በ20ኛው ሳፋሪኮም ቅድሚያ ለሴቶች የ5ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር የዓለም ታዳጊዎች ቻምፒዮኗ አትሌት መዲና ኢንሳ የውድድሩን ክብረወሰን በመስበር አሸነፈች። ውድድሩ ትናንት መነሻና መድረሻውን ቦሌ አትላስ በማድረግ የተካሄደ ሲሆን፣ በጠንካራ ፉክክር ታጅቦ ሊጠናቀቅ ችሏል።
የዘንድሮ ውድድር የተካሄደው ለ20ኛ ጊዜ ሲሆን ከ15ሺ በላይ ሴቶች ተሳትፈውበታል። ውድድሩ የተካሄደው ቦታዬ፣ መብቴ፣ ድምጼ በሚል መሪቃል ሲሆን፤ በውድድሩ ከተለያዩ ክለቦች፣ ማሰልጠኛ ማዕከላትና ከግል ተወዳዳሪዎች የተውጣጡ 130 አትሌቶች ተሳትፈዋል። በውድድሩ በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ መድረኮች ስኬታማ የሆኑ አትሌቶች ከፍተኛ ፉክክርን በማሳየት ውድድራቸውን ጨርሰዋል። ውድድሩ ታላቁ ሩጫ ከሚያዘጋጃቸው ውድድሮች በትልቅነቱ የሁለተኝነት ደረጃን እንደሚይዝም ተጠቁሟል።
በሳፋሪኮም ቅድሚያ ለሴቶች የ5 ኪሎ ሜትር ውድድር በተምሳሌት ሴቶች ዘርፍ ከ20 በላይ ስኬታማ ሴቶች ተሳትፈዋል። በውድድሩ 28 አካልጉዳተኛ ሴቶችና የ11 አገራት ሴት አምባሳደሮችም መሳተፍ ችለዋል። ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት 12 የጤና አሯሯጮችን በመመደብ የመሮጫ ሰዓቱን ለማፍጠን ሞክሯል።
በአዋቂ አትሌቶች መካከል በተደረገው ፉክክር በ2014 በታላቁ ሩጫ የ10 ኪሎ ሜትር ውድድርና በ2012 ቅድሚያ ለሴቶች ውድድር አሸናፊዋ ፅጌ ገብረሰላማ፣ የዓለም የታዳጊዎች ቻምፒዮና የብር ሜዳለያ ባለቤት መልክናት ውዱ፣ እንዲሁም የታላቁ ሩጫን የ10ኪሎ ሜትር ሁለት ጊዜ ማሸነፍ የቻለችው ፎይቴን ተስፋይ ከፍተኛ ፉክክርን ማሳየት ችለዋል።
በውድድሩ አትሌት መዲና ኢንሳ ከአማራ ማረሚያ የውድድሩን ክብረወሰን በመስበር አንደኛ ሆና ስታጠናቅቅ፣ ለአሸናፊነት ታጭታ የነበረችው አትሌት ፅጌ ገብረሰላማ ከአትዮ ኤሌክትሪክ ሁለተኛ ሆና ጨርሳለች። አትሌት መልክናት ውዱ ደግሞ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሦስተኛ በመሆን መጨረስ ችላለች።
አትሌት መዲና ሪከርዱን የሰበረችው 15:11:53 ሰዓት በመግባት ሲሆን የውድድሩ ክብረወሰን ባለቤት የነበረችውና የሁለት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ አትሌት ፋንታነሽ በላይ ነበረች። አትሌት ፋንታነሽ በላይ የቦታውን ክብረወሰን በ15:19:44 ይዛ የነበረ ቢሆንም አትሌት መዲና ኢንሳ በ7 ሰከንዶች በማሻሻል የግሏ ማድረግ ችላለች። አትሌት መዲና የዓለም ታዳጊዎች 5ሺ ሜትር ቻምፒዮን መሆኗ ይታወሳል።
የውድድሩ አሸናፊ አትሌት መዲና ኢንሳ የመጀመሪያ ተሳትፎዋ እንደሆነና ብዙ ዝግጅት እንዳላደረገች ገልጻለች። «ፉክክሩ በጣም ጥሩ ነበረ፤ ስላልተዘጋጀሁና ከእኔ የተሻሉ ልጆች ስለነበሩ አሸንፋለሁ ብዬ አለሰብኩም፤ ነገርግን መጨረሻ ላይ አቅም ስለነበረኝ አሸንፌያለሁ» ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች። ውድድሩ ዕድል ላላገኙ አትሌቶች መታያ መሆኑንም ጨምራ ገልጻለች።
በውድድሩ ተጠብቃ የነበረችውና ከአንድ ወር በፊት በአውስትራሊያ ባትረስት በተከናወነው የ2023 የዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮና የብር ሜዳሊያ አሸናፊ የሆነችው አትሌት ፅጌ ገብረሰላማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ሁለተኛ በመሆን ጨርሳለች። ፅጌ ውድድሩን ከሦስት አመታት በፊት ያለምዘርፍ የኋላውን በጊዜው የቦታው ክብረወሰን በሆነ 15፡19.50 ሰዓት በመቅደም ካሸነፈች በኋላ የርቀቱን የትራክ ሰዓቷን ወደ 14፡43.90 ዝቅ አድርጋለች፡፡ በተጨማሪም ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ በተከናወነው የቫሌንሺያ ግማሽ ማራቶን 01፡05፡46 በመግባት በሁለተኛነት ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡
በውድድሩ ሁለተኛ የወጣችውና የከዚህ ቀደሟ የውድድሩ አሸናፊ ፅጌ ገብረሰላማ ውድድሩ ቆንጆ እንደነበረና ለዚህ ውድድር ብላ አለመዘጋጀቷን ጠቁማለች። ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈችበት አንደኛ መውጣቷን ገልጻ፣ በአሁኑ ውድድር ትንሽ ህመም ስለተሰማት ተጽዕኖ እንዳሳደረባት ጠቁማለች።
በውድድሩ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ የጨረሰችው አትሌት መልክናት ውዱ በበኩሏ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፏንና የመወዳደሪያ ቦታው ቁልቁለታማና ዳገታማ በመሆኑ ውድድሩ ከባድ እንደነበረ አስረድታለች። በውድድሩ መሳተፋችን ያለንበትን አቋም እንድንፈትሽና ለቀጣይ ውድድሮች ለመዘጋጀት ይጠቅመናል በማለት አስረድታለች። ለአሸናፊ አትሌቶች የ50ሺ ብር እና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቷል። አንደኛ በመውጣት የውድድሩን ክብረወሰን ላሻሻለችው አትሌት ተጨማሪ የ50ሺ ብር ሽልማት ተበርክቷል።
የመጀመሪያዋ የቅድሚያ ለሴቶች የ5ኪሎ ሜትር ሩጫ ውድድር አሸናፊዋ አትሌት ቆንጅት ጥላሁን ስትሆን፤ እንደ ቲኪ ገላናና ሰንበሬ ተፈሪ ውጤታማ አትሌቶች የመጀመሪያ ውድድራቸውን ማሸነፍ የቻሉት በዚህ መድረክ እንደሆነም ይታወቃል።
በክብር እንግድነት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት አዳነች አቤቤንና የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ጨምሮ፤ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መሥራች ሻለቃ ኃይሌ ገ/ ሥላሴ፣ የውድድሩ አምባሳደር አትሌት መሠረት ደፋር፣ የውድድሩ የሦስት ጊዜ አሸናፊ አትሌት ሰንበሬ ተፈሪና የዓለም ቻምፒዮና የ5 እና 10ሺ ሜትር አሸናፊዋ ለተሰንበት ግዳይ መታደም ችለዋል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2015