በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ ውድድሮች ጠንካራ ተፎካካሪና ውጤታማ ከሆኑ ክለቦች መካከል ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በቀዳሚነት ይጠቀሳል። በዚህም ውጤታማነቱ በዓለም አቀፍ መድረኮች ኢትዮጵያን ወክለው ውጤታማ የሆኑ በርካታ ከዋክብት አትሌቶችን እያፈራ ይገኛል።
የኢትዮ- ኤሌክትሪክ ይህን ውጤታማነቱን አጠናክሮ ለመቀጠል በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አማካኝነት ለሚዘጋጁ ቀጣይ ውድድሮች ጠንካራ ዝግጅቶችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል። ክለቡ እየተካሄደ በሚገኘው የኢትዮጵያ የአጭር፣ የመካከለኛና የሜዳ ተግባራት ውድድር እንዲሁም ለ52ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ጠንካራ ዝግጅት ማድረጉን ገልፆ፣ በነዚህ አገር አቀፍ ውድድሮች ውጤታማ ከመሆን ባሻገር አገርን የሚወክሉ ጠንካራ አትሌቶችን ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
ክለቡ ከዚህ በፊት በአሰላ፣ ድሬዳዋና ደብረ ብርሃን በተካሄዱ አገር አቀፍ ውድድሮች ጥሩ ውጤቶችን ማስመዝገብ እንደቻለ የሚታወስ ሲሆን፣ በቀጣይም የተሻለ ውጤት ለማምጣት ጠንካራ ስራዎችን በመስራት ላይ መሆኑን ጠቁሟል። ለዚህም ክለቡ አትሌቶቹን በሜዳ፣ በመምና በጅምናዚየም ታግዞ እያዘጋጀ ይገኛል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ኢትዮጵያ ውጤታማ ባልሆነችባቸው በአጭር፣ መካከለኛና የሜዳ ተግባራት ውድድሮች በአገር አቀፍ ደረጃ ውጤት ከማስመዝገብ አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማ የሚሆኑ አትሌቶችን ለማፍራት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቋል። በነዚህ የውድድር አይነቶች የምስራቅ አፍሪካ አገራት ብዙም ያልተሰራባቸው ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኬንያ ትኩረት ሰጥታ በመስራቷ ተስፋ ሰጪ ውጤት እያስመዘገበች ትገኛለች። አትዮጵያም ትኩረት ሰጥታ ከሰራች ከምትታወቅበት የረጅም ርቀት ውድድሮች በተጨማሪ ውጤት ማምጣት ትችላለች በሚል እምነት ኢትዮ ኤሌክትሪክ እየተንቀሳቀሰ ነው። በአገር ውስጥ በሚደረጉ ውድድሮች ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሚያስመዘግባቸው ዉድድሮች የተሻሉ ውጤቶችን ማስመዝገብ እንደሚቻል ማሳየት ችሏል። ክለቡ ከተለመዱት የውድድር አይነቶች ውጪ በአጭር ርቀትና በሜዳ ተግባራት ውድድሮች በኦሊምፒክ ደረጃ ውጤት ማምጣት የሚችል አትሌት ማፍራትን አላማው አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል። በዚህም በአገር አቀፍ ደረጃ በሚደረጉ ውድድሮች የክለቡ አትሌቶች አመርቂ ውጤቶችን በማስመዝገብ ተስፋ እያሳዩ እንደሚገኙ ተጠቁሟል።
ክለቡ ከአትሌቲክስ በተጨማሪ በሁሉም የስፖርት አይነቶች የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ የቻለው ባደረገው መሰረታዊ የአስተዳደር ለውጦችና ወደ ክለቡ በቀላቀላቸው ባለሙያዎች መሆኑን ጠቁሟል። ባለሙያዎቹ ልምዳቸውና እውቀታቸውን በማጣመር ሳይንሳዊ የሆነ ስልጠናን በመስጠት አትሌቶቹ ለድል እንዲበቁ አሰተዋጾኦን እንዳበረከቱም ያምናል።
ክለቡ ይህን አጠናክሮ ለመቀጠል ታዳጊዎችን በመመልመልና በስልጠና ሂደቱ እንዲያልፉ በማድረግ ላይም ይገኛል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በርካታ ታላላቅና የኢትዮጵያን ባንዲራ በዓለም አደባባይ ያውለበለቡ ኮከብ አትሌቶችን ማፍራት ችሏል። ከቀድሞዎቹ የክለቡ ስኬታማ አትሌቶች መካከል አትሌት ጂኣ ይሳቅ፣ መሰለች መልካሙ የሚጠቀሱ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም በሪሁን አረጋዊ፣ ታደሰ ወርቁና ሌሎች ስኬታማ አትሌቶች ባለቤት ነው። የቀድሞ የክለቡ ስኬታማ አትሌቶችም አሁን ላይ ልምድና እውቀታቸውን ተጠቅመው ክለቡን በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ለክለቡ ውጤት ማማርም የአንጋፋ አትሌቶቹ ድርሻ ቀላል እንዳልሆነ ተገልጿል።
ክለቡ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ባደረጋቸው ለውጦች የውጤት መነቃቃት እንዲፈጠር ያደረገ ሲሆን፣ ለአትሌቶቹ ውድድር በማዘጋጀት ወቅታዊ ብቃታቸውን የመፈተሽና የተሻለ ብቃት ያላቸውን አስቀርቶ ጥሩ ያልሆኑትን የመቀነስ ስራ በዋናነት ተሰርቷል።
ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን በማወዳደር የሟሟላት ስራም በስፋት የተሰራ ሲሆን፣ በዚህም በየውድድር አይነቱና ተግባሩ ዋና ባለሙያ፣ ዋና አሰልጣኝ፣ ምክትል አሰልጣኞች ተቀጥረው ውጤታማ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ተጠቁሟል። በተጨማሪም ለአትሌቶችና ባለሙያዎች የደሞዝ ማሻሻያ የተደረገ ሲሆን፣ የአደረጃጀት ለውጦች ክለቡን ውጤታማ ሆኖ እንዲጓዝ አስችለውታል።
የአትሌቶች የስልጠና ሂደት ሳይንሳዊ ከመሆኑ ባሻገር ለስልጠና የሚሰጠው ትኩረት ከፍተኛ መሆኑም ክለቡ በርካታ አገርን መወከል የሚችሉ አትሌቶችን ለማፍራት እንዳገዘው ተጠቁሟል።
ክለቡ የራሱ የሆነ ማዘወተርያ ስፍራ ቢኖረውም በየውድድር አይነቱ እንደአስፈላጊነቱ የተሟላ ባለመሆኑ ፈታኝ ነገሮችን መጋፈጡ አልቀረም። ለዚህም መፍትሔ እንዲሆን ክለቡ በቀጣይ የራሱን የስፖርት አካዳሚ ለመገንባት እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ጠቁሟል። ለዚህም የግንባታ ፕሮፖዛል እየተዘጋጀ ሲሆን የግንባታው ቦታው የት እንደሚሆን ግን ውሳኔ ላይ አልተደረሰም። ለትግበራው ጥናት ከተደረገ በኋላ ወደ ስራ ለመግባት መታቀዱን ግን ከክለቡ ለማወቅ ተችሏል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን መጋቢት 14/2015