ከዓመታት በፊት የስፖርት አበረታች ቅመሞች (ዶፒንግ) ተጠቃሚነት በኢትዮጵያ የመኖሩ ዜና ሲሰማ በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ የፈጠረው ድንጋጤ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በዓለም ሕዝብ ዘንድ በአትሌቲክስ ስፖርት የተከበረች ሀገር በዚህ ጉዳይ ስሟ መነሳቱ የቆረቆራቸው የዘርፉ ባለሙያዎች እንዲሁም መንግሥታዊ አካላት ባደረጉት ርብርብም በአጭር ጊዜ ውስጥ አስደንጋጩ ማዕበል ሊረግብ ችሏል፡፡ በቆራጥነት በተሰራው ስራም የኢትዮጵያ ጸረ አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣንን በማቋቋም እና አስፈላጊውን ጥረት በማድረግ በአፍሪካ ደረጃ ዶፒንግን በመዋጋት ምሳሌት የሚሆን ስራ ተከናውኗል፡፡
ዓለም አቀፉ የጸረ አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ ባለሙያዎችም በተለያየ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ይህንኑ ሁኔታ አረጋግጠዋል፡፡ ከሰሞኑም የዓለም አቀፉ የጸረ አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ ፕሬዚዳንት ዊቶልድ ባንካ ከልኡካቸው ጋር በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ በአፍሪካ ደረጃ የኤጀንሲው ፕሬዚዳንት መሰል ጉብኝት ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያቸው ሲሆን፤ በቆይታቸውም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዲሁም ከኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ፣ የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነትን እንዲሁም የመንግሥት ስራ ኃላፊዎችን በማግኘት ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱም ፕሬዚዳንቱ ‹‹በአፍሪካ ትልቁ ተቋም›› በማለት ኢትዮጵያ ዶፒንግን ለመዋጋት እያከናወነች ያለችው መልካም ተግባር ማድነቃቸውን፤ የኢትዮጵያ ጸረ አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ይደርሳል ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ገልጸዋል፡፡ ለጉብኝቱ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች በአትሌቲክስ ስፖርት ተጠቃሽ ሀገር መሆኗ ሲሆን፤ ሌላኛው የሚደረገውን ጠንካራ የጸረ አበረታች ቅመሞች እንቅስቃሴ ይበልጥ ለማሳደግ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በአፍሪካም ሆነ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ባለው እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ የደጋፊነት ሚና እንዲኖራትና ይህንንም ማሳደግ እንድትችል ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ጋር በመነጋገር አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን አቶ መኮንን አስታውሰዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ዊቶልድ ባንካን ከመንግሥት ስራ ኃላፊዎች ጋር በየደረጃው ባደረጉት ውይይትም፤ ለእስካሁኑ ስራ ዕውቅና በመስጠት በቀጣይ ሊከናወኑ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡ በዚህም ዶፒንግን ለመዋጋት እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ይበልጥ ማጠናከር ተገቢ መሆኑንና በመንግሥት በኩል የሚደረገው ትኩረት ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ ቀዳሚው ነው፡፡
ሌላው በአፍሪካ ደረጃ ኢትዮጵያ ዶፒንግን ለመከላከል ያላትን ሚና በላቀ ሁኔታ እንድትወጣ የሚያስችል ነው፡፡ በኢትዮጵያ በኩልም የስፖርት አበረታች ቅመሞች መመርመሪያ ቤተ ሙከራ ለመገንባት የተጀመረውን ስራ በኤጀንሲው ድጋፍ እንዲያገኝ ጥያቄ ቀርቧል፡፡ ለቤተ ሙከራው ዕውቅና የሚሰጠውም ሆነ ቴክኒካዊ ድጋፍ የሚያደርገው ዓለም አቀፍ ኤጀንሲው እንደመሆኑ ይህንኑ የሚመለከት ሃሳብ መቅረቡንም ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡
ባለሥልጣኑ፤ ኤጄንሲው የሚያወጣቸውን ደንቦችና መመሪያዎች በመተግበር እንዲሁም መረጃዎችን በመለዋወጥ ረገድ ጠንካራ የሚባል ግንኙነትን መፍጠር ችሏል፡፡ ከሀገር ውስጥ የስፖርት ማህበራት እንዲሁም ከሚመለከታቸው አካላት (ከጤና ባለሙያዎችና ፍትህ አካላት) ጋርም በቅንጅት ይሰራል፡፡ በአበረታች ቅመሞች ቁጥጥር ዙሪያ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው ስራ ጠንካራ ሲሆን፤ ለዚህም ማሳያው የሕግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀትና መተግበር ነው፡፡ ተቋምን ከመገንባት አንጻርም በሰው ኃይልና በአሰራር ማጠናከር፣ ትምህርትና ሥልጠናን በሚመለከትም ባለሥልጣኑ ከሚሰራው ባለፈ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ5ኛ ክፍል አንስቶ በመደበኛ ሥርዓተ ትምህርት እንዲያውቁት በማድረግም ረገድ ዘርፈ ብዙ ስራ ተከናውኗል፡፡ እንደ ጀማሪ ሀገር ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ ያለው ነገር ግን በበቂ ሁኔታ ያልተሰበበት ምርመራና ቁጥጥርን የሚመለከት ነው፡፡ ይኸውም እንደ ኢትዮጵያ ያሉት በርካታ አትሌቶች በመሆናቸው እና ምርመራውም በውጭ ሀገር በመሆኑ ከውጭ ምንዛሬ ጋር በተገናኘ ያለው ውስንነት ባለሥልጣኑን በሚፈለገው ልክ ባያራምደውም መልካም በሚባል ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ለአትሌቲክስ ስፖርት ቢሆንም ሁሉም ስፖርት ከስፖርት አበረታች ንጥረ ነገሮች የጸዱ እንዲሆኑ ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም በዚህ ረገድ ሁሉም ዜጋ ሃላፊነት ያለበት በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ዳሬክተሩ አሳስበዋል። በተለይም የስፖርት ማህበራት፣ የስፖርት ባለሙያዎች እና ስፖርተኞች ከሚያገኙት ጊዜያዊ ጥቅም ይልቅ ሀገራቸውን በማስቀደም መስራት እንዳለባቸውም አክለዋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መጋቢት 21/2015