የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን(ዋልያዎቹ) ለ2023 የኮትዲቯር አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምድባቸውን ሶስተኛና አራተኛ ማጣሪያ ጨዋታ ከጊኒ ጋር መጋቢት 15 እና 18 ያከናውናሉ። ለዚህም አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከሳምንት በፊት ለሃያ ሶስት ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ዝግጅታቸውን በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ስቴድየም ሲያከናውኑ መቆየታቸው የሚታወቅ ሲሆን ከርዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር ያደረጉትን የአቋም መለኪያ ጨዋታም አንድ ለምንም አሸንፈዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከትናንት በስቲያ ምሽት ሁለቱን ፍልሚያዎች ወደሚያደርግበት ሞሮኮ የተጓዘ ሲሆን፣ ከጉዞው ቀደም ብሎም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ሥራ-አስፈፃሚ አቶ ባህሩ ጥላሁንና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ መግለጫ ሰጥተዋል።
ዋልያዎቹ ከጊኒ ጋር ለሚያደርጉት የደርሶ መልስ ጨዋታ ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ አድርገው ከመጋቢት 6 ጀምሮ ሲዘጋጁ መቆየታቸውን ያስታወሱት አሰልጣኝ ውበቱ፣ በህመም እና በክለብ ግዴታ ምክንያት ያልተገኙ ተጫዋቾች ቡድኑን እንዳልተቀላቀሉ ተናግረዋል። አቡበከር ናስር በጉዳት፣ ይገዙ ቦጋለ ደግሞ አንድ ቀን ከቡድኑ ጋር ልምምድ ሰርቶ የጉልበት ጉዳት በማስተናገዱ ከስብስባቸው ውጭ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሁለቱ ተጫዋቾች ምትክም ለቡድኑ አዲስ ያልሆኑ ተጫዋቾችን እንደጠሩ አብራርተዋል። ቡድኑ የ4 ቀን ልምምድ ተሞክሮ ከዚህ በፊት እንዳልነበረው የገለፁት አሰልጣኙ፣ በርዋንዳው የአቋም መለኪያ ጨዋታ ላይ ቡድናቸው ጥሩ ነገር ማሳየቱን ተናግረዋል።
“በዋናነት ፍላጎታችን የ2023ቱን የአፍሪካ ዋንጫ መቀላቀል ነው። ለዚህ ደግሞ የጊኒው የደርሶ መልስ ጨዋታ ወሳኝ ነው። በዚህም ከጨዋታዎቹ የበለጠውን ነጥብ ለማግኘት እንጥራለን። 6 ነጥብ መሪነታችንን ያስቀጥላል ፤ ቢያንስ ግን 4 ነጥብ ለማሳካት ነው ጨዋታዎቹን የምናደርገው” ያሉት አሰልጣኝ ውበቱ፣ በስብስቡ ውስጥ የሚገኙት ተጫዋቾች በጥሩ ተነሳሽነት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ከጊኒ ብሔራዊ ቡድን አጨዋወት ጋር በተገናኘ በተለይ ከቆሙ ኳሶች እና ተሻጋሪ ኳሶች ጋር ተያይዞ ቡድኑ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነና የተጋጣሚ ቡድን የተካነበትን የአጨዋወት መንገድ ማጥፋት ስለማይቻል በተቻለ መጠን ለመቀነስ እየተዘጋጁም አሰልጣኙ አመላክተዋል። ከዚህ ውጪ በልምምድ ወቅት መጠነኛ ጉዳት ያስተናገደው ረመዳን የሱፍ ጉዳቱ ለክፉ እንደማይሰጠው አክለዋል።
የዋልያዎቹ ተጋጣሚ ጊኒ ሞሮኮ ላይ ዝግጅቷን ከቀናት በፊት መጀመሯ ይታወቃል። በምድብ አራት ከኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ማላዊ ጋር የተደለደለችው የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ጊኒ አሠልጣኝ ካባ ዲያዋራ ከቀናት በፊት ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ ያደረጉ ሲሆን፣ ከግብ ጠባቂው ካማራ ሙሳ ውጭ በስብስቡ ሁሉም ተጫዋቾች ከአገር ውጭ የሚጫወቱ ናቸው።
የቡድኑ አሰልጣኝ ካባ ዲያዋራ ከዋልያዎቹ ጋር የሚደረጉትን ሁለት የደርሶ መልስ ጨዋታዎች አሸንፈው ሙሉ ስድስት ነጥብ እንደሚወስዱም ተናግረዋል፡፡
ሁለቱን የደርሶ መልስ ጨዋታዎች አስመልክተው ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ ያደረጉት አሰልጣኝ ዲያዋራ “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በሚገባ እናውቀዋለን፣ በምናውቃቸው መጠንም ተዘጋጅተናል” ብለዋል፡፡
« የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዘጠና በመቶ በላይ በአገር ውስጥ ሊግ በሚጫወቱ ልጆች የተገነባ ብሔራዊ ቡድን ነው፤ የባለፈው የቻን ውድድር በደንብ እንድናያቸው ዕድል ፈጥሮልናል፣ ኳስ ይዘው መጫወት ይፈልጋሉ፣ ብዙ ይሮጣሉ፣ ሶስቱንም ጨዋታዎቻቸውን ተመልክተን ለነሱ የሚሆን ታክቲክ አዘጋጅተናል፤ ሁለቱንም ጨዋታዎች አሸንፈን ስድስት ነጥብ ከኢትዮጵያ ላይ ወስደን ወደ ኮት ዲቯር እናቀናለን፡፡» ሲሉም እርግጠኛ ሆነው ተናግረዋል።
ከሜዳቸው ውጭ መጫወታቸው በውጤቱ ላይ ልዩነት ይፈጥር እንደሆነ የተጠየቁት አሰልጣኙ ሲመልሱ፣ ሞሮኮን የመረጡት ሁለቱም ፌዴሬሽኖች በስምምነት መሆኑን አስረድተዋል። ጨዋታዎቹ የሚካሄዱት የረመዳን ጾም ወቅት በመሆኑም ቡድናቸው በመሃል ጉዞ ሳያደርግ መጫወቱ ጥቅም እንደሚኖረውና የትራንስፖርት ወጪም እንደሚቀንስ አክለዋል። “በርካታ ጊኒያውያን በሞሮኮ እንደመኖራቸው በኛ ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖራል ብዬ አላስብም፣ ዋናው ነገር በርካታ ጊኒያውያውያን በስታዲየም ተገኝተው ጨዋታውን እንዲመለከቱ መጋበዙ ላይ ነው” በማለትም አሰልጣኙ አስተያየት ሰጥተዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መጋቢት 13 ቀን 2015 ዓ.ም