ዘመናዊ የፈረስ ስፖርትን በትርኢት መልክ ለማቅረብ የታሰበ ሲሆን፣ በቅርቡ በአማራ ክልል እንጅባራ ከተማና በኦሮሚያ ክልል ለገጣፎ በተካሄዱ የፈረስ ውድድሮች በመሳተፍና ትርኢቶችን በማሳየት መልካም ግንኙነቶችን ለመፈጠር ተችሏል።
አሶሴሽኑ ወደ ፌዴሬሽን እንዲያድግ መጀመሪያ የውስጥ አደረጃጀቱ መጠናከር እንደሚገባው የተገለፀ ሲሆን፣ አሶሴሽኑ የየክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮዎችን በጥምረት በመያዝ እንደሚሠራም አሳውቋል። የባሕልና ስፖርት ሚኒሰቴር አሶሴሽኑን ከክልሎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ ቴክኒካልና የፋይናንስ ድጋፎችን በማድረግ እገዛ እንደሚያደርግ ቃል የገባ ሲሆን፣ በክልል ደረጃ ለሚቋቋመው ፌዴሬሽን የመተዳደሪያ ደንብ በማዘጋጀት ድጋፍ ያደርጋል። የሥራ አስፈጻሚ አባላት ምርጫን ደግሞ አሶሴሽኑ የቴክኒክ ድጋፍና የግንዛቤ ማስጨበጥ እገዛን እንደሚያደርግ ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ፈረስ ስፖርት አሶሴሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘሪሁን ቢያድግልኝ፣ “አሶሴሽንና ፌዴሬሽን ሁለቱም በሕግ ደረጃ እኩል ቢሆኑም፤ ነገር ግን ወደ ፌዴሬሽን ደረጃ አደገ ሲባል የክልሎችን ተሳትፎ ያካትታል” ይላሉ። እንደ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው ገለፃ፣ የስፖርቱ እንቅስቃሴ እስከ አሁን በአዲስ አበባ ዙሪያ ብቻ ተገድቦ ቆይቷል። በቀጣይ ስፖርቱ እንዲሰፋ በአምስትና ስድስት ክልሎች ስፖርቱን ማዳረስ አሶሴሽኑ ወደ ፌዴሬሽን ማደግ አለበት። ይህም የስያሜ ለውጥ ብቻ አይደለም።
አቶ ዘሪሁን አክለውም፣ አሶሴሽኑ ወደ ፌዴሬሽን ማደጉ የአባላቶቹንና የተወዳዳሪውን ቁጥር ስለሚጨምር ለስፖርቱ መስፋፋትና እድገት እገዛ እንደሚያደርግ ተነግሯል፡፡ በስፖርቱ እንቅስቃሴ ውስጥ አሁን ላይ ስምንት ክለቦች የሚገኙ ሲሆን ስድስቱ በአዲስ አበባና ሁለቱ በኦሮሚያ ክልል ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ በፈረስ ሃብት የታደለችና ከዓለም በስምንተኛና ከአፍሪካ በአንደኛ ደረጃ እንደምትገኝም ያስታወሱት አቶ ዘሪሁን፣ ይህን ሀብት ባሕላዊውንና ዘመናዊው ስፖርት ተጠቅሞ ማሳደግ እንዳልተቻለ በቁጭት ይናገራሉ። ውድድሮችን በስፋት ለማዘጋጀት ስፖርቱን ውድ መሆኑ አንዱ ተግዳሮት ሲሆን፣ ለአንድ ታዳጊ ፈረስ ግዢ በትንሹ አርባና ሃምሳ ሺ ብር ይፈጃል። ፈረሱን ማሰልጠን ጤንነቱን መጠበቅና ሌሎች ነገሮችን ለማሟላትም ከፍተኛ ወጪ ማስፈለጉ ሌላው ፈተና ነው። በመሆኑም እነዚህ ሁሉ ወጪዎች አዳጋች ስለሆኑ ስፖርቱ የሚመራበትን ሕግ ማሻሻል ግዴታ እንደሚሆን አቶ ዘሪሁን ይናገራሉ። እንደሌሎች ስፖርቶች በክለብ ደረጃ ለውድድር የመጣውን ብቻ አባል አድርጎ መቀበል ስፖርቱን ለማሳደግ ስለማይቻል የአባልነት መስፈርት ላይ አንድም ሁለትም ተወዳዳሪዎችን መቀበል እንደሚያስፈልግ አቶ ዘሪሁን አስረድተዋል፡፡
የስፖርቱ ሌላ ችግር የሆነው የማዘውተሪያ ስፍራ እጥረትን ለመቅረፍም ጃንሜዳ ያለውን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለመሥራት ከአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮና ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ እንደሚሠሩ አቶ ዘሪሁን ጠቁሟል፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን መጋቢት 22/2015