የሮም ማራቶን ነገ ይካሄዳል። በዚህ ውድድር ላይ ታዲያ አንድ ለየት ያለ ተወዳዳሪ ብቅ ይላል ተብሎ ይጠበቃል። 15 ሺ ያህል ሰዎች በሚሳተፉበት በዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያዊው ኤርሚያስ አየለ ሙሉውን ማራቶን በባዶ እግሩ እንደሚሮጥ ተረጋግጧል። የ45 ዓመቱ የቀድሞው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ኤርሚያስ አየለ ይህንን የሚያደርገው ታላቁን የማራቶን ጀግና አበበ ቢቂላን ታሪክ በሰራባቸው የሮም ጎዳናዎች ላይ ለመዘከር በማሰብ ነው። ለዚህም ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቋል። ውድድሩን ከ3፡30-4፡00 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ያሰበው ኤርሚያስ በመቀጠልም በአቴንስ፣ ቶኪዮና ፓሪስ ማራቶኖች ላይ በተመሳሳይ በባዶ እግሩ በመሮጥ አበበ ቢቂላን እንደሚዘክር ገልጿል። ከዚህ ቀደም በዳይሬክተርነት ይመራው በነበረው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሁለት ጊዜ እንደዚሁም በሃዋሳ ግማሽ ማራቶን አንድ ጊዜ በተመሳሳይ በባዶ እግሩ ተወዳድሯል። ሙሉ ማራቶን በባዶ እግሩ ለመሮጥ ሲዘጋጅ ግን ይህ የመጀመሪያው ነው።
አበበ ዘመን የማይሽረውን የሮም ኦሊምፒክ የማራቶን ገድል ከፈጸመ ከ63 ዓመት በኋላ ነገ በሚካሄደው የሮም ማራቶን ከኤርሚያስ በተጨማሪ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ተመሳሳይ ነገር ለማድረግ መሰናዳታቸውም ተሰምቷል። አበበ ቢቂላ ከኢትዮጵያ ባሻገር የጥቁር ሕዝቦች የመጀመሪያውን የኦሊምፒክ ማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ካጠለቀ ከስድስት አስርት ዓመታት በኋላ የአገሩ ልጆች ልክ እንደሱ በባዶ እግራቸው አርባ ሁለት ኪሎ ሜትርን በመሮጥ ሊዘክሩት መዘጋጀታቸው የአለም መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ስቧል።
የጀግናውን አትሌት ገድል ለማስታወስና ሃሳቡን በተግባር ለማሳየት የተዘጋጀው ኤርሚያስ ‹‹አበበ ቢቂላ የስኬትን መንገድ የቀየሰው ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያንም ጭምር ነው። እሱ የመጀመሪያውን የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀ የመጀመሪያው ጥቁር አትሌት ነው። ይሁንና የሚገባውን ያህል ክብር አግኝቷል ብዬ አላስብም። ታሪኩ ሁሌም ስለሚደንቀኝም እሱ ታሪክ በሰራበት ስፍራ ላይ እሱ እንዳደረገው ባዶ እግሬን ለመሮጥ አሰብኩ። በዚህም እሱ ለኢትዮጵያ እና ለአትሌቲክስ ያበረከተውን አስተዋጽኦ ማሳየት እፈልጋለሁ›› በማለት ተናግሯል።
በእርግጥ በሮም ማራቶን ተካፋይ መሆን የታሪክ አካል መሆን ብቻም አይደለም። ስለሩጫው የሚያውቁ በሮም ማራቶን መሮጥ ‹‹ሙዚየም ውስጥ እንደመሮጥ ነው›› በማለት ብዙዎች ይናገራሉ። ምክንያቱ ደግሞ በጥንታዊቷና ውቧ ከተማ መሮጥ ከፉክክር ባለፈ በርካታ አስደሳች ጉዳዮች ስላሉት ነው። ለ41 ዓመታት በቆየው በዚህ ተወዳጅ ውድድርም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተካፍተለውበታል። ነገ በሚካሄደው የዘንድሮው ውድድርም 15ሺ ሯጮች የሚካፈሉበት ሲሆን፤ እንደቀደሙት ዓመታት በድምቀት ለማካሄድም ዝግጅቱ ተጠናቋል። ለሩጫው ድምቀት የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም የሩጫውን ቀን ብቻ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።
በወንዶች በኩል ያለፈው ዓመት በዚሁ ውድድር ተካፍሎ የቦታውን ክብረወሰን በመስበር አሸናፊ የነበረው ኢትዮጵያዊው አትሌት ፍቅሬ በቀለ በዚህ ዓመትም ድሉን ለመድገም መዘጋጀቱ ተረጋግጧል። ከሁለት ደቂቃ በላይ በማሻሻል 2:06:48 ሰአት በመሮጥ የሮም ማራቶን ባለ ፈጣን ሰዓት አትሌት የሆነው ፍቅሬ በዚህ ውድድርም በተመሳሳይ አሸናፊነቱ ከእጁ ሊወጣ እንደማይችል ተገምቷል። በርካታ አፍሪካውያን አትሌቶች እንደሚሮጡ በታወቀበት በዚህ ውድድር ሰዓታቸው ከ2፡00 ሰዓት ከ 10 ደቂቃ በታች የሆኑ በርካቶች ሲሆኑ፤ ሶስት የሚሆኑት ደግሞ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው።
ህም ለፍቅሬ ፉክክሩን ፈታኝ ሊያደርግበት የሚችል እንደሆነ ቢታወቅም በዚያው ዓመት በሊዝበን ማራቶን ተካፍሎ ያለውን ፈጣን ሰዓት በ32 ሰከንዶች ማሻሻል መቻሉ አትሌቱ ያለውን አቅም የሚያስገነዝብ ነው። አትሌቱ ፍራንክፈርትን ጨምሮ በተለያዩ ማራቶኖች በመሮጥ ያዳበረውን የዓመታት ልምዱን በመጠቀም በተከታታይ አሸናፊ ሊሆን እንደሚችልም ቅድመ ግምቱን አግኝቷል። አትሌት አለሙ ገመቹ፣ ብርሃኑ ሃዬ እና ሲሳይ ፍቃዱ ደግሞ በኢትዮጵያ በኩል ተሳታፊ የሚሆኑና ለአሸናፊነትም ግምት ያገኙ አትሌቶች ናቸው።
ሴቶች በኩልም በተመሳሳይ አፍሪካውያን አትሌቶች በብዛት ተሳታፊዎች ሲሆኑ፤ አትሌት ዝናሽ ደበበ ደግሞ ለአሸናፊነቱ ተጠባቂ ሆናለች። በዚህ ውድድር በተለይ ሴት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ስኬታማ ናቸው። ዝናሽ እአአ በ2018 የጉዋንዙ ማራቶንን የፈጸመችበት 2፡27፡15 የሆነ ሰዓት የግሏ እንዲሁም በውድድሩ ከሚካፈሉ አትሌቶች ፈጣን ነው። ይህም አትሌቷ አሸናፊ ልትሆን ትችላለች በሚል እንድትገመት አድርጓል። ፎዚያ አሚድ እንዲሁም እጸገነት እዢው የተባሉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም ተሳታፊዎች ናቸው።
በዚህ ውድድር በሁለቱም ጾታዎች ክብረወሰን የተያዘው በኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሲሆን፤ በወንዶች ፍቅሬ በቀለ እንዲሁም በሴቶች መገርቱ አለሙ እአአ በ2019 የተመዘገበው 2:22:52 የሆነ ሰዓት ነው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መጋቢት 9 ቀን 2015 ዓ.ም