በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ለአምስት ቀናት የሚካሄደው የኢትዮጵያ ክለቦች አጭር፣ መካከለኛ፣ 3ሺ ሜትር መሰናክል፣ እርምጃ እና የሜዳ ተግባራት ቻምፒዮና ነገ ይጠናቀቃል። ይህ ዓመታዊ ውድድር የሚካሄደው ኢትዮጵያ እምብዛም በማትታወቅበት የአትሌቲክስ ውድድሮች የተሻለ መነቃቃት እንዲፈጠር ቢሆንም አሁንም ተስፋ የሚሰጥ ውጤት እየታየበት አይገኝም።
በረጅም ርቀት አትሌቲክስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስኬታማ ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ፤ ለአጭር ርቀትና የሜዳ ተግባራት ውድድሮች የሚሆን የተፈጥሮ ጸጋ ቢኖራትም ውጤታማ ልትሆን አልቻለችም። አገር ውስጥ በሚካሄዱ መሰል ውድድሮች በተደጋጋሚ መገንዘብ እንደተቻለውም አትሌቶች በእነዚህ ስፖርቶች ከሌሎች ዓለማት ጋር መነጻጸር ከማይችሉበት ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ነው።
አትሌቶቹ ላይ ከብቃት ማነስ ባለፈ ጎልተው ከሚታዩት ችግሮች አንዱ ከህግ ጋር የተያያዙ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ናቸው። በነዚህ ውድድሮች ብዙ አትሌቶች ባለማወቅም ሆነ ባለመጠንቀቅ በውድድር ወቅት በሚፈጽሟቸው የቴክኒክ ስህተቶች ምክንያት ከተወዳዳሪነት ሲሰረዙ በተደጋጋሚ ታይቷል።
ከቀናት በፊት በተጀመረውና ነገ በሚጠናቀቀው ቻምፒዮናም በአንድ ውድድር ብቻ እስከ ሁለት የሚደርሱ አትሌቶች ከቴክኒክ ጋር በተያያዘ ከውድድር ውጪ ሲሆኑ ታይቷል። ይህ ሁኔታ ከአገር ውስጥ ውድድሮች ባለፈ በዓለም አቀፍ ቻምፒዮናዎችም ሊደገምና አገርን ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል መገመት አያዳግትም። በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የስልጠና ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ብርሃኑ፤ በዚህ ቻምፒዮና የቴክኒክ ጉዳዮች ኃላፊ በመሆን እየሰሩ ይገኛሉ። ውድድሩን እንደገመገሙት ከሆነም ከወትሮ የተለየ ነገር ያልታየበትና ቴክኒካዊ ችግሮችም በስፋት የሚታዩበት መሆኑን ያስረዳሉ። ለዚህም አትሌቶች በስልጠና ወቅት ከሚያገኙት ቴክኒካዊ ስልጠና ባለፈ ከዳኝነት ህጉ ጋር ያለውን ነገር አለማወቅ ዋነኛው ምክንያት መሆኑን ይጠቁማሉ።
እንደ አቶ ሳሙኤል ገለፃ፣ አንድ አትሌት ዓመቱን ሙሉ ስልጠና ላይ ቆይቶ በብቃት ዳብሮ ውድድር ላይ ቢገኝም፤ ከአነሳስ ጋር በተያያዘ በሚፈጽመው ስህተት ከውድድር ውጪ ሊሆን ይችላል። ይህ ሁኔታ ከአጭር ርቀት ሩጫዎች ባለፈ በውርወራም ሆነ ዝላይ ስፖርቶችም በብዛት የሚከሰት ነው። በመሆኑም መሰረታዊ የሆነውን ቴክኒካዊ ጉዳይ አሰልጣኞች ከሚያገኙት የአሰልጣኝነት ስልጠና ጎን ለጎን ከዳኝነት ጋር የተያያዘ ዕውቀት እንዲኖራቸው ማድረግን ይጠይቃል። ይህም ሲሆን አትሌቱ ህጉን ተከትሎ በጥንቃቄ ውድድሩን ሊከውን ይችላል። ፌዴሬሽኑ በዚህ ረገድ ቻምፒዮናዎች ሲካሄዱ በጥቂቱ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ጥረት ቢያደርግም፤ እንደ አጠቃላይ ከህግ ጋር ተያይዞ ያለው ነገር የተረሳ ሊባል የሚችል መሆኑን አቶ ሳሙኤል ያስገነዝባሉ።
ባደጉት አገራት አትሌቱን ከማብቃት እኩል ከህግ ጋር ተያይዞ ያሉ ጉዳዮች ላይ ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ ይደረጋል። በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ በመሆኑ ከዚህ ቀደም በተሳተፉባቸው ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሳይቀር ከውድድር ውጪ የሆኑበት አጋጣሚ እንደነበረ የቴክኒክ ኃላፊው ያስታውሳሉ። ክለቦች ከችግሩ ጋር በተያያዘ የአሰልጣኞችን ብቃት፣ ዓመቱን ሙሉ ውድድሮች አለመኖራቸውን እንዲሁም ለእነዚህ ስፖርቶች የሚሆኑ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችና ቁሳቁስ በተገቢው ሁኔታ አለመሟላትን እንደ ችግር ያነሳሉ። ነገር ግን ዘመናዊ ስልጠና አቅማቸውን ባሳደጉ አሰልጣኞች እንዲሁም በተሟላ ቁሳቁስ እየሰለጠኑ ባሉ አካዳሚዎችና የስልጠና ማዕከላት ያለው ሁኔታም ከዚህ የራቀ አለመሆኑን ዳይሬክተሩ ይጠቁማሉ።
እንደ ፌዴሬሽን ያልተሰራበትን ይህንን ዘርፍ ባለፈው ዓመት ከተካሄደው ቻምፒዮና የጀመረ ሲሆን፤ አሰልጣኞችን በማስገንዘብ አትሌቶቻቸውን እንዲቀርጹ ለማድረግ እየተሞከረ ነው። መሰረታዊ የሆነውና የዚህ ችግር መፍትሄ የሚሆነውም የአሰልጣኞች ስልጠና ላይ ከዳኝነትና ከህግ ጋር ዕውቀት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ አሰልጣኞች በራሳቸው ጥረት ዕውቀታቸውን ማሳደግ እንደሚገባቸውም ዳይሬክተሩ ይጠቁማሉ። በሌላ በኩል ስፖርቱን ከህጻናት አለመጀመር ለችግሩ አንድ መንስኤ ሊሆን ይችላል፤ ይኸውም ቴክኒካዊ ጉዳዮችን ይበልጥ ለመረዳት በታዳጊነት እድሜ ላይ መስራት የተሻለ በመሆኑ ነው።
እንደ አጠቃላይ ኢትዮጵያ በአጭር ርቀት፣ ዝላይና ውርወራ ያለባትን ክፍተት ለመሙላት በአፍሪካ ደረጃ የተሻለ ልምድ ካላቸው አገራት (ናይጄሪያ፣ ኡጋንዳ፣…) ተሞክሮ ለመቅሰም በፌዴሬሽን ደረጃ ጅማሬዎች አሉ። ከዚህ ባሻገር ከልምድ አሰራር ባለፈ ዘመናዊ የሆኑ መሳሪያዎችን ለመጠቀምም እንዲሁም ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ባለሙያዎቹ ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል። በመሆኑም በእነሱ በኩል ዝግጁ ሲሆኑ የልምድ ልውውጡ የሚከናወን መሆኑንም ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2015