ባለፈው እሁድ በአብያተ ክርስቲያናትና በሆቴሎች ላይ በተፈፀሙ የቦምብ ጥቃቶች እስካሁን ድረስ ከ320 በላይ ሰዎች የተገደሉባትና ከ500 የሚበልጡት ደግሞ የቆሰሉባት የደቡብ ምሥራቅ እስያዋ አገር ስሪ ላንካ በከባድ የኀዘን ድባብ ተውጣለች።
በጥቃቶቹ ዒላማ የተደረጉት ሦስት አብያተ ክርስቲያናትና አራት ሆቴሎች እንደነበሩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። ከጥቃቱ ሰለባዎች መካከል አብዛኞቹ ስሪላንካውያን ቢሆኑም የውጭ አገራት ዜጎችም እንደሚገኙበት ተገልጿል።
ለጥቃቱ ፈጥኖ በይፋ ኃላፊነት የወሰደ አካል ባይኖርም ራሱን እስላማዊ መንግሥት (ISIS) ብሎ የሚጠራው ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድን ትናንት ‹‹ጥቃቱን የፈፀምኩት እኔ ነኝ›› የሚል መግለጫ አውጥቷል።
የአገሪቱ ካቢኔ ቃል አቀባይና የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ግን ስሙ ብዙም የማይታወቅ አንድ እስላማዊ ድርጅትን ተጠያቂ አድርገዋል። የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ራጂታ ሴናራትኒ በኮሎምቦ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የፕሬዚዳንት ማይትሪፓላ ሲሪሴና መንግሥት ጥቃቱን ማክሸፍ አለመቻሉን ኮንነዋል።
ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ የአገሪቱ መንግሥት ከሳምንታት ቀደም ብሎ ስለጉዳዩ መረጃ ቢደርሰውም ችላ በማለቱ አሰቃቂው ጥቃት ሊፈፀም ችሏል።
«የውጭ አገራት የደህንነትና የስለላ ተቋማት አጥፍቶ ጠፊዎች ስሪ ላንካ ውስጥ ጥቃት ለመፈፀም እንዳቀዱ ከሁለት ሳምንታት በፊት ለመንግሥት አሳውቀው ነበር። የመከላከያ መስሪያ ቤቱም ለፖሊስ ኃላፊው ስለጉዳዩ አሳውቋል። የፖሊስ ክፍልም መረጃው ከደረሰው ከሁለት ቀናት በኋላ ለሚመለከተው የበላይ አካል ቢያሳውቅም አሳዛኙ አደጋ ተከስቷል፤ ተጠያቂዎቹ እኛው ነን፤ ሁሉንም ሰው ይቅርታ እንዲያደርግልን እንማጸናለን» ብለዋል።
የኮሎምቦ ሊቀ-ጳጳስ ማልኮም ራንጂት በበኩላቸው «የተፈፀመው ድርጊት እጅግ አሳዛኝና ልብ ሰባሪ ነው፤ አደጋው ሳይፈጸም በፊት መቅጨት ይቻል እንደነበር ባወቅን ጊዜ ደግሞ ኀዘናችን እጥፍ ሆኗል» ብለዋል።
በሌላ በኩል እሁድ ዕለት ከተፈፀመው ጥቃት ጀርባ የሌሎች ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድኖች እገዛ ሳይኖርበት እንደማይቀር የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። «አንድ ትንሽ ድርጅት ብቻ ይህንን ያህል ውድመት የሚያስከትል ጥቃት ይሰነዝራል ብለን አናስብም። ከሌሎች አካላት ተደርጎለታል ብለን የጠረጠርነውን ድጋፍና ቡድኑ መሰል ጥቃቶችን ለመፈጸም እንዴት አቅም እንዳገኘ በማጣራት ላይ ነን» በማለት ተናግረዋል።
በስሪ ላንካ ታዋቂ የሆኑ ሁለት እስላማዊ ድርጅቶች ጥቃቱን አውግዘው መንግሥት በድርጊቱ የተሳተፉትን ሁሉ ከባድ የተባለውን ቅጣት እንዲቀጣቸው ጠይቀዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በበኩሉ፣ አሸባሪ ቡድኖች ሌሎች ተጨማሪ ጥቃቶችን ሊፈፅሙ እንደሚችሉ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። የጥቃቱ ኢላማዎችም የቱሪስቶች መናኸሪያዎች፣ የገበያ ማዕከላት፣ ሆቴሎች፣ የአምልኮ ስፍራዎች፣ የትራንስፖርት ቦታዎችና የአውሮፕላን ማረፊያዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ መስሪያ ቤቱ በማስጠንቀቂያ መልዕክቱ ገልጿል። ጃፓንና አውስትራሊያን ጨምሮ ሌሎች አገራትም ዜጎቻቸው ወደ ስሪ ላንካ እንይጓዙ መክረዋል።
ተንታኞች እንደሚሉት አብያተ ክርስቲያና ትና ቱሪስቶች የሚቆዩባቸው ሆቴሎች የጥቃቱ ኢላማዎች መሆናቸው ቡድሂስቶች ለሚበዙባት አገር ያልተለመደና አስደንጋጭ ክስተት ነው። ጥቃቶቹ ከዚህ ቀደም በአል- ቃይዳና በእስላማዊ መንግሥት ከተፈጸሙት ጥቃቶች ጋር የሚያመሳስላቸው ነገር እንዳለም ተንታኞቹ ተናግረዋል።
በሁለቱ ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድኖች ላይ ያተኮሩ በርካታ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ያከናወኑት አልቶ ላበቱቡን የተባሉ ባለሙያ፣ ጥቃቶቹ ለስሪ ላንካ አዲስ እንደሆኑ ይናራሉ። እነዚህ የተቀነባበሩ ጥቃቶች ሁለቱ አሸባሪ ቡድኖች በመካከለኛው ምሥራቅና በደቡብ ምሥራቅ እስያ ከፈፀሟቸው ጥቃቶች ጋር የሚመሳሰሉባቸው ባህርያት አሉ። «ጥቃቶቹ ስሪ ላንካ ውስጥ ባሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ብቻ ይፈጸማሉ የሚል እምነት የለኝም። ምናልባትም በሕንድና በፓኪስታን የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች በጥቃቱ ተሳትፈው ሊሆን ይችላል» ይላሉ።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የእስያ ከፍተኛ የፀረ-ሽብር ዘመቻ ባልደረባ፣ ጥቃቶቹ በቂ ልምድና የሰው ኃይል ባላቸው ቡድኖች የተፈፀሙ እንደሆኑ ለርይተርስ ተናግረዋል። አራት ቦምቦች በተመሳሳይ ሰዓት የፈነዱ ሲሆን፤ተቀጣጣይ ነገሮችና ፈንጂዎች የተጫኑባቸው መኪናዎችም በተለ ያዩ አካባቢዎች መገኘታቸውን የአገሪቱ ባለሥል ጣናት ገልጸዋል።
ፕራቲዩሽ ራኦ የተባሉ ተንታኝ ደግሞ ጥቃቶቹን ከእስላማዊ መንግሥት ጋር ለማገናኘት የሚያስችል ምንም ዓይነት በቂ ማስረጃ እንደሌለ ይሞግታሉ። እርሳቸው እንደሚሉት የጥቃቶቹ አፈፃፀምና ጥቃቶቹ ያስከተሉት ውድመት ከጥቃቶቹ ጀርባ የውጭ ኃይሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ቢያመለክቱም፣ ጉዳዩን በቀጥታ ከእስላማዊ መንግሥት ጋር ለማያዝ የሚያስችል ተጨባጭ ማስረጃ ግን የለም። «የጥቃቶቹ መነሻ ግን የእስላማዊ መንግሥት አስተሳሰብና የጥቃት ዘዴ ሊሆን ይችላል»ይላሉ።
በሌላ በኩል መንግሥት ጥቃቶቹ እንዳይፈጸሙ ቀድሞ ያደረገው ጥረት አለመኖሩ የፖለቲካ ቁማር ያለበት ነው የሚሉ ወገኖችም አልታጡም። የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ራጂታ ሴናራትኒ በጋዜጣዊ መግለጫቸው የአገሪቱን የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥራቸው ስር ያደረጉትን ፕሬዚዳንት ማይትሪፓላ ሲሪሴናንና አስተዳደራቸውን ወቅሰዋል። የሚኒስትሩ ወቀሳ የተሰማው ጠቅላይ ሚኒስትሩ «ፕሬዚዳንቱ ጥቃት ሊፈፀም እንደሚችል የሚጠቁም መረጃ ነበራቸው» ካሉ በኋላ ነው።
ባለፈው ጥቅምት ወር ፕሬዚዳንት ሲሪሴና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከስልጣናቸው ስለማሰናበታቸው ይፋ አድርገው ኮሎምቦ መንግሥታዊ ቀውስ ሲንጣት ነበር። በመጨረሻም የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፕሬዚዳንቱን ውሳኔ ውድቅ በማድረጉና ጠቅላይ ሚኒስትሩም ወደ ኃላፊነታቸው በመ መለሳቸው ውጥረቱ በረድ ሊል ችሏል። ከዚያ ወዲህ በጠቅላይ ሚኒስትሩና በፕሬዚዳንቱ መካከል ያለው አለመግባባት ተባብሷል። የሰሞኑ አደጋ ደግሞ ወትሮውንም ቢሆን የማይጣጣሙትን ሁለቱን ሰዎች ለባሰ ፍጥጫ ዳርጓቸዋል።
በአገሪቱ ምክር ቤት የተቃዋሚው ፓርቲ አባል የሆኑት ናማል ራጃማክሳ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ካቢኔያቸው በጥቃቱ ላይ የያዙትን የፖለቲካ ቁማርና ጨዋታ ማቆም አለባቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥቃት ሊፈፀም እንደሚችል ለመንግሥት ደርሷል ስለተባለው መረጃ እንደማያውቁ ከተናገሩ በኋላ ተጠያቂነቱን ወደ ፕሬዚዳንቱ በማዞር የፖለቲካ ነጥብ ለማስቆጠር የሚያደርጉት ሙከራ ተቀባይነት የለውም» ብለዋል።
ዘግየት ብለው በወጡ መረጃዎች መሠረት ደግሞ የጥቃቶቹ ዋነኛ ተዋናይ የነበሩት የአንድ ባለፀጋ ቅመማ ቅመም ነጋዴ ልጆች የሆኑ ሁለት ወንድማማቾች እንደሆኑ ተገልጿል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ ከሟቾቹ መካከል ከ45 በላይ የሚሆኑት ሕፃናት እንደሆኑ ይፋ አድርጓል። የሟች ሕፃናት ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም የድርጅቱ ቃል አቀባይ ጀኔቫ ውስጥ በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል።
አንድ የስሪ ላንካ መከላከያ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣን፣ በጥቃቶቹ መንስዔ ላይ ያተኮረው ምርመራ የመጀመሪያ ደረጃ ውጤት እንደሚያሳየው ጥቃቶቹ ባለፈው መጋቢት ወር ኒውዚላንድ ውስጥ በሚገኙ መስጊዶች ላይ ለተፈጸሙት ጥቃቶች የተሰነዘሩ የበቀል እርምጃዎች ናቸው ብለዋል።
ጥቃቱን ተከትሎም የስሪላንካ መንግሥት ሁሉንም የማኅበራዊ ሚዲያ በጊዜያዊነት መዝጋቱን ይፋ አድርጓል። የፕሬዚዳንቱ ቃል አቀባይ ኡዳያ ሴኔቪራንቴ የሀሰት መረጃዎችን ስርጭት ለመቆጣጠር ሲባል መንግሥት ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በጊዜያዊነት መዘጋታ ቸውን ተናግረዋል።
እሁድ ዕለት የተፈፀሙት ጥቃቶች በታ ሚል ተገንጣዮችና በመንግሥት መካከል ለ26 ዓመታት ያህል ሲካሄድ የቆየው ደም አፋሳሹ የእርስ በእርስ ጦርነት ካበቃበት (እ.አ.አ ከ2009) ወዲህ የተፈፀመ የመጀመሪያው አሰቃቂ ጥቃት ነው ተብሏል።
ከ100ሺ በላይ ሰዎችን ሕይወት በቀጠፈው የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት መሰል የቦምብ ጥቃቶች የተለመዱና የስሪ ላንካ የየዕለት ገጠመኞች ነበሩ። ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የእርስ በእርስ ጦርነት በዚያች አገር የሚገኙ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ቦምቦችንና ጥቃት መፈፀሚያ ሌሎች ጦር መሣሪያዎችን በቀላሉ እንዲያገኙ ዕድል እንደሚሰጣቸውም ተንታኞች ያስረዳሉ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16/2011
በአንተነህ ቸሬ