ሎካ ዓባያ ወረዳ በሲዳማ ክልል ከሚገኙ ወረዳዎች መካከል በቆዳ ስፋቱ ቀዳሚው ነው።የአየር ጠባዩ ከፊል ቆላማ ሲሆን፣ ከሌሎች የክልሉ ወረዳዎች በበለጠ በበልግና በመኸር በቆሎና ቦሎቄ በስፋት ይመረትበታል።ወረዳው በእንስሳት ሀብቱም ጭምር ይታወቃል።በክልሉ መንግሥት የሚተዳደር 50 ሺ ሄክታር የሚሸፍን ብሔራዊ ፓርክም በወረዳው ይገኛል። ከሁለት ዓመታት በፊት የተመረቀው የጊዳቦ ግድብ የሚገኘውም በዚሁ ወረዳ ነው።ግድቡ በሲዳማ ክልል ብቻ አምስት ሺ ሄክታር መሬት በመስኖ ሊያለማ ይችላል።በአሁኑ ወቅት በግድቡ ባለሀብቶች በሞተር ፓምፕ በመጠቀም የተለያዩ የግብርና ልማት ሥራዎች እያከናወኑ ይገኛሉ።
የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ መስፍን መልካሙ እንደሚሉት፤ በወረዳው በዝናብ እና በመስኖ ልዩ ልዩ ሰብሎች ይመረታሉ። አባያ ዙሪያ ተብሎ በሚጠራው በእዚህ አካባቢ በርካታ የአገሪቱ ታዋቂ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ተሰማርተው አትክልትና ፍራፍሬ፣ የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት እና ሌሎች ሰብሎችን እያለሙ ናቸው፡፡ ‹‹የጊዳቦ ግድብ ፕሮጀክት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከተመረቀ አመታት ተቆጥረዋል፤ በኦሮሚያ በኩል ሥራው በአጠቃላይ ተጠናቆ ወጣቱም አርሶ አደሩም ወደ ሥራ ገብተዋል›› የሚሉት አቶ መስፍን፣ በሲዳማ ክልል በኩል ግን ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ወደ ሥራ አልገባም ሲሉ ይጠቁማሉ። ‹‹በፕሮጀክቱ አለመጠናቀቅ ላይ አርሶ አደሩ ቅሬታውን ሲያቀርብ፣ እኛም ከታች ወደላይ ሪፖርት ስናደርግ ቆይተናል›› ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፣ አሁን የክልሉ መንግሥት ትኩረቱን በእዚህ ግድብ ላይ አድርጎ እየሠራ መሆኑን ያብራራሉ።
ዋና አስተዳዳሪው የሎካ ዓባያ አካባቢ የኢኮኖሚ ኮሪደር ተደርጎ መለየቱን እና ግድቡም ለይርጋ ዓለም አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በቅርብ ርቀት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ የአግሮ ኢንዱስትሪው በአካባቢው መገንባት አንዱ መነሻም ይኸው ፕሮጀክት መሆኑን ይናገራሉ። በቅርቡ በዚሁ አካባቢ አንድ ሺ 200 ወጣት የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን በዘመናዊ መስኖ ልማት እንዲሰማሩ የሚያስችል ፕሮጀክት ሐዋሳ ላይ ይፋ ተደርጓል።ፕሮጀክቱ በተለይ ለሎካ አባያ ወረዳ ትልቅ የምሥራች ይዞ ከተፍ ብሏል። ግድቡ በሲዳማ እና ኦሮሚያ ክልል በአጠቃላይ 13 ሺ ሄክታር መሬት ሊያለማ የሚችል ነው።በሲዳማ ክልል በኩል አምስት ሺ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ያስችላል። ምሩቃኑም ይህን መሬት እና የጊዳቦ ግድብን ተጠቅመው በዘመናዊ መስኖ እንዲሰማሩ ይደረጋል።ፕሮጀክቱ ለአምስት አመታት የሚተገበር ሲሆን፣ ከተባበሩት አረብ ኤምሬት ባንክ በሚገኝ 935ሚሊዮን 511ሺ 444 ብር የሚካሄድም ነው።
ይህ የሲዳማ ክልል የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ምርታማነት ማሳደጊያ ድጋፍና የወጣቶች ሥራ ፈጠራ በሚል የሚጠራው ፕሮጀክት ይፋ በተደረገበት ወቅት የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ሙሉጌታ ጳውሎስ በሰጡት ገለጻ እንዳብራሩት፤ ፕሮጀክቱ ለሥራ እድል ፈጠራና ለድህነት ቅነሳ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው የተቀናጀ ፕሮጀክት ነው።ለአገር ምጣኔ ሀብታዊ እድገትም ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል።የግብርና ምርትና ምርታማነት የሚያሳድግ በመሆኑ ምርቶቹ ለአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሲቀርቡ የውጭ ምንዛሬም ያስገኛል።የውጭ ምንዛሬ ሲገኝ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ገቢ ላይ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል። በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እየተደረጉ ሲሆን፣ ወጣቶቹ የሚሰማሩት በመንግሥት ለተገነቡት አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚያስፈልጉ ምርቶችን በማምረት ላይ ይሆናል።የግብርና ምርትና ምርታማነት እድገትን በመጨመር በአገሪቱ ያሉትን አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የግብአት ፍላጎት ማሟላትን ታሳቢ ያደረገ ፕሮጀክት ነው።
ጊዳቦ ግድብ ፕሮጀክት የተገነባው ሰፊ መሬት ባለበት አካባቢ ሲሆን፣ በተለምዶ ከሚሠራው የግብርና ሥራ ወጣ ባለ መልኩ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የእርሻ ሥራ በማካሄድ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግን አላማው ያደረገ ነው።በቅርቡ ይፋ የተደረገውና የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ወጣቶች የሚሳተፉበት ፕሮጀክትም የዚህ ተከታይና ወደ ትግበራ የሚገባበት መሆኑ ተጠቁሟል። ፕሮጀክቱ ከሌሎች የመስኖ ፕሮጀክቶች ይለያል፤ ከዚህ በፊት የተተገበሩ በርካታ የመስኖ ፕሮጅክቶች የየአካባቢውን ማህበረሰብ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥን ታሳቢ ተደርገው የተቀረጹ ናቸው። ይህ ፕሮጀክት ግን የአካባቢውን ማህበረሰብ ይዞ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ሥራ አጥ ወጣቶችን እንደ ሙያቸው በማደራጀት በአምስት አመት ውስጥ መካከለኛ ባለሀብት እንዲሆኑ ማስቻል መሆኑ ተመልክቷል።
እንደ ፕሮጀክቱ አስተባባሪ ገለጻ፤ ምሩቃኑ ወደ ሥራው እንዲገቡ የሚደረገው በማህበር በማደራጀት ነው፤ አንድ ማህበር 12 የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ወጣቶችን ይይዛል፤ ጊዳቦ ላይ 100 ማህበራት ይኖራሉ።አንድ ማህበር ደግሞ በስሩ ያልተማሩ ወይም ሰርቲፋይድ ያልሆኑ 100 ወጣቶችን አንዲይዝ ይደረጋል።በመቶ ማህበራት ውስጥ ከምሩቃኑ ጋር ወደ 12 ሺ ወጣቶች ከዚህ ፕሮጀክት ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።በተዘዋዋሪ መንገድ ደግሞ በግንባታው ሂደት ከ15 ሺ በላይ ሰዎች የሥራ እድል ያገኛሉ።ሁለቱ ሲደመር በትንሹ ከ28 ሺ በላይ ሰዎች ከዚህ ፕሮጀክት ተጠቃሚ ይሆናል ተብሎ ይገመታል። በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ ባራሳ እንዳሉት፤ ክልሉ ከተመሠረተ ባለፉት ሁለት አመታት የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራቸው ከሚገኙ ተግባሮች መካከል አንዱ ወጣቱን ተጠቃሚ ማድረግ ነው። በተለይ ትምህርታቸውን አጠናቀው የሚመለሱ ወጣቶች መቀጠር ብቻ ሳይሆን፣ ራሳቸው ሥራ ፈጥረው መቅጠር፣ ሀብት ማፍራት የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ታቅዶ ሲፈጸም ቆይቷል።
ባለፉት ሁለት አመታትም ቁጥራቸው ጥቂት ያልሆኑ ወጣቶች በራሳቸው ሠርተው ሀብት ማፍራት የቻሉበት ሁኔታ መፈጠሩን ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ ጠቅሰው፣ ሁሉንም ወጣቶች ለመድረስ የሚያስችሉ እድሎችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። የፌዴራል መንግሥት ከመስኖ ልማት ጋር በማቀናጀት ወጣቱን ተጠቃሚ ለማድረግ ፕሮጀክት ነድፎ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን አመልክተው፣ አሁን ፕሮጀክቱ ወደ ተግባር የሚተገበርበት ደረጃ ላይ መደረሱን አስታውቀዋል።የፌዴራሉ መንግሥትም ለጋሽ ድርጅቶችን አፈላልጎ ለአምስት አመት የሚተገበር፣ ወጣቱን ማእከል ያደረገና ምርታማነትን የሚያሳድግ የተቀናጀ የልማት ፕሮግራም አዘጋጅቶ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባቱን ጠቅሰው፣ ይህ ፕሮግራም የታለመለትን ግብ እንዲመታ የሁሉም አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
‹‹ፕሮጀክቱ ከሚካሄድበት ከጊዳቦ ግድብ የመስኖ ካናል ጋር በተያያዘ ያላለቁ ግንባታዎች እንዲጠናቀቁና ከዚህ ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ሌሎች ሥራዎችም ፈጥነው እንዲያልቁ የፌዴራሉ መንግሥት ከክልሉ መንግሥት ጋር ተባብሮ ፈጣን እርምጃዎችን በመውስድ ያስተካክላል ብለን እንጠብቃለን›› ሲሉም ገልጸዋል።‹‹ፕሮጀክቱ በፍጥነት እንዲተገበርና በተለይም ወጣቱን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ተግባራዊ እንዲደረግ ሥራውን እንዲመራ የተሰየመው የስትሪንግ ኮሚቴ አባላት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅብናል›› ብለዋል፡፡
ሥራው ወጣቶችን በማደራጀት የሚተገበር እንደመሆኑ ከዚህ አንጻር የተደራጀው የክልሉ ቢሮ በዚህ መስክ ፈጣን እርምጃ ለመውሰድ የሚጠበቅበትን ለማድረግ እየተዘጋጀ እንደሚገኝም ጠቅሰው፣ ሥራው ከአግሮ ኢንዱስትሪ ጋር ተሳስሮ ልማቱ እንዲፋጠን የሚደረግበት መሆኑን ገልጸዋል። ‹‹ይህ ወጣቱን ተጠቃሚ ለሚያደርገውና ምርትና ምርታማነትን ለሚያሳድገው ለዚህ ፕሮጀክት መሳካት ሁላችንም የሚጠበቅንን በጊዜና በሰዓቱ በማድረግ እንረባረብ›› ሲሉም ጥሪ አስተላልፈዋል። የክልሉ ውሃ፣ ማእድንና መስኖ ቢሮ ኃላፊ አቶ ውብሸት ጸጋዬ እንደተናገሩት፤ ክልሉ ካለው የቆዳ ስፋት አንጻር ሲታይ ሲዳማ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አለበት። በክልል ደረጃ በዚህ ላይ መግባባት ላይ ተደርሶ እየተሠራም ነው።
‹‹የዚህ ፕሮግራም ዋናው አላማ ባለን አካባቢ ምን ዓይነት ሥራ ብንሰራ ተጠቃሚ ያደርገናል የሚለውንም የያዘ ነው›› ያሉት አቶ ውብሸት፣ ይህ ፕሮጀክትም ወጣቱን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ይገልጻሉ። ለዚህ የሚያስፈልጉ የመሬትና የመሠረተ ልማት ዝግጅቶች እንዳሉም ጠቅሰው፣ ከክልሉ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ጋር በመሆን ከአግሮ ኢንዱስትሪ ጋር የትስስር ሥርዓት መፍጠር እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ። ወጣቱን ሙያው በሚፈልገው ስብጥር መሠረት ማደራጀት ያስፈልጋል ያሉት የቢሮ ኃላፊው፣ ሥራው በጋራ እንደሚሠራና ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ይወጣሉ የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል። ይህ ሥራ መፍጠንና መጠናከር እንዳለበትም አስገንዝበው፣ ‹‹የጊዳቦ መስኖ ፕሮጀክት የዋና ካናል ሥራው በተባለው ልክ ሳይጠናቀቅ ሁለተኛና ሦስተኛ የመስኖ ካናሎችን ሥራ ለማከናወን ይቸግራል›› ብለዋል።ግንባታውን ያካሄደው አካል የዋናውን ካናል ሥራ እንዲጨርስም ጠይቀዋል።በአካባቢው ተደራጅተው ለሚገቡት ወጣቶች የሚያስፈልጉ እንደ ካምፕ፣ ትምህርት ቤቶች፣ የህክምና ተቋም፣ የኃይል አቅርቦት የመሳሰሉት መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የፕሮጀክቱ አንዱ አካል ማህበረሰቡንና ወጣቱን ተጠቃሚ ማድረግ መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹ለቀጣይ ሥራችን መፋጠን ትልቅ ፋይዳ ያላቸው እነዚህ መሠረተ ልማቶች እንዲገነቡ አስፈላጊው ሁሉ እንዲደረግ የግድቡን ግንባታ ላካሄደው አካል መልዕክት አስተላልፈዋል። የክልሉ መንግሥት ወደ ጊዳቦ ግድብ የሚወሰደውን እስከ ቡክቶ ያለውን መንገድ ቀላል በማይባል ሀብት በጠጠር መንገድ በራሱ በጀትና ኃይል በመሥራት መገንባቱንም ጠቅሰው፣ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልጉትን በማቅረብ በኩልም እየተጋገዝን እንድንሠራ አደራ እላለሁ ብለዋል።እኔም እንደ ቢሮዬ በመስኖ ልማት ኤጀንሲ ስር ያለውን አካል በማጠናከር፣ በመከታተልና በመደገፍ አሠራለሁ ሲሉም አረጋግጠዋል።
ፕሮጀክቱ በሦስት ክልሎች የሚካሄድ ሲሆን፣ ሥራውም እንደ አገር በስትሪንግ ኮሚቴ የሚመራ ነው፤ በክልል ደረጃም ለጉዳዩ ትኩረት ከመስጠት አኳያ በሲዳማ ክልልም በምክትል ርእሰ መስተዳድሩ የሚመራ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጣ ስትሪንግ ኮሚቴ መቋቋሙን የቢሮ ኃላፊው ጠቅሰው፣ ሥራው ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ለማድረግ ኮሚቴው ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል። በቆላማ አካባቢና መስኖ ልማት ሚኒስቴር የብሔራዊ ፔስኤፔ/ productive inhancement support for agroindustry parks / ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ጌታሰው መኮንን በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳሉት፤ ፕሮጀክቱ በአማራ፣ ሲዳማና ኦሮሚያ ክልሎች ላይ ይሠራል።በአማራ ክልል በጣና እና በለጪት የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች፣ በአሮሚያ ክልልና ሲዳማ ክልል ደግሞ በጊዳቦ ግድብ ፕሮጀክት ላይ የሚተገበር ነው።በአጠቃላይ 12 ሺ 600 ሄክታር መሬት በላይ በመስኖ ማልማት የሚያስችል ነው፤ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ሦስት ሺ ወጣቶችንም ያሳትፋል።ለሦስቱ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግብአት እንዲያቀርብ ተደርጎም የተቀረጸ ነው።
አቶ ጌታሰው ይህን ፕሮጀክት ለየት የሚያደርገው ሞዴል ፕሮጀክት ይሆናል ተብሎ በመታሰቡ መሆኑን ይገልጻሉ።ወጣቶች ከግብርና ጋር በተገናኘ ማሽኖችን መሠረት ባደረገ መልኩ የዘመናዊ አርሻ መሣሪያዎችን በመጠቀም የእርሻ ሥራውን በማሳለጥ ለሌሎች ፕሮጀክቶች ሞዴል ተደርጎ የሚሠራበት መሆኑን ጠቁመዋል። እንደ አቶ ጌታሰው ገለጻ፤ ከግድቡ ግንባታ አለመጠናቀቅ ጋር የተያያዘውን ችግር በጋራ መፍታት ይገባል። ፕሮጀክቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት እንደተጠቆመው የክልሉ መንግሥት ተቋራጮች የፕሮጀክት ኃላፊዎች አመራሮች ቁጭ ብለው መምከርና ችግሮቹ በጋራ የሚፈቱባቸውን መንገዶች መቀየስ ይኖርባቸዋል። ቶሎ ቶሎ እየተገናኙ ሂደቱን መገምገም መቻል አለባቸው። ምክንያቱም የክልል ርእሳነ መስተዳድሮች ትልቅ ስልጣን አላቸው።ስለዚህ ከሲሚንቶ አቅራቢ ድርጅቶች ጋር እየተነጋገሩ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ፕሮጀክቶች ቅድሚያ እንዲሰጥ ማድረግ አለባቸው።
‹‹ወደፊትም በተባለው ፍጥነት ፕሮጀክቶች እንዳይጠናቀቁ የሚያደርጉ ችግሮችን መለየት ያስፈልጋል›› ያሉት አቶ ጌታሰው፣ ‹‹ችግሩ ተለይቷል፤ ዋናው ፋይናንስ ነው።በዚህ ፕሮጀክት ደረጃ የምናየው ዋናው የተባበሩት አረብ ኤምሬት ልማት ባንክ ድጋፍ ነው፤ ድጋፉ ሲመጣ ተቋራጮችንና አማካሪዎችን ለይቶ ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደረጋል›› ሲሉ ገልጸዋል።
‹‹ይህን ፕሮጀክት ይዞት የነበረው የኢትዮጵያ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ነው።ስለዚህ ሥራውን ለማፋጠን አዲስ ጨረታ ከማውጣት ለእሱ ሰጥተነው የኮንትራት አስተዳደሩን አሻሽሎ ሥራዎችን በአግባቡና በሚፈለገው ፍጥነት እንዲሄድበት ከእኛ ከአሰሪው መስሪያ ቤት ክትትልና ቁጥጥር ያስፈልጋል›› ሲሉም አስገንዝበዋል።
‹‹ፕሮጀክቱ በተለያዩ ምክንያቶች መዘግየቱን ጠቅሰው፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ይህን ኃላፊነት ወስዶ ወደ አምስት የሚሆኑ ሰከንደሪ ካናሎችን በፍጥነት ለመገንባት ከኢትዮጵያ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ጋር ውል ለማድረግ ድርድር እያደረገ ነው፤ እሱን ማፋጠን ይገባል። የፕሮጀክት አመራራችንንና ኮንትራት አስተዳደራችንን በደንብ ማሻሻል ይኖርብናል።በዚህ መሠረት አምስቱን ሰከንደሪ ካናሎች ወደ ሥራ ማስገባት ከተቻለ ችግሮች እየተፈቱ ይሄዳሉ ብዬ አገምታለሁ። የፕሮጀክት እና ኮንትራት አስተዳደራችንን የክትትል ሥርዓታችን ሲስተም ማሻሻል ይገባናል፤ ይህን ይህን ካሻሻልን ችግሮች የማይፈቱበት ምንም ምክንያት አይኖርም ሲሉ ገልጸዋል።
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 11 ቀን 2015 ዓ.ም