መተከዣ፤
ይህ አምደኛ ምስኪኗንና አይተኬ አገሩን ሁሌም የሚመስላት በትራዠዲ ታሪኮችና ድርሰቶች ምንጭነት ነው። አገላለጹ «ሀሰት!» ተብሎ የመከራከሪያ አጀንዳ ይከፈትለት የማይባል እውነታ ስለመሆኑም ማስተባበል አይቻልም። ማሳያዎቹ ደግሞ ባለፉት ረጂም ዓመታት በዚሁ አንጋፋ ጋዜጣ ላይ ጥቂት በጥቂት ከመራር አገራዊ አሳሮቻችን ውስጥ እየቆነጠርን ስንቆዝምባቸው የከረምንባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች ማስታወሱ ብቻ በቂና ከበቂ በላይ ስለሆነ በማስረጃነት ለመጥቀስ አይገድም።
ጸሐፊው በሕይወት ዘመኑ ስሜቱ እጅግ ተጎድቶ ካነበባቸው የግል ገጠመኞቹ መካከል ሁለቱ መሪር ኀዘኖች ከቶም በቀላሉ የሚረሱ አይመስሉም። አንዱ የሩቅ ሌላኛው የቅርብ ጊዜ ሊባሉ የሚችሉ ገጠመኞች ናቸው። ሕወሓት/ኢህአዴግ አዲስ አበባን በተቆጣጠረበት ዕለት ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም በሸጎሌ የጦር መሣሪያ ማከማቻ መጋዘን (ዴፖ) ላይ በተፈጠረው ፍንዳታ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ዜጎች በሚዘገንን አሟሟት አካላቸው እንደ ጨርቅ ተበታትኖ ያለቁትንና ለማይሽር አካላዊ ጉዳት ሰለባ የሆኑትን ወገኖች ሲያስታውስ እምባው ከከረጢቱ እስኪሟጠጥ ድረስ ቢያነባም መሪሩ ኀዘን ከውስጡ ታጥቦ ሊወጣለት አልቻለም።
መኖሪያ ቤቱ ከፍንዳታው ቦታ በመቶ ሜትሮች ርቀት ላይ ይገኝ ስለነበር ትራዤዲው በተፈጸመበት ቦታ ቀድሞ በመገኘት የዐይን እማኝ መሆኑ ይበልጥ ኀዘኑ እንዳይረሳ ምክንያት ሆኗል። የፍንጥርጣሪው ዳፋም ደጃፉ ድረስ ደርሶ ስለነበር ለአስከፊነቱ ተቀዳሚ ምስክር ነው። በሣምንቱ ግንቦት 27 ቀን በበቅሎ ቤት የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ በተፈጠረው አደጋ መከራው ወድቆባቸው ቤተሰቦቻቸውንና ወዳጆቻቸውን ያጡ ወገኖችን ለማጽናናት የተቻለው ከተሰበረው ልባችን ውስጥ የሚንጠባጠበው ደም ቁለቁል ወደ ውስጣችን እየፈሰሰ ነበር እንጂ እምባችንማ ተሟጦ አልቆ የጠብታ ያህል እንኳን እያዋጣን ልናስተዛዝናቸው ከቶውንም አልቻልንም። «እንዳያልፉት የለም» እንዲሉ እነዚያ ክፉ ቀናት ትተውብን ያለፉት ቁስሎች ዛሬም ሆነ ወደፊት ማመርቀዛቸው በቀላሉ ፈጥኖ የሚጠግግ አይመስልም።
የአጋጣሚ ጉዳይ ይሁን ወይንም ከሰው ልጆች መረዳት አቅም በላይ በሆነ የግጥምጥሞሽ ምሥጢር ብቻ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን አዲሱ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቲቪ) አዲሱ የሕንፃ ኮምፕሌክስ የተገነባው በፍንዳታው በወደመው የቀድሞ የሸጎሌ ዴፖ ላይ ነው። ተቋሙ ያንን መራር የታሪካችንን ጥቁር ምዕራፍ በአግባቡ የሚያስታውስ አንድ ቋሚ መዘክር ወይንም መታሰቢያ በግቢው ውስጥ ቢያቆም አንድም የሙያ ሥነምግባሩ ግድ ይለዋል፣ አንድም የአካባቢው ወራሽ ከመሆኑ አኳያ በእምባ አባሽነት ክሬዲቱ ሊያዝለት ይችል ይመስለናል።
የሁለተኛው መራራ ኀዘን ምክንያት በቅርቡ በሚባል ሰሞን ለመዲናችን አዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው በደብረ ብርሃን አካባቢ በሚገኝ መጠለያ ጣቢያ ተፈጽሞ የተሰማው ታሪክ ነው። በዚያ ጊዜያዊ ማረፊያ ውስጥ የተጠለለው ወገን በጦርነት ተሰዶ፣ በሸማቂዎች ከአካባቢው ተፈናቅሎና ኑሮ የአቀበት ያህል ከብዶት ከቀዬው ተነቅሎ የተከማቸ የምንዱባን ስብስብ ነው።
በዚያ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ አንድ አባት ገና ጥርሱን ነቅሎ ካልጨረሰ ታዳጊ ልጃቸው ጋር ፈንጠር ብለው ተቀምጠው ይወያያሉ። ልጅ አባቱን ይጠይቃል፡-
«አባባ ለምን ወደ አገራችን አንመለስም?»፣
አባት፡- «ልጄ ምን አገር አለንና ወዴት እንመለሳለን»፣
«እንዴት አገር የለንም አባባ?»፣
«አገር አልባ እንድንሆን ተፈርዶብን»፣
«ማነው የፈረደብን አባባ?»፣
«እግዜሩና ጉልበተኞች»፣
«ታዲያ ሁልጊዜ እዚሁ ነው የምንኖረው?»፣
«አይ ልጄ ከዚህ ቦታም ልንሰደድ እንችላለን»፣
«ለመንግሥት ለምን አንነግርም?»፣
«አገር ቢኖረንም አይደል መንግሥትን የምንጠይቀው፣ አገር አልባ እኮ ነን ልጄ። በቅርቡ ከዚህም ተነሱ ተብለን ልንባረር እንችላለን»፣
«ደግሞ ወዴት?»፣
«እግር ወዳደረሰን»፣
«እናስ አባባ መጨረሻችን ምንድን ነው?»፣
«መሰናበት! ለዚያውም መቀበሪያ ካገኘን።»
ያ ሕፃን ልጅ ምርር ብሎ ለምን ያለቅስ እንደነበር ለመጠየቅ ወደ አባትዬው ጠጋ ሲባል ነበር ይህንን ልብ ሰባሪ ታሪክ ማድመጥ የተቻለው። የልጁ እምባ ለጊዜውም ቆሞ ሊሆን ይቻላል፤ አባትዬውም ከልጁ ጋር ያደረገውን ያንን ውይይት ሁለቱም ምንዱባን ሊዘነጉት ይችሉ ይሆናል። እኔና ይህንን ታሪክ ያደመጡ ወዳጆቼ ግን ታሪኩ ትዝ ባለን ቁጥር እስከ ዕለተ ፍጻሜያችን ድረስ እምባችን ከዐይናችን ላይ መመንጨቱ የሚቆም አይመስለንም።
ኢትዮጵያ ሆይ! እንደነዚያ አባትና ልጅ በአገሩ አገር አልባ ያደረግሽውን «የምስለ ዜጋሽን» ቁጥር በእውነቱ ታውቂው ይሆን? የገመናሽ ጉድ እንኳን የሩቅ ባዕዳንን ቀርቶ እኛን ዜጎችና ራስሽንም ቢሆን ሀፍረት የሚያከናንብ ስለሆነ ድምጻችንን አስተባብረን «ኤሎሄ! ኤሎሄ! ላማሰበቅታኒ!» እያልን በጋራ ልንቃትት ይገባል። የሃይማኖት መምህራኖቻችን «ከመጥምቁ ዮሐንስ» ሕይወት እንዳስተማሩንም «የፍትሕ ያለህ!» እያልን በምድረ በዳ ልንጮኽ ይገባል። በጽንስ ደረጃ ላይ የሚገኘው የሽግግር ፍትሕ እንቅስቃሴም በይሉኝታ ሳይሽኮረመም በእኛ መልክና አምሳል ተቀርጾ ወደ ትግበራ እንዲገባና ችግሮቻችን ላያዳግሙ ፍርጥርጥ ተደርገው እንዲፈተሹ ከወዲሁ የአደራ ቃላችንን ለሚመለከተው ሁሉ ይድረስልን እንላለን።
ባጉራህ ጠናኝ መረታታችን ይብቃ፤
በአየራችን ላይ እየናኙ ካሉት የሰሞኑ አገራዊ የመወያያ አጀንዳዎች መካከል አንዱ የሽግግር ፍትሕ (Transitional Justice) የሚባለው በቀዳሚነት ይጠቀሳል። ስለ ጽንሰ ሃሳቡ፣ ስለ አካሄዱና አተገባበሩ «የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አቅጣጫ አማራጮች» በሚል ርዕስ ከባለ ድርሻ አካላት ግብአት ለመሰብሰብ በጥር ወር 2015 ዓ.ም ተዘጋጀ የተባለውን ረቂቅ ሰነድ ይህ ጸሐፊ በሚገባ አንብቦታል።
ከሰነዱም በተጨማሪ በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተዘጋጁ በርካታ ዓለም አቀፍ የጥናት ውጤቶችንና ተሞክሮው ያላቸው አገራት እነማን እንደሆኑም ጊዜ ወስዶ ለመመርመር ሞክሯል። የሽግግር ፍትሕ የሚለው ጽንሰ ሃሳብ የተዋወቀው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቅ በኋላ የናዚዎችን ወረራና ግፍ እንዲመረምር (እ.ኤ.አ ከ1945 – 1946) በተቋቋመው የኑረምበርግ ወታደራዊ ችሎት አማካይነት ነበር። ለችሎቱ መቋቋም መንስዔ የነበረው መሠረታዊ ጉዳይ «የጦርነቱ ዋና ቀስቃሽና ተጠቂ አገራት እነማን ናቸው?» «በጦርነቱ ወቅት የነበራቸው ሚናስ ምን ነበር? የትኛው አገር በማን ተጠቅቷል? ምንስ ጉዳት ደርሶበታል? ለደረሰበት ጉዳትስ የትኛው አገር ማንን ይካስ? የካሳው ዓይነትና መጠንስ ምንና ስንት ይሁን? ከአገራቸው የተሰደዱና ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችስ እንዴት ፍትሕ አግኝተው ወደየቄያቸው ይሰባሰቡ? መሰል ጥፋቶችና ውድመቶች ዳግም በዓለማችን ላይ እንዳይፈጠሩ ምን ስልትና ዘዴ ይቀየስ? የሚሉትን ወሳኝ «ፍትሕ ነክ ጉዳዮች» መርምሮ ውሳኔ በመስጠት መንግሥታት ተረጋግተው የፈራረሰውን ሉዓላዊነታቸውን መልሰው እንዲገነቡ ለማገዝ ተወጥኖ የተቋቋመ ዓለም አቀፋዊ የፍትሕ አካል ነበር። ችሎቱ ምን ሠራ? ተልዕኮውን ያጠናቀቀው በምን ውጤት ነበር? ለሚሉት ጥያቄዎች በአገሬ ላይ ወራሪው የኢጣሊያ ፋሽስት የፈጸማቸው ግፎች እንደምን ተድበስብሰው እንዳለፉ ብቻ አስታውሶ ማለፉ ይቀላል።
ውሎ ሲያድር «የሽግግር ፍትሕ» እየተባለ የተዋወቀው ጽንሰ ሃሳብ በአገር ደረጃ ወርዶ እያንዳንዱ አገር በፖለቲካና በሥርዓተ መንግሥታት የሽግግር ወቅት የተለያዩ ችግሮች፣ የእርስ በእርስ ግጭቶችና ጦርነቶች ሲያጋጥሙት በየአገራቱ ዐውድ መሠረት ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች ተልዕኮ ገዘፍ ያሉ ጉዳዮችን ለመዳኘት የሽግግር ፍትሕ እንዲተገበር ምክረ ሃሳብ ቀርቦ ተቀባይነት በማግኘቱ በየአገራቱ ተጨባጭ ሁኔታ መሠረት ተግባር ላይ ሊውል ችሏል።
የሽግግር ፍትሕ አስኳል ግብ በሰብዓዊ መብቶች ላይ የተፈጸሙ ጥሰቶችን መርምሮ ውሳኔ መስጠት ሲሆን፤ መሠረታዊ አእማድ እንደሆኑ የሚታመኑት አላባዊያኑም (ፍሬ ነገሮች) እውነትን ገላልጦ ማሳየት፣ ፍትሕ ሳይሸራረፍ እንዲተገበር ማድረግ፣ የተፈናቀሉና የተሰደዱ ዜጎች ወደ መኖሪያ ቀዬአቸው መመለሳቸውን ማረጋገጥ፣ መሰል ክፉ ድርጊቶች ዳግም እንዳይፈጸሙ መከላከል፣ ለተጎዱት ዜጎችና ቡድኖች ተገቢውን ካሣ መክፈልና ተቋማዊ ሪፎርም በማድረግ አመቺ የፍትሕ ሥርዓት መዘርጋት የሚሰኙት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
ኢትዮጵያን ከፊት ለፊቷ ተጋርጠው ከሚጠብቋት ወቅታዊና ወሳኝ የቤት ሥራዎች መካከል አንዱና ምናልባትም ተቀዳሚው ዋና ጉዳይ ይህንን የሽግግር ፍትሕ የመተግበር ኃላፊነት እንደሆነ ታምኖበት እየተሠራ መሆኑን ዕለት በዕለት ዜናውን እየተመገብን አለን።
መቼም እንደ አገር «አለባብሰን አርሰን፤ በአረም የተመለስንባቸው» አገራዊ ታሪኮቻችን ከ እስከ ተብለው ተዘርዝረው የሚያልቁ አይደሉም። የእርስ በእርስ መቆራቆዞችም ሆኑ መረር ያሉ ግጭቶችና ጦርነቶች ለእኛ አገር ብርቅም ድንቅም አይደሉም። እስከነአካቴው ያለ ግጭትና ያለ እርስ በእርስ መገፋፋት አትኑሩ ተብሎ የተፈረደብን እስኪመስል ድረስ በአገራችን ታሪኮች ያላለፍናቸው የፈተና ዓይነቶች አሉ ለማለት አያስደፍርም።
በብዙ አገራት ውስጥ ለተፈጸሙ የእርስ በእርስ ግጭቶችና መመሰቃቀሎች እያንዳንዱ አገር በየራሱ ዐውድ የሽግግር ፍትሕ ለማስፈን በሞከረበት አጋጣሚም የከፊል አገራት ጥረት በክሽፈት ሲጠናቀቅ ለአንዳንድ ልበ ሰፊ አገራትም ዘዴው እንደሠራላቸው ተደጋግሞ ተገልጾልናል። ዝርዝሩን መከለሱ እጅግም አይጠቅምም።
ጉዳዩን ከራሳችን አንጻር እነመርምረውና የቆምንበት አብዛኛው የታሪካችን መሠረት ለሽግግር ፍትሕ ባዕድ ከመሆኑ የተነሳ አገራዊ ታሪካችን በአብዛኛው እየተነባበረ ሲለበጥ የኖረው በግፍ ድርጊቶች ነው። የሩቁን ትተን እንኳን የቅርብ ጊዜውን ብናስታውስ ወታደራዊው ደርግ ሥልጣን በያዘበት ማግሥት በግፍ የተጨፈጨፉት የንጉሡ ዘመን ሹማምንት ደም ፍትሕ በመሻት ወደ ፀባኦት ከመጮኽ የታቀበ አይመስልም። የደርግ መንግሥትና እርሱን የሚቃወሙት የፖለቲካ ተብዬ ቡድኖች በደም የተጨማለቀ ታሪክም ዛሬም ድረስ ምዕራፉ የተዘጋ አይመስልም። ወያኔ/ኢህአዴግ ከወታደራዊው መንግሥት ሥልጣን ከነጠቀበት ጊዜ ጀምሮ ሲተገብራቸው የኖሩት የግፍ ዓይነቶችም እንዲሁ በበቀልና በደም የቀለሙ ነበሩ።
እነሆ ዛሬም እንደምናስተውለው ስሙና መለያው ይለያይ ካልሆነ በስተቀር ምድራችንን የተጫነው የግፍ ደመና ይህ ልኩ የሚባል አይደለም። ዱር በቀል ቡድኖች «ንጹሐንን ገደሉና አፈናቀሉ» የሚለው መርዶ አደንዝዞን የምንይዘውንና የምንጨብጠውን አሳጥቶናል። ይሄም አነሰ ተብሎ ያለዋጋ ዜጎችን የገበርንበት የትናንቱ ስም የለሽ ጦርነት ያሸከመን የግፍ ሸክምም ከግምት የገዘፈ የጥቁር ታሪካችን አንዱ ምዕራፍ ነው።
የገበርነው ነፍስና የወደመው ሀብት ግምት እንኳንም መከራ ባደነዘዘው የእኛ አእምሮ ሊሰላ ቀርቶ አሸማቃቂ ታሪካችንን ለምናወርሰው ለመጻኢው ትውልድም ቢሆን ሳይወሳሰብበት የሚቀር አይመስለንም። እህህ ያሰኘን አገራዊ አበሳችንን በሙሉ እንዘርዝር ካልን በቂምና በበቀል ቁርሾ ስለምንሰክር «በሆድ ይፍጀው» ማለፉ ይበጅ ይመስለናል።
የሽግግር ፍትሕ እያልን ነጋ ጠባ ቃሉን በመጥራት እንደ ርሃብ ቀን ሰብል የምንጓጓለት ፍትሕ የማስፈን ሥርዓት በአግባቡ እንዲተገበርልን የምንመኘው ይኼን ሁሉ የታሪካችንን ስብራት ይጠግንልናል፣ ዕለት በዕለት የሚያስለቅሱንን አዳዲስ የግፍ ድርጊቶችም ይገታልን ይሆናል ብለን ተስፋ በማድረግ ነው። ያለምክር ተጸንሶ በጭንገፋ እንደተጠናቀቀው «የእርቀ ሰላም ኮሚሽን» መክኖ እንደማይቀርም እምነታችን ጽኑ ነው።
የሽግግር ፍትሑን ትግበራ በተመለከተ ይህ ጸሐፊ ሰሚ ባገኘሁ ብሎ የሚመኘው አንዳንድ መሻት አለው። «የሌሎችን ተሞክሮ በመቀመር» የሚባልለትን አስተሳሰብ ለጊዜው አቆይተን ስለምን ከራሳችን አገር በቀል እሴቶች አንጀምርም? ከየብሔረሰቡ የከበሩና አንቱታን ያተረፉ ዕድሜ ጠገብ የዕውቀት አባቶችና እናቶች ተሰብስበው በቅድሚያ በነፃነት እንዲመክሩ ዕድል ቢመቻችላቸውስ? ለምሳሌ፡- ደም የተቃቡ ወገኖች ሲታረቁበት የኖሩትን ባህላዊውን «ጉማ – የደም ካሣን» ዘመኑን በዋጀ መልኩ ዐውዱን አስጠብቀው ምክረ ሃሳብ እንዲያቀርቡ ቢደረግ አይጠቅምም? አፈርሳታው፣ አውጫጭኙ ወዘተ. በዘመናችን ልክ እየተሟሸ ቢሞከርስ? በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምሥራቅ በምዕራብና በመካከለኛው የአገሪቱ ክፍል ለሽግግር ፍትሑ የሚጠቅሙን አገር በቀል እውቀቶችንና ጥበቦችን ቀድመን እንፈትሽ። የተቀረውን የባዕዳን ተሞክሮ ከዚያ በኋላ እንደርስበታለን።
ያለበለዚያ ግን የሌሎችን ተሞክሮ ለመቅሰም በሚል ምክንያት ብቻ ባህር ተሻግሮ ለመሄድ ማሰፍሰፉን ለጊዜው ገታ በማድረግ ከራሳችን ባህላዊ ጓዳዎች መፍትሔዎችን መፈለግ ብልህነት ነው። እስከ መቼስ ለትልቅ ለትንሹ፣ ለተቸገርንበትም ላልተቸገርንበትም ጉዳዮች «የሌሎች አገራትን ተሞክሮ» እያልን ወደ ባዕዳን እናንጋጥጣለን? እነርሱስ ከእኛ እንዲማሩ ለምን በተግባር ፈትነን ያተረፍንባቸውን ትሩፋቶቻችንን ቀምረን አናማልላቸውም? እኮ እስከ መቼ አገር በቀል እውቀቶቻችንን «ባይተዋር ቤትኛ» አድርገን የሌሎች አገራትን እንዳንቆለጳጰስን እንኖራለን?። ያለንን አክብረን የሌለንን መዋሱ ላይ መበርታት የአመራር ጥበብ አንዱ መገለጫ ነው። እንምከርበት። ሰላም ለሕዝባችን፤ በጎ ፈቃድ ለዜጎች።
(በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን መጋቢት 9 ቀን 2015 ዓ.ም