55 ዓመት በፊት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በተለይም እየተጋመሰ በሚገኘው መጋቢት ወር የወጡ ዘገባዎችን ዛሬው ዓምዳችን ለማስታወስ ወደናል። ከመራረጥናቸው ዘገባዎች መካከል አሥር ጥጃ በአገራችን ስለወለደችው ላም፣ ሲጃራ 5 ሳንቲም ጨምረው በ65 ሳንቲም ሲሸጡ የነበሩ ግለሰብ 50 ብር በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ክትትልና ቁጥጥር ስለመቀጣታቸው ይነግሩናል። እነዚህና ሌሎች ዘገቦችን ዛሬ ላይ መለስ ብለን ስንመለከታቸው ግርምትን የሚፈጥሩ ዘገባዎችን እንደሚከተለው እናስታውስ።
ላሟ ፲ ጥጃዎች ወለደች
አሰላ፤ (ኢ.ዜ.አ) አንዲት ላም በአንድ ጊዜ አሥር ጥጃዎች ወለደች። ከተወለዱት አሥር ጥጃዎች መካከል አንዱ በተፈጥሮው ትክክለኛ ጥጃ ሲሆን፤ ዘጠኙ ደግሞ መጠናቸው ትንንሽ ነበረ። እነዚሁ መጠናቸው አነስተኛ የሆኑት ጥጆች ወዲያውኑ ሲሞቱ፤ መጠኑ ከነርሱ ከፍ ይል የነበረው 10ኛው ጥጃ ደግሞ ስድስት ቀን ቆይቶ ሞቷል።
የላሚቱ ባለቤት አቶ ወትዩ ድልብቶ የሚባሉት ሲሆኑ፤ በአሩሲ ጠቅላይ ግዛት በጭላ አውራጃ ኮፈሌ ወረዳ ቆሩ ሁዱጋ በሚባለው ቀበሌ የሚኖሩ መሆናቸው ተገልጧል።
(መጋቢት 15 ቀን 1960 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን)
ለ፭ ሳንቲም ብልጫ ፶ ብር ተቀጡ
ከአዲስ ዘመን ጋዜጠኛ
የሐሰት ስም በመስጠትና ‹‹መሐመድ አህመድ ነኝ›› በማለት ሲያስቸግሩ የቆዩት አቶ ደላሞ አብደላ የተባሉ በተሰማ አባቀማው መንገድ ላይ የሚገኙ ነጋዴ ፷ ሳንቲም መሸጥ የሚገባቸውን ሲጃራ አምስት ሳንቲም አስበልጠው በ፷፭ ሳንቲም ስለሸጡ፤ የስድስተኛው ወረዳ ፍርድ ቤት ፶ ብር ቀጥቷቸዋል ሲል የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ማስታወቂያ ክፍል ገለጠ።
አቶ ደላሞ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ የቻሉት፤ ቀደም ብሎ በተሰጠው ተገድደው እንዲቀርቡ በሚለው በዳኛው ትዕዛዝ መሠረት፤ ሐያ አራት ሰዓት ፖሊስ ጣቢያ ገብተው ከታሰሩ በኋላ ነው። ይህም የሆነው፤ ሦስት ጊዜ የፍርድ ቤት ጥሪ ደርሷቸው ባለመቀበላቸውና ሕግን በመጣሳቸው ሲሆን አቶ ደላሞ እስር ቤት እያሉ የንግድ ሱቃቸው ዝግ ነበረ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፍርድ ቤት ቀርበው ዋጋ በማስበለጥ ተከሰው ከተቀጡት ነጋዴዎች መካከል፤ አቶ ደላሞ አስረኛው ናቸው። ተከሳሹ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተላኩ ተዘዋዋሪ ምድብ የዋጋ ተቆጣጣሪዎች (እንስፔክተር) በከፍተኛ ዋጋ ሲሸጡ እንደያዙዋቸው ተጠይቀው አምነዋል። ፍርድ ቤቱ አሻሽሎ ፶ ብር የቀጣቸውም፤ ወንጀሉን የፈጸሙት በማወቅ ሳይሆን፤ ባለማወቅ በስሕተት መሆኑን አቶ ደላሞ ስላመኑ፤ አስተያየት ተደርጎላቸው መሆኑንም የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ማስታወቂያ ክፍል በተጨማሪ አብራርቷል።
ከዚህም ጋር በማያያዝ ከዚሁ ክፍል የተሰጠው መግለጫ እንደሚመለክተው፤ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የዋጋ ቁጥጥር ክፍል፤ የከተማውን የዋጋ ሁኔታ በመደበኛና በተወሰነው መሠረት እንዲከበር ለማድረግ ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ የማይቆጠብ መሆኑንም ለመረዳት ተችሏል።
(መጋቢት 17 ቀን 1960 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን)
ዓመፀኛው ዝንጀሮ ተገደለ
አዲስ አበባ፤ (ኢ.ዜ.አ) ሁለት ቀን ሙሉ በመንደር ውስጥ እየተዘዋወረ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሰ ዝንጀሮ ተገደለ። በልደታ ወረዳ መካኒሳ ቀበሌ ውስጥ ከመጣበት ያልታወቀ አንድ ገመር ዝንጀሮ መጋቢት ፲፰ ቀንና መጋቢት ፲፱ ቀን ፯ ሰዎች ነክሶ ከማቁሰሉም በላይ፤ በመንደሩ የሚገኙትን ውሾች ሁሉ እንዲባረሩ አድርጓል።
በዚሁ ዝንጀሮ ከተነከሱት ፯ ሰዎች መካል ፬ቱ በብርቱ ስለቆሰሉ ለሕክምና ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ከአሜሪካ ሉተራን ሚሲዮን ቄስ ዓለም ታደሰ በላይ ገልጠዋል። በአውሬው ጉዳት እንዳይደርስባቸው ይከላከሉ ከነበሩት ሠፈርተኞች መካከል የስካንስካ ጋራዥ ሠራተኞች ትናንት በ፲፩ ሰዓት ገደማ ላይ በሦስት ጥይት ከመቱት በኋላ፤ ዝንጀሮው የሞተ መሆኑን ከሠፈርተኛው ለመረዳት ተችሏል። ዝንጀሮው ጤነኛ ወይም በውሻ በሽታ የተለከፈ መሆን አለመሆኑ የመካኒሳ ቀበሌ ምክትል ፖሊስ ጣቢያ ሊያረጋግጥ አልቻለም። በሠፈርተኛው ሰው ላይ ጉዳት ያደረሰው ዝንጀሮ እሬሳ አሁንም ከመካኒሳ በታች ከሚገኘው ወንዝ ዳር ተጥሎ ይገኛል።
(መጋቢት 21 ቀን 1960 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን)
የመንግሥት ሹማምንት ሚስት ማግባት አለባቸው
ከናይሮቢ፤(ሮይተር) ‹‹ የሌላውን ሰው ችግር ለመገንዘብ እንደችሉ፤ መሪዎች ሆኑ ሁሉ ሚስቶች ስለሚያስፈልጓቸው፤ የኬንያ ካቢኔ ሚኒስትሮች፤ ሌሎችም ከፍተኛ ሹማምንትና የምክር ቤት አባሎች ሚስቶች ማግባት አለባቸው ሲሉ አንድ የኬንያ ምክር ቤት እንደራሴ ከትናንት ወዲያ ሀሳብ አቀረቡ።
የኬንያ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሚስተር ቻርልስ ንጆንጆ ትዳር መያዝ የማስፈለጉን ጉዳይ እንዲገነዘቡት በሀሳብ አቅራቢው ተጠይቀው እንደነበር ታውቋል።
አርባ ዘመናቸውን ያለ ሚስት ያገባደዱት ሚስተር ንጆንጆ ግን ‹‹ ይህ የግል ጉዳይ ነው። ›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ንግግራቸውን በፈገግታ እያሳመሩ በሰጡት ምላሽ ለማግባት ሀሳብ ኖሮኝ ምኞቴን በገቢር ለመግለጽ ብዙ ሴቶች ጠይቄ እንቢም ብለውኝ ለብቻ መኖሬን ለምክር ቤቱ ለመግለጥ የማልፈልገው ነበር ›› አሉ።
(መጋቢት 17 ቀን 1960 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2015