የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን(ዋልያዎቹ) በ2023 የኮትዲቯር አፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ዛሬና ከቀናት በኋላ ሶስተኛና አራተኛ የምድብ ጨዋታቸውን ከጊኒ ብሔራዊ ቡድን ጋር ሞሮኮ ላይ ያደርጋሉ።
ዋልያዎቹ ባለፈው ግንቦት ከሜዳቸው ውጭ በመጀመሪያው የማጣሪያ ጨዋታ በማላዊ አቻቸው የ2ለ1 ሽንፈት ቢገጥማቸውም በቀናት ልዩነት እዚያው ማላዊ ላይ የምድቡ ጠንካራ የሆነችው ግብፅን 2ለ0 ማሸነፋቸው ይታወሳል። በዚህም ምድባቸውን መምራት የቻሉ ሲሆን በአፍሪካ ዋንጫ ዳግም ለመታየትም ድንቅ እንቅስቃሴያቸው ተስፋ ጭሮ ነበር። ያም ሆኖ ከረጅም ወራት በኋላ የዚያኔ የነበረው የዋልያዎቹ ስብስብና አሁን ያለው ቡድን ላይ ከወሳኝ ተጫዋቾች በጉዳት ምክንያት ካለመኖር ጋር ተያይዞ በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ጥርጣሬና ስጋት መፈጠሩ አልቀረም።
የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ስብስብ ቢያንስ አራት ያውም የአጥቂ ስፍራ ወሳኝ ተጫዋቾቹን አጥቶ ነው ጊኒን የሚገጥመው። የቡድኑ ቁልፍ አጥቂ ጌታነህ ከበደ ዋልያዎቹ ፈርኦኖቹን በረቱበት ጨዋታም አልተካተተም ነበር። ጌታነህ ከወራት በፊት ራሱን ከብሔራዊ ቡድኑ በማግለሉም ዋልያዎቹ የእሱን አገልግሎት አያገኙም። ያም ሆኖ ጌታነህ በሌለበት የተሻሉ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋቾች ቡድኑን መጥቀም ችለዋል። አቡበከር ናስር፣ ዳዋ ሆጤሳ፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል የዋልያዎቹ ወሳኝ ፊታውራሪዎች ቢሆኑም ዛሬ ላይ በጉዳት ምክንያት ከቡድኑ ጋር አብረው አይገኙም። ወትሮም የጨራሽ ተጫዋቾች ክፍት ላለበት የዋልያዎቹ ስብስብ ይህ ትልቅ ጉዳት ነው። አሰልጣኝ ውበቱ እነዚህን ተጫዋቾች ለመተካት አዳዲስ ወጣት ተጫዋቾችን ጭምር ለማካተት ሞክረዋል። አዳዲስ ተጫዋቾች በቡድኑ መካተታቸው ለረጅም ጊዜ እቅድ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ለእንደዚህ አይነት ወሳኝ የነጥብ ጨዋታዎች ነባሮቹን ከአዳዲሶቹ አዋህዶ በአጭር ጊዜ እንዴት ውጤታማ ሊሆን እንደሚቻል ለብዙዎች ጥያቄ ነው። አሰልጣኝ ውበቱም ከርዋንዳው የወዳጅነት ጨዋታ በኋላ የዝግጅት ጊዜ እንዳጠራቸው አልሸሸጉም።
በርዋንዳው የወዳጅነት ጨዋታ ዋልያዎቹ እንደ ቡድን ጥሩ ነበሩ ማለት ይቻል ይሆናል። ግን ብዙ ክፍተቶች እንዳሉባቸው ደግሞ መሸሸግ አይቻልም። አሰልጣኝ ውበቱ ከፍተኛ የተጫዋቾች እጥረት ገጥሟቸዋል። ቡድኑ አሁንም የአጥቂ ችግሩ አልተቀረፈም። ለዚህ ደግሞ አሰልጣኙ እንደ ጌታነህ፣ አቡበከር፣ ዳዋና አማኑኤል ያሉ ተጫዋቾችን ለመተካት የግድ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። በአጥቂ ስፍራ ላይ አንድ መልካም ዜና ቢኖር በኦማን ሊግ ለአል-ሱዋይቅ ክለብ በመጫወት ላይ የሚገኘው ኡመድ ኡኩሪ ከረጅም ጊዜ በኋላ በዋልያዎቹ ስብስብ ውስጥ መካተቱ ነው። ይህ የተሻለ ልምድ ያለው አጥቂ ክለቡ አል-ሱዋይቅ ከቀናት በፊት አል ባሻይርን 4-2 ባሸነፈበት የሊግ ጨዋታ አንድ ግብ ማስቆጠር የቻለ ሲሆን ከወሳኙ አማካኝ ስፍራ ተጫዋች ሽመልስ በቀለ ጋር የሚፈጥሩት ጥምረት የዋልያዎቹን ግብ የማስቆጠር ችግር ለጊዜውም ቢሆን ሊቀርፍ ይችላል ተብሎ ተስፋ እንዲደረግ ያስችላል።
የአማካይ ክፍል ተጫዋቾችን በተመለከተም ኳስን በተገቢ መንገድ ለአጥቂ ከማድረስ ይልቅ ዋልያዎቹ ወደ ግራ እና ወደ ቀኝ ከማንሸራሸር የቀደመ ልምድ አሁንም መላቀቅ አልቻሉም። ኳስን ተቆጣጥሮ መጫወት ብቻ ደግሞ አስፈላጊውን ነጥብ ሊያስገኝ አይችልም።
የተከላካይ መስመሩን በተመለከተ አላስፈላጊ ኳስ ወደ ኋላ የመመለስ ጉዳይ በርዋንዳው ጨዋታ በተደጋጋሚ ተስተውሏል። ይህ ቡድኑን ዋጋ ሊያስከፍል የሚችል መሆኑን በበርካታ ጨዋታዎች ታይቷል፣ መታረም አለበት። በተከላካዮች የሚሰሩ አላስፈላጊ ስህተቶችና ጥፋቶችም ትኩረት ሊደረግባቸው ይገባል። በወዳጅነት ጨዋታውም የርዋንዳ ተጫዋቾች የመጠቀም አቅም እንጂ ዋልያዎቹ ግብ ማስተናገድ የሚችሉበት እድል ሰፊ ነበር። ዋልያዎቹ ዛሬ የሚገጥሙት ርዋንዳን ወይም ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ቡድኖችን ሳይሆን በትልልቅ የአውሮፓ ሊጎች ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ስብስብ ያላት ጊኒን ነው። በዚህ ላይ የጊኒ ተጫዋቾች ፍጥነትን ከአካል ብቃት ጋር ያጣመሩ እንደመሆናቸው ጥቃቅን የተከላካይ ስህተቶችን ተጠቅመው ዋልያዎቹን የመቅጣት እድላቸው ሰፊ መሆኑን ለሰከንድም መዘንጋት አይገባም።
በአንዳንድ ጨዋታዎች የቡድኖች የተጫዋች ጥራት፣ ጥንካሬና ግዙፍ ስም ውጤት ላይወስን እንደሚችል በብዙ አጋጣሚ ተመልክተናል። በዚህ ረገድ ዋልያዎቹ ከሁለቱ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ነጥብ የሚያገኙበት ሌላ እድል ሊኖራቸው ይችላል። ዋልያዎቹ በሁለተኛው የማጣሪያ ጨዋታ የምድቡ ጠንካራ አገር የሆነችው ግብፅን አሸንፈው በመሪነት መቀመጣቸው በስነ ልቦና ረገድ የሚሰጣቸው ጥቅም እንዳለ እውን ነው። ያንን ስነ ልቦና ይዘው በጥሩ የራስ መተማመን ወደ ሜዳ ከገቡ ዝቅ አድርገው የተመለከቷቸው ጊኒዎችን ልክ እንደ ግብፅ ሊቀጡ የሚችሉበት እድል ጠባብ አይሆንም።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/2015